Sunday, 10 May 2015 15:29

ህፃናትን በዘመናዊ መንገድ የመቅረፅ ጅማሮ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

በሕፃናት አስተዳደግ ዙሪያ ጥናትና ምርምር ያደረጉ አንዳንድ ምሁራን፣ የሰው ልጅ ማንነት ወይም የወደፊት ሰብዕና የሚቀረፀው ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ባለው ዕድሜ ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የለም ከሁለት እስከ ሰባት ዓመት ነው ይላሉ፡፡
የሁለት ዓመት ልዩነት ብዙ አያከራክርም፡፡ ዋናው ነጥብ የሕፃናት የወደፊት ማንነት የሚቀረፀው በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ መሆኑን መገንዘብ ነው፡፡ ልጅ ከበላ፣ ከጠጣ፣ ከለበሰ ምን ያስፈልገዋል? የሚለውን ባህላዊና ልማዳዊ የልጆች አስተዳደግ በዘመናዊ ዘዴ መተካት የግድ ነው፡፡ ልጅ ምንም አያውቅም? በማለት ሰብዕናቸውን የሚጐዳ ነገር ከመናገርና ከመተግበርም መቆጠብ አለብን፡፡ የ6 ወር ሕፃን፣ ቤተሰቦቿ፣ በሞባይል ሲያወሩ አይታ ሞባይል ወይም ሌላ ነገር አንስታ ወደ ጆሮዋ ስትወስድ፣ የ2 ዓመት ልጅ ወላጆቹ የማይችሉትን የሞባይል ጌም አቀላጥፎ ሲጫወት ቢያዩ አይገረሙ። ሕፃናት ብዙ ያውቃሉ፡፡ ቢያውቁም ግን መልካሙን የሚያሳያቸውና ወደ ጥሩ ነገር የሚመራቸው ይፈልጋሉ፡፡
ሕፃናት፣ ከወላጆች ቀጥሎ የሚያገኙት አሳዳጊ ሞግዚቶችን ነው፡፡ ትንሽ ከፍ ብለው አፀደ ሕፃናት ሲገቡ ደግሞ የአፀደ ሕፃናት መምህራንና ሞግዚቶች ይቀበሏቸዋል፡፡ እነዚህ ሞግዚቶችና መምህራን ሕፃናቱን በጥሩ መንገድ ለመምራትና የወደፊት ማንነታቸውን ለመቅረፅ፣ የልጆችን አስተዳደግና ሥነልቡና መማርና ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ችግር በአንዳንድ አፀደ ሕፃናት ይታያል፡፡
አብ ሁለገብ ማሠልጠኛ ማዕከል በደፈናው ችግሩ እንዳለ ከመግለፅ ባሻገር የችግሩ ስፋት ምን ያህል እንደሆነ፣ መምህራንና ሞግዚቶች ምን ዓይነት በሳይንስ የተደገፈ ሥልጠና እንደወሰዱ ለማወቅ በሕፃናት አስተዳደግ፣ ክብካቤ፣ ክትትል፣ አመጋገብ፣ ጤና፣ ሥነልቦና… ማስትሬትና ዶክትሬት ባላቸው ምሁራን መመዘኛ መስፈርቶች አዘጋጅቶ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ባሉ አፀደ ሕፃናት ጥናት ማድረጉ የማዕከሉ  የሥልጠና ኃላፊ አቶ መሐመድ ሰዒድ ተናግረዋል፡፡
በጥናቱ ያገኘነው ውጤት ከገመትነው በላይ ነበር ያሉት አቶ መሐመድ፤ በአገሪቷ፣ በመንግሥትም ሆነ በግል ለአፀደ ሕፃናት ሞግዚቶችና መምህራን ሥልጠና የሚሰጥ ተቋም ስለሌለ፣ ሞግዚቶቹ በልምድ ከሚያውቁትና ከሥራ መምሪያ ውጭ ሳይንሳዊ ሥልጠና እንዳላገኙ ማረጋገጥ ቻልን፡፡ የነገ አገር ተረካቢ ሕፃናት ሞግዚቶችና መምህራን ሳይንሳዊ ሥልጠና ቢያገኙ ጥሩ መሠረት ይሆኗቸዋል በማለት የጥናት ውጤቱን ለየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አቀርብን ብለዋል፡፡
ከመስተዳደሩ ያገኙት ግብረ መልስ አበረታች ስለነበር በዚህ ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት ለማጥበብና የዜግነት ግዴታቸውን ለማበርከት ፕሮጀክት ቀርፀው፣ ከት/ሚር የሞግዚቶች ሥልጠና ጋር አቀናጅተው ሳይንሳዊ ሥልጠና መስጠት እንደጀመሩ ባለፈው እሁድ ለ2ኛ ጊዜ በሞግዚትና በአፀደ ሕፃናት ረዳት መምህርነት ያሰለጠኗቸውን 126 ተማሪዎች ባስመረቁበት ወቅት ገልፀዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር በየካ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ አፀደ ሕፃናት ት/ቤቶች ለተውጣጡ 200 ሞግዚቶችና ረዳት መምህራን የ3 ወር ሥልጠና ሰጥተው በሰርቲፊኬት ማስመረቃቸውን ጠቅሰው፣ የ2ኛ ዙር ሠልጣኞች ከየካ፣ ከላፍቶና ከቦሌ ክፍለከተማ አፀደ ሕፃናት ት/ቤቶች የተውጣጡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ማዕከሉ የሚሰጠው ሥልጠና በሕፃናት ሥነ ልቡና (ሳይኮሎጂ)፣ በትምህርት አሰጣጥ፣ በሕፃናት አያያዝና እንክብካቤ፣ በንፅህና አጠባበቅ፣ በመጀመሪያ ደረጃ ዕርዳታ (ፈርስት ኤይድ) አሰጣጥ፣ በሕፃናትና በሞግዚቶች መካከል መኖር ስላለበት ትስስር (ፍቅር) ሲሆን ኮርሶቹ የሚሰጡት ጥናቱን ባካሄዱት፣ ኮርሶቹን ባዘጋጁትና በዘርፉ ጥልቅ እውቀት ባላቸው ምሁራን እንደሆነ ታውቋል።
ሠልጣኞቹ ወደ እኛ ሲመጡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሲኖሩ የለመዱትንና ያዳበሩትን ልማድ ይዘው ነው ያሉት አቶ መሐመድ፤ ይዘውት የመጡትን ባህላዊና ልማዳዊ ጐጂ የሕፃናት አስተዳደግ በሳይንሳዊ ስልጠና ከውስጣቸው እንዲፍቁ አድርገን እናሠለጥናለን፡፡ እያንዳንዱ ክህሎት የሚዳብረው በሂደት ስለሆነ ሁሉም ሠልጣኞች በሂደት ተመሳሳይ እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው እናደርጋለን ብለዋል፡፡ ሕፃናቱም የወላጆቻቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ባህርይ ይዘው እንደሚመጡ ኃላፊው ጠቅሰው፣ ሞግዚቶቹ፣ እነዚህን የተለያየ ባህርይ ያላቸውን ሕፃናት እንዴት በፍቅር ቀርበውና ፍቅር ሰጥተው እንዲወዷቸውና እንዲቀርቧቸው ማድረግ አለባቸው፤ አንዳንድ ሕፃናት በትንሽ ነገር ሆድ እንደሚብሳቸው እንደሚነጫነጩ ጠቅሰን ሌላው ደግሞ ተንኳሽና ተደባዳቢ፣ አንዳንዱ ጐበዝ፣ ሌላው ሰነፍ፣ ስለሚሆነው ምን ማድረግና እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው እናስተምራቸዋለን በማለት አስረድተዋል፡፡
ከየካ ክፍለ ከተማ የመጣችው መሠረት ብርሃኑ ዕድሜ 30 ሲሆን በመምህር ረዳትነት ነው የለጠነችው። በካይዘን ማኔጅመንት ፅንሰ ሐሳብ መሰልጠኗን ጠቅሳ ሕፃናቱን እንዴት መንከባከብና ችግሮቻቸውን እንዴት መረዳት እንዳለባቸው ግንዛቤ ማግኘቷ ገልጻለች። ከዚህም በላይ ልጆች ምንም አያውቁም የሚባለው ትክክል ስላልሆነና ልጆች ብዙ ነገር ስለሚያውቁ ትኩረት መስጠት እንዳለባት መረዳቷን ተናግራለች፡፡
“ሕፃናት ከቤት እንደወጡ የምንረከባቸው እኛ ነን፡፡ ከሥልጠናው ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ፡፡ ሕፃናት የኅብረተሰቡን መልካም እሴቶች እንዲያውቁ አደርጋለሁ” ያለችው በሞግዚትነት የሠለጠነችው የ35 ዓመቷ ሐና ዘውዴ ናት፡፡ ሕፃናት አስቸጋሪ መሆናቸውን በማስተምርበት ት/ቤት አውቀዋለሁ፡፡ ዕድሜያቸው ሲጨምር ባህሪያቸው እንደሚለዋወጥ ከዚህ ስልጠና ተረድቻለሁ፡፡ ስለዚህ ሁሉንም በትዕግሥት እየተቀበልኩ በፍቅር አስተናግዳቸዋለሁ ብላለች።
ወ/ሮ ይመኙሻል ሰብስቤ የ50 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ ከልጆች ጋር መዋልና የገቢ አቅማቸው አነስተኛ የሆኑ ቤተሰብ ልጆችን ማስተማር ይወዳሉ። የኮንዶሚኒየም ዕጣ ደርሷቸው አሁን የሚኖሩት ሰሚት አካባቢ ነው። ሰፈር ከመልቀቃቸው በፊት ቀበና አካባቢ ወላጅ የሌላቸውንና የድሃ ልጆችን በራቸው ላይ መጠለያ ሠርተው ለ8 ዓመት በነፃ ማስተማራቸውን ተናግረዋል፡፡ አንዲት የድሃ ልጅ እናቷ መንገድ ላይ እየለመኑ የሚያገኙት ስለማይበቃቸው አንዳንድ ጊዜ እሳቸው ጋ እየሄደች ትመገብ ነበር፡፡ እናቷ ሲሞቱ ልጅቷን እቤታቸው አስገብተው እያስተማሩ 9ኛ ክፍል እንደደረሰችላቸው ገልፀዋል፡፡
ቀደም ሲል በሕፃናት መምህርትነት ሰልጥነው ስለነበር አሁን በሚኖሩበት ሰሚት አካባቢ ሸቡ ኤጀርሳ በተባለ ት/ቤት እያስተማሩ ነው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት ይሰጣል ሲባል የእውቀት ትንሽ የለውም በማለት ሥልጠናውን ጀምረው የማያውቁትን ከፍተኛ እውቀት መገብየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ልጆች በዕድሜ ደረጃ መያዝ እንዳለባቸው፣ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ማወቅ፣ እንዴት መንከባከብና ንፅህናቸውን መጠበቅ ከወላጅ ይበልጥ ሞግዚት መከታተል እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ የምግብ መያዣ ዕቃቸው ንፁህ መሆኑንና ያለመሆኑን መቆጣጠር፤ በሽታና ጠረን ማወቅ እንዳለባቸው፣ የልጆቹ ባህርይ፣ የምግብና የጨዋታ ፍላጐታቸው ምን እንደሆነ ማጥናት እንደሚገባቸው፣ በካይዘን ማኔጅመንት፣ በሕፃናት አስተዳደግና በሳይኮሎጂ ትምህርት ያገኙ በርካታ እውቀት መሠረታዊና ለሥራቸውም የሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሌላው ጠቃሚ ትምህርት የሕፃናት ጤና ስለሆነ ልጆች እጃቸውንና ጣቶቻቸውን እንዴት መታጠብ እንዳለባቸው፣ ሕፃናት ሳሙና በእጃቸው ላይ መፈግፈግ ስለማይችሉ ፈሳሽ ሳሙና መጠቀም እንዳለባቸው፣ በት/ቤቱ ፈሳሽ ሳሙና ባይኖር እንኳ ሳሙናውን ቀጥቅጠን በፈላ ውሃ ውስጥ በመበጥበጥ በሃይላንድ ውሃ መያዣ ውስጥ ጨምረን በመክደን ክዳኑን በስተን ፊጭጭ በማድረግ ልጆች በሰልፍ መጥተው እጃቸውንና አፋቸውን እንዲታጠቡ ማድረግን የተማርኩት እዚህ ማሰልጠኛ ነው በማለት ከሥልጠናው ያገኙትን እውቀት አስረድተዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ያሉት አፀደ ሕፃናት ሙያው ባላቸው ሞግዚቶች እንዲጠቀሙ የማድረግ የአጭር ጊዜ ዕቅድ አለን ያሉት የሥልጠና ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ አሳየ ተክሉ፤ በረዥም ጊዜ ዕቅዳቸው በ2012 ዓ.ም በመላ አገሪቷ ያሉ አፀደ ሕፃናት የሙያው ባለቤት በሆኑ መምህራንና ሞግዚቶች እንዲሰለጥኑ ማድረግ እንደሆነ ገልፀዋል።
አቶ አሳየ ሥልጠናውን ሲጀምሩ ሁለት ችግሮች አጋጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አንደኛው ዘርፉ አዲስ በመሆኑ ከቴክኒክና ሙያ ጽ/ቤት ባለሙያዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የአፀደ ሕፃናት መምህራንና ሞግዚቶች ሳይንሳዊ ሥልጠናና ብቃት ያስፈልጋል የሚለውን ሃሳብ ለማስረፅና ለማሳመን ከፍተኛ ችግር ገጥሟቸው ነበር፡፡
ሌላኛው ችግር አፀደ ሕፃናት ማስተማሪያ ት/ቤት ባለቤቶች የፈጠሩባቸው ችግር ነበር፡፡ ይኼውም ሠራተኞቻቸው ሳይንሳዊ ሥልጠና ካገኙ ባለሙያ ስለሚሆኑ የተሻለ ክፍያ ፍለጋ ጥለውን ይሄዳሉ በሚል ስጋት ሰራተኞቹ ወደ ስልጠናው እንዳይሄዱ ያደርጉ ነበር፡፡ ሥልጠናው ከተጀመረ በኋላ ከሁለቱም ክፍሎች ያገኙት ምላሽ ጥሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡         

Read 5231 times