Monday, 03 November 2014 09:11

አጃኢብ ያሰኙኝ የፍቅር ደብዳቤዎች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(52 votes)

           አንድ የሙያ ባልደረባዬ ባለፈው ሳምንት ስልክ ይደውልልኝና “የአንድ የፍቅር ደብዳቤ አውደ ርዕይ ተከፍቷልና ብትጐበኚው ምን ይመስልሻል” አለኝ፡፡ የፍቅር ደብዳቤ አውደ ርዕይ የሚባል ሰምቼም አጋጥሞኝም ስለማያውቅ፣ ነገሩ ትንሽ ግር ቢለኝ ከባልደረባዬ ማብራሪያ ጠየቅሁ፡፡ ከዚያበቀጥታ ከደብዳቤዎቹ ፀሐፊ ጋር በመደዋወል ቀራኒዮ መድሃኒያለም አካባቢ ወደሚገኘው የፍቅር ደብዳቤ አውደ ርዕይ ነው ያመራሁት፡፡ አጃኢብ ነው እናንተዬ፤ እንዲህም አለ እንዴ ስል ራሴን ጠየቅኩኝ፡፡ መቼም በምድር ላይ እንዲህ አይነት ብዛትና ጥልቀት ያለው ደብዳቤ የተፃፈላት የመጀመሪያዋ ይህቺ ሴት እንደምትሆን ገመትኩ፡፡
በ1984 ዓ.ም ገደማ የአቶ ስዩም ገ/ፃዲቅ የቅርብ ጓደኛ የሆነ ሰው ሐረር፣ ጨለንቆ የተባለ ከተማ ውስጥ በቀያሽነት ይሰራል፡፡ የዚህ ሰው እጮኛ በወቅቱ ሳዑዲ አረቢያ ጂዳ ትሰራ ነበር፡፡ ታዲያ ሀረር ጨለንቆ የሚሰራው ጓደኛው ጂዳ ለምትገኘው እጮኛው የረቀቀ የፍቅር ደብዳቤ አይደለም የሰላምታ ደብዳቤ ጽፎ ወደ ጂዳ ለመላክ ጨርሶ አይመቸውም፡፡ በቦታውም በስራውም ምክንያት፡፡ ይህንን የጓደኛውን ችግር የተረዳው አቶ ስዩም፤ ጓደኛውን በመወከል ለጓደኛው እጮኛ የተከሸኑ የፍቅር ደብዳቤዎችን እየፃፈ መላክ ይጀምራል፡፡ ደብዳቤዎቹ ከትውልድ አገሩና ወገኑ በብዙ ማይል ርቀት ላይ ለሚገኝ ስደተኛ የአዕምሮ ምግብ፣ የልብ፣ መጽናኛ፣ ብርታትና ጉልበት ስለሚሆኑ ይህቺ ልጅ የስዩምን ደብዳቤ በየሁለት ሳምንቱ በጉጉት ትጠብቅ እንደነበር አውደ ርዕዩን የከፈተው የደብዳቤዎቹ ፀሐፊ አቶ ስዩም ገ/ፃዲቅ አጫውቶኛል፡፡
እንኳን ደብዳቤው የሚላክላት ሴት ሌሎችም ኢትዮጵያውን ሴት ጓደኞቿ ደብዳቤውን ተሰባስበው የማንበብ ልምድ ስለነበራቸው በጉጉት ሚጠብቁት ነገር ነበር ይላሉ፡፡ አቶ ስዩም ይሄን ከሰሙ በኋላ ነው ለሴቶቹ አንድ ጥያቄ ያቀረቡት፡፡ “እንዲህ አይነት ደብዳቤ እንዲፃፍላት የምትፈልግ ሴት ከመሃላችሁ ካለች በሰንጠረዥ ሰርቼ የምልከውን ጨዋታ በትክክል ሰርቶ የላከ አሸናፊ ይሆናል፤ ከዚያም ሽልማት የሚሆን ደብዳቤ ይላክለታል” በማለት ፈተናውን ላኩላቸው” ይላሉ አቶ ስዩም፡፡ ከእነዚህ በርካታ ሴቶች  መካከል ገነት ጥጋቡ ክብረቴ የተባለች ሴት ብቻ ሰንጠረዡን በትክክል ሰርታ መገናኘት ያለባቸውን ቁጥሮች አገናኝታ አሸናፊ ሆነች፡፡ ያቺ ሴት የዛሬዋ የአቶ ስዩም ገ/ፃዲቅ የትዳር አጋር ሆና ላለፉት ሰባት ዓመታት በትዳር አብራቸው ዘልቃለች፡፡ እሷ ሳዑዲ አረቢያ እየሰራች በነበረችበት ከ1988 እስከ 1994 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ስድስት አመታት የተፃፉላት ልብ አቅላጭ የፍቅር ደብዳቤዎች ናቸው ለህዝብ እይታ የቀረቡት አጃኢብ ነው፡፡
“ከ1986 እስከ 1988 ዓ.ም ድረስ እኔና ገንዬ በሶስተኛ ወገን ማለትም በጓደኛዬ እጮኛ በኩል ስንፃፃፍ የቆየነው የተራ ጓደኝነት ዓይነት ደብዳቤ ነበር ይላሉ፡፡ አቶ ስዩም፡፡ ሆኖም የጓደኛው እጮኛ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ፣ አግብቶ እንደሆነ፣ እጮኛ ይኖረው እንደሆነ በመጠየቅ ነፃ መሆኑን ስታውቅ ለምን ከገኒ ጋር የፍቅር ግንኙነት አትጀምሩም በማለት እንደጠየቀችው  የሚያስታውሰው አቶ ስዩም፤ የገነትን ፈቃደኝነት ካረጋገጠ በኋላ ገና ሳይተያዩ በደብዳቤ ብቻ ወደ ፍቅር መግባታቸውን አጫውቶኛል፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ አፍሪካ ህብረት አካባቢ ተወልደው ያደጉት አቶ ስዩም፤ ለስነ - ፅሁፍ ትልቅ ፍቅር እንደነበራቸው ይናገራሉ፡፡ በአይንህ ያላየሃትን ሴት ምርጫህ ትሁን አትሁን ሳትለይ በደብዳቤ ብቻ ወደ ፍቅር ግንኙነት መግባት አይከብድም በማለት ጠየቅኋቸው፡፡ “እኔ ሁሌም መልክና ቁመና አስደንቆኝ አያውቅም፤ ገንዬ በሶስተኛ ወገን ስንፃፃፍ የምትልክልኝ ደብዳቤዎች በሳልና አስተዋይ መሆኗን ከደብዳቤዋ መረዳት ችዬ ነበር፡፡ ለእኔ ደግሞ ይሄ በቂ ነበር” ነው ያለኝ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ለስድስት ተከታታይ አመታት ደብዳቤዎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ጐረፉ፡፡ የፍቅር ንፋስ እያከነፈ ጂዳ የሚያደርሳቸው እነዚህ ምህታታዊ ደብዳቤዎች መልስ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፤ ብዛታቸው ወደ ጂዳ የሚሄደውን ያህል ባይሆንም፡፡
የደብዳቤዎቹ አይነቶች
በጣም የሚገርመው የደብዳቤዎቹ ብዛት ከሁለት መቶ በላይ መሆኑ ወይም፤ በአማረ የእጅ ጽሑፍና በምርጥ ቃላት መከሸናቸው አይደለም፡፡ በጣም አፍዞና አደንግዞ የሚያስቀረው ደብዳቤዎቹ ሳይሰለቹ እንዲነበቡ የሚዘጋጁበት የወረቀት ቅርፅ፣ ቀለምና መጠን ነበር፡፡ ደብዳቤዎቹን የማሳያችሁ በምስል ቢሆን እንዴት ደስ ባለኝ፡፡ በጣም ትንሽ መጠን ያላት ደብዳቤ የአንድን ሰው ግማሽ መዳፍ ታክልና በልብ ቅርፅ ተሰርታ፤ በሮዝ፣ በቢጫና በነጭ የወረቀት ቀለሞች የተዘጋጀች ስትሆን፣ 32 ገፆችን አካታለች፡፡ ትልቁ መቶ ገጽ ያለው ደብዳቤ ደግሞ በተለያየ ቅርጽ በተቆረጡና ደብዳቤዎች ሶስት አይነት ቀለም ባላቸው ወረቀቶች የተዘጋጀ ነው፡፡ ሶስት ሜትር ርዝመት ያለው ደብዳቤ፤ አጃኢብ ከሚያሰኙት አንዱ ሲሆን ወረቀት ተቀጣጥሎ በኡሁ እየተጣበቀ ነው ያን ያህል የረዘመው፡፡ ደብዳቤው ግን አንድ ወጥ ነው፡፡ በልብ ቅርፅ፣ በብሮሸር መልክ፣ በእንቁላል ቅርጽ፣ በክብ፣ በአበባ መልክ ተቀርፀው የተዘጋጁት ደብዳቤዎችም እንደትንግርት የሚታዩ ናቸው፡፡
ቀራኒዮ መድሃኔዓለም ከአይመን ህንፃ ገባ ብሎ ባለው መንደር ውስጥ የተከፈተው ይሄው አውደ ርዕይ፤ ገና ወደ ግቢ ሲገባ በረጃጅም ሰንበሌጥና በተለያዩ የሳር አይነቶች የተከበበ ሲሆን የአንድ አርሶ አደር ግቢ የገቡ ስለሚመስለዎት በዛፉና በለምለሙ ሳር መንፈስዎ ይታደሳል፡፡ ደብዳቤዎቹ በሰባት ረድፍ ተደርድረዋል፣ በወቅቱ ደብዳቤዎቹን ለመላክ አቶ ስዩም ይጠቀምባቸው የነበሩ ቴምብሮች፣ ፖስት ካርዶችና መላኪያ ፖስታዎቹም ጭምር የአውደ ርዕዩ አካል ናቸው፡፡ አቶ ስዩም ሌላው ቀርቶ የእግሩን ቅርፅ በወረቀት ቀርፆ በማውጣት እዚያ ላይ የፍቅር ደብዳቤ ፅፎ ልኮላታል፡፡ “ይህ የሚወዱትን ሰው ለማግኘት እግር እስኪቀጥን መሄድን ያመለክታል” ብለዋል፡፡
ለመሆኑ ይህን ሁሉ ደብዳቤ በምን ጊዜሽ ታነቢዋለሽ? ለሚፃፍልሽስ ደብዳቤ መልስ የመፃፍ ልምድ ነበረሽ ወይ ስል ወ/ሮ ገነትን ጠየቅኋት፡፡ ጐንደር ውስጥ አዲስ ዘመን የሚባል ከተማ ተወልዳ ያደገችውና አጐቷ ጋር ለመኖር ወደ አዲስ አበባ እንደመጣች ያጫወተችን የአቶ ስዩም ባለቤት፣ ከዚያም እህቷ ጅዳ እንደወሰደቻት ገልፃ፣ ስዩምን በጓደኛዋ በኩል እንደተዋወቀችው ነግራኛለች፡፡ “እኛ ለጓደኛችን የሚፅፍላትን ደብዳቤ እናነባለን፤ እረፍት ወጥተን የሚልከውን ደብዳቤ እስከምናነብም እንቸኩል ነበር” የምትለው ወ/ሮ ገነት፣ በቀጥታ ለእኔ መፃፍ ከጀመረ በኋላ እረፍት ስወጣ ዋናው ስራዬ የእሱን ደብዳቤ ማንበብና ለእሱ ምላሽ መፃፍ ነበር” ብላለች፡፡ “እኔ መልስ የምፅፈው ስለጤንነቴ፣ ስለ ስራዬና አሰሪዎቼ፣ ስለኑሮና ጓደኞቼ ስለሚጠይቀኝ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት እንጂ እንደ እሱ ረቀቅ ያለ ደብዳቤ መፃፍ አልችልም በማለት አክላለች፡፡
በእያንዳንዱ ደብዳቤ ላይ ምክር አዘል፣ ለፍቅር ማጠናከሪያነት የሚያገለግሉ፣ ስለ ትዳር ክቡርነትና ስለታማኝነት የሚገልፁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተካትተዋል፡፡
በእያንዳንዱ ደብዳቤ ጀርባ ወይም ፊት ለፊት ላይ በረቀቀ አፃፃፍ “ገስ” የሚል ፅሑፍ ይታያል የገነትና የስዩም የመጀመሪያ ፊደሎች ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ደብዳቤ ላይ “ገኒዬ እወድሻለሁ” የሚለውም ቃል አይቀርም፡፡ አንዱ ደብዳቤ ሶስት ሜትር ከ28 ሳ.ሜ ርዝመት ያለው ሲሆን በጀርባውም በፊት ለፊቱም ፅሁፍ አለው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አውደ ርዕዩን ምሁራን፣ የስነ-ፅሁፍ ሰዎች፣ ተማሪዎች፣ እየጎበኑት ይገኛሉ፡፡
“ቦታውን ቀራኒዮ ነው ስትያቸው እንደ እውነተኛው ቀራኒዮ ሩቅ አድርገው ይስሉታል፤ በዚህ ምክንያት በጣም ብዙ ሰው ሊጎበኘው ሲችል እየጎበኘው አይደለም” የሚሉት አቶ ስዩም፤ በአሁኑ ሰዓት እነዚህ ደብዳቤዎች የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትም ጭምር ስለሆኑ በደንብ እንዲጎበኙና በግልፅ እንዲታዩ ከፖስታ ድርጅት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል፡፡ “ለመሆኑ ከ1994 እስከ 2000 ዓ.ም ባሉት አመታት እንዴት መፃፍ አቆሙ?” የሚል ጥያቄ አንስቼላቸው ነበር፡፡ “እውነት ነው በእነዚህ ዓመታት በጣም አልፎ አልፎ ብፅፍም ሙሉ ለሙሉ ግን አቁሜ ነበር ማለት እችላለሁ ምክንያቱ ደግሞ ቴክኖሎጂው ተንቀሳቃሽ ስልክን ፈጠረና ከገኒ ጋር በየጊዜው መደዋወልና ሃሳባችንን መለዋወጥ ጀመርን” ብለዋል አቶ ስዩም፡፡ ከዚያ ለኢትዮጵያ ሚሌኒየም መጥታ ተጋባን፤ ይሄው በትዳር ሰባት ዓመታትን አስቆጠርን፤ በሰላምና በፍቅር እየኖርን ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡ እርግጥ ነው ልጆች አላፈሩም፤ ምክንቱን ጠይቄው እኛ ፈጣሪን ጠይቀናል፤ ምላሽ እየጠበቅን ነው፡፡ ባይሳካም ዋናው ፍቅራችን ስለሆነ እንደችግር አንቆጥረውም፤ እነዚህ ደብዳቤዎች ልጆቻችን ናቸው በማለት መልሰዋል፡፡
ወ/ሮ ገነት በበኩሏ “ስዩም መልካም ባል ነው፤ በተለይ አረብ አገር እያለሁ እሱን ከተዋወቅሁ በኋላ በሚፅፍልኝ ምክር፣ አፅናኝ ቃላት፣ በሚሰጠኝ ፍቅር ብርታትና ጉልበት አግኝቼ ስራዬን በጥንካሬና በብቃት አጠናቅቄ እንድመጣ ረድቶኛል” ስትል ስለባሏ ያላትን አስተያየት ሰንዝራለች፡፡
“በአሁኑ ሰዓት በእነዚህ ደብዳቤዎች ላይ ጥናት እየሰራሁ ነው” የሚለው አቶ ስዩም፤ ትልልቅ ምሁራን ከጎበኙት በኋላ ለምርምር፣ ለማስተማሪያነትና ለመሰል አገልግሎቶች ይውላል እንዳሉት ገልፆ፣ ምን ያህል ቃላትን እንደተጠቀምኩ፣ ስሟንና እወድሻለሁ የሚለውን ለስንት ጊዜ እንደፃፍኩ፣ ምን ያህል ወረቀትና ገፆች እንደተጠቀምኩና መሰል ሁነቶችን የሚገልፅ ወደ 80 ገፅ የሚጠጋ ፅሁፍ ፅፌያለሁ፤ ግን ይቀረኛል በማለት አብራርተዋል፡፡ ምሁራን በሰጡኝ ጥቆማ “ጊነስ ቡክስ ኦፍ ሬከርድስ” ላይና በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በጉዳዩ ዙሪያ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ለመምከር አቅጃለሁ ከዚያ በፊት ግን ግልፅና አማካይ የሆነ ቦታ ላይ አውደ ርዕዩን ለህዝብ ክፍት ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ ነኝ ሲልም ተናግረዋል፡፡
አውደ ርዕዩን ጎብኝተው አግራሞታቸውንና አድናቆታቸውን ከቸሩት ውስጥ “የጉንጉን” እና የየወዲያነሽ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር መርከብ መኩሪያ ይገኙበታል፡፡
አቶ ስዩም ወ/ፃዲቅ አፍሪካ ህብረት ሳር ቤት አካባቢ ተወልደው ያደጉ ሲሆን በፍሬህይወትና በሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤቶች ተምረው 12ኛ ክፍልን ካጠናቀቁ በኋላ በኢትዮጵያ አየር ሃይል ውስጥ በግራውንድ ቴክኒሺያንነት ለሰባት አመታት አገልግለዋል፡፡ በሬዲዮ ኤሌክትሮኒክስ ስራ አስመራ ውስጥ ለሁለት አመታት መስራታቸውንም አጫውተውኛል፡፡ በተለያዩ የመንግስት ስራዎች ከሰሩ በኋላ በመንግስት ለውጥ ጊዜ ስራቸውን ለቀው አሁን ከጓደኞቻቸው ጋር “ፍኖት የማስታወቂያ እና ህትመት ስራ ድርጅትን” በመክፈት በግል እየሰሩ ሲሆን የሲኒማና የፎቶግራፍ ትምህርት ማስተር ት/ቤት ተምረው ተመርቀዋል፡፡ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ የተዋወቋን ፍቅረኛቸውን አግብተው በመኖር ላይ ሲሆኑ የተዋወቁበትን 20ኛ ዓመት አስመልክተው ከሐምሌ 19 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ይህን የደብዳቤ አውደ ርዕይ ከፍተው በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡   

Read 37111 times