Monday, 05 February 2024 15:31

የዘመን ነገር ከዘመን በፊት!

Written by  -ዓለማየሁ ገላጋይ-
Rate this item
(0 votes)

አንዳንድ  ጭውውት አልፎ ሲያስታውሱት የትንቢት ቁመና ይይዛል።…..
… አስራ አምስት ዓመት ያልፈዋል፡፡ ከአንድ ፀሐፊ ወዳጄ ጋር ስንገናኝ ከሰላምታ ቀጥሎ የምንጠያየቀው የተለመደ ባለሁለት አፅቅ ወቅታዊ መረጃ አለን፡፡
        “ምን እያነበብክ ነው?” እለዋለሁ፤ ይነግረኝና…
        “አንተስ?” ይለኛል፡፡
“ምን እየፃፍክ ነው?” ድጋሚ እጠይቃለሁ፡፡ ይመልስና፤
        “አንተስ?” የሱ ጥያቄ ይሆናል፡፡
ንባቡም ሆነ ጽሁፉ ጥቂት ማብራሪያ ካስፈለገው “እንዲህ ነው፤ እንዲህ ነው” እንባባላለን፡፡ “እንዲህ”ታው አንዳንዴ ሙሉ ጊዜያችንን ይወስዳል፡፡ በተመሳሳይ አንድ ጊዜ የነገረኝ ታሪክ እንደወትሮው አላከራከረንም ወይም ደግሞ አልተረሳልንም፤ እንዲሁ ብቻ በፀጥታ እያብሰለሰለን ብዙ ሰዓት አቆየን፡፡ ወዳጄ ጉዳዩን አሰበበት እንጂ ገና አልፃፈውም ነበር፡፡ (አሁንም የፃፈው አይመስለኝም) ታሪኩ ተመላልሶ የተፃፈ ያህል ተራግፎና ጥርት ብሎ ነበር የተተረከለት፡፡
        “ተውኔት ልፅፍ ጫፍ ደርሻለሁ” አለኝ፡፡
“ድራማ’ኮ ፅፈህ አታውቅም”
“አዎ፣ ግና የታሪኩ አደረጃጀት ለድራማ የተመቸ ሆነብኝ”
“እንዴት ያለ ነው?”
“እንዲህ እንዲህ ነው…” ብሎ ጀመረ፡፡
የትረካ ውሎው የሚከናወነው ቤተመንግስት ውስጥ ነው። ንግሥት ተጨንቀዋል፡፡ ንጉሥ አደባባይ ከዋሉ በመሰንበታቸው በየግዛቱ “ጉም ጉም” መባል ተጀምሯል፡፡ ንግሥት ይንቆራጠጣሉ፡፡ ሀገር ሊነቃነቅ፤ በንቅናቄውም ሊፈርስ ተቃርቧል፡፡ መፍትሄው ንጉሱን ይዞ አደባባይ መውጣት ነው፡፡ ይሄ አልተቻለም፡፡ “ንጉስ ሞተዋል” የሚናፈሰው ወሬ ነበር፡፡
የታሪኩ ሁነት በዓለም ዙሪያ ብዙ ንጉሶችና ነገስታት የሚያጋጥማቸው ነው፡፡ የእኛዎቹ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ መሰል ታሪክ አላቸው፡፡ ጸሐፊ ትእዛዝ ገብረሥላሴ “ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ፣ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” መጽሐፋቸው ላይ “ራስ ጎበና ከፈረሰ ወድቆ አጥብቆ ታመመ” ይላሉ፡፡ “ህዝቡም የንጉሱን (ዘመቻ ሄደው) ወሬ መጥፋት፣ የራስ ጎበናን መታመም ባየ ጊዜ አገሩ ተናወጠ፡፡ የህዝቡንም መጨነቅ ወይዘሮ ጣይቱ በሰሙ ጊዜ ከዚያች ከፍል ውኃው አጠገብ ከተሰራችው ቤት ወርደው ተቀመጡ፡፡ ከተማ መስራትም ተጀመረ፡፡ መኳንንቱም ቦታውን እየተመራ ቤቱን ይሰራ ጀመር፡፡ ሕዝቡም ወይዘሮ ጣይቱ ከሜዳ ወርደው ከተማ ማሰራትዎን ባየ ጊዜ ያጼ ምኒልክን ደህንነት በዚህ አወቅነው ብሎ ዳር እስከዳር ረጋ፡፡” (ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ገፅ 143)
የጓደኛዬ “ንግሥት” ግን የዘየደችው ከወይዘሮ ጣይቱ ይለያል፡፡ “ንጉሱን የመሰለ ሰው ፈልጉ” አለች ሁነኛ አሽከሮቿን፡፡ ተፈለገ፣ ተፈለገና ዳር አገር ተገኘ፡፡ ቁርጥ በአምሳል ንጉሱን!! ንግሥት፡-
“በሉ ጭቶውን እስኪያራግፍ ተንከባከቡና አቅርቡልኝ” አለች፡፡ አሽከሮችም፡-
“ኧረ ጭቶም የለው፤ የማንንም እየቀማና እየዘረፈ ሲበላ የኖረ ሌባ ነው፡፡” አሉ፡፡
        “አቅርቡት” ቀረበ፡፡
        “የንጉሱን ልብስ አልብሱት!”
        ለበሰ፡፡
        “አቅርቡት” ቀረበ፤
        ንግሥት አማተበች፡፡ ቁርጥ ሟቹን ንጉስ፡፡ ብቻ ይሄ ይቁለጨለጫል፡፡
        "አንት ሌባ! ወዲያ ወዲህ ትልና ወዮልህ” አለችው፤ በትረሥልጣኑን እንደጨበጠ ይብረከረካል፡፡ “እንዲች ብለህ ካፍህ አንዳች ነገር ይወጣና በሌባ ደንብ እጅህን ነው የምቆርጠው፤”
    ከድንጋጤው የተነሳ መመለስ‘ኳ” አልቻለም፡፡ ዝም ብሎ መብረክረክ ብቻ! ለስሙ ቢሆንም መንበሩን ሌባ ያዘው፡፡ ቤተመንግሥቱ ላይ አባ ላፈው ፈነጨበት፡፡ ይሁንና ከሥመ- መንግሥትነት ሆነ ከንግሥናም ቢሆን ሌብነቱ ላይ ተስፋ ያለው ሰው ነበር፡፡ የተቀመጡ የጌጥ ዕቃዎች ሲያገኝ አንስቶ ካባው ውስጥ ከከተተ በኋላ በማገናዘብ ይመልሳል፡፡ የሌብነት አመል ነውና፡፡ በበር ሲጠበቅ በመስኮት ይገባል፡፡
ሌብነት አልተወው ያለው የደም ውስጥ በሽታ ሆኖበታል፡፡ ልማደኛ ሌቦች ተይዘው ዙፋን ችሎት ሲቀርቡ፣ የሚመረምራቸው ካለበት የንግሥና ወጥመድ ነፃ ሲወጣ ለመስረቅ የሚያስችል መረጃ ለመሰብሰብ ነው፡፡
        “አገሬው ሌሊት ስትዘርፉት መሳሪያ አያወጣም?”
        “መሳሪያው ተሰብስቧል”
        “ኧረ?”
        “ይሙቱ!”
        “ተመችቷላ?”
        “በጣም!”
       “እኔ የማውቀው ሀገር በረቱና ግርግሙ የሚሰራው ከቤቱ ሥር ስለሆነ ገና ኮሽ ሲል ገበሬው ይነቃል፡፡”
    “አይ እኛ የምንዘርፍበት አገር ሙቀት ስለሆነ በረቱና ግርግሙ ከመኖሪያ ቤት ራቅ ተደርጎ ነው የሚሰራው።”
    “ኧከከከከ… ይሄማ ለዘራፊ የተመቸ ዓለም ነው!”
    “በጣም እንጅ…”
የዙፋን ችሎቱ እንዲህ ይካሄዳል፡፡ እየሳቁ ቁስል ይገሸለጣል፡፡ በቸልተኝነት የጠገገ ህመም ለይስሙላ ከተኛበት ይቀሰቀሳል፡፡ ጥበብ እንዲህ ነው፤ በሚያለቅሱበት ህማም ላይ ስላቅና ሳቅ መፍጠር:: ማንነት እስከመሆን የደረሰን ህመምን ከታማሚው ነጥሎ ማሳየት። እውነታን መስታወት አድርጎ ፊት ለፊት በማቆም ከገዛ አስቀያሚነት በተንፀባረቀ ቀልድ መሰል ማልገጥ!!
    ተውኔቱን ወዳጄ አልጻፈውም፤ በንጉሱ ወይም በንግስቲቱ ስም የሚነሳው ተቃውሞ ያኔም አስፈርቶት ነበር፡፡ ስለዚህ መልካችንን ነፈገን። የሣቅ ትምህርታችንን ከለከለን፡፡ ስንኖር ያልተቃወምንበትን ሲያሳዩን መገንፈል ልማድ አድርገናልና አይፈረድበትም፡፡ የሌብነት ሥርዎ መሠረት ለተጠናወተው ለእንደኛ አይነት ህዝብ፣ እንደ ኮሶ የሚያሽር ጥበብ ግዱ ነበር፤ ግን አልሆነም….
    …. ጉቦ ጌጣችን ሆኖ ኖሯል፤ “መታያ” የሚል የአደባባይ ስም ሰጥተን ተዛምደነዋል፡፡ መኳንንቱ ሁሉ በጉቦ ጉዳይ አያፍርም፤ እንደውም ይኮራበታል፡፡ ሌብነትን እንደበቅሎ መረሸት የሚኮፈስበት፣ አደባባይ የሚወጣበት ጌጡ አድርጎታል፡፡ የታሪክ ምሁሩ ተክለጻድቅ መኩሪያ “የሕይወቴ ታሪክ” ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው፣ አንድ ባለጉዳይ በጉቦ እንዴት እንደሚካለብ ሲፅፉ…
“… ነገረተኛው (ወረቀት ተፅፎ) ሲቀበል የቀላጤ ሩብ ይከፍላል፡፡ ነገር ግን መከረኛው ነገረተኛ ወጭው በዚህ ብቻ አይወሰንም፡፡ ወደ ጌቶቹ ለመቅረብ ላጋፋሪዎችና ለልፍኝ አስከልካዮች ከአንድ እስከ አምስት ብር እንደ ችሎቱ ይከፍላል፡፡ ከዚያ ለጌቶቹ እላይ እንደተባለው የቻለውን ከሁለት እስከ መቶ ብር ወይም እንጨት ወይም ሰንጋ መታያ ያቀርባል፡፡ ከዚያ ፀሐፊው ሳይዘገይ በቶሎ ጽፎ እንዲሰጠው ከቀላጤው ሩብ በቀር ካንድ እስከ አምስት ወይም አስር ይከፍላል፡፡ አዲስ አበባ ነገሩ ሲዛወር ነገሩ በችሎት በሚታይበት ጊዜ ለወንበሮችና ለአጋፋሪዎች፣ ለፍርድ ጸሐፊዎች የሚከፈለው በዚሁ አካባቢ እንደነገሩና እንደ ኃጢአቱ ክብደትና ቅለት ነው፡፡”
ይሄ የነገረተኛ መዋከብና በመንጋ ጉቦኛ ገላውን መቦትረፍ ዛሬም መልኩን ሳይቀይር አለ፡፡ መልካችን ብቻ ታይቶ በመምሰላችን በትረ-ሥልጣን በየደረጃው የተሰጠን ሌቦች ብዙ ነን፡፡ ቀበሌ መታወቂያ ለመስጠት የነገሠ ተራ ሌባ አለ፡፡ ክፍለ ከተማ የቤት ካርታ እንዲያፀድቅ ዙፋን የተበጀለት “ሿሿ” አለ፡፡ መንገድ ትንስፖርት የመኪና ሊብሬ ላይ የዙፋን ችሎት የዘረጋ ማጅራት መቺ አለ፡፡ ገቢዎች ግብር እንዲሰበስብ ዘውድ የጫነ ኪስ አውላቂ አለ፡፡ በህምና ሰጪ ተቋምነት ስም ለታመመ ሌላ የወጪ  ውጋት የሆነ ቁጭ ይበሉ አለ፡፡ ሊፈተሽ  የሚገባው ፈታሽ፣ መጠበቅ ያለበት ጠባቂ፣ በአይነቁራኛ መታጀብ ሲገባው የአጃቢነቱ ሥፍራ ላይ የተገኘ ተክለፍላፊ ብዙ ነው…
… ህይወታችን በትረ-ሥልጣን ለጨበጡ ሌቦች ክፍቱን ተትቷል፡፡ የእነሱ መዝረፍ በጎ ዕጣ-ፈንታቸው መምሰሉ ብቻ ሳይሆን የእኛ ለዝርፊያ መጋለጥ የተፈጠርንለት አላማ እየሆነ መምጣቱ ነው ዋናው የኑሮ መሰናክል … እና፤ እንዲህ ላለው ኹነታችን፤ እንዲያ ያለው የባልንጀራዬ ጥበብ ፍቱን አልነበረም ትላላችሁ? ሥር ለሰደደው ህማማችን የተመጠነ መድኃኒቱ ጥበብ እንዳይቀርብ አለመመቸታችን፣ በራስ ላይ መለገም አይሆንም?... ግዴላችሁም፣ ወዳጄ ይፃፍ… ተመቹት!!

Read 1360 times