Saturday, 29 July 2023 12:22

“በቅርብ ያለ አማች ወፍጮ ላይ ይቀመጣል”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ሁለት ታሪኮች አሉ፡፡ ተመሳሳይም የሚለያዩም፡፡ አንደኛው የቡልጋሪያውያን ጋቭሮቮዎች ታሪክ ነው፡፡ ሁለተኛው የኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው፡፡
የቡልጋሪያው ታሪክ እንዲህ ነው፣
በስግብብነታቸው ይታወቃሉ ከሚባሉት ጋቭሮቮዎች አንደኛው ብዙ ብርቱካን ይዞ እየበላ ወደ ሰፈሩ ይመጣል፡፡ የመንደር ጓደኞቹም ዘመዶቹም ብርቱካን መብላቱን አይተዋል፡፡ ከነሱም መካከል ብርቱካን ያላቸው አሉ፡፡ ሆኖም ሲበሉ ያያቸው ስለሌለ የራሳቸውን ብርቱካን ደብቀው ከእሱ ብርቱካን እንዲያካፍላቸው ጠየቁት፡፡ አጅሬም እንደነሱ ጋቭሮቮ ነውና፤
“አልሰማችሁም እንዴ ጎበዝ? እዚያ ወዲያ እሩቅ ከሚታየው መንደር እኮ ብርቱካን በነፃ እየታደለ ነው፡፡ እኔም ያመጣሁት ከዚያ ነው፡፡”
የሰፈሩ ጋቭሮቮች ብርቱካን ይታደላል ወዳላቸው ቦታ ነቅለው መሮጥ ጀመሩ፡፡ በየመንገዱ ያገኙት ህዝብም ሲጠይቃቸው ብርቱካን በነፃ እንደሚታደል ይናገራሉ፡፡ የሰማው ላልሰማው እየነገረ አገሩ በሙሉ ብርቱካን ወደሚገኝበት መንደር በሩጫ እየጎረፈ ሄደ፡፡
ይሄኔ ያ በመጀመሪያ በነፃ ይታደላል ብሎ የዋሸ ጋቭሮቭ ነገሩ አጠራጠረው፡፡ ሲያይ የህዝቡ ቁጥር ይብስ እየጨመረ ሄዷል፡፡ ስለዚህ፤
“አሀ! ይሄ ነገር እውነት ይሆን እንዴ?” ብሎ እራሱን ጠይቆ፣ ወደዚያው በፍጥነት መሮጥ ጀመረ፡፡
***
የኢትዮጵያው ታሪክ ደግሞ እንዲህ ነው፡፡
በአንድ ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረ አንድ ሌባ ንብረት ዘርፎ ይሰወራል፡፡ ንብረቱ የተዘረፈበት ለመንግሥት ያመለክታል፡፡ መንግሥት ለህዝቡ ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ “የገባችሁበት ገብታችሁ ይህን ሌባ ፈልጋችሁ አምጡ!” ብሎ፡፡ ስለሆነም ህዝቡ በሙሉ ሌባ ፍለጋ ተሰማራ፡፡ ሌባው ግን አልተገኘም። በመካከል አንድ በመልክም በቁመትም ልክ ያንን ሌባ የመሰለ ሰው ከባላገር ይመጣል፡፡ ህዝቡ ሮጦ ይህን ሰው ይይዘዋል፡፡ ሰውየው “እባካችሁ በመልክ ሌባውን መስያችሁ ነው እንጂ እኔ ሌባ አይደለሁም፡፡ ምንም የሰረቅኩት ነገር የለም” አለ፡፡ የሚያምነው ጠፋ፡፡ የማርያም ጠላት አደረጉት፡፡ ጩኸቱ በዛበት፤ “ሌባው አንተ እራስህ ነህ! ዛሬ ቀን ብታምን ይሻልሃል! እኛን በጭራሽ ለማታለል አትችልም፡፡ ይልቅ ተናገር!” እያሉ አፈጠጡበት፡፡ ያም ሰውዬ በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፤
“አሁን ይሄ ሁሉ ህዝብ እንዴት ይሳሳታል? በፍፁም አይሳሳትም፡፡ … እኔ እራሴ መስረቄን እረስቼው ይሆናል እንጂ!” በመጨረሻም “አዎ እኔ ነኝ” ብሎ አመነና ወደ ወህኒ ወረደ፡፡
***
በቡልጋሪያም ሆነ በኢትዮጵያ ወይም በሌላ አገር ህዝብ ህዝብ ነው፡፡ የቡድን ስሜት የቡድን ስሜት ነው፡፡ አንድ አቅጣጫ ይዞ ያንኑ ቦይ ተከትሎ መፍሰስ ከጀመረ ማቆሚያ የለውም፡፡ አንድም በመጭበርበር፣ ወንዝ ፈጥሮ፣ ወንዝ ሆኖ ሊጎርፍ ይችላል፡፡ አንድም ትእዛዝ አክብሮ፣ በታዛዥነት እየፈሰሰ ግለሰቦችን እየተጫነ፣ አንዴ መውረድ ወደጀመረበት አሸንዳ በጀማ ይጓዛል፡፡ ላቁምህ፣ ልገድብህ ቢሉት በእጄ አይልም፡፡ የመንገኝነት ስሜት (Herd instinct) በበጎም በክፉም ሊነዳ የሚችል ብርቱ ስሜት ነው፡፡  ልዩ ጥንቃቄ የሚፈልግ አደገኛ ቡድናዊ ደመ-ነብስ ነው፡፡ በተለይ እንደ እኛ አገር ባህላዊ ህብሩ፣ ኢኮኖሚያዊ ትግግዙ፣ ጎሳዊ ትስስሩና አገራዊ አንድነቱ ቋጠሮው በጠበቀበትና ውስብስብ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ፤ የእያንዳንዱ ቀልጣፋ ግለሰብ ወይም ደፋር ቡድን ፍላጎት፤ የብዙሃኑን ፍላጎት የሚቃኝና የሚመራበት ሁኔታ ሀያል ነው፡፡ ግለሰቦች፤ ቡድኖች፣ ድርጅቶች፣ ፓርቲዎችና ማህበራት አዋሹን ህዝብ ወዳፈተታቸው አቅጣጫ ለመውሰድ በማባበልም፣ በመደጎምም፣ በማታለልም፣ በማዘዝም፣ በማስፈራራትም ቦይ ለመቅደድ መጣጣራቸው አይቀርምና የመንገኝነት ጉዳይ አጠያያቂና አደገኛም ሊሆን ይችላል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ሁሉም የህዝብን ችግርና ብሶት መሰረት ያደረገ ቋንቋ አንግቦ ይነሳል፡፡ አንደበተ-ቀናው፣ ዲስኩር የሚዋጣለት በቀላሉ ይደመጣሉ፡፡ የእኛ ህብረተሰብ የተራኪና አድማጭ ህብረተሰብ (Story-teller society) ነው፡፡ ደህና ተናጋሪ ካገኘ አዳምጦ ወደ ማመን እንጂ መርምሮ ወደ መረዳትና ተንትኖ ወደ መቃወም ገና ሙሉ በሙሉ የተሸጋገረ አይደለም፡፡ በግሉ አስቦ፣ በግሉ መርምሮ፣ በግሉ ለራሱ የሚቆም ጥቂት ነው፡፡ መብቱን ለማስከበር የሚራመደው ገና ጎረቤትና ጎረቤት ተያይቶ፣ እነ እገሌ ምን አሉ ተባብሎ፤ ነው፡፡ ስለዚህም የነቃ ይቀድመዋል፡፡ ጮሌ እንዳሻው ይነዳዋል፡፡ አንደበተ-ቀና ያሳምነዋል፡፡ አስገራሚው ነገር ግን የዞረ ዕለትም ያው ነው፡፡ ሲገለበጥም እንደዚያው ነው፡፡ የዚያኑ ያህል ደመ-መራራ ነው፡፡ የተከተለውን ሊያባርረው፣ የካበውን ሊንደው፣ ያከበረውን ሊንቀው ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ በማህበረሰቡ ዘንድ የመንገኝነት ስሜት መሪ ሚና መጫወቱን አለመዘንጋት ነው፡፡
ይህን የመንገኝነት ስሜት የሚመራ ሁሉ የተቀደሰ ዓላማ አለው ለማለትም አይቻልም፡፡ “ሆድ ዕቃው የተቀደደበት እያለ ልብሱ የተቀደደበት ያለቅሳል” ይሏልና፡፡ ስለዚህም እውነተኛውን ከሀሳዊው፣ ዋናውን ከትርፉ፣ ኦርጅናሌውን ከአስመሳዩ፣ ምርቱን ከግርዱ ለይቶ፣ አይቶ መጓዝ የሚያስፈልግበት ሰዓት ነው፡፡ ኤሪክ ሆፈር የተባለው ፀሐፊ፤ “አብዛኞቹ የቅዱስ ሰው ምርጥ ሃሳቦች ከሃጢያተኝነት ልምዱ ያገኛቸው ናቸው።” ያለውን አለመዘንጋት ነው፡፡ የወቅቱ መዞሪያ-ኩርባ (Turning point) መቼና የት እንደሆነ የማያይ ቡድን ወይም ፓርቲ እንደ እቴቴ ሽረሪት ድር ራሱን በራሱ ተብትቦ፣ ራሱን በራሱ ውጦ ለባላንጣው ሲሳይ የሚሆን ነው፡፡ ትንሽ መንገድም ቢሆን በሚያግባባቸው አቋም አብረው ሊሄዱ የሚችሉ የፖለቲካ ሰዎች ወይም ቡድኖች ሲነጋ በቀኝ ጎናቸው ሊነሱ ይችላሉ። ለመንቃት በርትቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ዳተኝነትን ማስወገድና የቤት ስራን መስራት ያስፈልጋል፡፡ “ሰነፍ ይፀድቃል ወይ ቢለው፣ ገለባ ይበቅላል ወይ አለው” እንዳለው ገለባ ሆኖ ላለመቅረት ማለት ነው፡፡
ዛሬም የሦስት ምክሮች ዘመን ነው- ስለዚህ ባንድ በኩል “ዝግጅት! ዝግጅት!  አሁንም ዝግጅት!” ማለት ተገቢ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ፅናት! ፅናት! አሁንም ፅናት!” ማለት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ምክር አዲስ እንዲወለድ የሚጠቅመውን ያህል ነባሩ በቀላሉ እንዳይፈረካከስ ይጠቅማልና የጠንካራ ድርጅት መሰረት ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችን የመበታተን ሥጋት እንደ ሀገር ችግር ማየት ተገቢ ነው፡፡ አንዲት ነብሰጡር ሴት ጎረቤቷ በምትወልድበት ቀን ልውለድ ብትል እንደማይሆንላት ሁሉ፤ የፖለቲካ ድርጅቶችም የራሳቸውን ዕድሜና ብቃት፤ የማፍሪያና የማዘርዘሪያ ከዚያም ለፍሬ መብቂያ ጊዜ አይተው ብቻ ነው መነሳት ያለባቸው፡፡ ሌላው ከሚቀድመን ተብሎ ሳይጠነክሩ የሚሰራ ስራ የብልህ መንገድ አይደለም፡፡ የማያስተማምን ውህደት በሰም የተጣበቀ ጥርስ መሆኑን መርሳትም አይገባም፡፡ “ዛሬ የትላንትና ተማሪ ነው” እንዳለው ቶማስ ፉለር፤ ትላንትን ማሰብ የተማሪውን አስተማሪ እንደማወቅ ይሆናል፡፡ ማሰብ፣ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ነው፡፡ “ቀጥቃጭ ሲያረጅ ዱልዱም ይቀጠቅጣል” እንዲሉ የሞተ ነገር ላይ መነታረክ ያልሞተውን ነገር እንዳናይ ያደርገናል፡፡ ሳያስቡ መጓዝ መፈክርን ያስነጥቃል፡፡ ሳያስቡ መጓዝ የተገኘን እድል በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ያደርጋል፡፡ ባገኙት ድል ክፉኛ አለመፈንደቅ ብልህነት ነው፡ በደረሰ ጊዜያዊ ሽንፈትና ችግር የመጨረሻ የመንፈስና የአካል መፈረካከስ ድረስ መውረድም ደካማነት ነው-”የሚደኸይ ጉሮሮ ሁሌ ጣፋጭ ነገር ይመኛል” እንዲል መጽሐፍ፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሽኩቻ፤ ከመሰነጣጠቅ ለበያቸው ሲሳይ ከመሆን መቼ ይሆን የሚወጡት? የሚለው ጥያቄ ዛሬም አለ፡፡ ዛሬም ከመከፋፈል፣ ዛሬም ከመጠላለፍ እንዳይወጡ የሚያደርጋቸው የመርገምት አዙሪት ያው እንደተለመደው የት/ቤት፣ የአፈር ፈጭ አብሮ አደግነት፣ የመጠፋፋትና የአውቅሁሽ ናቅሁሽ ፖለቲካ ይሆን? “በቅርብ ያለ አማች ወፍጮ ላይ ይቀመጣል” የሚሉት ዓይነት ማለት ነው።



Read 1849 times