Saturday, 11 July 2015 11:56

‹‹የታሪክ መጨረሻ እና የመጨረሻው ሰው››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

‹‹ማንም ሰው ሊገምት እንደሚችለው፤ ንጉሡ ለሉዓላዊ የንጉስነት መብታቸው ፍፁም ቀናተኛ ናቸው፡፡
ይህን ሉዓላዊ ሥልጣናቸውን በሆነ መንገድ የሚነካ በመሰላቸው ጉዳይ ላይ መለሳለስ አያውቁም--”

የመጨረሻው ክፍል
አውሮፓውያን ለጥቁር ህዝብ ያላቸው ንቀት የበዛ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ፤ ቀና አመለካከት እና ከቴዎድሮስ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ያለው ፕላውዴን ወደ ለንደን ይልከው የነበረው መልዕክት እንኳን፤ ይኸው መጥፎ ንቀት የሚታይበት ነበር፡፡ የአክብሮት ሐሳቦችን በያዙት በእኒያ የፕላውዴን ደብዳቤዎች ውስጥ የአውሮፓ በሽታ የሆነውን የንቀት ስሜት በግልፅ ማየት ይቻላል፡፡
‹‹ማንም ሰው ሊገምት እንደሚችለው፤ ንጉሡ ለሉዓላዊ የንጉስነት መብታቸው ፍፁም ቀናተኛ ናቸው። ይህን ሉዓላዊ ሥልጣናቸውን በሆነ መንገድ የሚነካ በመሰላቸው ጉዳይ ላይ መለሳለስ አያውቁም፡፡ ሆኖም፤ በእኩያነት አቋም ከምዕራብ ኃያላን መንግስታት ጋር ግንኙነት የመመስረት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፤ በቅርቡ አምባሳደሮቻቸውን ወደ እነዚህ ሀገራት የመላክ ሐሳብ አላቸው›› ሲል ለሐገሩ መንግስት ደብዳቤ የላከው ፕላውዴን፤ አክሎ፤ ‹‹አስቸጋሪ የሆነው ዓመላቸው የሚመነጨው ከዚሁ ቀናተኛነታቸው ነው፡፡ አለማወቅን እየተመገበ የሚፋፋው ኩራታቸው፤ በዓለም ላይ እንደሳቸው ያለ ታላቅ ንጉሥ መኖሩን ለመቀበል የሚቸገሩ ሰው አድርጓቸዋል›› በማለት ፅፏል፡፡
እርግጥ፤ አፄ ቴዎድሮስን፤ የለውጥ አራማጅ እና ባለራዕይ መሪ አድርገው የሚመለከቱ ፀሐፊዎች የመኖራቸውን ያህል፤ ይህን የማይቀበሉና አፄ ቴዎድሮስ የዘመነ መሳፍንት የመጨረሻው መሪ እንጂ የአዲስ ዘመን አዋጅ ነጋሪ መሪ አይደሉም በሚል የሚከራከሩ መኖራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ እንደ ሪቻርድ ፓንክረስት እና ዶናልድ ክረሚ ያሉ የታሪክ ፀሐፊዎች ግን፤ ‹‹አፄ ቴዎድሮስ፤ የዘመናዊ ኢትዮጵያ የታሪክ የመጀመሪያው ምዕራፍ ገላጭ መሪ እና የዘመናዊት ኢትዮጵያ አባት ናቸው›› ይላሉ፡፡
የአፄ ቴዎድሮስን ታላቅ የጦር ሰውነት፣ በቅፅበት የመወሰን ችሎታ እና አስተዋይነት ብቻ ሣይሆን፤ ታላቅ ህልም የነበራቸው መሪ መሆናቸውን በርካታ ፀሐፊዎች ይመሰክራሉ፡፡ ሆኖም፤ በተከታታይ በተቀዳጁት ወታደራዊ ድል በተወሰነ ደረጃ የሐገሪቱን አንድነት ማረጋገጥ ቢችሉም፤ በተከታታይ ያገኙትን ወታደራዊ ድል ለማደላደል እና የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያግዝ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ዕውቀት እና ችሎታ እንዳልነበራቸው ይገልፃሉ፡፡ በእንግሊዛዊያን የታሪክ ፀሐፊዎች እና ጋዜጠኞች አስተያየት፤ ለንጉሡ ጥሩ መካሪ እና ዘካሪ ነበሩ የሚባሉት ባለቤታቸው የወ/ሮ ተዋበች እና እንግሊዛዊው ወዳጃቸው ጆን ቤል እና ፕላውደን በሞት መለየታቸው ብዙ ጎድቷቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ መካሪ አጥተው፣ ሁሉን ጠርጣሪ ሆነው፣ በቅፅበታዊ ስሜት የሚገፉ እና ያለ ምክር የሚወስኑ እየሆኑ በመሄዳቸው ብዙ ነገር እንደተበላሸም ያመለክታሉ፡፡
ፕላውዴን፤ ገና አፄ ቴዎድሮስ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት፤ በራስ ዓሊ ዘመን በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ቆንስላ ሆኖ ቆይቶ፤ ‹‹እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ግንኙነት ብትመሰርት ተጠቃሚ ትሆናለች›› የሚል ሐሳብ ለእንግሊዝ መንግስት አቅርቦ ጉዳዩ ስለታመነበት የንግድ ስምምነት እንዲፈራረም ወደ ኢትዮጵያ ተልኮ ነበር። ከቴዎድሮስ በፊት ከራስ ዓሊ ጋር የንግድ ስምምነት ለመፈራረም ጥረት ሲያደርግ፤ ራስ ዓሊ ‹‹አሁን ይኸ ምን ይረባል ብለህ ነው›› እያሉ ፍፁም ደስ ሳይላቸው ከፕላውዲን ጋር የንግድ ስምምነት ቢፈራረሙም፤ ብዙ ሳይቆዩ በአፄ ቴዎድሮስ ስልጣናቸው ተነጠቀ፡፡
ፕላውዲን ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ተመሣሣይ የንግድ ስምምነት ለማድረግ ብዙ ቢደክምም፤ አፄ ቴዎድሮስ እምቢ አሉት፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከፕላውዴን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ቢኖራቸውም ከእንግሊዝ ጋር የንግድ ስምምነት ለመፈራረም ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ የኢትዮጵያ ነገስታት አውሮፓውያንን በጥርጣሬ ይመለከቱ ስለነበር፤ በዚህ የተነሳ፤ ራስ ዓሊም ሆኑ አጼ ቴዎድሮስ የአውሮፓ ቆንስሎች በኢትዮጵያ ምድር እንዲቀመጡ ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ስለዚህ፤ የአምባሳደር ተልዕኮ የነበራቸው አውሮፓውያን መቀመጫ የቱርክ ግዛት የነበረችው ምፅዋ ነበረች፡፡
በስምምነቱ አለመፈረም የተበሳጨው የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፤ ‹‹በአስቸኳይ ወደ ምፅዋ እንድትወርድ ይሁን›› የሚል ትዕዛዝ በመላኩ፤ ፕላውዴን በወቅቱ በቱርክ እጅ ወደ ነበረው ምፅዋ ሲወርድ በመንገድ ያደፈጡ ሽፍቶች ተኩሰው አቆሰሉት፡፡ በዚሁ ጥቃት ክፉኛ የቆሰለው ፕላውዴን በ1860 ዓ.ም (እኤአ) ለሞት በቃ፡፡
ከዚያ በኋላ፤ ንጉሡ በማንንም ላይ እምነት ማሳደር የማይችሉ ሰው በመሆናቸው፤ እርሳቸው እንደተመኙት፤ የኢትዮጵያ መድኅን በመሆን ፋንታ አጥፊ የሆኑበት ሁኔታ እንደ ተፈጠረ እና ሠራዊታቸውም በህዝቡ ዘንድ መርገምት እና ስጋት ሆኖ መታየት መጀመሩንም የታሪክ ፀሀፊዎች ያወሳሉ፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ሠራዊት ለዘመቻ ወጥቶ ሲመለስ፤ በየጊዜው ቁጥሩ እየጨመረ ስለሚሄድ፤ በመንግስት ግምጃ ቤት በነበረው ሐብት ለመተዳደር የማይችል እየሆነ በመምጣቱ፤ የሠራዊቱን ቀለብ ለመሸፈን ሲባል በቤተክህነት እጅ ይገኝ የነበረን ጦም የሚያድር መሬት መውሰድ ጀመሩ፡፡ እንዲሁም ከህዝቡ መሬት እየነጠቁ፤ የቤት የለሽ እና የስርዓተ - አልበኛውን ሰው ቁጥር ከፍ አደረጉት ይላሉ፡፡                
በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን፤ ለስብከት የመጡ አውሮፓዊ የኢየሱሳውያን፣ የፕሮቴስታንት እና የካቶሊክ ቄሶች  በኢትዮጵያ ይኖሩ ነበር፡፡ ሆኖም፤ አፄ ቴዎድሮስ ከአውሮፓ ይፈልጉ የነበረው ሰባኪዎችን ሳይሆን ሙያተኞችን ነበር፡፡ አፄ ቴዎድሮስ እንዲያ የሚጠሏቸውን ሚሲዮናውያንን በሐገራቸው እንዲኖሩ የፈቀዱት ጥበብን ፍለጋ ነበር፡፡ የሐይማኖት ሰዎቹን የሚጠሏቸው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንድም፤ አፄ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያውያን ከኦርቶዶክስ ሌላ ተመራጭ ሐይማኖት የለም ብለው ያስቡ ስለ ነበር ነው፡፡ አንድም፤ የተለያዩ ሐይማኖቶች መኖር የሐገሪቱን ህዝብ ለክፍፍል እና ለግጭት የሚዳርግ ችግር ይፈጠራል የሚል እምነት ስለነበራቸው ነው፡፡
በተለያዩ የክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች መካከል ፉክክርና ፍትጊያ ተፈጥሮ ብዙ ችግር መፈጠሩን የሚያወሱ አውሮፓውያን ፀሐፊዎች፤ የእነዚህ ተፎካካሪ ሐይማኖቶች አድራጎት በኢትዮጵያ ላይ ዘመን የተሻገረ ተፅዕኖ አስፍሯል ይላሉ፡፡ በአጠቃላይ ለውጭ ሰዎች (ክርስትያን ቢሆንም ባይሆንም) ጥላቻና ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው አድርጓል ሲሉም ፅፈዋል፡፡ ‹‹አበሾች መሠሪ፣ ተጠራጣሪ እና ቀናተኞች ናቸው›› የሚሉት እነኚሁ ፀሐፊዎች፤ ‹‹ጃዝዊቶች፤ በርካታ ምዕተ ዓመታት ማለፍ እንዲዘነጋ ያላደረገውን ትምህርት አስተምረዋቸዋል ሄደዋል›› በማለት አስተያየታቸውን አስፍረዋል፡፡  
አፄ ቴዎድሮስ፤ አውሮፓውያኑ ሰባኪዎች፤ ፈላሾችን (ቤተ-እስራኤላውያን) እና የክርስትና ሐይማኖት ተከታይ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንን እንዲሰብኩ የፈቀዱ ቢሆንም፤ ወደ ክርስትና የሚገቡትን ሰዎችን የሚያጠምቁት ግን የኦርቶዶክስ ካህናት ብቻ እንዲሆኑ አድርገዋል። ፕሮቴስታንት እና ካቶሊኮቹ ቄሶች እንዲሰብኩ እንጂ እንዲያጠምቁ አልፈቀዱላቸውም፡፡ በአንፃሩ፤ ሚሲዮናውያኑ ጋፋት ላይ የማይፈልጉትን ምድራዊ ተግባር በማከናወን የተጠመዱት፤ ‹‹ውሎ - አድሮ፤ አጼ ቴዎድሮስ እንደ ልብ እንድንሰብክ ይፈቅዱልን ይሆናል›› በሚል ተስፋ ነበር፡፡
ሆኖም፤ የአጼ ቴዎድሮስ ዋና ፍላጎት ሙያተኛ ከሆኑት አውሮፓውያን ዕውቀቱን በመቅሰም፤ የሐገሪቱን የቴክኖሎጂ አቅም በመገንባት፤ ኢትዮጵያን ከውጭ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥገኝነት ነፃ ማውጣት እንደ ነበር ምሁራን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ቴዎድሮስ ከውጭ የሚመጣባቸውን ጫና ለመቋቋም፤ በቅድሚያ ህዝባቸውን መለወጥ እና ማሻሻል በጣም አስፈላጊ መሆኑን የተረዱ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ንጉስ ናቸው›› የሚሉት ዶናልድ ክረሚ፤ የአፄ ቴዎድሮስ ሐገርን የማዘመን ጥረት ትኩረት ያደረገው፤ ነባሩን የሐገሪቱን ህግ መሠረት አድርገው በመንግስት እና በቤተክህነት መካከል አንድነት በመፍጠር፣ ለረጅም ጊዜ በዘለቀ ጦርነት ፈራርሰው የጠፉትን ነባር መንግስታዊ ተቋማት እንደገና በማቆም፣ የህዝቡን ሞራላዊ አቋም በማሻሻል እና ሠራዊቱን በተሻለ መሠረት መልሶ በመገንባት፤ እንዲሁም ከአውሮፓ ሐገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመመስረት ላይ እንደነበርም ያመለክታሉ፡፡
‹‹የአፄ ቴዎድሮስ ውድቀት እና ምናልባትም ኃይለኝነት ለሚንፀባረቅበት ባህርያቸው መነሻ ምክንያት የሆነው፤ በህግ የበላይነት ላይ በተመሠረተ አሰራር ሥልጣንን ለሌሎች ማከፋፈል አለመቻላቸው ነው›› የሚሉት ዶናልድ ክረሚ፤ ‹‹በዚህ የተነሳ አፄ ቴዎድሮስ፤ ሐገር ከመምራት እና ህዝብን ከማስተዳደር ይልቅ፤ የአመጽ እሳትን በማጥፋት ጊዜያቸውን ጨርሰዋል›› ሲሉ ፅፈዋል።
እንደ ዶናልድ ክረሚ ያሉ አንዳንድ የታሪክ ፀሐፊዎች፤አፄ ቴዎድሮስ አውሮፓውያኑ የሚያሳይዋቸው ዝቅተኛ ግምት፤ በእነሱ መካከል ይታይ የነበረው የውስጥ ሽኩቻ እና ትንቅንቅ፤ እንዲሁም ፖለቲካዊ ሴራቸው በተለያየ መልክ እየተገለጠ፤ ግራ እንዲጋቡና ትኩረታቸውን እንዲረበሽ አድርጎታል ይላሉ፡፡
የአውሮፓውያን የፖለቲካ አጋርነት በምን ላይ እንደሚመሰረት ያልተረዱት እና በ‹‹ክሪሚያው›› ጦርነት (Crimean war) ‹‹ክርስቲያናዊ ሐገራት›› ብለው የሚያስቧቸው ፈረንሳይ እና እንግሊዝ፤ ኢስላማዊ አድርገው ከሚመለከቷት ቱርክ ጋር አብረው፤ ሌላዋን ክርስቲያናዊ ሐገር ሩሲያን ለማጥቃት መሰለፋቸው፤ ለአፄ ቴዎድሮስ በጣም ግራ አጋቢ ጉዳይ ነበር፡፡ የፖለቲካ አጋርነት በሐይማኖት ላይ ብቻ እንደማይመሠረት ያልተረዱት አፄ ቴዎድሮስ፤ ይህን የአውሮፓውያን ድርጊት ለመረዳት ወይም ለመቀበል ተቸግረዋል፡፡
አፄ ቴዎድሮስ በምዕራባውያኑ ነገር ግራ የሚጋቡትን ያህል፤ በአካል የሚያውቋቸው ምዕራባውያንም በአፄ ቴዎድሮስ ዓመል በእኩል ደረጃ ግራ ይጋቡ ነበር፡፡ ፍፁም ደግ እና ርኅሩህ ሰው ናቸው ለማለት የጀመሩትን ዓረፍተ ነገር ሳይጨርሱ፤ ፍፁም ጨካኝ እና አረመኔ ሊሏቸው ይገደዳሉ፡፡ አንድም ቀን እንደ ንጉስ ክብር እና ማዕረግ ያለው ኑሮ ሳይመኙ የህዝባቸውን ህይወት ለመለወጥ ከተራ ሰው የማይሻል ኑሮ እየኖሩ ዘመናቸውን የገፉ፤ አጥፍቻለሁ ማለት የማይከብዳቸው፣ በኃይማኖተኛ ሰው ዘንድ ሊታይ የሚችል ትህትና ያላቸው ሰው ብለው ከጀመሩ በኋላ፤ መልሰው ‹‹ከእኔ በላይ ታላቅ ንጉሥ የለም ባይ ናቸው›› በማለት ለመደምደም የሚሞክሩ ናቸው፡፡ አሁን፤ ‹‹እንደ ባህር የሰፋ ትዕግስት ያላቸው መሪ ናቸው›› ብለው፤ መልሰው፤ ‹‹ድንገት በቁጣ ቱግ የሚሉ እና መረን የለቀቀ ስሜታዊነት የተጠናወታቸው መሪ ናቸው›› የሚል ቃል ለመናገር የሚያስገድዱ ሆነውባቸው ተቸግረው ነበር፡፡  
የጨርቅ ነጋዴ ልጅ ለሆነው እና በአፍሪካ የተመቸ መኖሪያ ለማግኘት ሲንከራተት ገንዘቡን የጨረሰው ሄንሪ ዱፍተን፤ ሊጅን (LeJean) የተባለ የሐገሩ ሰው፤ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ቆንሲል ሆኖ ተልኮ ወደ ኢትዮጵያ ሲጓዝ አግኝቶት፤ እሱን ተከትሎ ኢትዮጵያ መግባቱን የሚገልፁት የታሪክ ፀሐፊዎች፤ ‹‹አጼ ቴዎድሮስ፤ ዱፍተን ገንዘብ አጥቶ መቸገሩን ሲሰሙ በታላቅ ቸርነት እና ደግነት ተቀብለውት አስተናገዱት›› በማለት የአፄ ቴዎድሮስን ደግነት እና ርህራኄ ያትታሉ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ለፈረንሳይ መንግስት ለላኩት ደብዳቤ ገና መልሱ ሳይመጣ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ኑሮ የሰለቸው ሊጅን ‹ወደ ሐገሬ መሄዴ ነው› ብሎ ቢነሳ፤ አፄ ቴዎድሮስ አሰሩት፡፡ ለአንድ ቀን ካሰሩት በኋላ፤ በማግስቱ ከእስር ቢለቁትም፤ ወደ ፈረንሳይ ለላኩት ደብዳቤ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ ከሐገር እንዳይወጣ ከለከሉት፡፡ በመጨረሻም፤ ብራድል የተባለ ሰው ደብዳቤ ይዞ መጣ፡፡ ፈረንሳይ ብራድልን ምላሽ አስይዛ ብትልከው፤ የፈረንሳይ መልዕክተኛ ሆኖ እንዲሰራ ግን ፈቃደኛ አልነበረችም። በዚያን ጊዜ ንጉሱ፤ ሊጅንን ሰድበው፤ በኦክቶበር 2፣ 1863 ዓ.ም (እኤአ) ከሀገር እንዲወጣ አዘዙት›› በማለት ቁጡና ስሜታዊ አድርገው ይገልጧቸዋል፡፡
ዱፍተንም፤ ቻርልስ ዲከን ካሜሩን የተባለው የእንግሊዝ ቆንስላ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አራት ወራት ካሳለፈ በኋላ ኢትዮጵያን ለቅቆ ሄደ የሚሉት የታሪክ ፀሐፊዎች፤ አዲስ የእንግሊዝ መንግስት አምባሳደር ሆኖ የመጣው ካሜሩን ወታደር እና ከፍተኛ ልምድ የነበረው ዲፕሎማት መሆኑን ያወሳሉ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ፤ እንግሊዝ የምትፈልገውን የንግድ ስምምነት ለመፈራረም ከፕላውዴን የተሻለ ጥረት ሊያደርግ ይችላል የሚል እምነት በሀገሩ መንግስት የተጣለበትን ካሜሮንን አልወደዱትም፡፡ በውስጡ ያለውን ንቀት ላለማሳየት የማይጠነቀቀው ካሜሩን ከተቀመጠበት ሳይነሳ ደብዳቤ ሲሰጣቸው፤ ፂሙን በእጁ እየሞዠቀ ሲያናግራቸው በጣም ይበሳጩ ነበር፡፡ የእንግሊዙ መልዕከተኛ ካሜሮን፤ ከተቀመጠበት ሳይነሳ ለንጉሱ ደብዳቤ መስጠቱን፤ ከእንግሊዝ መንግስት እንዲያደርስ የተሰጠውን ደብዳቤ በሰው ልኮ ምፅዋ እና ከሰላ ሲንገላወድ ከርሞ የመምጣቱን ጉዳይ ምዕራባውያን የታሪክ ፀሐፊዎች፤ ከተለያየ የጤና ችግር ጋር ሊያይዙት ቢሞክሩም፤ የካሜሮን ዋናው ችግር አውሮፓዊ የንቀት በሽታ ነበር፡፡   
አፄ ቴዎድሮስ፤ በዘመነ መሳፍንት የተከፋፈለችውን ኢትዮጵያ አንድ ለማድረግ ቻሉ፡፡ ግን ከጦርነት ጨርሶ መውጣት ወይም አመጽ ከማዳፈን ሥራ በመገላገል የመሪነት ሚናቸውን ለመጫወት የሚያስችል ዕድል ሳያገኙ እንዲሁ እንደባከኑ ዘመናቸውን አሳለፉ፡፡ በወቅቱ፤ አረቦች እና ቱርኮች ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሀገራቸውን ድንበር በመግፋት ላይ ነበሩ፡፡ ስለዚህ፤ በሩቅ ያለችውን ኢየሩሳሌምን ከያዙት እና ድንበራቸውን እየገፉ ከሚያስቸግሯቸው ቱርኮች እና አረቦች ስጋት የሚገላግል እና ሐገራቸውን ለመከላከል የሚያግዝ ወታደራዊ እርዳታ ሊሰጣቸው የሚችል ክርስቲያናዊ መንግስት አጥብቀው ይሹ ነበር፡፡
ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት፤ አምባሳደሮቻቸውን ወደ እንግሊዝ የመላክ ሐሳብ እንዳላቸው በመግለፅ ለንግስት ቪክቶሪያ ደብዳቤ ፃፉ፡፡ ሆኖም ለደብዳቤያቸው ምላሽ አላገኙም፡፡ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ደብዳቤውን ገፋ አድርጎ ረሳው፡፡ ከኢምፓየሩ አጠቃላይ ፖሊሲዎች እና አጣዳፊ ጥቅሞች ጋር አገናዝቦ፤ ለአፄ ቴዎድሮስ ደብዳቤ ምላሽ የመስጠቱን ጉዳይ ያን ያህል አስፈላጊ ሆኖ አላገኘውም፡፡ ስለዚህ፤ ሣጥን ውስጥ ወርውሮ ረሳው፡፡
አፄ ቴዎድሮስ ቅር አላቸው፡፡ ክብራቸውን የሚነካ አድራጎት ሆኖ ታያቸው፡፡ ስለዚህ ለእንግሊዞች ንቀት አፀፋ ለመስጠት እና የእንግሊዝ መንግስት ምላሽ እንዲሰጥ ለማስገደድ ሲሉ የእንግሊዝን ቆንስላ ካሜሩንን ጨምሮ ወደ 70 የሚደርሱ አውሮፓውያንን ሰብስበው ወህኒ አወረዷቸው፡፡ ከዚያ የእንግሊዝ ልዑክ መሪ ሆኖ ሆርሙደዝ ራሳም መጣ፡፡ እሱንም አሰሩት፡፡ የመቅደላ ዘመቻ ተፀነሰ፡፡
የማያልቅ ወሬ ጀምሬ ተቸገርኩ፡፡
ስለዚህ፤ ከዚህ በላይ ጊዜአችሁን እና የጋዜጣውን ገፅ መውሰድ አልሻም፡፡ ይሁንና አንድ ነገር ሳልናገር መደምደም አልፈልግም፡፡ እርሱም፤ የጀነራል ናፒር የመቅደላ ዘመቻ ከብዙ ምጥ እና ልዩ ዝግጅት በኋላ የተደረገ መሆኑ ነው፡፡ እንግሊዝ እንደ መቅደላው ዘመቻ ብዙ ያሰበችበት እና የተጨነቀችበት ጦርነት አለመሆኑንም የታሪክ ፀሐፊዎች ይጠቅሳሉ፡፡ በእስረኞቹ ቤተሰቦች እየተላኩ፤ በወቅቱ በነበሩት የእንግሊዝ ጋዜጦች ይታተሙ የነበሩትና አንዳንዴም የፈጠራ ሊሆኑ የሚችሉት የኢትዮጵያ እስረኞች ታሪክ፤ የእንግሊዝ መንግስት እና ህዝብ ለእስረኞቹ (በኋላም ለጦርነቱ) የተለየ ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡ ህዝቡ ጉዳዩን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መከታተል በመጀመሩም የጋዜጦች ተነባቢነት እንዲጨምር አደረገው፡፡ አልፎ ተርፎ፤ የእንግሊዝ መንግስት ባይወደውም ለዘመቻ እንዲዘጋጅ ከፍተኛ ጫና አሳደረበት፡፡ የኢትዮጵያ እስረኞች ጉዳይ፤ የእንግሊዝ እና የሌሎች ሐገራት የህዝቦችን ቀልብ እንደሳበ የተመለከቱት ጋዜጦችም፤ ከጀነራል ናፒር ወደ መቅደላ በመሄድ ዘገባዎችን የሚልኩ ጋዜጠኞችን ለመላክ እንዲወስኑ አደረጋቸው፡፡ የጦርነት ዘገባም እንዲህ ተጀመረ፡፡


Read 2662 times