Monday, 12 December 2016 12:08

“ምጡቅ ትውልድ እየመጣ ነው”---- ድንቄም!?

Written by  ኢዛና አብርሃ
Rate this item
(5 votes)

    የዓሣ ህይወቱ ባህሩ እንደሆነ ሁሉ የስኬትም ህልውና የሚወሰነው በአንድ ጉዳይ ላይ በፈሰሰው ድካም ልክ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለም መሬት አለኝ ብሎ ጎተራውን ጠራርጎ ቁጭ ብሎ የሚጠብቅ ገበሬም የለም፡፡ አንድ መሬት ምን ለም ቢሆን ዘር ካልረጩበት፣ ቡቃያውን ካላረሙት፣ ከወፍና ከመሰል እንስሳት ጥፋት ካልታደጉት ውጤት አይኖረውም፡፡
አንዳንድ ግዜ … ምን አንዳንድ ግዜ፣ አብዛኛውን ግዜ እንጂ … ጉንጭ አልፋ ሙግት ውስጥ መግባቴ አልቀረም፡፡ ባለፉት ቀናት ግን የገጠሙኝ እንደው እንደ ዋዛ ላልፈው የምችለው አልሆኑም፡፡ አንድ ባልደረባዬ “ዳይናሚክ” ትውልድ እየመጣ እንደሆነና አገራችንም ግሩም ተስፋ እንዳላት አበክሮ ይሞግተኝ ጀመር፡፡
 “ዳይናሚክ”… ባልደረባዬ ምን አይነት ራዕይ እንደተገለጠለት አላውቅም፡፡ ግን አንዳንድ ማሳያዎችን ሰነዘረልኝ፡፡ “እንዴ... አንድ የእህቴ ልጅ ገና በሶስት አመቱ የሞባይል ጌም እንዴት እንደሚጫወት ብታየው”፣ “አንተ እኮ ጉድ ትላለህ፣ ጌሙ የት እንደተቀመጠ እንዴት ጎርጉሮ እንደሚያወጣው…” ሌሎችም ማሳያ መሰሎችን አክሏል፡፡ “አትጠራጠር፣ ዳይናሚክ ትውልድ እየመጣ ነው፡፡” አለኝ፡፡
ይሁን መቼስ ይህን የመጠቀና የረቀቀ ትውልድ ማየት ማንም አይጠላም፡፡ ሆኖም እሱ በታየው ግዝፈት ለእኔ አልታየኝም፡፡ ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው እንዲሉ …እኔ ደግሞ እያስፈራኝ ያለው እየመጣ ያለው ትውልድ ነው፡፡ በርግጥ በየዘመኑ ያሉ ሰዎች አዲሱ ትውልድ ላይ ተስፋም ፍራቻም ሲያሳድሩ ይታያል፡፡ እንደ እኛ ያለ ማህበረሰብ ደግሞ ከእምነትና ትንቢቶች ጋር አያይዞ ዘመኑን በተለየ መነጽር መመልከቱ ይታወቃል፡፡
ለምሳሌ እኔ ልጅ እያለሁ ከባልንጀሮቼ ጋር የምንፈጽመውን ድርጊት በጥሞና የሚከታተሉ አንድ አዛውንት፤ “አይ የስምንተኛው ሺ ልጅ” እያሉ ይገረሙብን ነበር፡፡ በርግጥ በወንዞችና በጅረቶች የተሞላችው አረንጓዴዋ መንደራችን (እዚሁ አዲስ አበባ ቤላ አካባቢ መሆኑ ነው) በፈጠረችልን እድል ተጠቅመን፣ አባ ንጉሴ መዋኘታችን፣ ጥንስስ የተባለ ባህር ድረስ መሄዳችን ለሳቸው ጉድ የሚያሰኝ ቢሆንም፣ ለእኛ ግን ከቁብ የምንቆጥረው አልነበረም፡፡ በርግጥ እሳቸው ምናልባት በፍካሬ እየሱስ እንዳነበቡት ወይም ሲባል እንደሰሙት እኛ “የስምንተኛው ሺ ልጆች” በአግባቡ ብንያዝ … እንደ ማነው ስሙ በዋና ከመጨረሻ አንደኛ ላንወጣ እንችል ነበር፡፡ ግን ከዋና ስንመጣ፣ ፊታችን አሸቦ ሲመስል እርግማንና እንዲያም ሲል ደህና ጥፊ እንቀምስ ነበር፡፡   
የዘመኑም ልጆች እንደ ማንኛውም ትውልድ የራሳቸው ቀለምና ዝንባሌ ያለቸው እንደሆኑ ይገባኛል፡፡ ዘመኑ የፈጠረላቸው በርካታ መልካም በረከቶች ከበዋቸዋልና፡፡ ያም ሆኖ “ዩዘር ፍሬንድሊ” የሆነ ሞባይል ጌም መጠቀም መቻል ብቻ ዳይናሚክ ትውልድ ያሰኛል? የሚለው አንድ አስፈላጊ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ ይህንኑ ጥያቄ ለባልንጀራዬም አቅርቤለት ነበር፡፡
“እንዴ! አንተ እኔ እኮ አንድ ጊዜ የመጀመሪያዋን ክፍል መጫወት አልችልም… እሱ እንዴት ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ እንደሚሸጋገር ብታየው?” በሚል ምላሽ ብጤ ሰጠኝ፡፡
ጥሩ እንግዲህ ለሱ የታየው ትውልድ  የተለየ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ ያው እኛም የስምንተኛው ሺ ምናምን እንደተባልነው… አካባቢያችን በፈጠረው እድል ስለተንቦራጨቅን ብቻ… መልካም፡፡ እኔ ደግሞ “ዳይናሚክ ትውልድ መጣ፣ ወርቃማ ዘመናችን…” የሚባሉ አባባሎችን ስጠላቸው፡፡ እንደው ሶፋ ተደግፎ አሳ ይዝነብልኝ አይነት ምኞት ይሆንብኛል፡፡ (ዓሣ … ለካ ድሬ ዓሣ ዘንባለች…እንዲያማ ከሆነ መመኘትም እንችላለና)፡፡
ለምን መሰላችሁ ወርቃማ ዘመንንም ሆነ ምጡቅ ትውልድን እንፈጥረዋለን እንጂ አናገኘውም፡፡
ሙግታችን እየከረረ ሲሄድ ወዳጄ “ፔሲሚስት ነህ እንዴ?” አለኝ… እኔ እስከማውቀው ድረስ ተስፈኛ አይደለሁም፣ እሱ እንደለጠፈብኝም ጨለምተኛ አይደለሁም፡፡ እና ምንድን ነኝ? … አይ እኛ?... ሁልጊዜም ሁለት አማራጮችን ይዘን፣ ጽንፍና ጽንፍ ላይ ተቀምጠን በመካከል ላይ ላለው ሰፊ ስፍራ ጀርባ የምንሰጥ ፍጡሮች፡፡ በቃ እንደዚህ ካልሆን እንደዛ ነን፡፡ ፍረጃ የማይታክተን፡፡ እኔ ራሴን እስከማውቀው ድረስ በተጨባጭና ቢያንስ በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ አሳማኝ በሆነ ጉዳይ የማምን ሰው ነኝ (ሪያሊስት ልትሉኝ ትችላላችሁ)… ይህ ማለት ግን ኢምፔሪሲስት ነኝ ማለት ላይሆን ይችላል፣ ማለቴ በዓይኔ አይቼ፣ በጆሮዬ ሰምቼና በእጄ ዳስሼ…የማረጋግጥ አይነት አይደለሁም… የኛ የሰዎች እውቀትና የማወቅ እንዲሁም የመገንዘብ አድማስ ከዚያም በላይ ነው ባይ ነኝ፡፡
አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚያስረዳኝ፤ የትውልዱ ንጹህ አዕምሮ በአውሮፓ ኳስ እየናወዘ… ኤፍ ኤሞቻችን አፋቸውን የሚያሟሹት ስቴቭን ዤራርድ አቋሙ ምን ይመስላል እያሉ ባለበት…በተማሪዎቻችን ደብተር ፊትና ጀርባ ላይ ጊዜ ቤት፣ ልኬቶችና መሰል ስሌቶች  ሳይሆን የፊልም አክተሮች፣ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ምስል ተንቆጥቁጦ… ቴሌቭዥኖቻችን ሃያ አራት ሰዓት የአረብ ሳትና የመሳሰሉትን እጅግ ዘግናኝ ካርቱኖችና ሌሎች ፊልሞች እያራገፉብን፣ አልፎ ተርፎ የምንከፍለው ታክስና የምንገዛውን ምርትና አገልግሎ ባስገኘላቸው ትርፍ ማስታወቂያ በሚያስነግሩ ባለሃብቶች የሚተዳደሩ፤ ነገር ግን ወጣቱንና ሕፃናቱን በቱርክ ፊልም የሚያነሆልሉ ጣቢያዎች እንደ ልባቸው እየፈነጩ፣ ባህላችንን፣ እንደ አገር ያለምነውን ራዕይ፣ … የማይመጥኑ ይዘቶች ማራገፊያ ሆነን…ጎበዝ እንዴት ነው ዳይናሚክ ትውልድ፡፡ አንተ ባልንጀራዬ ሆይ… የታየህ ራዕይ ሳይሆን ቅዠት እንዳይሆን ተጠንቀቅ እላለሁ፡፡
ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የትምህርት አሰጣጣችንስ እንዴት ነው፡፡ በዘመነ ግሎባላይዜሽ ሁሉ ነገር ለገበያ ቀርቧል፡፡ የመንግስት ትምህርት ቤቶች በግብዐት እጥረት የተሞሉ ናቸው፡፡ መማሪያ መጽሃፍት፣ የላቦራቶሪ ቁሳቁሶች፣ ኮምፒውተሮችና የመሳሰሉት አሁንም እንደ ቅንጦት እቃ እየተቆጠሩ ናቸው፡፡ ይህንን እንኳ በመጠኑ ለማሟላት መንግስት ጥረት እያደረገ ነው ብንልም፣ በቂ ባለሙያ አለን ወይ… ትምህርት ቤቶች ባስገኙት ውጤት ጥራት ሳይሆን አግበስብሰው ባሳለፉት ተማሪዎች ብዛት እየተመዘኑ… የእከሌ ትምህርት ቤት ዘጠና ዘጠኝ ምናምን ፐርሰንት ሲልም መቶ አሳለፈ ተብሎ ዲቤ እየተደለቀ፣ በአሳፋሪ ሁኔታ ኩረጃ እንዲስፋፋ መምህራን እራሳቸው ቴክኒኮችን ለተማሪዎች እየነገሩ (ሁሉንም ማለቴ አይደለም) ባለበት ሁኔታ ዳይናሚክ ትውልድ መጠበቅ ከራዕይነት ይልቅ ቅዠትነቱ እጅግ ይልቃል፡፡  
የግል ትምህርት ቤቶች፣ እነሱም ከየት እንዳመጡት በማያውቁት ካሪኩለም ተማሪዎቻቸውን ሲያደናብሩ እየዋሉ፣ ልጆቹ ወገባቸው እስኪጎብጥ ሁለት አይነት ደብተርና መፅሀፍ እየተሸከሙ፤ የመንግስት ካሪኩለም አይከተሉም እንዳይባሉ የመንግስትን መጽሀፍ ለተማሪዎቻቸው ያድላሉ ወይም ይሸጣሉ፣ ደብተርም ይዘጋጃል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የቤቱ እስፔሻል ነው መሰል፣ እራሳቸው ያዘጋጁት መጽሃፍና ይህንኑ የሚማሩበት ደብተር መሆናቸው ነው፡፡ እና አገሪቱ ባላት ኤክስፐርቶች ተጠንቶ የተዘጋጀው ካሪኩለም የግል ትምህርት ቤት ውስጥ ቦታ የለውም። ያገሪቱን ኔታ፣ ባህል፣ ራዕይ፣ የልጆቹን ስነልቡና ያላማከለ ጥራዝ ነጠቅ ትምህርት እየተሰጠና በኩረጃ ተደግፈው መቶ ፐርሰን አሳልፈው፣ ይህንኑ ነውር በየበራቸው ላይ የሚለጥፉ “ትምህርት ቤቶች” በፈሉበት አገር ዳይናሚክ ትውልድ….
አገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ ኩረጃን በማጠናከር ፈታኞችና ሱፐርቫይዘሮች እንዲሁም ጣቢያ ሃላፊዎችን ሳይቀር በገንዘብ  እየተደለሉ….ይቺ ናት ዳይናሚክ ትውልድ፡፡ ለእኔ ዳይናሚክ ትውልድ ወርቃማ ዘመን የሚፈጥር ነው፡፡ የዶት ኮም ሪቮሊዩሽኑ አባት ሰር ቲንበር ሊ፣ ቀደም ሲልም እነ አይንሽታይን፣ በቅርቡ ደግሞ እነ ዘከርበርግ፣ ራዕይ ካለው ትውልድ ውስጥ አስፈላጊው እገዛ ተደርጎላቸው በትምህርት ዳብረው የተገኙ እንጂ በምኞት የመጡ አይመስለኝም፡፡ ተደክሞባቸው የተፈጠሩ እንጂ እንዲያው ሶፋ ደገፍ ብለው የተመኟቸውና ከሰማይ ዱብ ያሉ ክስተቶች አይደሉም፡፡ የትኛውም ትውልድ በቤተሰብ ደረጃ፣ በማህበረሰብና በመንግስትም በቂ ጥንቃቄ ከተደረገለት ወርቃማና ዳይናሚክ ይሆናል ባይ ነኝ፡፡
አለበለዚያ ወርቃማና ዳይናሚክ ትውልድ የሚፈጥረውን እጅግ ለአጠቃቀም ቀላል የሆኑ ነገሮችን ልጆቻችን ሲጠቀሙ እያየን (ፋንታሳይዝ የምናደርግ) ከሆነ ዋጋ አይኖረንም፡፡ (ቴክኒሻን ለዚህ ጽሁፍ የሚሆን ሙዚቃ ጋብዝልኝማ!)

Read 3108 times