Sunday, 07 May 2017 00:00

የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የኮሚሽኑን ሪፖርት እንደማይቀበል አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(9 votes)

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሚያዚያ 10 ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረበው ሪፖርት፣ በጌዴኦ ዞን የተቀሰቀሰውን ሁከትና ብጥብጥ የጌዴኦ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ደርጅት (ጌሕዴድ) እንደቀሰቀሰውና እንዳባባሰው የተገለፀው የሀሰት ውንጀላ በመሆኑ እንደማይቀበለው አስታወቀ፡፡
ጌህዴድ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፤ ድርጅቱ ዓላማው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ማኅበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያውያን ጋር የተቀናጀ ትግል ማድረግ መሆኑን ጠቁሞ ኮሚሽኑ፣ “ከጌዶኦ ውጭ ያሉ ብሔሮች ዞኑን ለቀው ይውጡ” በማለት ቀስቅሷል ሲል ቢወነጅልም ፍፁም ሀሰት ነው ሲል አስተባብሏል፡፡
የጌዴኦ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር ለዘመናት የተጋባና የተዋለደ፣ ከዞኑም ውጪ በሌሎች ክልሎች በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶና ሰርቶ፣ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በሰላም የሚኖር መሆኑን ጌሕዴድ ስለሚያውቅ፣ ህዝብን የህዝብ ጠላት የማድረግ ፍላጎት የለውም ያለው መግለጫው፣ ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት አምባገነናዊ ሥርዓት ለማስወገድና ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ማስቆም እንደማይቻል ጌሕዴድ በጥብቅ ይረዳል ብሏል፡፡
የሁከቱ መሰረታዊ መንስኤ ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የመብት ጥሰት፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ … መሆኑን ያልሸሸገው ኮሚሽኑ የእነዚህ ችግሮች ዋነኛ ፈጣሪ ገዢው ፓርቲ እንደሆነ እየታወቀ፣ ተጠያቂነቱን በጌሕዴድና በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ መለጠፉ ለሪፖርቱ ኢ-ተአማኒነትና ፖለቲካዊ ወገንተኝነት አንዱ ማረጋገጫ ነው ብሏል፡፡
በማጣራቱ ሂደት እኛን ወደ ጎን ገፍቶ፣ ገዢውን ፓርቲ አነጋግሮ እኛን መወንጀሉ፣ ለወገንተኛነቱ ሌላው ማረጋገጫ ስለሆነ ይህንን ወገናዊ ሪፖርት ጌሕዴድ አይቀበለውም፡፡ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ማጣራት እንዲካሄድም እንጠይቃለን በማለት አስገንዝቧል፡፡

Read 4367 times