Saturday, 21 February 2015 13:39

የ100ሺ ብር ግጥም

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ዳሽን ቢራ አክሲዮን ማኅበር የመጀመሪያውን ዓመት “ዳሽን የኪነ ጥበባት ሽልማት” ጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ማካሄዱ ይታወቃል፡፡ በዚሁ ወቅት በስነ - ግጥም ዘርፍ ለውድድር ከቀረቡ 157 ግጥሞች መካከል 1ኛ በመውጣት 100.000 ብር ሽልማት አሸናፊ የሆነው የሰለሞን ሞገስ ግጥም ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡

ሕልሞቻችሁን ፈልጉ

በንስር ጉልበቶቻችሁ በጉንዳን ጽኑ ሥርዓት፣
በቆሰለ ጅብ ተጋድሎ በሴቴ ሸረሪት ብልሃት፣
በረቂቅ የጣዝማ ጥበብ በአናብስት የወኔ ሙላት፣
ሕልሞቻችሁን ፈልጉ እስከ ከፍታችሁ አናት፡፡
    በየብስና በባህሩ፣
    በበረሃና በዱሩ፣
    በህዋው ላይ በጠፈሩ፣
    መቼም ይሁን የትም ሥፍራ፣
    በመሬት እንደ አደን ውሻ፤ በሰማይ እንደጆቢራ፣
የሰው ልጆች ሆይ ተነሱ!  
ያንቀላፋውን ማንነት ፍጥረታችሁን ቀስቅሱ፣
መክሊታችሁን ፈልጉ ሕልሞቻችሁን አስሱ፡፡
    የየመንገዱ ትብታብ ድር ክንፎቻችሁን ያሰረ፣
    እምቅ ወኔን የፈተተ የእልህ ጉልበት የጨመረ፣
    መገፋት፣ መውደቅ፣ መታሸት፣ መወቀጥን ያስተማረ፣
    እንኳንስ ኖረ ጨለማ እንኳን እሾህ ተፈጠረ፡፡
    አውራ ዶሮ እንኳ በአቅሙ አምፆ ባይሆን በቁጣ፣
    መች ያየው ነበር ዓለሙን ቅርፊቱን ሰብሮ ባይወጣ?
    ወትሮስ ጨለማ ከምንጩ፣ ፅልመት ፊቱን ባይፈጠር፣
    ብራው ቀን ጨለማ አልነበር?
    ወርቅም ዘመን እስኪያነሳው፣
    አፈር ላይ ነው የሚተኛው፡፡
    እና…
የውስጣችሁን ዝማሬ የነፍሶቻችሁን ቅኝት፣
የልባችሁን ተመስጦ የሕልሞቻችሁን ምሪት፣
የተፈጥሯችሁን ጥሪ የመሻታችሁን ትዕይንት፣
    የናፍቆት በገናችሁን የተስፋችሁን ነጋሪት፤
    የልባችሁን ውብ ቋንቋ፣
    የውስጣችሁን ሙዚቃ፤
    ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ አልሙ፣
    በእውቀት፣ በጥበብ ማማ ላይ  በኩራት፣ በክብር ቁሙ፡፡
        እንደ ሰንደቅ ዓላማ ክብር በከፍታ እንድታርጉ፣
        መደንዘዝ የሰወረውን መክሊታችሁን ፈልጉ፡፡
        በራስ ለራስ ዋጋ ማነስ ቅስማችሁን አታድቅቁ፣
        በተስፋ ማጣት ስብራት ስፍራችሁን አትልቀቁ፣
        ከአፈር፣ ከጭቃ መሃል ነው የሚገኘው እፁብ ወርቁ፡፡
        ጋንም እንደጥራጊ የትም መበተን ምን ይሆን?
        ዋርካ ሲቻል ሰንሰል መሆን፡፡
        በሉ እንጂ ጃል!            
በልባችሁ ላይ ያለውን ጭሱን፣ ጭጋጉን ጥረጉ፣
የነፍሳችሁን ብርሃን ሕልሞቻችሁን ፈልጉ፡፡
          ለአደን፣ ለግዳይ ተነሱ!
        እምቅ ብቃትን አስሱ!!
    የኑሮ ውጣ ውረዱ ቁልቁለትና ዳገቱ፣
    የብቸኝነት በረሃው ራብ፣ ጥምና እንግልቱ፣
    አሻጋሪ የለሽ ባህር የቀን ጨለማው ብርታቱ፣
    የአማሳኙ፣ የአዋሻኪው፣ የሸንጋዩ፣ የጽልመቱ፤
    ሕልም ካለ ይታለፋል!
ጉም፣ ጭጋጉ ይገፈፋል፡፡
ምሬት ገ’ተህ፤ እንባ አቁመህ፤ ሰበብ ጥለህ እልህ ጨምር፣
ብሶት ትተህ ማርሽ ቀይር፣
የነግ ፀሐይ ጎህ ሲወለድ፤ መጪው ዘመን አቤት ሲያምር!!
ስንት ንቀት ቢለጥፉ ስንት አሉታ ቢከምሩ፣
አበበ ነው ድል ያ’ረገው ይህን ዓለም በሌጣ እግሩ፡፡
አትሰወር!  አትደበቅ!  አንተም ንገስ በከፍታ፣
ተራራ  ሁን ወይ ኮረብታ፡፡
    ንሳ ጎበዝ!
    በጎ ተስፋ ካላለሙ ዕድሜ ከሆነ ሕልም የለሽ፣
    እንደ ደረቀ ቅጠል ነው የሰው ሕይወት ረብ የለሽ፡፡
    ራዕይ የሌለው አገር ሕልም የሌለው ትውልድማ፣
    ነፍስ የሌለው አሻንጉሊት መብራት የጠፋው ከተማ፡፡
    አዎን ጎበዝ!....
ዘመናችሁ እንዲከብር ዱካችሁ “ እከሌ” እንዲሰኝ፣
ሕይወታችሁ እንዲጣፍጥ ኑሯችሁ ትርጉም እንዲያገኝ፤
ስማችሁ በምርጦች ተራ በቀለመ - ወርቅ እንዲፃፍ፣
ፍሬያችሁ ከዘመን ዘመን እርሿችሁ ለትውልድ እንዲያልፍ፤
ተነሱ በአጭር ታጠቁ! ወገባችሁን ሸብ አ’ርጉ፣
መክሊታችሁን አስሱ ሕልሞቻችሁን ፈልጉ!!
የእናት አባት ብቻ አ’ደለም አምጦ የመፍጠር ግዱ፣
ሕልማችሁን ፀንሳችሁ እራሳችሁን ውለዱ፡፡
    የድል፣ የአርበኝነት ውሎን ለየራሳችሁ ንገሩ፣
    እንደ ያሬድ ሰባቴ ነው ወድቆ መነሳት ምስጢሩ፡፡
    መንገዳችሁ ላይ ከበራው አምፖል ከያዘው ሰማዩ፣
    ሕልም ይበልጣል ከፀሐዩ፡፡
    የሰው ልጆች ሆይ ተነሱ!
    ያንቀላፋውን ተፈጥሮ እምቅታችሁን ቀስቅሱ፣
    ጉልበታችሁን አበርቱ፤ ክንፎቻችሁን አድሱ፣
መክሊታችሁን ፈልጉ ሕልሞቻችሁን አስሱ፡፡

Read 4595 times Last modified on Saturday, 21 February 2015 13:45