Saturday, 16 January 2016 09:58

አለማቀፉ ማህበረሰብ ለድርቁ እርዳታ እንዲለግስ “ሴቭ ዘ ችልድረን” ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

    በኢሊኖ ምክንያት በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ አሰቃቂ ገጽታን እየተላበሰ መምጣቱን በመጠቆም አለማቀፍ ማህበረሰብ የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ “ሴፍ ዘ ችልድረን” የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ጥሪ አቀረበ፡፡
የህፃናት አድን ድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ድርቁ በተከሰተባቸው አፋርና አማራ ክልሎች ለሁለት ቀናት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን መንግስት እያደረገ ያለው እርዳታ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው እንዲያም ሆኖ ግን የአለማቀፉ ማህበረሰብ እርዳታ ያስፈልጋል ብለዋል።
መንግስት ድርቁን ለመቋቋም በአጠቃላይ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ማስታወቁ ይታወሳል። በአፋር ክልል በነበራቸው ቆይታ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸው አልቀው ለእርዳታ እጃቸውን መዘርጋታቸውን የገለፁት የግብረ ሰናይ ድርጅቱ አመራሮች፤ በአማራ ክልልም እየቀረበ ያለው እርዳታ በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከመንግስት ጐን ተሰልፎ እየሰራ መሆኑን የገለጸው የህፃናት አድን ድርጅቱ፤  እስካሁን ከ250ሺህ በላይ ለሚሆኑ የድርቁ ተጐጂዎች እርዳታ ማድረጉንና በተለይ ለህፃናት አልሚ ምግቦችን በማቅረብ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡  
በሁለቱ ክልሎች  የድርቁን ሁኔታ ተዘዋውረው የተመለከቱት የፊንላንድ፣ የኖርዌይና የአሜሪካ የህፃናት አድን ድርጅቶች ስራ አስፈፃሚዎች፤ በጉብኝቱ ስለ ድርቁ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ጠቁመው ይህንንም ለየአገሮቻቸው እንደሚያሳውቁና እርዳታ እንዲለግስ ግፊት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

Read 1870 times