Monday, 29 September 2014 08:37

የግሼ ዓባይ የኪነት ቡድን ለምን ፈረሰ

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(4 votes)

               ስሙን ያገኘው የዓባይ ወንዝ መፍለቂያ ከሆነውና ሰከላ ወረዳ (ጐጃም) ከሚገኘው ቦታ ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ እንደ ንጋት ኮከብ ደምቀው ከነበሩት የክፍለ ሀገር ኪነት ቡድኖች አንዱ የጐጃሙ ግሼ ዓባይ ይገኝበታል፤ የወሎው ላሊበላ፣ የትግራይ፣ የአርሲ እና የወለጋ ክፍላተ ሀገር የኪነት ቡድኖችም በወቅቱ ስመጥር ነበሩ፡፡ የጽሑፌ ዓላማ በጐጃሙ ግሼ ዓባይ ላይ ያተኮረ ስለሆነ ሌሎችን አቆያቸዋለሁ፡፡ በ1971 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የኪነት ቡድን የሙዚቃ ሥራውን እየተዟዟረ ሲያሳይ ቆይቶ፣ በወቅቱ የጐጃም ክፍለሀገር ዋና ከተማ ወደነበረው ደብረማርቆስ ያመራል፡፡ በወቅቱ በክፍለሀገሩ ውስጥ ይገኙ ከነበሩት እጅግ በጣም ጥቂት ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች አንዱ ከነበረው ድብዛ ት/ቤት አዳራሽ ተገኝቶ ትርኢቱን ማቅረብ ይጀምራል፡፡ በወቅቱ ኪነት ከፍተኛ ተወዳጅነት ነበረውና የትምህርት ቤቱ አዳራሽ በተመልካች ጢም ከማለቱም በላይ የክ/ሀገሩዋ አስተዳዳሪ የነበሩት ሻለቃ ካሳዬ አራጋውና ሌሎች የክፍለሀገሩ ባለሥልጣናትም ታዳሚዎች ነበሩ፡፡

የኪነት ድግሱ እየሞቀ ሲሄድ ድንገት አንድ ችግር ተፈጠረ፡፡ እሱም የኪነት ቡድኑ አስተዋዋቂ ቡድኑን “የጐጃም ክፍለሀገር የኪነት ቡድን” ብሎ በማስተዋወቁ ትልቅ ግርግር ተነሳ፤ አንዳንድ ተመልካቾች እንዲያውም ከአዳራሹ ውጭ በመውጣት ጣራውን በድንጋይ መደብደብ ጀመሩ፡፡ ሁኔታው ሲረጋጋ የችግሩ ምክንያት “አስተዋዋቂው የጐጃም ክፍለሀገር ኪነት ብሎ የሚያስተዋውቀው ማን ወክሎት ነው?” የሚል ቅሬታ ሆኖ ተገኘ፡፡ እግረመንገዱንም የህዝቡ የኪነት ቡድን ይቋቋምልን ጥያቄ ግልጽ ሆነ፡፡ ይህንን ጥያቄ የክፍለሀገሩ ዋና አስተዳዳሪ በዋዛ አላለፉትም ነበርና ሳይውል ሳያድር ኮሚቴ ተቋቋመ፤ በወቅቱ ከነበሩት ሰባት አውራጃዎች ማለትም ደብረ ማርቆስ፣ ሞጣ፣ ብቸና፣ ባህርዳር፣ መተከል፣ ቆላ ደጋዳሞት እና አገው ምድር አውራጃዎች ውስጥ ከሚገኙ 35 ወረዳዎች ፍላጐቱና ችሎታው ያላቸው ወጣቶች እንዲመለመሉ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ከብሔራዊ ቲያትር የመጡ ባለሙያዎች ምልመላውን እንዲያካሂዱ፣ የ35 ወረዳዎች ዋና አስተዳዳሪዎችም ለዚሁ ዓላማ ብቁ ናቸው ያሏቸውን ወጣቶች ደብረማርቆስ ከተማ ድረስ እንዲልኩ ቀጠሮ ያዙ፡፡

ከየወረዳው የመጡት ወጣቶች ደብረማርቆስ ቤተመንግስት አዳራሽ ዘፈኖቻቸውን እያቀረቡ ከመሃላቸው የተሻሉት ከብሔራዊ ቲያትር በመጡት ባለሙያዎች ተመለመሉና ህዳር 25 ቀን 1972 ዓ.ም እዚያው ደብረማርቆስ ከተማ ከሚገኘውና “ድኩማን ድርጅት” በመባል ይታወቅ ከነበረው ተቋም በማሰባሰብ ሥልጠና ተጀመረ፡፡ በወቅቱ የተመለመሉት ወጣቶች ሰባ አንድ ሲሆኑ፤ ከአማራ፣ አገው፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ወይጦና ቅማንት የተውጣጡ ነበሩ፡፡ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ የሚተዳደሩበት ገንዘብም ከየወረዳው ህዝብ የተሰበሰበ ነበር፡፡ ለስምንት ወራት ሲሰጥ በቆየው ስልጠና የአባላት ቁጥር ወደ ሰላሳ ስድስት ዝቅ አለ፡፡ የዚህ ምክንያቱ በዲሲፕሊንና በችሎታ ማነስ ስለሚባረሩ ነው፡፡ ከስምንት ወራት የዳንኪራ (ውዝዋዜ)፣ የአቀንቃኝነት (ድምጻዊነት)፣ የተውኔትና የሙዚቃ (በተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች አጨዋወት) ስልጠና በኋላ ሐምሌ 5 ቀን 1972 ዓ.ም የወቅቱ የባህል ሚኒስትር ሻለቃ ግርማ ይልማና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ተመረቀ፡፡

ከሁለት ቀናት በኋላም መኖሪያውን ወደ ባህርዳር ለማድረግ ጓዙን ጠቅልሎ ተጓዘ፡፡ ብዙም ሳይቆይ በ5ኛው የአብዮት በዓል ላይ ለመገኘት ወደ አዲስ አበባ መጣ፤ የወቅቱን የሱዳን መሪ ጃፋር ኤል - ኑሜሪንና የሃንጋሪያው ፕሬዚዳንት ፓል ሎሼንሲ የክብር አቀባበል ላይ በመገኘት ትርዒቱን አቀረበ፤ ከዚያም የክፍለሀገሩን ልዩ ልዩ ዘፈኖች በብሔራዊ ቲአትርና በተለያዩ አዳራሾች በማቅረብ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስመ ገናና ሆነ፡፡ በወቅቱ ይታተሙ በነበሩት “አዲስ ዘመን” ፣ “የካቲት” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ላይ ተደጋጋሚ ሙገሳዎችን ከማግኘቱም በላይ የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችም ከብዙ ሙገሳ ጋር የቡድኑን ዘፈኖች በተደጋጋሚ በማቅረብ ጣቢያዎቻቸውን ተወዳጅ ለማድረግ ጣሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ቡድኑ በአርሲ፣ በወለጋ፣ በሲዳማ፣ በሐረር፣ በባሌ፣ በሸዋ፣ በትግራይ፣ በኤርትራ፣ በወሎ፣ በጐጃምና በጐንደር ክፍላተሀገር በመዘዋወር ድንቅ ብቃቱን ማሳየቱን ተያያዘው፡፡ በምሥራቅ ግንባር በነበሩት በሺላቦ፣ በለምበል፣ አህመድ ጐሬ፣ ኢላላ፣ ጐዴ እና በመሳሰሉት፤ በሰሜንም በተለይ በኤርትራ ግንባር፤ ምፅዋ፣ አልጌና (መርሳተኽላይ፣ መርሳቡልቡል፣ ሰምበር፣ እንቁላል…) ወዘተ በመዘዋወር ሥራውን ለሠራዊቱና ህዝቡ በማቅረብ ተወዳጅነቱን ጣራ እንዲነካ አድርጓል፡፡ በትግራይ ግንባር ለነበረው ሠራዊትም ተመሳሳይ ተግባር በማከናወን በሠራዊቱ ልብ ውስጥ የማይረሳ ትዝታ መፍጠር የቻለ ቡድን ሆነ፡፡ በተለይም በምርጥ አቅራሪነቷ (ሽለላዋ) ዝነኛ የነበረችው ዘቢደር አምሳሉ፤ “ነግረኸው፣ መክረኸው ምክርህን ካልሰማ፣ አደንቁረው በዕርሳስ ጆሮው እስቲገማ፡፡ የሱማሌ እረኛ እንዴት ተዋረደ፣ ታንኩን አስረክቦ ጣሳ ይዞ ሄደ፡፡ የሶማሌ ጊደር የላትም ወይ አውራ? አንበሳው ላይ ወጥታ ቀረች ተሰባብራ፡፡ ነግረኸው ካልሰማ ከርፋፋ ወንበዴ፣ አጭዶ መከመር ነው እንዳፈራ ስንዴ…” እያለች ስታንጐራጉር የሠራዊቱን ወኔ እንደ ቋያ እሳት ታቀጣጥለው ነበር፡፡ አለማየሁ ቦረቦር “አገር መስታውቴ” እና “ያችውና መጣች”፣ አለባቸው ተፈራ “ሃሜት መወጣጫው”፣ ወይኒቱ አንዱር “አንበሳውያን፣ አስናቆ ኢላላ፣…”፣ አቡኔ አበጀሁ “ሉላ”፣ ማናማሁ ሲራጅ “ቀናበል ከአንገትህ፣ አያ እንግዳ…” እናንዬ አደራ “የመኩ የመኩ፣ ጐፈሬው ዘመመ…” ሲራጅ ኢድሪስ “አያ በለው…”፣ አዳነች ጣሰው “ሞት ፈርቶ ትግል የለም”፣ ይሁኔ በላይ “የአገሬ ልጅ…”፣ ሰማኸኝ በለው “አንቱየዋ!”፣ ታደሰ ላቀው “ነይልኝ ማርቆስ…”፣ አያሌው ፀጋዬ “ደኔ ደኔ…” ወዘተ በተባሉ ዘፈኖቻቸው ተመልካችን ከመቀመጫው ብድግ ቁጭ የማድረግ ልዩ አቅም ነበራቸው፡፡ በሙዚቃ መሣሪያ ተጨዋችነትም ሁለገቡ ሙዚቀኛ አሳየ ዘገየ፣ ሰጠኝ አጠናሁ፣ ሙሉጌታ፣ ይኩኖአምላክ አዱኛ፣ አቡሃ ይባዬ፣ መሐባው ግዛቸው፣ ምትኩ ገላው፣ ሰላምሰው ግዛቸው፣ አንዱዓለም፣ ገበየሁ ማሞ፣ ሐብቱ ንጋቱ (አንሙቴ) ወዘተ የማይረሱ ምርጥ ባለሙያዎች ናቸው፡፡

በዳንኪራ በኩል፣ የዝባየሽ ታረቀኝ፣ ባኬ አንተነህ፣ እሱባለው ጫኔ፣ እንኰይ ትኩ፣ ሞላ ፈጠነ፣ ሽፈራው ወርቅነህ፣ የሹሜ ነጋሽ፣ ታደሰ ወንዴ፣ ዓለመወርቅ አስፋው፣ አልጋነሽ ለገሠ፣ ብዙአየሁ ጐበዜና ሌሎችም እንደ ባህር ቄጠማ ሲውዘፈዘፉ የተመልካችን ቀልብ የመሳብ መግነጢሳዊ ኃይል ነበራቸው፡፡ ጌታቸው ተሥፋዬ፣ አበረ አዳሙ፣ እቴናት ደባሱ፣ ፍቅሬ ገ/ኪዳንና ታሪክ ታምሩ በተውኔት በኩል የቡድኑ ፈርጦች ነበሩ፡፡ ከተጫወቷቸውና ለቡድኑ ዝናን ካተረፉለት ተውኔቶች ውስጥ “ማነህ? ነገ፣ የወጣቷ ህይወት፣ እናት ሃገር፣ ድርብ ምጥ፣ ድርብ ታጋይ፣ የስልኩ ምስጢር፣” በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሲሆን ሌሎች ተውኔቶችንም በማቅረብ ህዝብን አስተምረዋል፤ አዝናንተዋል፤ አሳውቀዋል፡፡ በነገራችን ላይ ቲያትር የሚጫወቱት በውዝዋዜ፣ በድምጽና በሌላም ሥራ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ሁለገብ ወጣቶች ነበሩ፡፡ የግሽ ዓባይ ኪነት ቡድን ይህንን ሁሉ ሲያከናውን ያለምንም ችግር አልነበረም፡፡

የቡድኑ ትልቁ ሀብት የእርስበርስ ፍቅር ነበር፤ እንጂማ በችግር አለንጋ የሚገረፍበት ጊዜ በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ ጊዜ የመበተን አደጋ ያጋጥመው እንደነበር በህይወት ያሉ አባላት በምሬት ያስታውሳሉ፡፡ ቡድኑ የሚተዳደረው ከህዝብ በተዋጣ ገንዘብ ነበር፤ የዚህ ምክንያቱ ቋሚ በጀት ያለተያዘለት ከመሆኑም በላይ የሚተዳደረውም በኮሚቴ ነበር፡፡ ኮሚቴው ጠንከር ብሎ መንቀሳቀስ ሲጀምር የቡድኑ ህይወት መጠነኛ እፎይታ ያገኛል፤ ካልሆነ ግን አባላት ደሞዝ የሚያገኙት ከ3 እና 4 ወራት ለቅሶ በኋላ ነበር፡፡ ግን ይህ ሁሉ ችግር እያለ የአባላቱ የእርስበርስ መተሳሰብና ጥልቅ የሙያ ፍቅር ትልቁ ስንቃቸው ነበር፡፡ ከህዳር 1972 እስከ 1973 ዓ.ም በኮሚቴ ሲመራ ቆየና ችግሩ እየባሰ ሲመጣ፣ ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቡድኑን የማስተዳደር ኃላፊነት ተረከበ፡፡ ሆኖም እሱም በተገቢ መንገድ መምራት ስላልቻለ፣ በ1975 ዓ.ም ወር ተረኛነቱ ለባህልና ስፖርት ጉዳይ ቅርንጫፍ መ/ቤት ተዛወረ፡፡ ቡድኑን ከፍተኛ ፈተና የገጠመውም በዚሁ ጊዜ እንደነበር አባላት በምሬት ያወሳሉ፡፡ የዚህ ምክንያቱ መደበኛ በጀት ያልነበረው በመሆኑና ከህዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ በማለቁ ነበር፡፡ “እንኳንስ ዘንቦብሽ…” አይነት የነበረው የኪነት ቡድኑ አስተዳደር ውጥንቅጡ እየበዛ፣ ቢሮክራሲያዊ ድሩ እየተወሳሰበ ሲሄድ አባላትም ተሥፋ መቁረጥ ጀመሩ፡፡ በዚህ የተነሳ ሥራቸውን እየጣሉ ወደ አዲስ አበባ መኮብለል ያዙ፡፡ ያነጋገርኋቸው አባላት እንደሚያስታውሱት፤ 1977 ዓ.ም የቡድኑ የፈተና ወቅት ነበር፤ ደሞዝ በማጣት ተራቡ፤ ተጐሳቆሉ፣ አንዳንዶችም በዕዳ ምክንያት በየፍትሕ ተቋማቱ መጐተት ጀመሩ፡፡

ወቅቱ ደግሞ ዘግናኙ የ1977 ድርቅ በወሎና ትግራይ ህዝብን እንደ ቅጠል የሚያረግፍበት ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ የባለሥልጣናት ትኩረት አነስተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የኮብላዮች ቁጥር ሲበዛ፣ የቡድኑ ፈጠራ በከፍተኛ ሁኔታ ሲቀዛቀዝ፣ የኋላ ኋላ አንድ መላ መፈጠር ነበረበትና የወቅቱ ባለሥልጣናት በ1978 ዓ.ም የገቢ ማሰባሰቢያ ፌስቲቫል አዘጋጁ፡፡ በውጤቱም ግማሽ ሚሊዮን ብር መገኘቱን በወቅቱ ለበላይ አካላት የቀረበ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ ሰማኸኝ በለውና ይሁኔ በላይ ቡድኑን የተቀላቀሉትም ከዚህ በኋላ ነበር፡፡ የገንዘቡ ችግር በዚህ መልኩ ቢቃለልም የአስተዳደሩ ጉዳይ ግን ዘላቂ መፍትሄ አልተገኘለትም፡፡ በዚህ ጊዜም ከባህል ሚኒስቴር ቅርንጫፍ መ/ቤት “ቦርድ” ወደሚባል ሌላ ኮሚቴ ተዛወረ፡፡ ኮሚቴ ደግሞ ያው ኮሚቴ በመሆኑ ለጊዜው መጠነኛ መሻሻል ያደረገ ቢሆንም ለቡድኑ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ አልቻለም፡፡ እንደ ያዝባየሽ ታረቀኝ እና እንኮይ ትኩ ያሉ ድንቅ ችሎታ በነበራቸው አባላቱ በ “ህዝብ ለህዝብ ኢትዮጵያ” ኪነት ቡድን እና በ13ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ፒዮንግያንግ (ሰሜን ኮርያ) ላይ በመገኘት የክፍለ ሀገሩን ህዝብ ባህል ያስተዋወቀው ግሽአባይ፣ እንደ ሰማኸኝ በለው (ሰሜ ባላገር) እና ይሁኔ በላይ፣ ተዘራ ተችሎ፣ አንሙቴ፣ ወዘተ ያሉ ድንቅ ባለሙያዎችን ለአገራችን ያበረከተው ግሽአባይ፣ በጎጃም ክፍለ ሃገር ህዝብ ገንዘብና በልጆቹ የተቋቋመው ግሽአባይ ዛሬ ነበር ሆኗል፡ ለቡድኑ ህልውና ማክተም ምክንያት የሆነው የሥርዓት ለውጡ ነው፡፡

ደርግ በህአዴግ ሥልጣኑን ሲቀማ፣ ቡድኑን በኮሚቴ አባልነት ይመሩ የነበሩት የመንግስት ባለስልጣናት አንዳንዶቹ ለስደት ሌሎችም ለእስር ቤት ሲዳረጉ፣ ቡድኑ ሜዳ ላይ ቀረ፡፡ ሆኖም የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ታምራት ላይኔ ቡድኑን የባህርዳር ማዘጋጃ ቤት ተረክቦ እንዲያስተዳድረው ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡ ግን የቡድኑ አባላት መንታ መንገድ ላይ ቆሙ፤ አንዳንዶች “በተሰጠን ዕድል እንጠቀምና ማዘጋጃ ቤቱ ያስተዳድረን፤ ሙያችንንም እንቀጥል” ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ “የከተማዋን ንፅህና በአግባቡ መጠበቅ የተሳነው ማዘጋጃ ቤት ሊያስተዳድረን አይችልም” በሚል አቋም ፀኑ፡፡ መጨረሻ ላይ ከመንግስት ተሰጥታው ሲገለገልባት የነበረችውና 27 ሰዎችን የመጫን አቅም የነበራት ፊያት መኪና፣ ማቀዝቀዣዎች፣ አልባሳት፣ የሙዚቃ መሳሪያዎችና ሌሎችም የቡድኑ ንብረቶች በመናኛ ዋጋ እየተሸጡ፣ ለእያንዳንዱ አባል እዚህ ግባ የማይባል ብር ደረሰው፡፡መኪናን የሚያህል ንብረት ተሸጦ ለእያንዳንዱ አባል የደረሰው አንድ ሺህ ብር አይሞላም ነበር፡፡ ከንብረት ሽያጭ የደረሳቸውን እጅግ መናኛ ገንዘብ ከተከፋፈሉ በኋላ አባላት ተበታተኑ፤ በኢትዮጵያ የኪነት አየር ላይ እጅግ ደምቆ የነበረው የግሽአባይ ቡድን ውበትም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በንኖ ጠፋ፡፡

በቡድኑ ውስጥ የላቀ ሚና ይጫወቱ ከነበሩት መሃል፡- አለማየሁ ቦረቦር፣ ዘቢደር አምሳሉ፣ አለባቸው ተፈራ፣ ታደሰ ወንዴ፣ አያሌው ጸጋዬ፣ ሲራጅ እንድሪስ፣ አለመወርቅ አስፋው፣ ማናማሁ ሲራጅ፣ አንሙቴ (ሐብቱ ንጋቱ)፣ እንኮይ ትኩ፣ የህዝባየሽ ታረቀኝ፣ ወርቁ፣ ብዙአየሁ ጎበዜ የተባሉት በህይወት የሉም (ነፍሳቸውን ይማር)፡፡ ሌሎች ግን በውጭና በአገር ውስጥ በተለያዩ የሥራ መደቦች ተሰማርተው ኑሮአቸውን እየገፉ ናቸው፡፡ ማስታወሻ፡ በጊዜ ብዛትና መረጃ በማጣት ስማቸውን ያልጠቀስኋቸው አባላት ካሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

Read 4808 times