Saturday, 12 December 2015 10:23

በመብራት መቋረጥ 3 ህሙማን ሞተዋል የሚለውን ዘገባ ሆስፒታሉ ተቃወመ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

• “መብራት ተቋርጦ ሶስት ህሙማን ሞተዋል” - የሆስፒታሉ ባለሙያ
• “መብራት የተቋረጠው ከሆስፒታሉ አቅም በላይ በሆነ ችግር ነው” - የሆስፒታሉ አስተዳደር


        በሀዋሣ ሪፈራል ሆስፒታል፤ መብራት በመቋረጡ ምክንያት፤ በፅኑ ህክምና ክፍል 3 ታማሚዎች እንደሞቱ፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን በመጥቀስ አዲስ አድማስ  ያወጣውን ዘገባ፣ ሆስፒታሉ ተቃወመ፡፡ ህሙማኑ መሞታቸውንና መብራት መቋረጡን ሆስፒታሉ ቢያምንም፤ ህሙማኑ የሞቱት በመብራት መቋረጥ ሳቢያ እንደሆነ የሚያረጋግጡ በቂ መረጃዎች በዘገባው አልቀረቡም፤ ሚዛናዊነትንም አያሟላም በማለት ቅሬታ አቅርቧል፡፡ ቅሬታዎቹ ብዙ ናቸው፡፡
የመብራት መቋረጥ ከሆስፒታሉ አቅም ውጪ የሆነ ክስተት እንደሆነ የሆስፒታሉ አስተዳደሩ ሲያስረዳ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ መስመር በመጥፋቱ ምክንያት የተፈጠረ ክስተት መሆኑን የመብራት ኃይል ተቋም አረጋግጦልኛል ብሏል ለአዲስ አድማስ በፃፈው ማስተባበያ ደብዳቤ፡፡ በኤሌክትሪክ መቋረጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን በጀኔሬተር ለማቃለል ከፍተኛ ርብርብ አድርጌአለሁ በማለት የሆስፒታሉ አስተዳደር ጽፏል፡፡ እነዚህ መረጃዎች በዘገባው አለመካተታቸውን ተችቷል፡፡
3 ህሙማን ሞተዋል የሚለው ዘገባ ስህተት ነው ሲል ሆስፒታሉ አስተባብሏል፡፡ ስህተቱንም ሲያስረዳ፤ ሁለቱ ህመምተኞች የሞቱት ህዳር 20 ቢሆንም አንድ ወላድ ህመምተኛ የሞተችው ህዳር 18 ቀን ነው ብሏል፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሆስፒታሉ ባለሙያ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መረጃ፤ በሁለቱም ቀናት መብራት ተቋርጦ ችግር እንደተፈጠረ አረጋግጠው፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሦስት ህሙማን መሞታቸው እውነት ነው ብለዋል፡፡ በሁለቱም ቀናት መብራት መቋረጡንና በጀነሬተር ችግሩን ማቃለል አለመቻሉን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የሆስፒታሉ የህግ ክፍል ተወካይ፤ በደብዳቤ ከተፃፈው ምላሽ ውጭ ጥያቄዎችን ማንሳት አስፈላጊ አይደለም ብለዋል፡፡
የሆስፒታሉ አስተዳደር የፃፈው ደብዳቤ ግን ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ አልሆነም፡፡
ችግሩን ለማቃለል ርብርብ ማድረጉን፤ ታካሚዎቹ ህመም ፀንቶባቸው እንደነበር፣ ወላዷ እናት የሞተችው “በዋነኛነት” በመብራት መቋረጥ ሳይሆን በህመሟ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ነው ደብዳቤው በደፈናው የሚገልፀው፡፡ በመብራት መቋረጡ ሳቢያ በህሙማን ላይ ጉዳት መድረስ አለመድረሱን በሚመለከት የተጠየቁት የህግ አገልግሎት ኃላፊ አቶ በቀለ በኩካ “በዘገባው ላይ በተገለፀው ዕለት መብራት መጥፋቱ የማይካድ ሃቅ ነው፤  በዚሁ ምክንያት የሰው ህይወት አልፏል ወይንስ አላለፈም በሚለው ጉዳይ ላይ ግን በማስተባበያ ደብዳቤው ላይ በተገለፀው መሠረት ብቻ ማረሚያ አውጡ” በማለት ለጥያቄያችን ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የሆስፒታሉ ተጠባባቂ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብይ ሚካኤል፤ መረጃ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው፤ “ምላሻችንን በኢሜይል እልካለሁ” ካሉን በኋላ፤ “ከሆስፒታሉ ሃኪሞች ጋር መነጋገር አለብኝ” በማለት ምላሽ ሳይሰጡን መቅረታቸው ይታወሳል፡፡    
ሆስፒታሉ፤ ሁሉም የጤና ባለሙያዎች ተጋግዘው የሚሰሩበትና ነርሶችም በኃላፊነት ከሃኪሞች ጋር የህክምና አገልግሎት በመስጠት የሚሳተፉበት አሰራር እንዳለ ደብዳቤው አክሎ ገልጿል፡፡  

Read 2103 times