Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62

Saturday, 15 October 2011 12:20

“ሁለት ለአንድ” ተመረቀ

ሽፈራው መኮንን ጽፎት መስፍን ጣፋ ያዘጋጀው “ሁለት ለአንድ” የፍቅር ኮሜዲ ፊልም ከትናንት ወዲያ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ትያትርና ባህል አዳራሽ ተመረቀ፡፡ 100 ደቂቃ በሚፈጀው ለማጠናቀቅ 15 ወራት በወሰደው ፊልም ላይ ሊዲያ ጥበቡ፣ ጀንበር አሰፋ፣ ወንድወሰን ብርሃኑ (ዶክሌ)፣ ሳምሶን ግርማ፣ ፀጋ ንጉሴ እና ሌሎች ተውነውበታል፡፡ ሁለት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ጓደኛማቾች አንዲት ሴት አፍቅረው የግላቸው ለማድረግ የሚያደርጉትን ፉክክር የሚያሳየውን ፊልም ያቀረበው ኢትዮ ቪዥን ኢንተርቴይመንት ነው፡፡ በምርቃቱ መጨረሻ ለፊልሙ ባለሙያዎችና ደጋፊዎች ከተሰጠው የምስክር ወረቀትና የአበባ ስጦታ በተጨማሪ ለሁለት ባለሙያዎች የክሪስታል ዋንጫና ሽልማት የተደረገ ሲሆን ሁለቱም ከፍቅረኞቻቸው ጋር በኩሩፍቱ ሪዞርት ለአንድ ቀን በነፃ እንዲዝናኑ የተበረከተላቸውን ስጦታ ከክብር እንግዳው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትያትር ጥበባት ተባባሪ ፕሮፌሰር በላይነህ አቡኔ ተቀብለዋል፡፡

Saturday, 15 October 2011 12:18

ዶስትየቭስኪ ይዘከራል

የታላቁ ሩስያዊ ፀሐፊ ፊዮዶር ዶስትየቭስኪ 190ኛ ዓመት ልደት በተያዩ ሥነጽሑፋዊ ዝግጅቶች እንደሚከበር አዲስ አበባ የሚገኘው የሩስያ የሳይንስና ባህል ማዕከል አስታወቀ፡፡ በመጪው ሐሙስ ከቀኑ 11 ሰዓት በማዕከሉ አዳራሽ ከሚቀርቡት ዝግጅቶች ሌላ የዶስትየቭስኪ መፃሕፍት አውደርእይ እና ሳሞቫር የሩስያ ባህላዊ ሻይ አፈላል ሥነስርዓት ለታዳሚዎቹ ይቀርባል፡፡  
ዶስትየቭስኪ “ወንጀል እና ቅጣት” |የስርቻው መጣጥፍ´ በሚል ወደ አማርኛ በተተረጐሙት የረiም ልቦለድ ሥራዎቹ በይበልጥ በአማርኛ አንባቢዎች ዘንድ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያን አይዶል የዘንድሮ አሸናፊዎቹ በደሴና በከሚሴ ከተሞች የማበረታቻ ሽልማት እንደተደረገላቸው ድርጅቱ አስታወቀ፡፡ የድርጅቱ ዋና አስተባባሪ አቶ አብይ ሳህሌ እንደገለፁት፤ አሸናፊዎቹና 16 የድርጅቱ ሠራተኞች ሽልማትና ስጦታ አግኝተዋል፡፡ በዚህም መሠረት አንደኛ የወጣው ተመስገን ታፈሰ (የከሚሴ ተወዳዳሪ) ከከሚሴ ከተማ አስተዳደር የቤት መስሪያ መሬትና 60ሺህ ብር፣ ከደሴ ከተማ አስተዳደር 10ሺህ ብር፣ ሁለተኛ የወጣው የደሴው ሀሰን አራጋው ከከሚሴ 10ሺህ ብር፣ ከደሴ 10ሺህ ብር፣ ሦስተኛ የሆነው የባህርዳሩ ማስተዋል እያዩ ከከሚሴ 10ሺህ ብር፣ ከደሴ 10ሺህ ብር ሲያገኙ በደረጃ አምስተኛ የነበረው የአዲስ አበባው ይድነቃቸው ገለታ ተክለፃድቅ ከሁለቱ ከተሞች አምስት አምስት ሺህ ብር አግኝቷል፡፡ 16 የውድድሩ አዘጋጆች እያንዳንዳቸው ከከሚሴ የአካባቢውን የባህል ልብስ፤ በደሴ ጋቢ ተበርክቶላቸዋል፡፡



ከጋብቻ ውጭ ተወልጄአለሁ የምትለው የታዋቂው ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ ልጅ አንጋፋው አርቲስት ከሞተ ከ21 ዓመታት በኋላ የወጋየሁ ንጋቱ ልጅነቴ በሕግ ይረጋገጥልኝ በማለት ፍርድ ቤት ልትሄድ ነው፡፡ ልጅነቴን የብሔራዊ ትያትር የሥራ ባልደረቦቹ ያረጋግጡልኛል፤ የዘረመል (DNA) ምርመራ ለማድረግም ዝግጁ ነኝ ስትል አስተያየቷን ለዝግጅት ክፍላችን የሰጠችው ዲያና ወጋየሁ ንጋቱ የሕግ ባለሙያ እያማከረች መሆኑን ገልፃ፤ የፍርድ ቤት ቅድመ ሁኔታዎች እስኪሟሉ በመገናኛ ብዙሃን የተቻላትን ጥረት በማድረግ የአርቲስቱ ልጅነቷን እንደምታስተዋውቅ ተናግራለች፡፡ ባለትዳር የሆነችው ወ/ሮ ዲያና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት የጠቅላላ አገልግሎት ክፍል ባልደረባ ስትሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ባልደረባ ከሆነችው እናቷ ወ/ሮ ማሜ ኃይለስላሴና ከአርቲስት ወጋየሁ መወለዷን ገልፃ አሁን በሕይወት የሌሉት እናትየው አባትነቱን ለማረጋገጥ በሕግ ከመጠቀማቸው በፊት አሁን በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ባልረቦቻቸው እንደከለከሏቸው እንደነገሯት ጠቅሳ፤ ይህ ግን መቆም አለበት ብላለች፡፡ ወጋየሁ በሞተበት ወቅት የወራሽነት ተቃውሞ እናትየው ለፍርድ ቤት እንዳታቀርብ እነዚሁ ባልደረቦች ሥምና ዝናውን እንጠብቅለት በማለት እንደተከላከሉ የነገረችን ዲያና፤ አሁን ልጅነቴ ይታወቅልኝ እንጂ ውርስ አልጠይቅም ብላለች፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ባልደረባ የሆነው አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ፤ ከዚህ ዓለም በሞት የለየው ሕዳር 6 /1982 ዓ.ም ሲሆን ወ/ሮ ማሜም በ1997 ዓ.ም አርፈዋል፡፡
የአርቲስቱን ቤተሰቦች አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ስልኮቻቸው ጥሪ ባለመቀበላቸው አልተሳካም፡፡

በቁም ነገር መጽሔት ላይ በምትስላቸው የገፀ ሰብ ካርቱን ስእሎች ታዋቂነትን ያገኘችው ሰዓሊ ብርትኳን ደጀኔ ሥዕሎች እና ካርቱኖች ለአውደርእይ ቀረቡ፡፡ በመጪው ሐሙስ ከቀኑ 10፡30 በአምስት ኪሎው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዘክር የቀረቡት ስእሎች “Reflection” በሚል ርእስ ነው፡፡ አውደርእዩ ለአንድ ሳምንት ለሕዝብ እይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ 58 ሥዕሎችና ካርቱኖች ለአውደርዕዩ ቀርበዋል፡፡
አምና የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ በኤምባሲአቸው አማካይነት ባዘጋጁት “አራቱ ነፃነቶች” በሚል ርእስ ባዘጋጁት የሥዕል ውድድር ሰዓሊ ብርትኳን ከአሸናፊዎቹ አንዷ ሆና የገንዘብ ሽልማት መሸለሟ ይታወሳል፡፡ በሌላም በኩል የፎቶግራፈር ሙሉጌታ አየነ 25 ፎቶ ግራፎች አወድርእይ በአልያንስ ኢትዮፍራንሴ ትናንት የተከፈተ ሲሆን እስከ ጥቅምት 18 ለሕዝብ ክፍት ሆነው ይቆያሉ፡፡ ፎቶግራፈሩ “የካፒታል” የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ባልደረባ ሲሆን የዘንድሮውን የውጭ ጋዜጠኞች ማህበር ሽልማት ማሸነፉ ይታወቃል፡፡

|904´ የሚደመጥ ኮሜዲ ገበያ ላይ ዋለ
አማኑዔል መሀሪ ጽፎት ቢኒያም ወርቁ ያዘጋጀው “ሰባ ሰላሳ” የአማርኛ ፊልም ነገ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ይመረቃል፡፡ ፊልሙን የሰራው አስቴር ፊልም ፕሮዳክሽን እንደገለፀው፤ የአዲስ አበባው ዋነኛ ምርቃት ከቀኑ 8 ሰአት በአምባሳደር ሲኒማ ይከናወናል፡፡ በዘጠና ደቂቃ ፊልሙ ላይ ደበበ እሸቱ፣ የሻሽወርቅ በየነ፣ ፍቃዱ ከበደ፣ ይገረም ደጀኔ፣ ዳግማዊት ፀሐዬ፣ ሰሎሞን ቦጋለና ሌሎችም ተውነዋል፡፡ በሌላም በኩል የአቶ አብርሃም መለሰ “እናት የግጥም ጓዳ” የግጥም መፅሐፍ ዛሬ ጧት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ይመረቃል፡፡ 113 ገፆች ያሉት መፅሐፍ 30 ብር ይሸጣል፡፡ይህ በእዚህ እንዳለ “904” አዲስ የኮሜዲ የሚደመጥ (audio) ሲዲ ገበያ ላይ ዋለ፡፡ የሲዲው አቅራቢ ቴዎድሮስ ታለ (ኩኩሻ) ነው፡፡ ኩኩሻ ካሁን ቀደም ለኮሜድያን ስክሪፕት በመፃፍ ይታወቃል፡፡ በድምፅ ብቻ በሚደመጥ ኮሜዲ ማሳቅ ከባድ ነው ያለው ኮሜዲያኑ፤ ተስፋዬ ካሳ ግን የተዋጣላት እንደነበር ተናግሯል፡፡

የዛሬ ሳምንት ምሽት በጀርመን ባህል ተቋም ቀርቦ የነበረው ኪነጥበባዊ ዝግጅት በሕዝብ ጥያቄ ዛሬ ከቀኑ 11፡30 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር በድጋሚ ሊቀርብ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ ፋቡላ የጥበባት ማህበር ከዘለስ የባህል ቡድን ጋር በሚያቀርቡት ዝግጅት፤ ወጣት ታዋቂ ገጣምያንና ሰዓሊያን ሥራዎቻቸውን በሙዚቃ ታጅበው እንደሚያቀርቡ የዝግጅቱ አስተባባሪ ኬር ማስታወቂያና ፕሮሞሽን ገልጿል፡፡ ለዝግጅቱ ኬር አድቨርታይዚንግ፣ ጐተ ኢንስቲትዩት፣ ጃፋር መፃሕፍት መደብር፣ ፕሮቴክ ፕሪንቲንግና አድቨርታይዚንግ እና ማርክ ማተሚያ ቤት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ከሁሉ የስነ-ጥበብ ዘርፎች አዲሱ ወይም ወጣቱ Advertising (ማስታወቂያ) ነው፡፡ ከሱ በፊት እቃህን ይዘህ ገበያ ትወጣለህ፣ ለውጠህ ወይ ሸጠህ ትመለሳለህ፡፡ Advertising ከመጣ ወዲህ ግን አብዛኛውን ልብሳችንን ሳይቀር በማስታወቂያ ተመርተን ነው ምንገዛው (የተመራነው ደግሞ ሳይታወቀን ሊሆን ይችላል!) Shaping Public Opinion (የህዝብን አስተሳሰብ መቅረፅ) የሚባል፣ የሳይኮሎጂና የአትንሮፖሎጂ ውህደት የሆነ የሙያ ዘርፍ አለ፡፡ የማስታወቂያ ስራ ተራውን የዚህ የሙያ ዘርፍ መሆኑ ነው፡፡

ይህ ርእሰ ጉዳይ በዋንኛነት በአዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ ያለውን የቤቶች ግንባታ መልሶ ማልማትን ብቻ የተመለከተ ነው፡፡ በከተማዋ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች እየተካሄዱ በመሆናቸው ለመዳሰስ የምሻው በመልሶ ማልማት ዙሪያ እየፈረሱ ስላሉት አንዳንድ የከተማችን ወረዳዎች ይሆናል፡፡ ይህ ትኩረትም በተለምዶ ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ እየተባለ በሚጠራውና በመንግስት መዋቅር በአራዳ ክፍለ ከተማ በወረዳ 9 ያለውን የመልሶ ማልማት የተመለከተ ትዝብታዊ ምልከታም ነው፡፡ እንደ አንድ የከተማዋ ተወላጅና ነዋሪ ይመለከተኛል ያልኩትንና የከተማዋ መስተዳደር፤ ክፍለከተማና ወረዳው ቢያስተካክሉአቸው ልቤ የወደዳቸውን የአሰራር ግድፈቶች ማንሳቴን ሁሉም የመንግሥት አካላት በቀና ልቦና ይመለከቱት ዘንድም እጠይቃለሁ፡፡

ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ለ7 አመታት ያህል ከ2ሺህ በላይ ህፃናትና ወጣቶችን በማሰባሰብ በእግር ኳስ፣ በአክሮባት፣ በቅርጫት ኳስ፣ በቦክስ፣ በእጅ ኳስ...የሚሳተፉ 120 ክለቦችን አቋቁመዋል፡፡ ከ2ሺህ አባላት አንድ መቶ የሚደርሱት ሴቶች ነበሩ፡፡ በወጣትነታቸው “ምዕራብ አዲስ አበባ ስፖርት ማህበር”ን መሥርተው የነበሩት አቶ በላቸው ኃይሌ፤ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሳተላይትና ሲስተም ክፍል የቀጥታ ስርጭት ንብረት ክፍል ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አድማሱ ብርሃኑ ሰሙ ከባለታሪኩ ጋር ዊንጌት አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ያደረገው ቆይታ ይህንን ይመስላል፡፡