Monday, 27 July 2015 11:18

የትውልድ ቅብብሎሽ የተነፈገው ሥነ-ፅሁፋችን!

Written by  አለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(2 votes)

ቀጠሮዬ “ይብሳ ህንፃ” ነው፡፡ ህንፃው በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትና በጃንሜዳ መካከል እንደሚገኝ ተነግሮኛል፡፡ በቅጡ ስለማላውቀው እየጠየኩ ወደዚያው አዘገምኩ፡፡ ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት አንፃር ሲታይ አካባቢው ላይ ሁለት ባለ አራት ድርብ ህንፃዎች ብቻ አሉ፡፡ አንዱ ተጠናቋል፣ ሌላኛው በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ “የትኛው ይሆን?” እያልኩ ጥቂት እንደተጓዝኩ መንገደኛ ጠየኩ፡፡ “ይብሳ ህንፃን” አሳዩኝ፡፡
 መጀመሪያ አላመንኩም፡፡ መልሼ ሌላ ሰው ጠየቅሁ፡፡ በድጋሚ ያንኑ ቤት አመላከቱኝ፡፡
ግር አለኝ …
… “ይብሳ ህንፃ” በሸክላ የተሰራ መደዳ ቤት ነው፡፡ ደርብ የሚባል የለውም፡፡ ታዲያ ስለምን “ህንፃ” ተባለ? ማንም ሊነግረኝ አልቻለም፡፡ ሁሉም የሚያውቀው “ይብሳ ህንፃ” መባሉን እንጂ ለምን እንደተባለ አይደለም፡፡ ከመመርመር ወደ መጠርጠር ተሸጋገርኩ፡፡ በአፄ ምኒልክ ዘመን አካባቢው ላይ “ከላሾች” ሰፍረው ነበር፡፡ “ከላሾች” ቀላህ ሰብስበው እርሳስ እያቀለጡ አረር በመሙላት ለዳግም ጥይትነት የሚያበቁ ሙያተኞች ናቸው፡፡ በወቅቱ ከላሾቹ የጥይቱን ሜዳ ላይ ደርድረውና በጣሳ ሰፍረው ይሸጡ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ እነዚህ ከላሾች ጥይት አረር የሚሞሉበት ሥራቸው ሆዳቸውን ሞልተው ከማደር ውጪ ጥሪት ለመሰብሰብ የሚያስችል አልነበረምና የሚኖሩበት ጎጆም እንደ ነገሩ የተጠጋገነ ነበር፡፡ እንግዲህ ከእነሱ መካከል ፊውራሪ ይብሳ አንድ ቀይ ሸክላ ቤት አስገነቡ፡፡ ለአካባቢው ብርቅ እና ድንቅ ከመሆኑም ባሻገር ከሩቅ የሚታይ መለያም ጭምር ነበር፡፡ ስለዚህ ቤቱ በንፅፅር ደምቆ በመታየቱ የገዘፈ ሥም አገኘ “ይብሳ ህንፃ”፡፡
ሳቅኩ!! በዕድሜ ጠገቡ ቤት ላይ ሳቅኩ፡፡ እኔ አይደለሁም የሳቅኩት ትውልድ ነው፡፡ አባቶች ካሉበት ዘመን አንፃር ነፅረው ያገዘፉት ለእኔ ኮሰሰብኝ፡፡ መጀመሪያ “ይብሳ ህንፃ” ስባል ለግምት እዝነ ልቦናዬ ላይ የተደረደሩት የዘመኑ ህንፃዎች በታሪኬ ላይ እንድስቅ አስገደዱኝ፡፡ ትውልድ እንዲያ ነው፡፡ ተቀባብሎ የማደግ ሰዋዊ የተፈጥሮ ህግ ከትንሽ ወደ ትልቅ መጓዝን ግድ ይላል፡፡ ባለፈው መሳቅ ከማገናዘብ በፊት ይቀድማል፡፡ ትውልድ እንዲሁ ነው፡፡
በመጀመሪያው ካሜራ ቢሳቅ የትውልድ ወግ ነው፡፡ የሚከራይ ቤት መስሎን ስንጠይቅ ካሜራ መሆኑ ሲነገረን ለምን አንስቅ? እንስቃለን!! ጡሩንባ መስሎን ያየነው፣ የመጀመሪያው ግራማፎን መሆኑ ሲነገረን አሁንም እንስቃለን!! ምክንያቱም ትውልድ አሻሽሎ የሰጠን ለማንፀሪያነት አለን፡፡
… የሚያሳዝነው ግን የትውልድ “ሳቁ” በሁሉም ዘርፍ አይተገበርም፡፡ በተለይ የእኛን አገር ሙዚቃ፣ ሥዕል፣ ስፖርት፣ ሥነ-ፅሁፍ … ስንቃኝ ትውልድ በቀደመው ትውልድ ከመደመም ወጥቶ ለሳቅ አይዳዳውም፡፡ ጥላሁን ገሠሠና ዘመኑ የዚህ ትውልድ መሰረት ሳይሆኑ ከላያችን ያሉ ጣሪያዎች ናቸው፡፡ ለምን? የአገኘሁ እንግዳ ሥዕሎች እንደ “ይብሳ ህንፃ” የሚሳቅባቸው እርቀት ላይ አይደለንም፡፡ ለምን? እግር ኳስ እነመንግሥቱ ወርቁ ጋ ቀርቷል ብለን ስለምናስብ የዘመኑን ጨዋታ በእነ ሳልሀዲን ሳይሆን በእነሱ ብንገጥም እንደምናሸንፍ ደምድመናል፡፡ ለምን? በአማርኛ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ ጥቂት ደራሲያን ብቻ የመጀመሪያም የመጨረሻም ተደርገው ተደምድሟል፡፡ የመጀመሪያ መባላቸው ይሁን፤ እንዴት የመጨረሻ ተብሎ በእነሱ ተደመደመ? ለምን? ….
… ተፈጥሯዊውን የትውልድ ዕድገት መርህ ተፃርረን!! የኋሊት ብቻ የመመልከት ዕጣ - ለእራሳችን አውጥተናል፡፡ የትውልድ አቅጣጫ ወደፊት መሆኑን ዘንግተናል፡፡ በአዲስ ጎዳና ላይ ያለፈ ትውልድ ዱካ እንፈልጋለን፡፡ ያንን ዱካ ለመሳፈር እንቃብዛለን፡፡ ኦታምፑልቶ (ኢትዮጵያዊው ደራሲ በቅርቡ በ Penguin Book የታተመለት አንድ መፅሐፍ አለ፡፡ ርዕሱ “Catch your Thunder” ይሰኛል፡፡ እዚህ 517 ገፅ ያለው ሥራ ውስጥ ትውልድን ከእግር ዱካ ጋር አጣምሮ የሚመረምር ንዑስ ምዕራፍ አለ፡፡ “The root prints that you see ahead of you are not that of your ancestors. They rather are of your children.” እውነት ነው፤ ያለፈ ትወልድ ዱካ እንዴት መጪ ትውልድ መንገድ ላይ ይነጠፋል? ምንጊዜም ከፊትህ የሚገኘው ፈለግ የልጅህ እንጂ የአባቶችን ሊሆን አይችልም፡፡
… ይብሳ ህንፃ መለስ ብለን የምናየው የአባቶቻችን እግር ፈለግ ነው፡፡ ከዘመኑ ውጪ ሲታይ ስያሜው ይከብደዋል፤ ህንፃ መባሉ ያዋርደዋል፡፡ ይህ እንዲህ የሆነው በግንባታ መለስተኛ የትውልድ ቅብብል ስለተከናወነ ነው፡፡ ፍርቅርቁ አሁን ለንፅፅር የሚታዩ ጥቂት ህንፃዎች ዘንድ አድርሶናልና፡፡ እስክናገናዝብ የፌዝ ሳቅ ቢያመልጠን ለታሪክ ፍርድ አንቆምም፡፡ በተፃራሪው በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በሥነ ፅሁፍ… የትውልድ ቅብብል ስላልተከናወነ ይሆን ባለፉት ስራዎች የፌዝ ሳቅ የማያመልጠን? የግማሽ ምዕት ትውልድ ምን ዋጠው? ዱካውን ምን ሰለበው? ምንስ ሲሰራ መሽቶ ነጋለት? እንዴትስ ከሱ በፊት የነበሩትን መጋረድ ተሳነው? … እነዚህ ጥያቄዎች የሚቀርቡ የተለያዩ ምላሾች አሉ፡፡ አንደኛው የነቢይ መኮንን ተሃዝቦ ነው፡፡ “ሥውር ስፌት ቁ.1” ላይ “ደረጃ የሌለው መሠላል” በተሰኘ ርዕስ እንዲህ ይላል፡-
ይሄ ያገሬ ሰው እኮ፣ መሠላል አወጣጥ ያቃል
አንዱን እርከን ረግጦ ሲያልፍ፣ ነቅሎ ጉያው
ይከተዋል
ደሞ ቀጣዩን ይረግጣል …
ነቅሎ ጉያው ይከተዋል …
እንዲህ እንዲያ እያለ ዘልቆ፣ ከዝና በላይ
ይወጣል፤
ከጥቅምም በላይ ይሰፍራል …
እንደኮራ እንደተዝናና፣ ቃል ሳይናዘዝ ይሞታል፡፡
በቀብሩም ሥርዓት ላይ
“ደግ ለሰው አሳቢ
ለተቸገረ ደራሽ…”
የሚል የህይወት ታሪክ ወግ፣ ይፋ ይነበብለታል። ከቀን በኋላም ገኖ፣ ሀውልቱ ገዝፎ ይታያል፡፡
ያም የደረጃ እርከን - እንጨት፣ መቃብር አጥሩ ይሆናል!!
የትውልድ መንገድ አግዳሚ የሌለው መሰላል መሆኑ መወጣጫ ነሳን፡፡ ስለዚህ ያለፉትን አንጋጦ መመልከት የህይወት ፍልስፍናችን ሆነ፡፡ ታሪክ እንደ ትልም፣ ነባር እንደ ግብ ታየ፡፡ እንደ መስታወት ክትር ከጀርባችን የምንደብቀው፣ የምንጋርደው አጣን፡፡ እንደሌለን ሆንን፡፡ አባቶቻችን በእኛ ላይ የምንግዜም አንደኛ ሆኑ፡፡ ልጆችን በእኛ ዘንድ የምንጊዜም ምንም ሆኑ፡፡ የትውልድ ንብብሮሽ ፈረሰ፡፡ አንዱ ከሌላው ማጅራት አልፎ ማየት ተሳነው፡፡ ቅብብሎሹ ተዛነፈ፤ ሰጪ ተቀባይ፣ ተቀባይም ሰጪ አጣ …
… ትውልድ ሲቀበል ልደቱ ሲሰጥ ሞቱ ይከናወናል፡፡ እኛ ዘንድ ልደትም ሞትም የለም፡፡ ትወልድ አልጌ ተከናንቦ ረግቷል፡፡ የሚያፋስሰው አጥቷል፡፡ የሚያነባብረው የሙሴ በትር ተነስቷል፡፡ እይታችንን ዳፍንት፣ ቁመታችንን  ክፋት አሳጥሮብናል፡፡ የታየን እንደግማለን፣ በተደረሰበት ቁመታችንን እንለካለን …
… እንግሊዛዊው ሳይንቲስት አይዛክ ኒውተን (1642-1727) ስለትውልድ ንብብሮሽ የሚለው አለው፡፡ “If I have seen a little farther than others, it is because I have stood on the shoulders of giants.” (በጥቂቱም ቢሆን ከሌሎች በተሻለ አርቄ ለመመልከት የቻልኩበት ምክንያት በግዙፉ ትከሻ ላይ በመቀመጤ ነው፡፡)
አዲስ ትውልድ በጥቂቱም ቢሆን አሻግሮ መማተር ካልቻለ፣ የነባሮቹ ትውልድ ትከሻ የለም ማለት ነው፡፡ ትውልድ የመደዳ ድርድር ከሆነ የሚታየው ከማጅራት ፈቅ አይልም፡፡ ደራሲ አዳም ረታ “በአዲስ ነገር” ጋዜጣ ላይ ያለው ይሄንኑ ነው ያለው፡፡ “ያለፉት ትውልዶች ትከሻ እንደጠርሙስ ልሙጥ ነው፤ አያስቀምጥም” እንደ ይብሳ ህንፃ በሀዲስ አለማየሁ፣ በበዓሉ ግርማ፣ በፀጋዬ ገብረመድህን፣ በመንግሥቱ ለማ … ላይ መሣቅ ያቃተን ለዚህ ነው፡፡ ከማጅራት ከፍ ባላለ እይታ በምንና በማን አንፅረን በሥነ ፅሁፎቹ “ይብሳ ህንፃዎች” ላይ እንሳቅ???

Read 1776 times