Saturday, 16 July 2016 12:52

ትጋት - ወደ ድህነት ግብዓተ መሬት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ሌሊቱ እንደ ልማዱ አሸልቦ ማለዳው ለረፋዱ ቦታውን ሲለቅ ዝናቡም በካፊያ ይተካ ጀመር፡፡ ቀስ በቀስም ሰማዩ እየጠራ ብሩህ ቀን ከፊት ለመዘርጋቱ ተስፋ ይሰጥ ጀመር፡፡
 ሰኔ 23 ቀን 2ዐዐ8 ዓ.ም፣ ቢሾፍቱ ከተማ፡፡ የጨለለቃን ሀይቅ የሚጎራበተውና ሁሌም ፀዓዳ የማይለየው ባለግርማ ሞገሱ ጄክዶ ኦፖርቹኒቲ ፎር ቼንጅ የሥልጠና ማዕከል ግቢ ድባቡ ከወትሮው ለየት ብሏል፡፡ አለፍ አለፍ ብለው በተተከሉ ነጫጭ ድንኳኖች፣ በፌዴራልና በክልል ባንዲራዎችና በማስታወቂያ ባነሮች አሸብርቆ ለሁለተኛ ጊዜ የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማትን የመልካም ተሞክሮ ዓመታዊ በዓል ለማክበር ዝግጅቱን ሁሉ አጠናቅቋል፡፡
የዕለቱ ዝናብ ያልበገራቸው የማህበረሰብ ምስርት ተቋማት አመራሮችም በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ለወራት ሲለፉበት የነበረውን ድግሳቸውን ለማቋደስ ጉብኝዎቻቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
በኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (ኢ/ህ/ማ/ል/ድ) አዘጋጅነት “የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት አጋርነት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ይህ በዓል ከተለያዩ የአገሪቷ ክልሎች የተወጣጡ 60 የሚደርሱ የኢ/ህ/ማ/ል/ድ አጋር የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማትን ያሳተፈ ነው፡፡ ለችግር ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ሁለገብ ድጋፍ በመስጠት የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ በማስቻል ሥራ ላይ ከተጠመደ 30 ዓመታትን ያስቆጠረው ኢ/ህ/ማ/ል/ድ  በአሁኑ ሰዓት በአማራ፣ በኦሮሚያና በደ/ብ/ብ/ህ ክልሎችና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በተለያዩ የማህበረሰብ ልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገ ነው፡፡ በተለይ ላለፉት 15 ዓመታት የማህበረሰብ አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ በመሥራትና አቅማቸውን በተለያየ መልኩ በመገንባት ሕብረተሰቡ የራሱን ችግር በራሱ እንዲፈታ በማስቻል በኩል ጠንካራ ልምድ አካብቷል፡፡ የዚሁ ጥረቱ አካል የሆነው የቢሾፍቱው መርሀ-ግብርም ያለፉትን ስኬቶች ከመዘከር በሻገር የወደፊት አቅጣጫዎች የሚመላከቱበት፤ ማህበራቱም ጠቃሚ ተሞክሮዎችን የሚጋሩበትና የእርስ በርስ ትስስርም የሚፈጥሩበት መድረክ ነው፡፡
የተለያዩ ከተሞች የመንግስት ጽ/ቤቶች፣ የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት፣ የለጋሽ ድርጅቶች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ሁሉ ቀስ በቀስ ወደማዕከሉ እየደረሱ ጊቢውም ሞላ ማለት ጀመረ፡፡ የዕለቱ ዋነኛ ባለጉዳዮች የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት ተወካዮችም እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ተፍ ተፍ ማለታቸውን አላቋረጡም፡፡  
ልክ ከጠዋቱ 3፡3ዐ ሰዓት ሲሆን የዕለቱ የክብር እንግዳ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ ተወካይ፣ ወ/ሮ ዘውድነሽ አሰፋ የበዓሉን በይፋ መከፈት አበሰሩ፡፡ እናም የሁሉም ትኩረት የመጀመሪያው መርሀ-ግብር ወደሆነው ወደ ተቋማቱ የልማት አስተዋፅኦ ዐውደ-ርዕይ ሆነ፡፡ ይሄን ጊዜ በማህበረሰባቸው ለማህበረሰባቸው የተቋቋሙትና በሰዎች ሞት ጊዜ ከመረዳዳት ባሻገር በድህነት ግብዓተ መሬት ላይ ለመረባረብ የቆረጡት ዕድሮች ያካበቷቸውን ልምዶች በፎቶግራፍና በሠነድ አስደግፈው በተራ በተራ በርቱዕ አንደበት ለታዳሚው ማካፈል ጀመሩ፡፡ ሁሉም ጆሮውን ሰጥቷል፤ ባየውና በሰማው መደሰቱንና አድናቆቱን ይገልጻል፤ ተጨማሪ ማብራሪያ የፈለገ ይጠይቃል፤ ሌላው ዐውዱን በፎቶ ግራፍና በተንቀሳቃሽ ምሥል ለማስቀረት ይጣጣራል ወዘተ. ብቻ ከአንድ ነጭ ድንኳን ወደ ሌላ ነጭ ድንኳን ሲታለፍ ሌላ ቁም ነገር፣ ሌላ ስኬት፣ ሌላ መደመም!
ክብርት ወ/ሮ ዘውድነሽ አሰፋ ዐውደ ርዕዩን አስመልክተው ሲናገሩ “መርሀ-ግብሩ ህብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት ያለው የልማት ሥራ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንዲሰራጭ ልዩ ዕድል ይፈጥራል” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ የማህበራቱ ተወካዮችም ይህንኑ መስክረዋል፡፡ “ተረጂዎችን በተናጠል ከመደገፍ ይልቅ ዘላቂነት ባለው መልኩ ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ በቡድን በማደራጀት የገቢ ምንጫቸውን እንዲያዳብሩ ለማስቻል በሌሎች ማህበራት የሚደረገውን ጥረት ተምረን በሥራ ላይ ለማዋል አስበናል” በማለት የጋይንት ንፋስ መውጫ ከተማ የዕድሮች ህብረትን ወክለው የተገኙት አቶ መቆያ ፈንቴ የክብርት ወ/ሮ ዘውድነሽን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡
በዐውደ ርዕይው የተደመሙትና ከማህበራቱ በርካታ ተሞክሮ የተቋደሱት የበዓሉ ታዳሚዎች በባህላዊ ጭፈራ እየተዝናኑ አጠር ያለ የሻይ እረፍት ካደረጉ በኋላ ወደተንጣለለው የማዕከሉ አዳራሽ በመከተት ወደተከታዩ መርሀ-ግብር ተሸጋገሩ፡፡
ከጥቂት ክንውን በኋላም ሁሉንም ያስጨበጨበ የምሥራች ከማህበራቱ ዘንድ ተሰማ፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ
ለ5,974 ለችግር የተጋለጡ ህፃናት የተቀናጀ ድጋፍ በመስጠት፣
ለ4,670 ለችግር የተጋለጡ ህፃናት አሳዳጊዎች፣ ቤተሰቦች እና ሴቶች የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ በመስጠት፣
ለ956 ለችግር የተጋለጡ ወጣቶች የሥልጠናና የሥራ ፈጠራ ዕድል በማመቻቸት፣ እንዲሁም
1,750 ለሚሆኑ የማህበረሰብ አባላት በዘላቂ የማህበረሰብ ልማት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት የዜጎች ህይወት እንዲለወጥ ትልቅ ሚና ተጫውተናል፤  ወደፊትም የበለጠ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የኢ/ህ/ማ/ል/ድ አጋር የሆኑ 46 የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት በተወካያቸው አማካይነት ለቤቱ አሳወቁ፡፡
ተከታዩ ዝግጅት የፓናል ውይይት ነበር፡፡ በውይይቱ የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት ለዘላቂ ልማት ያላቸውን አስተዋፅኦ ዙሪያ የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ግኝት ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ እንደጥናቱ ከሆነ  ተቋማቱ በዘላቂ ልማት ውስጥ ያላቸው ሚና እንደማያጠያይቅ እና ለዚህም ያበቃቸው አደረጃጀታቸውና አሠራራቸው ሕዝባዊ መሠረት ያለው መሆኑ፤ አመራራቸው በበጎ ፈቃደኞች መሸፈኑ እና ከመንግሥትና ከሕግ አስፈፃሚ አካላት ጋር ያላቸው ትብብርና ትሥሥር ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እንዲያም ሆኖ የጥናቱ ሌላ ገፅታ የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት ግሥጋሤ ከተግዳሮቶች የፀዳ አለመሆኑን አሳይቷል፡፡ በበጎ ፈቃደኝነት የሚያገለግሉ ተተኪዎችን የማፍራት ሥራ ከፍተኛ ጥረት መጠየቁ እና የግል ባለሀብቶችን በማስተባበር ሀብት የማሰባሰቡ ሥራ በስፋት አለመሠራቱ በዚህ ረገድ ከተነሱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል ናቸው፡፡  ከዚህ ባሻገር ከተለያዩ አካላት ጋር ያለውአጋርነት፣ አዎንታዊ የሆነ አስተሳሰብ ለውጥ ማስፈን እና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር መቀናጀት በማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት አማካይነት ዘላቂ ልማትን ለማምጣት የሚያስችሉ ጠቃሚ መሣሪያዎች እንደሆኑ በውይይቱ ተመላክተዋል፡፡
በውይይቱ ከተሠነዘሩና ማህበራቱን በእጅጉ ካበረታቱ ሀሳቦች መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው የተከበሩ አቶ ታጠቅ አምሳሉ፣ የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ ቃል ነው፡፡ “ዘላቂ ልማት በመንግሥት ብቻ አይመጣም” በማለት የጀመሩት ክቡር ከንቲባው “የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት የመንግሥት የልማት አቅሞች እንደመሆናቸው መጠን መንግሥት ተቋማቱን በቅርበት ማወቅና ማገዝ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ አክለውም “ማህበራቱን ከማወቅ በዘለለ የሚጎላቸውን ለይቶ አውቆ ያንን ክፍተት በመሙላት በኩል ከህበረተሰቡና ከመንግሥት ብዙ ይጠበቃል” ብለዋል፡፡ በመንግሥት የልማት ዕቅዶች ውስጥ የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማትን ፍላጎትና ያልተነካ አቅም ማካተትና መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ከንቲባው ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡በዓሉ ከመጠናቀቁ በፊት የተከናወነው ሌላ ቁም ነገር 60 ለሚሆኑ የነቃ የልማት ተሳትፎ ላደረጉና 7 የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማት እውቅናና የማበረታቻ ሽልማት መስጠት ነው፡፡ በመጨረሻም አዘጋጆቹም ሆኑ ተጋባዦች ሁሉም ባዩትና በሰሙት ረክተው፣ የገበዩትንም እውቀት ለነገአቸው ሰንቀው በታላቅ ቁርጠኝነት ተሰነባበቱ፡፡ ማን ነበር “ነገ ዛሬ ጠንክረው ለሠሩት ነው” ያለው?

Read 1627 times