Saturday, 18 June 2016 12:52

የአገራችን ሦስቱ ሳጥኖች!!

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(16 votes)

“---- በገንዘብ መግዛት ሀብትን፤ በሥልጣን መግዛት ጉልበትን፣ በውበት መግዛት ፍትወትን፣ በመዋቅር መግዛት ሹመትን ያሳያል። በሐሳብ መግዛት ግን ልህቀትን ያመለክታል። ----”
ኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ሳጥኖች አሉ። ሁለቱ ሳጥኖች በጣም ይፈለጋሉ። ስለሚፈለጉ ወይ ይዘረፋሉ፤ ወይ ይሰረቃሉ። አንደኛውን ሳጥን ግን ዞሮ የሚያየው የለም። ሁለቱ በውስጣቸው በጣም ተፈላጊ ነገር አለ ተብሎ ስለሚታመን፤ ሳጥኖቹ በፖሊስ በዘበኛ፣ አንዳንዴም በወታደር ይጠበቃሉ። አንደኛው ሳጥን ግን ጠባቂ የለውም። ውስጣቸው ያለው ነገር ሲጨምር የሚያመጡት ለውጥ አለ ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ሁለቱ ሳጥኖች ቶሎ ቶሎ ይቆጠራሉ። አንደኛው ሳጥን ግን የሚያስታውሰው የለም።
ሁለቱ ሳጥኖች የምርጫ ሳጥንና የገንዘብ ሳጥን ናቸው። አንዱ ውስጥ ሥልጣን፣ ሌላው ውስጥ ገንዘብ አለ። ሥልጣን ያለበትን ሳጥን ፖለቲከኞች ይፈልጉታል። ስለዚህም ይሰብሩታል፣ ይገለብጡታል። ገንዘብ ያለበትን ሳጥን ሙሰኞች ይጓጉለታል። ይሰብሩታል፤ ይገለብጡታል። ሕዝቡም ስለ እነዚህ ስለ ሁለቱ ሳጥኖች ጉዳይ ይከታተላል። ሲዘጉና ሲከፈቱ ኮሚቴ ያቋቁማል። ሲቆጠሩና ሲመዘኑ ማወቅ ይፈልጋል። ሥልጣንና ገንዘብ ስላለባቸው።
ሦስተኛው ሳጥን ግን ከእነዚህ ሁሉ ይለያል። ዘጊ እንጂ ከፋች የለውም። ሠሪ እንጂ ተከታታይ የለውም። በውስጡ ያለውን ነገር ለማወቅ ባለቤቱም፤ ሕዝቡም አይጓጉም። ማንም እንደ ልቡ ያገኘዋል። ግን አይጠቀምበትም። ጥበቃ የለውም፤ ግን ማንም አይሰብረውም። ተመልካች ያጡ ወረቀቶችን በውስጡ እንደያዘ በየግድግዳው ላይ አርጅቷል። ሰዉም በዚህኛው ሳጥን ውስጥ ለማስገባት ብዙም አይፈልግም። እንደ ሁለቱ ሳጥኖች ፈላጊ የለውም ብሎ ያምናልና። ለምን?
ምክንያቱም ሦስተኛው ሳጥን ‹የሐሳብ መስጫ ሳጥን› ስለሆነ። ዓለምን የቀየረው ሐሳብ ቢሆንም እኛ ሀገር ግን ብዙም ፈላጊ የለውም። መሥሪያ ቤቶችም የተሰጣቸውን ርዳታ እንጂ የተሰጣቸውን ሐሳብ ሪፖርት አያደርጉም። ሀገር የምታድገው፣ የምትለወጠውና የምትሠለጥነው በሐሳብ ነው። ያውም በሰላ ሐሳብ። ያደጉ ሀገሮች ማለትም ታላላቅ አሳቢዎችና ታላላቅ ሐሳቦች ያሏት ሀገር ማለት ናት።
እስኪ አንድ እንኳን የሀገሪቱ መሪ፣ የፖለቲካ ልሂቅ፣ ባለ ሥልጣን፣ ሀገሪቱ ያፈራቻቸውን አሳቢዎች ከመጽሐፎቻቸው፣ ከንግግሮቻቸው፣ ከአባባሎቻቸው በንግግሩ ውስጥ ሲጠቅስ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? እውነት ዐሳቢዎች ሳይኖሩን ቀርተን ነው? ይህች ሀገርስ እንደ ሀገር ለዘመናት የኖረቺው ያለ ሐሳብ ነው? እንዴት ተደርጎ። ነገር ግን ለሐሳብና ለዐሳቢዎች የምንሰጠው ቦታ ኢምንት ስለሆነ ነው። በየቦታው የተጣሉት የሐሳብ መስጫ ሳጥኖች የሚነግሩንም ይኼንን ነው።
የአኩስምን ሐውልት ቆሞም ተጋድሞም አግኝተነዋል። ግን እነማን ነበሩ ያህንን ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ከአንድ ወጥ ድንጋይ ለመሥራት ያሰቡት? እንዴት ነበር ያሰቡት? ለምን ነበር ያሰቡት? ሐሳባቸውን በምን መንገድ ነበር የገለጡት? ጻፉት? ሞዴል ሠሩት? በሥዕል ገለጡት? በዜማ አቀረቡት? ከመላ ምት በቀር የምናውቀው ነገር የለም? ለዐሳቢዎች ቦታ ስለማንሰጥ። የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ቅዱስ ላሊበላ እንዴት ነበር ሊያስብ የቻለው? ሐሳቡን በምን ገለጠው? የሰው ኃይሉን፣ ቁሳቁሱን፣ በጀቱን፣ የሥራ ሂደቱን እንዴት ነበር ያደራጀው? ሕንጻውን እንጂ ሐሳቡን አላገኘነውም።
ፓል ሄንዝ አብያተ ክርስቲያናቱ ሲታነጹ ሊወጣ የሚችለው አፈር በአቡ ሲምባል የሚገኘው የግብጻውያን ታላቁ መቅደስ ሲሠራ ከወጣው አፈር አምስት እጅ የሚበልጥ ነው ይላሉ። ሥራውን ማንም ያከናውነው ፕሮጀክቱ ግን አያሌ የሰው ኃይልን ማንቀሳቀስን፣ የውቅሩን ሥራ እጅግ ሞያዊ በሆነ መንገድ መከታተልን፣ ያንን ግዙፍ የሥራ ኃይል እንዳለ ጠብቆ ለረዥም ጊዜ ለማቆየት የሚያስችል በቂ ሀብትን የሚጠይቅ ነው። በውቅሩ ላይ ምንም ዓይነት ስሕተት መሠራቱን የሚያመለክት ነገር የለም። ሞዴሎችና በጥንቃቄ የተዘጋጀ ዐቅድ መኖሩ አያጠራጥርም። አስደናቂው ደግሞ የውስጡን ቅርጽ ለመስጠትና ለማሣመር የተኬደበት መንገድ ነው። ይህ ሁሉ የተደረገው ደግሞ በችቦ መብራት ነው። (Layers of Time, 52) ያን ሁሉ ከየሥራው የወጣ አፈር የትና እንዴት ነው የደፉት? እርሱን ብናገኘው እንዲህ የግንባታ ቦታዎቻችን ሁሉ በቆሻሻ ባልተሞሉ ነበር። ታድያ የዚህ ታላቅ ፕሮጀክት የሐሳብ መዝገብ ለምን አልደረሰንም? ሕንጻዎቹን ብቻ ለምን አገኘናቸው? ምናልባት ለሐሳብ ተገቢውን ቦታ ስለማንሰጥ ይሆን?
በዘመናዊቱ የኢትዮጵያ ታሪክ እንኳን ሀገሪቱን ሲመክሩና ሲዘክሩ የነበሩ፤ ከአውሮፓ እስከ ጃፓን አርአያ ይሆናሉ የሚባሉትን ሀገሮች መንገድ እየጠቀሱ፣ ሀገሪቱ በዚያ መንገድ እንደትጓዝ ሐሳብ ያቀረቡ፤ በኋላ የሚሆነው ቀድሞ ታይቷቸው የመንግሥትን አስተዳደር፣ የሕዝብን አመራር፣ የሥልጣንን ጉዞ፣ ሰላማዊ የለውጥን መንገድ የጠቆሙ አሳቢዎች ነበሩን። በተለይም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ችግሮች እየተባባሱ ሲመጡና ቁስሉ የበለጠ እያመረቀዘ መሆኑ ሲታይ ንጉሡንም ሀገሪቱንም ተነቃናቂ ተማሪዎቹንም ከማዕበል ለማትረፍ አያሌ ሊቃውንት ሐሳባቸውን አቅርበው ነበር። የሰማቸው ባለመኖሩ ግን ከለውጥ ይልቅ ለነውጥ ተዳረግን።
ዛሬም ድረስ ለሐሳብና ለዐሳቢዎች ቦታ እንደሌለን የሐሳብ መስጫ ሳጥኖቻችን በየግድግዳው ላይ ቆዝመው ቆመው እየመሰከሩ ነው።
ሰው በመዋቅር፣ በድርጅት፣ በኮሚቴ፣ በማኅበር ሊያስብ አይችልም። እነዚህ ሁሉ ሐሳብን በተቀናጀ ሁኔታ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚጠቅሙ እንጂ ማሰቢያዎች አይደሉም። ሰው በግሉ ያስባል፣ በጋራ ይመክራል፤ በጋራ ይሠራል። አሁን አሁን ግን በደርጅት፣ በማኅበር፣ በመዋቅር፣ በኮሚቴ ለማሰብ እየተሞከረ ነው።
ሰው የተፈጠረው በግል ስለሆነ የሚያስበውም በግል ነው። መላእክት የተፈጠሩት በማኅበር ነው። ስለዚህም ያለ ልዩነት በማኅበር ሊያስቡ ይችሉ ይሆናል። እንስሳትም የተፈጠሩት በወገን በወገን ነው። ስለዚህም ተመሳሳይ እንስሳት ተመሳሳይ ጠባይ ይኖራቸዋል። ሰው ግን በግለሰብ ደረጃ ነው የተፈጠረው። ስለዚህም ሐሳብ ግለሰባዊ ነው። የግለሰቦች ሐሳብ ተሞግቶ፣ ተሞርዶ፣ ዳብሮና በልጽጎ ሌሎችን እያሳመነ የማኅበር፣ የድርጅት፣ የፓርቲ፣ የተቋም፣ የኮሚቴ የጋራ ግንዛቤ፣ ዐቅድ፣ መግባቢያ፣ ዕውቀት፣ ልምድ ይሆናል እንጂ ሰው በጋራ ሊያስብ አይችልም። አንዳንድ ጊዜ ድርጅቶች፣ ኮቴዎች፣ ማኅበሮች፣ ፓርቲዎች ይመሠረቱና ሰዎች በዚያ ውስጥ ተሰብስበው ለማሰብ ይሞክራሉ። ምን እንሥራ? ይላሉ። መጀመሪያ ምን ለመሥራት ተሰበሰቡ? ለሐሳብ ድርጅት ከመፍጠር ይልቅ ለድርጅት ነው ሐሳብ እየተፈለገ ያለው። ለልጅ ስም ይሰጣል አንጂ፣ እንዴት ለስም ልጅ ይወለዳል? ሰዎች በጋራ ለማሰብ ከሞከሩ ላለማሰብ እየሞከሩ ነው ማለት ነው። ሐሳብም ቦታውን ለመግቦት ለቅቋል ማለት ነው።
መግቦት ማለት አንድ ሐሳብ ከሆነ ቦታ ይመጣል። አይጠየቅም፤ አይተችም፤ አይከረከርም፤ አይለወጥም፤ እንዳለ እንደ መድኃኒት ይወሰዳል። ይዉጡታል አንጂ አይገነዘቡትም። ይቀበሉታል እንጂ አይጋሩትም። ከበሮው አንድ ቦታ ይመታል። የሌላው ሰው ድርሻ ምቱን እየጠበቀ እስክስታ መውረድ ብቻ ነው። አሠልጣኙ የሆነ ቦታ ይቆማል፤ የሌላው ሰው ድርሻ ተቀመጥ ሲሉት መቀመጥ፣ ተነሣ ሲሉት መነሣት ብቻ ነው። ለምን ? ብሎ አይጠይቅም።
የሰው ልጅ መግነጢሳዊ ጠባይ እየተዘነጋ ነው። አንድ ሰው የአንድ ጎሳ ወይም ዘውግ አባል ስለሆነ ብቻ አንድ ዓይነት ሐሳብ ሊኖረኝ ይገባል ብሎ የሚያስብ ከሆነ ሰውነትን ያህል ክብር እየለቀቀው ነው። ትልቁ አንድነት የቀለም፣ የጎሳ፣ የቋንቋ፣ የትውልድ አንድነት አይደለም። ይህማ በተፈጥሮ የተቀበልከው፣ በሐሳብ የማትለውጠው ነው።
እነዚህ በምርጫ ያልመጡ አንድነቶች ስለሆኑ በአንድነቱ ውስጥ ያለውን ሰው ብቃት አያመለክቱም። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱን አንድነት በእንስሳትም ውስጥ ስለምናገኘው።
ትልቁ የአንድነት ልህቀት የሐሳብ አንድነት ነው። ተከራክሮ፣ ተወያይቶ፣ ተሳስሎ፣ ተሞራርዶ ሐሳብን ገንዝቦ (ገንዘብ አድርጎ) አንድነት ሲመሠረት። የሰውን አንድነት ከአንድነትና ከኅብረት አውጥቶ ‹አሐተኒ› የሚያደርገው የሐሳብ አንድነት ነው። ይህንን የላቀ አንድነት ለማምጣት ደግሞ የሚገዛ መዋቅር፣ ድርጅት፣ ማኅበር፣ ፓርቲ ሳይሆን የሚገዛ ሐሳብ ያስፈልጋል። ትልቁ ገዥነት የሃሳብ ገዥነት ነው። በገንዘብ መግዛት ሀብትን፤ በሥልጣን መግዛት ጉልበትን፣ በውበት መግዛት ፍትወትን፣ በመዋቅር መግዛት ሹመትን ያሳያል። በሐሳብ መግዛት ግን ልህቀትን ያመለክታል።
የሀገር አንድነት ወደ አሐተኒ እንዲያድግ ከፈለግን፣ ልዕልና ያላቸውን ሐሳቦች የሚያቀርቡ፣ የሐሳብ ገዥዎች ያስፈልጉናል። ከተለያየ ዘውግ፣ ጎሳ፣ ብሔር፣ ባህል፣ እምነት፣ ልማድ፣ ክልል፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የእድሜና የጾታ ክልል የምንመጣ ሰዎችን እንደ ሥርዓተ ፀሐይ (Solar system) የሚያስተሣሥረን፤ እንደ ፍኖተ ሐሊብ (Milk way) ውጥንቅጣችንን በአንድ የተግባባ መንገድ የሚያስጉዘን፣ የምንገዛውና የሚገዛን ሐሳብ ያስፈልገናል። የሚገባንና የሚያግባባን ሐሳብ ያሻናል።
ለዚህ ደግሞ ለሐሳብና ለዐሳቢዎች ቦታና ክብር የሚሰጥ ማኅበረሰብና ሥርዓት መኖር አለበት። ለምርጫና ለገንዘብ ሳጥኖች የሰጠነውን ቦታ፣ ለሐሳብ ሳጥኖች መስጠት ካልጀመርን፣ ተፈጥሮ ለውበት የሰጠችንን ልዩነት እኛ ለማስጠሎነት እናውለዋለን። መዋቅሮችና አደረጃጀቶችም የታላላቅ ሐሳቦች ማስፈጸሚያዎች መሆናቸው ቀርቶ የማሰቢያ ‹ጭንቅላቶች› እንሁን ካሉ በሠራው ሠንሠለት እንደታሠረ አንጥረኛ እንሆናለን።
ዕድገትና ማዕዶትን (Development and Transformation) በፍጥነት ለማምጣት፣ የገንዘብና የምርጫ ሳጥኖች የያዙትን ቦታ የሐሳብ ሳጥኖች መረከብ አለባቸው።

Read 15892 times