Sunday, 14 July 2024 11:31

ኢትዮ ቴሌኮም የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ፈተና እንደሆነበት አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮ ቴሌኮም፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ዕጥረትን ጨምሮ ሌሎች ተግዳሮቶች ፈተና እንደሆኑበት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ አስታውቀዋል። ባለፈው ረቡዕ፣ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል የኩባንያው የ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም በቀረበበት ወቅት፣ የተመዘገቡ ስኬቶች በጉልህ ተጠቅሰዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ባቀረቡት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው፣ የኔትዎርክ አቅምን የማሳደግ፣ የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻልና የአገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት ላይ በዋናነት ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን ተናግረዋል። አክለውም፣ 462 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎችን በማቋቋም፣ የሞባይል ኔትዎርክ አቅምን ማሳደግ መቻሉን ያስረዱት ፍሬሕይወት፣ በበጀት ዓመቱ 86 ሚሊዮን አዳዲስ የሞባይል ኔትዎርክ ደንበኞችን ማፍራት ማስቻሉን ነው የገለጹት።
እ.ኤ.አ. ከ2020 ወዲህ የደንበኞችን የኢንተርኔት ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ስራዎች እንደተሰሩ ያወሱት፣ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ “የ4G ኔትዎርክ ሽፋንን የማሳደግ ስራ ተሰርቷል፤ በዚህም 424 ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። የ5G ኔትዎርክ ስራ ወደ መደበኛ አገልግሎት የገባ ሲሆን፣ በቅርቡ በሌሎች ከተሞች አገልግሎቱ እንደሚጀምርም ተነሯል።
በግጭት ወቅት ውድመት የደረሰባቸው 179 ማዕከላት ጥገና እንደተደረገላቸው   ወ/ት ፍሬሕይወት ባቀረቡት ሪፖርት  አመልክተዋል።
በተጨማሪም፣ በበጀት ዓመቱ 78 ነጥብ 3 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች እንዳፈራ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጠቁመው፣ ይህም ከታቀደው ዕቅድ አንጻር የ100 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት እንደተመዘገበበት አስረድተዋል።
በትንሹ አንድ ሚሊዮን ዲጂታል መታወቂያ ለዜጎች ለማቅረብ መታቀዱ፣ በቀጣይ “ለውጥ ይፈጥራል” ተብሎ በስራ አስፈጻሚዋ ለተገለጸው ፕሮጀክት እንደሚያገለግል ነው የተጠቆመው።
ለ307 ሺህ 300 ዜጎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረ በሪፖርቱ ተወስቷል።
በበጀት ዓመቱ 93 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ትርፍ የተገኘ ሲሆን፣ ከዕቅዱ 103 ነጥብ 6 በመቶ እንደተሳካ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል። አያይዘውም፣ ካለፈው ዓመት አንጻር ሲመዛዘን፣ የ21 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል። በውጭ ምንዛሬ በኩል 198 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ እንደተገኘ አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ በርካታ ስኬቶች ቢመዘገቡም የተለያዩ ተግዳሮቶችም ገጥመውታል። በመግለጽ፣ በዋናነት የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ዕጥረት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥና መሰል ችግሮች ለኩባንያው እንቅስቃሴ ፈተና እንደሆኑበት ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ከቀጠለው ግጭት አንጻርና በአገልግሎት ተደራሽነት ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ፍሬሕይወት ታምሩ ገጥመውታል። “ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው። ለሁሉም የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሚከፈት ተስፋ አለን። ነገር ግን እንደኢኮኖሚ ተቋማት ላሉ ሌሎች ድርጅቶች አገልግሎቱን እየከፈትን ነው።” ብለዋል።
የውጭ ምንዛሬ ዕጥረትን ለመቅረፍ ስለታቀዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተጠይቀውም ሲመልሱ “ከአበዳሪዎች ጋር ተደራድረን ጨርሰናል። አበዳሪውም አንድ የአሜሪካ የፋይናንስ ኩባንያ ነው። የብድር ድርድሩ በቶሎ ሊሳካ የቻለው የኦዲት አፈጻጸማችን ታይቶ ነው።” ብለዋል።
GSMA የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ ሁለተኛ፣ በዓለም አስራ ሰባተኛ ደረጃን የያዘ ትልቅ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ተቋም ነው።






Read 1103 times