--አሁን የወነጨፉት ቀስት ጲላጦስ በጭራሽ ሊቋቋመው የሚችለው አይነት አይደለም፡፡ አይሁድ ይህንን ያውቃሉ፡፡ ጉዳዩን ፖለቲካ አደረጉት፡፡ ሊያውም የስልጣን፡፡… ጲላጦስ፣ ኢየሩሳሌምን ያስተዳድር ዘንድ የተሾመው በሮማው ቄሳር ነው፡፡ እናም የሿሚውን ክብርና ጥቅም ሊያስጠብቅ ግድ አለበት፡፡--
እነሆ ዛሬ የትንሣኤ በዓል ዋዜማ “ቀዳም ስዑር” ነው፡፡ ቀዳም ስዑርን “ቅዳም ሹር” ይለዋል ሀገሬው- ከራሱ ዘዬ ጋር አልምዶና አዋህዶ፡፡ ሊባኖንን “ሊባኖስ”፣ አሪስቶትልን “አሪስጣጣሊስ”፣ ፕሌቶንን “አፍላጦን” እንደሚለው፡፡ “ነገርን ነገር ይጠራዋል” እንዲሉ፣ ዕለቱን ማሰቡ ያልኩትን አስባለኝ እንጂ ነገሬስ ከዛሬ 2000 ዓመታት በፊት ትናንት አስበነው በዋልነው ዕለተ አርብ ጠዋት፣ በኢየሩሳሌም ከተማ በጲላጦስ ችሎት ስለሆነውና ስለሁነቱ ሰበብ “መጣፍም የሊቅ አፍም” የሚሉትን ቅጥ አስይዞ ማውሳት ነው፡፡
የዕለተ አርቡን ሁነት ሳስብ የክስተቱ ሰበዝ የሚመስሉኝ ሳይበድል መከራ ተቀበሎ የተሰቀለው ኢየሱስ፣ ወንጀለኛ ሆኖ ሳለ “በለስ ቀንቶት” እና በደሉን የሚወርስለት አግኝቶ ከእስር ነጻ የወጣው በርባን እና በአይሁድ ሤራ ተጠልፎና ለፍርድ ተቸግሮ አብዝቶ የዋለለው ጲላጦስ ናቸው፡፡… ኢየሱስ፣ በርባን፣ ጲላጦስ!
ህዝቡን ሲያስተምር የነበረው ኢየሱስ፤“ህዝቡን አስቶአል! አሳምፆአልም! ንጉሥ ነኝ፤ የእግዚአብሔርም ልጅ ነኝ ብሎአል!”… ብለው የካህናትና የህዝቡ አለቆች ባቀረቡበት ክስ ተይዞ፣ ሌሌቱንም ሙሉ በሹሙ በቀያፋ ግቢ መከራን ሲቀበል አድሮ፣ አርብ ጠዋት የኢየሩሳሌም ገዢ በነበረው በጲላጦስ ችሎት በጲላጦስ ፊት ለፍርድ ቆሞአል፡፡ አብዝተው ቢያንገላቱትም ተቃውሞ፣ ለፌዝና ሹፈታቸውም ምላሽ አልሰጠም። ጥያቄዎቻቸው ተንኮልን እንዳቋቱ ያውቃልና ለመመለስ ብዙም አልተበረታታም፡፡…
በርባን ወንጀለኛ ነው፡፡ ሊያውም ከመንጠቅ ነፍስ እስከማጥፋት የደረሰ፡፡ በዚህም በመላው ኢየሩሳሌም የሚታወቅና እጅጉን የሚፈራ ወንበዴ!... ስለሆነም በእስር ቤት ተጥሎ፣ በጥብቅ እየተጠበቀ ነው፡፡ የበርባን ወንጀል የበዛና የከፋ ነውና ከእስር ነጻ ሊወጣ የሚችልበት አንዳችም ምክንያት የለም። ምናልባትም ወደፊት እስከ ሞት ሊደርስ የሚችል ቅጣት ሊደርስበት ይችላል፡፡ ማንም የሚያውቀው ይህንን ነው፡፡ እውነቱ ይህ ነውና፡፡ የሆነው ግን ሌላ ነው፡፡ ለምን?.... የመሆኑ ጓዝና ሰበብ ብዙ ነው፡፡ እንደሚመስለን የበርባን ነጻ መለቀቅ ህዝቡ “በርባንን ልቀቀው!” በማለት አብዝተው ወደ ጲላጦስ ስለጮሁ ብቻ የሆነ አይደለም፡፡ ሤራ አለው፡፡ ከአጋጣሚና ከእድል ያለፈ ሤራ!
ጲላጦስ፤ ኢየሩሳሌምን ያስተዳድር ዘንድ በሮማዊው ቄሳር የተሾመ የኢየሩሳሌም ገዢ ነው፡፡ በመሆኑም በግዛቱ የሚኖረውን ህዝብ ሊያስተዳድር ብቻ ሳይሆን በተለይም የቄሳሩን ጥቅምና ክብር ሊያስጠብቅ ግዴታና ኃላፊነት አለበት፡፡… ከከተማው ህዝብ ጋር በተለይም ከካህናትና ከህዝቡ አለቆች ጋር ብዙ ቅሬታዎች ቢኖሩትም ተንኮለኞችና ቀናተኞች መሆናቸውን ያውቃልና ሁሌም ጉዳያቸውን የሚያየው በጥንቃቄ ነው፡፡ እነሆ ዛሬም አርብ ማለዳ እነዚሁ የአይሁድ አለቆች፣ ኢየሱስ ላይ ያቀረቡትን ክስ መርምሮ ይፈርድ ዘንድ አፉን እንኳ በቅጡ ሳያብስ ተጣድፎ በችሎቱ ተሰይሞአል፡፡
የካህናትና የህዝቡ አለቆችም ጲላጦስ ኢየሱስ ላይ ሞት ይፈርድበት ዘንድ እጅጉን አሲረውና ተስፋ አድርገው በጉጉት በችሎቱ ፊት ቆመዋል፡፡ ኢየሱስ ሊያሰቅለው የሚችል ጥፋት እንዳልፈጸመ ያውቃሉናም ጲላጦስን አጣብቂኝ ውስጥ ከትተው፣ ኢየሱስ ላይ ሞት ሊያስፈርዱ ሤራን አሲረዋል፡፡ ታላቅ ሤራ!
እንግዲህ የሆነው ሁሉ መሆን የጀመረው እንዲህ ነው፡፡ ከሳሾች፣ ተከሳሽና ዳኛ በችሎቱ ቆመዋል። ከእዚህ ጉዳይ ጋር በምንም ሁኔታ የማይገናኘው ወንጀለኛው በርባንም በእስር ቤት ሆኖ የሚሆነውን እየጠበቀ ነው፡፡… እነሆ የክሱን ሂደት ተከትሎ አይሁድ የቀበሩት ፈንጂ መፈንዳት፣ ያደሩት ሤራ መተርተር፣ የቆፈሩት ጉድጓድም የምር ማጥለቅ… ጀመረ፡፡
በውጤቱ በርባን ነጻ ቢወጣም፣ ኢየሱስ ቢሰቀልም፣ አይሁድ ቢደሰቱም… “ሳይወድ” የዚህ ሁሉ ዋና ተዋናይ የሆነው ግን ጲላጦስ ነው- ቃታውን ባይስብም ለሳቢዎች አሳልፎ የሰጠው!... “ሳይወድ” ያልኩት ከነገሩ አብዝቶ ሊሸሽ በመሞከሩ ነው፡፡ እናም የሆነው ሁሉ የሆነበትን ሰበብና ግፊት እንረዳ ዘንድ ጲላጦስን ይዘን እንቀጥል፡፡
የህዝብ አለቆችና የካህናት አለቆችን ተንኮልና ክፋት የሚያውቀው ጲላጦስ፣ በኢየሱስ ላይ የቀረበውን ክስ በጥንቃቄ መመርመር ይዞአል። ለዚህም ክሱንና ምስክሮቻቸውን በጥሞና አድምጦአል፡፡ ኢየሱስንም ስላንተ በሚሉት ላይ “ምን ትላለህ?” ብሎ ደጋግሞ ጠይቆታል፡፡ እርግጡ ይህ ነው፡፡ ጲላጦስ ብዙ ቢደክምም አንዳችስ እንኳን ወንጀል ኢየሱስ ላይ አላገኘበትም፡፡ ግን ደግሞ በነጻ አለቀቀውም፡፡ ያም ቢቀር ቢያንስ ሰቅለው እንዳይገድሉት ማድረግ አልቻለም፡፡ ደግሞም ቀንተውና ተመቅኝተው እንደከሰሱት ያውቃል፡፡ ስልጣኑ እያለው፣ ሊያድነው እየቻለ ነው የወደዱትን እንዲያደርጉበት አሳልፎ የሰጣቸው፡፡ ለምን?
አንዱ መልስ በእርግጠኝነት “በነቢያት የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ” የሚለው ነው፡፡ እሱን ሳንገፋ በዚያች ቅጽበት የሆነው ሁሉ እንዲሆን ግፊት የነበሩ ጉዳዮችን ማውሳታችንን እንቀጥል፡፡ አሁንም ወደሆነው ሰበብ የሚያደርሰን ጲላጦስ ነውና ከእሱ ጋር ነን፡፡
ጲላጦስ፣ለአርብ አጥቢያ ሌሊቱን እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ከሚስቱ ከአብሮቅላ ጋር አድሮ ማልዶ ወጥቶአል፡፡ ሚስቱ ከተኛችበት ስትነቃ ጲላጦስ የለም፡፡ ሌሊቱን በህልሟ ስትሰቃይ አድራለችና ተጨነቀች፡፡ ደግሞም ጲላጦስ የማንን ክስ ለማየት እንደሄደ ታውቃለች፡፡… መልዕክት ላከችለት፡፡ እንዲህ ብላ፤ “በህልሜ አንተን ታላቅ ዘንዶ ሲውጥህ፣ እኔም በእሳት ስገረፍ አይቼአለሁና፣ እዚህ ሰው ላይ ክፉ ነገር እንዳታደርስ፡፡”
እንኳንስ ይህ መልዕክት ተጨምሮለት ኢየሱስ አንዳች እንዳላጠፋ ይልቁንም ከሳሾቹ ተመቅኝተው እንደከሰሱት ጲላጦስ ቢያውቅም ነጻ አላወጣውም። ከሳሾቹንና ያሰለፉትን ህዝብ ፈርቶአል፡፡… እናም በብልሀት ለማለፍ ይልቁንም ከነገሩ ራሱን ለማውጣት ይመስላል ዙሪያ ገባውን ቀዳዳ እየፈለገ ነው፡፡ በዚህ መካከል ታዲያ ከከሳሾቹ አንደበት አንዲት ቃል ወጣች፤ “ከገሊላ ጀምሮ እስከ እዚህ በይሁዳ ሁሉ ያስተምራል” የምትል፡፡
ጲላጦስ፤ “ገሊላ” የምትለውን ቃል ይዞ ማምለጫውን አሰመረ፡፡ የገሊላ ገዢ ሄሮድስ ነው። እናም በወቅቱ በኢየሩሳሌም ይገኝ ወደነበረው ሄሮድስ ኢየሱስን ላከው፡፡ ጲላጦስ ይህን ያደረገው ይህቺን ቀዳዳ በመጠቀም ከነገሩ ለማምለጥ አስልቶ እንጂ ፈልጎና አምኖበት አይደለም፡፡ እንዴት? ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ጲላጦስና ሄሮድስ ጠበኞች ናቸው። የጠባቸውም ምክንያት የግዛት ጥያቄ ነው። በመሆኑም ጲላጦስ ምንም ቢሆን እጁን ለሄሮድስ መስጠት አይፈልግም፡፡… ነገር ግን ሄሮድስ፤ ጲላጦስ የኔን ክብር ተረድቶአል ብሎ በመደሰት ራሱ ጉዳዩን ይዳኛል፤ እኔም ከነገሩ አመልጣለሁ ብሎ ተስፋ አደረገ፡፡ ሆኖም የጲላጦስ ቀመር ሳይሰራ ቀረ፡፡ ሄሮድስ፤ ጲላጦስ ባደረገው ነገር ቢደሰትም ኢየሱስን ጥቂት አንገላቶ ወደ ጲላጦስ መለሰው፡፡
ተስፋው የከዳው ጲላጦስ፤ ከራሱ ጋር ሲመክር ቆይቶ አሁንም ሌላ ማምለጫ መንገድ ፈጠረ፡፡ አቆብቁበው ወደሚጠብቁት ከሳሾች ፊቱን መልሶ፤ “ለፋሲካ በዓል አንድ እስረኛ ልፈታላችሁ ልማድ አለኝና ኢየሱስን ልፍታላችሁ” አላቸው፡፡… ከሳሾቹ ግን ቀላል አይደሉም፡፡ ቀድመው የሸረቡትን ሤራ አንቀሳቀሱት፡፡ ጲላጦስ ይህንን ሊል እንደሚችል ስለገመቱ፣ “ጲላጦስ ይህንን ሲል በርባንን ፍታልን ትላላችሁ” ብለው አሰልፈው ያመጡትን ህዝብ ቀድመው አሳምነዋል፡፡ ስለሆነም ህዝቡ፤ “በርባንን ፍታልን! ኢየሱስን ስቀለው!” አሉ፡፡ በዚህም ጠላታቸውና የሚፈሩት ወንበዴው በርባን ነጻ እንዲሆን አብዝተው ጮሁ፡፡… አንዳንድ ህዝብ እንዲህ ነው፡፡ አጥፊውን ይሻል፡፡
ግን ለምን በርባንን? አንዳንድ መረጃዎች እንደሚነግሩን፣ በርባን ወንበዴ ቢሆንም ከብዙዎቹ የኢየሱስ ከሳሾች ጋር ወዳጅነት ነበረው፡፡ እናም ጥቅማችን ነው የሚሉትን በርባንን ለማስፈታትና ጥቅማችንን ተቃውሞአል ያሉትን ኢየሱስን ለማሰቀል ተጣደፉ፡፡ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ!”… ጲላጦስ በርባንን ፈታው፡፡ ሸንጎና ዳኝነት ፍፁም አይደሉም፡፡ እንዲህ በሤራ ይፈታሉ፡፡ ይክሳሉ ሲባሉ እንዲህ ይበድላሉ፡፡ ይኸው ነው፡፡ አለማጥፋት ብቻውን በሸንጎ ፊት ነጻ አያደርግም!
አሁን ጲላጦስ መላወሻ አጥቶአል፡፡ የሞከራቸው ማምለጫዎች ሁሉ እጅጉን ተዘጋጅተው በመጡት የካህናትና የህዝብ አለቆች እየተዘጉ ነው፡፡… እናም “ኢየሱስን ምን ላድርገው?” የሚለው አቅም የለሽ ጥያቄው በአለቆቹ ተመክሮ ከመጣው ህዝብ፤ “ስቀለው! ስቀለው!” የሚል ምላሽ ተሰጠው፡፡… አንዳች ጥፋት እንዳላገኘበት ደጋግሞ ቢነግራቸውም አልሰሙትም፡፡ ይልቁንም ከሳሾቹ የመጨረሻ የሆነውን የቃላት ቀስታቸውን ወነጨፉ፡፡ እንዲህ ብለው፤ “የእስራኤል ንጉሥ ነኝ ይላል፡፡ ለቄሳርም ግብር አትስጡ ብሎአል፡፡ እኛ ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም፡፡ ካልሰቀልከው አንተ የቄሳር ወዳጅ አይደለህም!…”
አሁን የወነጨፉት ቀስት ጲላጦስ በጭራሽ ሊቋቋመው የሚችለው አይነት አይደለም፡፡ አይሁድ ይህንን ያውቃሉ፡፡ ጉዳዩን ፖለቲካ አደረጉት። ሊያውም የስልጣን፡፡… ጲላጦስ፣ ኢየሩሳሌምን ያስተዳድር ዘንድ የተሾመው በሮማው ቄሳር ነው። እናም የሿሚውን ክብርና ጥቅም ሊያስጠብቅ ግድ አለበት፡፡ እያሉት የነበረውም ይህንን ነው፡፡ ጲላጦስም ነገሩ ስለገባው በሚገባ ተደናገረ፡፡… እናም ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ሆኖ የመጨረሻ ሙከራውን ይፈጽም ዘንድ ተነሳ፡፡ ኢየሱስን አስገረፈው፡፡… ጲላጦስ ኢየሱስን ሲያስገርፍ አሁንም አንድ መውጫን ተስፋ አድርጎአል፡፡ በሕጋቸው የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀልም አይገረፍም፡፡ እናም ካስገረፍኩት ይተዉታል፣ አይሰቅሉትም… ብሎ አስቦ ነበር፡፡
የኢየሱስ ከሳሾች ግን ይህ አልገታቸውም፡፡ ይልቁንም ሤራቸው በመስራቱ እየተደሰቱ (ከሕግ ውጪ) በሮማ ግዛት ሁሉ ተፈጽሞ የማያውቀውን ሊፈጽሙበት ኢየሱስን እጃቸው አደረጉት፡፡ ይህንን የተረዳውና አቅሙን የጨረሰው ጲላጦስ የማይጠቅምና ያልረባ ነገር አደረገ፤ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንፁህ ነኝ” ብሎ እያልጎመጎመ እጁን ታጠበ፡፡ አቅም ያጣ ገዢ!
ኢየሱስን እያንገላቱ ወስደው በመስቀል ላይ ሰቀሉት፡፡ ጲላጦስ ግን ከዚህ ሁሉ ሽንፈት በኋላ አሁንም ተስፋ የቆረጠ አይመስልም፡፡ ኢየሱስ በተሰቀለበት መስቀል ራስጌ ላይ “ኢ.ና.ን.አ.” (የናዝሬቱ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ) የሚል ጽሑፍን አሰቀለ፡፡ የኢየሱስ ሰቃዮች፤ “ለምን እንዲህ ብለህ ትጽፋለህ?” ቢሉትም “የጻፍኩትን ጻፍኩ!” አላቸው፡፡ ጲላጦስ ለምን ይህንን ጻፈ? መልሱን ለማወቅ ቀድሞ ብዙ መጠየቅ ግድ ነው፡፡ ይህንን የመሰሉ ጥያቄዎች፡፡ ጲላጦስ ከዳኝነቱ ለመውጣትና ከነገሩ ለመሸሽ ለምን ፈለገ? ኢየሱስንስ ከመሰቀል ሊያድነው ለምን አብዝቶ ደከመ? ለምን...?
ሚስቱ ህልሟን ስለላከችበት ይሆን? ወይስ የከሳሾቹን ክፋት ያውቅ ስለነበር? ወይንስ ኢየሱስ ላይ ጥፋት ስላላገኘበት?... ያም ሆኖ ልቡ እንደ ብራና በየአቅጣጫው ተወጥራ ሲንገላታና ሲረታ ያረፈደው ጲላጦስ፣ በመጨረሻ የልቡን እምነትና ሀሳብ ኢየሱስ በተሰቀለበት መስቀል ራስጌ ላይ በመስቀል ያሸነፈ ይመስላል፡፡ “ኢ.ና.ን.አ”
መልካም ትንሣኤ!!