Saturday, 11 January 2014 11:17

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የደህንነት ሃላፊ ምን ይላሉ?

Written by  ኮሎኔል ግርማ ዘውዴ
Rate this item
(6 votes)

ጡረታዬ ባለመከበሩ በቤተሰቦቼ ድጋፍ እኖራለሁ….
ለማንዴላ ሃውልት ማሰሪያ ከደሞዜ 50ሺ ብር አበርክቼአለሁ …  
እስቲ ከትምህርትዎ እንጀምር፡፡ ምንድነው የተማሩት?
የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ፖሊስ ኮሌጅ ገባሁ፡፡ “አባዲና ኮሌጅ” ይባላል፡፡ እዚያ ገብቼ

የፖሊስ ጠቅላላ ትምህርት ተከታትዬ ግንቦት 19 ቀን 1947 ዓ.ም ተመረቅሁኝ፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያት በልዩ ልዩ የፖሊስ
ክፍሎች ተመድቤ ከሰራሁ በኋላ፣ በፖሊስ መምሪያ አስተዳደር ትዕዛዝ ወደ አባዲና ፖሊስ ኮሌጅ በመዛወር፣ ለዘጠኝ
አመታት በመምህርነት እና በአሰልጣኝነት አገልግያለሁ፡፡
ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዴት ገቡ?  
በኢትዮጵያ መንግስትና በአፍሪካ አንድነት ድርጅት መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት፤ በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ
ያለኝ ካርየር (ሙያተኝነቴ) ተጠብቆ በውሰት ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት በሻምበልነት ማዕረግ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ
ተልኬ፣ የድርጅቱ የጥበቃና የደህንነት ሀላፊ በመሆን፣ ከ30 ዓመታት በላይ ያልተቋረጠ አገልግሎት ሰጥቻለሁ፡፡
በ30 ዓመታት የስራ ዘመንዎ 42 የአፍሪካ አገራት ውስጥ የተደረጉ የመሪዎች ስብሰባዎችን የደህንነት ሁኔታ መርተዋል፡፡
ስለነዚህ አገራትና ቆይታዎ ያጫውቱኝ …
በእነዚህ አመታት የመሪዎች ስብሰባ ሲደረግ እና የድርጅቱ ዋና ፀሀፊዎች ጉብኝት ሲያደርጉ አብሬ በመሄድ፣ አርባ ሁለት
አገሮችን ለመጐብኘት ችያለሁ፡፡ ያው በ42ቱ አገራት ያሉትን የተለያዩ ባህሎች፣ ከተሞች እና የህዝቡን አኗኗር ለአጫጭር
ጊዜም ቢሆን አይቻለሁ፡፡
በነዚህ አገራትና በሰሩባቸው አመታት ከደህንነት፣ ከአፍሪካ መሪዎችና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ገጠመኞች
እንደሚኖርዎት እገምታለሁ …
በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ገጠመኞች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ግን የአንድ ድርጅት የደህንነት ሰራተኛ ሆነሽ ስትሰሪ፣ በመሪዎቹም
ሆነ በእያንዳንዱ ጉዳይ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን አሳልፈሽ ለመግለፅ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ደንብና ስርዓት ስለማይፈቅድ
ይህን ተላልፌ መናገር አልችልም፡፡
በአሁን ሰዓት ግን የድርጅቱ ሰራተኛ አይደሉም። ስራ ካቆሙ 14 አመት ሆኖዎታል፤ የድርጅቱን ስራ ካቆሙ በኋላም  
መናገር አይችሉም ማለት ነው?
አልችልም! ምክንያቱም በድርጅቱ የውስጥ መመሪያ መሰረት አንድ ሰው ከአንድ አባል አገር ተመርጦ በድርጅቱ ውስጥ
በሚሰራበት ጊዜ የላከው አገር መንግስትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሳያውቅ ማገልገልም ሆነ ምንም አይነት መረጃ
መስጠት አይችልም፡፡ ይህ ደንብ ባይገድበኝ ኖሮ ብዙ ገጠመኞችን አጫውትሽ ነበር፡፡
በተለያዩ አገሮች የድርጅቱ የመሪዎች ስብሰባ በሚኖርበት ጊዜ አንዳንድ መሪዎች ፕሮቶኮል አይጠብቁም፣ ከሆቴል
ወጥተው በመሄድ ለጥበቃ ያስቸግራሉ ይባላል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ነገሩ እውነት ቢሆንም ከላይ የገለፅኩልሽ ደንብ ስለሚከለክል፣ የዚህ አገር መሪ እንዲህ ነው፤ እንዲህ ያደርጋል ማለት
አልችልም፡፡ ደንቡን መተላለፍ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ስለ መሪዎቹ የግል ጉዳይ አልነግርሽም፡፡
ታዲያ እነዚህን ጉዳዮች ካልተጨዋወትን ምን ልናወጋ እንችላለን… ኮሎኔል?
እኔ ደንቡን ለመጠበቅ እንጂ ነገሮችን ለመሸፋፈን ፍላጐት ኖሮኝ አይደለም፡፡ ይህ አንዴ የድርጅቱ ሰራተኛ ስትሆኚ ቃል
ገብተሽ፣ ሀላፊነት የወሰድሽበት ጉዳይ በመሆኑ በህይወት እስካለሽ ድረስ መግለፅ አትችይም፤ አዝናለሁ፡፡
በስብሰባ ወቅት አንዱ መሪ ከሌላው አገር መሪ ጋር ግጭት ቢፈጥር የእናንተ ሚና ምንድን ነው?
ዌል! ደጋግሜ እንደነገርኩሽ የግል ጉዳያቸውን አልነግርሽም፡፡ አንዳንዴ እንዳልሽው ግጭቶችና አለመግባባቶችን የፈጠሩ
መሪዎች ካሉ፣ ስብሰባ ሲካሄድ የሚቀመጡበትን ቦታ እናራርቀዋለን፡፡ አንድ አካባቢ እንዳይቀመጡ ቦታቸውን
እናለያያለን፤ ከዚያ አይገናኙም፡፡ በፊደል ተራ እንኳን የሚገናኙ ቢሆን ግጭት ካላቸው ቦታቸውን እናለያያለን፡፡ ይሄ
አንዱ ቴክኒካችን ነው፡፡
በእርስዎ ጊዜ “አፍሪካ አንድነት ድርጅት” ነበር የሚባለው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ “አፍሪካ ህብረት” ተብሏል፡፡ ድርጅቱ
ከስም ለውጥ ባለፈ ምን ልዩነት አምጥቷል ብለው ያስባሉ?
በእኔ በኩል ምንም ልዩነት የለውም፡፡ በእኛ ጊዜ ድርጅቱ የጡረታ ዘላቂ መብት አልነበረም። የትምህርት መብትም
አልነበረም፡፡ አሁን አፍሪካ ህብረት ከተሰኘም በኋላ እነዚህ ነገሮች የሉም፤ ዋናው ነገር ይሄ ነው፡፡ አሁን ትንሽ ልዩነት
አለው ብዬ የማስበው፤ በፊት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሀፊዎች ወንዶች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ሴቶች ሆነዋል፡፡
አሁን ድርጅቱን የሚመሩት ዋና ፀሀፊም ሴት ናቸው፡፡ ልዩነቱ ይሄ ነው፡፡
ከፀጥታና ከደህንነት ስጋት ጋር በተያያዘ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች በራሳችን የደህንነት ሰራተኞች ካልተጠበቅን ብለው

ያስቸግራ፡፡ ለምሳሌ የቀድሞውን የሊቢያ መሪ ኮ/ል ሙአመር ጋዳፊን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ የደህንነት
ሰራተኞች ብቃት ላይ ጥርጣሬ ነበራቸው ማለት ነው?
እንዳልሽው ፕሬዚዳንት ጋዳፊ ለስብሰባ አዲስ አበባ በመጡበት ጊዜ እንዲህ አይነት ጭቅጭቅ አንስተው እንደነበር
ይታወቃል፡፡ ጠባቂዎቻቸው ሴት ኮማንዶዎች ነበሩ፡፡ ሲገቡ መሳሪያ እንደታጠቁ ነበሩ፡፡ በህጉ መሰረት ወደ ስብሰባ
አዳራሹ ማንኛውም ሰው መሳሪያ ታጥቆ መግባት አይፈቀድለትም፡፡ እነሱ ግን መሳሪያ ታጥቀው ለመግባት ሞከሩና

ተከለከሉ፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደነገርኩሽ ህጉ መሳሪያ ታጥቀው እንዲገቡ አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ የእኛ ደህንነቶች

አቆሟቸው። እኔ ግን ባለማወቅ እንጂ በእኛ ደህንነቶች ላይ እምነት ስለሌላቸው አይመስለኝም፡፡
እኔ ግን ኮሎኔል ጋዳፊ የድርጅቱ አባል አገር መሪ በመሆናቸው አጠቃላይ ደንብና ስርዓቱን ያጡታል የሚል እምነት
የለኝም…
እኔ ደግሞ ጠባቂዎቻቸው ደንቡን አላወቁም ባይ ነኝ፡፡ በመሆኑም የሀይል ሙከራ አደረጉ፡፡ የእኛዎቹ የፀጥታ ሀይሎች
ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ መሳሪያ ይዘው እንዳይገቡ አደረጓቸው፡፡
ስለ ቀድሞው የዩጋንዳው መሪ ኢዲያሚን ዳዳ ትንሽ ያጫውቱኝ …  
ኢዲያሚን ዳዳ ከ42ቱ የድርጅቱ አባል አገሮች አንዱ መሪ ነው፡፡ በምርጫ ለድርጅቱ መሪ ሆኖ ለአንድ አመት
አገልግሏል፡፡ በስብሰባ ወቅት በአራት እንግሊዞች ግራና ቀኝ በተያዘ ፕላትፎርም ላይ አስቀምጠውት ሲሄዱ
ይጨበጨብለት ነበር፡፡ ዩጋንዳ የእንግሊዝ ቅኝ ተገዢ ስለነበረች፣ ያኔ ደግሞ የአፍሪካ ጊዜ ነው በሚል  ቂማቸውን
ለመወጣት ያደረጉት ይመስለኛል፡፡ በእኔ እምነት ያ ተገቢ አይደለም፡፡ ማንዴላ ያስተማረውም ይቅር ባይነትንና
መቻቻልን ነው፡፡ ከአንድ ከሰለጠነ መንግስት ይሄ አይጠበቅም፡፡ ከዚህ በላይ ስለ አዲያሚን ዳዳ ብዙ ብነግርሽ ደስ
ባለኝ ግን አልችልም፡፡  
ስለ ማንዴላ ካነሳን አይቀር በርካታ ንግግሮቻቸውን በካሴት መቅረፅዎን ሰምቻለሁ…
በመጀመሪያ ስለ ማንዴላ የምነግርሽ ከሚያደንቁት ውስጥ አንዱ መሆኔን ነው፡፡ ስለ አፍሪካ አንድነት፣ ስለ ህዝባቸው

ነፃነትና እኩልነት ያደረጉትን ተጋድሎ በደንብ አውቃለሁ፡፡ በሮቢን አይላንድ በአፓርታይድ መሪዎች 27 አመት

መታሰራቸውን አለም ያውቀዋል፡፡ ነገር ግን ከዚያ ሲወጡ ቂማቸውንና በቀላቸውን ይወጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ፣ ችግር

ላደረሱባቸው አገሮችና ሰዎች ይቅርታን ለግሰው፣ ህዝቡን ማሳመን የቻሉ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ከዚህም መከራ አልፈው

ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ላይ ተጋበዘው አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ለአፍሪካ

መሪዎች፣ ለአምባሳደሮች፣ ለዲፕሎማቶች፣ ለኢትዮጵያ ባለስልጣናትና ለተጋባዥ እንግዶች የህይወት ውጣ ውረዳቸውን፣

የትግል ዘመናቸውን… አጠቃላይ ስለ ህይወታቸው… አንድ ሰዓት ተኩል የፈጀ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ በዛን ጊዜ ንግግሩ
ስለ እርሳቸው ይሁን እንጂ ጠቅላላ አፍሪካን የሚመለከት ስለነበር … ይህን ደግሞ በቃል ወይም በፅሁፍ መያዝ
ስለሚከብድ፣ (ነገር ግን መያዝ ያለበት ቁም ነገር ስለነበረ) ንግግራቸውን በቴፕ ቀድቼ አስቀረሁት፤ ስለ ኢትዮጵያና
ደቡብ አፍሪካ ግንኙነት፣ ለኢትዮጵያ ያላቸው አድናቆት፣ የትምህርት ቆይታቸውና መሰል በርካታ ነገሮች የተካተቱበት

ታሪካዊ ንግግር ነበር፡፡
አሁንም የተቀረፀው ድምፅ አለ?
በአሁኑ ሰዓት ድምፁ ከእኔ ጋር የለም። እንደሚታወቀው አንጋፋው አርቲስት ለማ ጉያ የማንዴላን ሀውልት ሰርተዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ተማሪዎችና ቱሪስቶች ደብረዘይት እየሄዱ ይጐበኙታል፤ የማንዴላን ሀውልት፡፡ ያንን ሀውልት አርቲስት
ለማ ጉያ ለደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ሲያስረክቡ፣ ያንን ታሪካዊ ንግግር አብረው ለኤምባሲው እንዲያስረክቡ ሰጥቻቸው  
አስረክበውታል፡፡
የማንዴላ ሀውልት በሚሰራበት ጊዜ እርስዎም አስተዋፅኦ ማድረግዎን ሰምቻለሁ፡፡ ምን ነበር የእርሶ አስተዋፅኦ?
በወቅቱ በስራ ላይ ነበርኩኝ፡፡ አርቲስት ለማ ጉያ ይህንን ሀውልት ለመስራት ብዙ ደክመዋል፡፡ በገንዘብ እጥረት ስራው

ብዙ ጊዜ ወስዶባቸዋል፡፡ እናም ከደሞዜ ላይ 50ሺህ ብር ለሀውልቱ ማሰሪያ ድጋፍ አድርጌያለሁ፡፡
አሁን ደግሞ ወደ ደህንነት ስራዎት እንመለስና … ስለ ሆስኒ ሙባረክ የግድያ ሙከራ እናውራ፡፡ በወቅቱ ስራ ላይ

ስለነበሩ የግድያ ሙከራው ክፍተት እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ይንገሩኝ?
ዌል! እንደማንኛውም መሪ በድርጅቱ ስብሰባ ላይ ለመካፈል መጡ፡፡ ቡሌት ፕሩፍ (ጥይት የማይበሳው) መኪናቸው ሁሉ

መጥቶ ነበር። እርሳቸው ከመምጣታቸው በፊት የአገሪቱን የደህንነት ሁኔታ ለማረጋገጥ የራሳቸው የደህንነት ሃላፊዎች

(ዲቴይልስ የሚባሉት) መጥተው ሁሉን አጣርተዋል፡፡ የግድያ ሙከራውን ያደረጉት ሰዎች በምን ሁኔታ እዚህ አገር

እንደገቡና ሁኔታው እንደተፈጠረ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ከአውሮፕላን ሲወርዱ ተተኮሰባቸው ተባለ፡፡ የእኛ አገር

ፖሊሶች በጉዳዩ ጣልቃ ገቡ፡፡ በዚህ የተነሳ የተገደሉ ሰዎች አሉም ይባላል፤ እርግጠኞች ግን አይደለንም፡፡ እኛም ሲወራ

ነው እንደማንኛውም ሰው የሰማነው። ነገር ግን የእርሳቸው የግድያ ሙከራ ጉዳይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የደህንነት

ችግር ነው ተብሎ አልተነገረም፤ አይደለምም፡፡
ግን የግድያ ሙከራው ተሳክቶ ሆስኒ ሙባረክ ሞተው ቢሆን ኖሮ ሀላፊነቱን የሚወስደው አካል ማን ይሆን ነበር?
በቀጥታ ሀላፊነቱን የሚወስደው የኢትዮጵያ መንግስት ነው፡፡  
አፍሪካ አንድነት ድርጅት ምንም ተጠያቂነት አይኖርበትም ነበር?
በፍፁም! ሆስት ያደረገው (ያስተናገደው) የኢትዮጵያ መንግስት እንደመሆኑ አጠቃላይ የአገሪቱን የፀጥታ ጉዳይ ማስጠበቅ

የነበረበት መንግስት እንጂ አፍሪካ አንድነት ድርጅት አይደለም። በዚህ ድርጅቱ ወቀሳም ተጠያቂነትም የለበትም፡፡

ምክንያቱም ጉዳዩ የተከሰተው አየር ማረፊያ እንጂ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ውስጥ አይደለም፡፡ ሆስኒ ሙባረክ ወደ

ድርጅቱ ግቢ ገና አልደረሱም እኮ፡፡ የድርጅቱ ግቢ ውስጥ አንድ ነገር ተደርጐና ችግሩ ተከስቶ ቢሆን ተጠያቂው አፍሪካ

አንድነት ድርጅት ይሆን ነበር፡፡
ሆስኒ ሙባረክ በመጡበት ሁኔታ ተመልሰው ወደ አገራቸው ሄዱ፡፡ ከዚያ በኋላም ኢትዮጵያን አልረገጡም …  
እውነት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ አልመጡም፡፡ አሁንም ስልጣናቸውን በህዝብ አመፅ ለቀው ያሉበት ሁኔታ

የሚታወቅ ነው፡፡
ፖሊስ ኮሌጅ ትምህርት ስትማሩ አሰልጣኞቻችሁ የስዊዲን ዜጐች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በኋላ ደግሞ እናንተ መምህርና

አሰልጣኝ ሆናችሁ ነበር፡፡ እስኪ ይህን ሂደት ያጫውቱኝ?
እኛ እጩ መኮንን ሆነን ፖሊስ ኮሌጅ በመጣንበት ወቅት ዋና አስተማሪዎች የስዊድን ፖሊስ መኮንኖች ነበሩ፡፡

ለእያንዳንዱ የስዊድን መምህራን ረዳት ኢትዮጵያዊ መምህራን ነበሩ፡፡ በዚህ መሰረት ከዋና አዛዥነት እስከ ዋና

መምህርነት ያሉት ስውዲኖች ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በላይዘን ኦፊሰር (ምክትል አዛዥ) ደረጃ ያስቀመጣቸው

የኢትዮጵያ ከፍተኛ መኮንኖችም ነበሩ፡፡ በዚህ መልኩ እኛም ረዳት መምህራን ሆነን ነበር የተቀጠርነው፡፡ በኋላ ጃንሆይ

“እስከመቼ የውጭ አገር መምህራን ሀላፊ ሆነው ይቀጥላሉ? ይሄ ነገር እንዴት አልታሰበበትም” የሚል ነገር

በማንሳታቸው፣ የእነሱን ስራ ለመረከብ የታጨነው አስተማሪዎች ቀረብን፡፡ በቀረብን ጊዜ ለእያንዳንዱ አስተማሪ እና

ለእያንዳንዱ ትምህርት ጃንሆይ “የኢትዮጵያ መኮንኖች የማስተማር ፍሬ” በሚል ንግግር አደረጉ፡፡ በዚህን ጊዜ ደስ

ብሏቸው እዚያ ለተሳተፉ መምህራን አዲስ አበባ ውስጥ 500 ካሬ ቦታ ለቤት መስሪያ እንዲሰጥ ወሰኑ፡፡ በጊዜው

የተወሰነውን ቦታ ያገኘም፣ ለማግኘት በሂደት ላይ ያለም ነበረ፡፡ ያገኙትም ሳይሰሩበት በለውጡ ምክንያት ተወሰደ፡፡
የእርስዎም ቦታ ተወስዷል?
እኔ መጀመሪያውኑም አልደረሰኝም፡፡  ለማግኘት በሂደት ላይ ከነበሩበት ውስጥ ነበርኩኝ፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የጡረታ መብት አላረጋገጠም ብለዋል፡፡ አሁን እርስዎ በምንድን ነው የሚተዳደሩት?
ጡረታ የለኝም! ባለቤቴ ዛምቢያ ኤምባሲ ለ25 አመት ሰርታለች፡፡ ገነት ስዩም ትባላለች፡፡ በእርሷ ደሞዝ እንተዳደር

ነበር፡፡ በሌላ በኩል ወንድምና እህቶቼ ውጭ አገር ናቸው፡፡ በብዛት አሜሪካ ነው ያሉት፤ አጠቃላይ 11 እንሆናለን፡፡

በቤተሰብ ደረጃ በመደጋገፍ እንኖራለን፡፡
ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት በውሰት እንደሄዱ ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖሊስ ሰራዊት ውስጥ ቋሚ ሰራተኝነትዎ

እንደተጠበቀ ነግረውኝ ነበር፡፡ በፖሊስነትዎ የሚያገኙት ጡረታስ የለም?
አሁንም ቢሆን ድርጅቱ ዘላቂ ጡረታ የለውም። ፕሮፊደንት ፈንድ የሚባል አለ፡፡ ሰራተኛውና ድርጅቱ የሚያስቀምጡት

ገንዘብ አለ፡፡ እሱ ተጠራቅሞ ስትወጪ ይሰጥሻል፡፡ እርሱም ብዙ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ወደ ድርጅቱ ስሄድ ካርየሬ

ተጠብቆ እንደጓደኞቼ የጡረታ መዋጮ አደርግ የነበረው፡፡ ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ስሄድ በሻምበልነት ማዕረግ

ሲሆን፤ ሙሉ ኮሎኔል እስክሆን ድረስ በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ ስታፍ (ቋሚ ሰራተኛ) ነበርኩኝ፡፡ የኮሎኔልነቱን ማዕረግ

ያገኘሁት በየጊዜው የነበሩት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ፀሀፊዎች ስለ ስራ ብቃቴ፣ ስለ ስነ ምግባሬ፣ ስላለኝ የስራ

ፍቅርና ተያያዥ ጉዳዮች በደብዳቤ ሪፖርት ያደርጉ ስለነበር ያ ተገምግሞ ነው ማዕረጉን በየጊዜው እያደግሁ ያገኙሁት፡፡
ታዲያ እዚህ አገር ይከፍሉ የነበሩት የጡረታ መዋጮ ጉዳይ እንዴት ሆነ?
ልነግርሽ ነው፡፡ ኮሎኔል ሆኜ ድርጅቱን ከለቀቅሁ በኋላ ለረጅም ጊዜ እዛ ብሰራም እዚህም ቋሚ ሰራተኝነቴ ተጠብቆ

የጡረታ መዋጮ ስከፍል ኖሬያለሁ፤ ጡረታዬ ይከበርልኝ ብዬ ጠየቅሁኝ። የፖሊስ ሰራዊት አዛዦች ጡረታው ሊከበርለት

ይገባል ሲሉ ለጡረታ ሚኒስቴር ፃፉልኝ፡፡ “አሟልቶ ከፍሏል፣ በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ የሚታወቅና ከፍተኛ አስተዋፅኦ

የነበረው ሰው ነው፣ ማዕረጉም በፖሊስ ሰራዊት እውቅና የተሰጠው ነው” ብለው አሳምረው ፃፉልኝ፡፡ ነገር ግን ጡረታ

ሚኒስቴር ሊከፍለኝ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
እንደ ምክንያት ያቀረበው ነጥብ አለ?
በዋናነት ያቀረቡት ምክንያት “ስትሰራ የኖርከው ለእኛ ሳይሆን ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ነው፤ ስለሆነም የጡረታ

መብትህ አይከበርም” ነው ያሉኝ። የፖሊስ ሰራዊት “የጡረታ መብቱን አስከብሩ” በሚል አምስት ጊዜ ፃፈልኝ፤ መስሪያ

ቤቱ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ከዚያ በኋላ ጉዳዩ የጡረታ ኮሚሽንን ጉዳይ የሚያዩ ዳኞች ጋ ደረሰ፤ ግን ሊረዱኝ አልቻሉም፡፡
ከዚያ በኋላ የጡረታዎ ጉዳይ በዚህ ተቋጨ ወይስ?
እኔም ስከፍል ኖሬ እንዴት እከለከላለሁ በሚል ጠበቃ ገዝቼ ተከራከርኩኝ፡፡ ክርክሩ ሰባት አመት ወሰደብኝ፡፡ በሰባት

አመት ውስጥ ዳኞቹ በየአመቱ ስለሚለዋወጡ ጉዳዩ እንደ አዲስ እየሆነ ቀጠለ፡፡ በሰባተኛው አመት ላይ “አንተ

የከፈልከው መዋጮ (Contribution) እንጂ ጡረታ ሚኒስቴር በወሰነው መሰረት ስላልሆነ እኛም ይህን መርምረን

ተስማምተንበታል፤ ጡረታ አይገባህም” ብሎ መለሰኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ይህን ሁሉ ብሶቴን ዘርዝሬ በጋዜጣ ላይ ፃፍኩ፡፡  

ጋዜጣውን አምጥቼ አሳይሻለሁ፡፡ አሁን ስራም ጡረታም የለኝም፡፡
ልጆች አለዎት?
ሶስት ልጆች አሉኝ፡፡ ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ልጆች አሉኝ፡፡ ሴቷ አሜሪካን አገር ማስተርሷን ልትሰራ ሄዳለች፡፡

ናሲሴ ግርማ ትባላለች፡፡ አንዱ ልጄ አብዲ ግርማ ይባላል፡፡ እዚሁ የመኪና አስመጪ ኤጀንት በሆነው የወንድሜ ኩባንያ
ውስጥ ይሰራል፡፡ አብሮኝ ነው የሚኖረው፡፡ ሶስተኛው ልጄም አሜሪካ ነው፡፡
እስቲ በማንዴላ ሞት የተሰማዎትን ይንገሩኝ…
በጣም አዝኛለሁ! ምክንያቱም ለእሳቸው የነበረኝ መልካም ስሜቴ የጨመረው፤ ከዚያ ሁሉ ስቃይ በኋላ ፕሬዚዳንት
ሆነው “ለሁለተኛ ጊዜ አልመራም፤ በቃኝ” ብለው ለሌሎቹ ሲለቁ፣ የስልጣን ጥመኛ አለመሆናቸውን ተገነዘብኩ፡፡ በጣም
አከብራቸዋለሁ፡፡
አሁን ምን እየሰሩ ነው?
አነባለሁ፡፡ ጋዜጣ ብትይ መፅሄት የሚቀረኝ የለም፡፡ መፅሀፍም አነባለሁ፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያዊነት ስለማምን ለፖለቲካ
ፍጆታ አይደለም የማነበው፡፡ ከመንቀፍም ከመደገፍም ውጭ ነኝ፡፡ ድርጅቶች ስራ እንስጥህ ቢሉኝ እንኳን አልፈልግም፡፡

ድሮ ባስተማርኳቸው ፖሊሶች በኩል “ስራ እንስጥህ” ተብዬ ነበር፤ አልተቀበልኩኝም፡፡ አሁን እረፍት ነው የምፈልገው፡፡
እረፍት ላይ እንደመሆንዎና ብዙ ነገርም እንደማወቅዎ ለምን መፅሀፉ አይፅፉም?
ይገርምሻል ጀምሬያለሁ፡፡ ብዙ ማጥራት ያሉብኝ ነገሮች ስላሉ ነው የዘገየሁት፡፡ አንዳንድ ነገሮችን በቀጥታ ለመናገር

የማይቻልበት ሁኔታ አለ፤ ግን እያወቅሽው እኮ ነው፡፡ ግን ዞሮ ዞሮ ካጠራኋቸው በኋላ መጽሐፉን እጨርሰዋለሁ፡፡
ከዚያም ለህዝብ ይደርሳል፡፡
ስለዚህ እየፃፉት ባለው መፅሀፍ ውስጥ ብዙ ነገሮችን እንጠብቅ ማለት ነው?
I hope so!!


Read 3317 times