Saturday, 01 August 2015 14:44

“ወሪሳ” - ሕይወትን በግሪንቢጥ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

   የጥበቡ ሰማይ - ጭርታ ውጦት፣ በዝምታ እያዛጋ ነው ለማለት የምንደፍርበት ጊዜ አይደለም፡፡ ግን ከሚወረወሩት ኮከቦች ስንቱ በዓመድ የተለወሰ፣ ስንቱ በውበት ዘውድ የነገሠ ነው ብሎ ለመምረጥ፣ የተደላደለ ሜዳና፣ ደፋር ሚዛን መጨበጥ ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ከጥበቡ ልዕቀትና ምጥቀት ይልቅ አድርባይነቱና አቅመ ቢስነቱ ከሰማይ ጋር ከንፈር ገጥሟልና!...ብዙ ውዳሴና ክንፍ ማወዛወዝ ለማጥገብ ብዙ ገለባዎች እንደ ሰሜን ንፋስ፣ እንደ አውራቂሳ ማዕበል እየተወረወሩ ነውና!
እንግዲያውስ በሥራ ቢሆን እንደ ኑረዲን ኢሳን የመሰሉ ፀሀፍት በጓዳችን ሙዳይ ውስጥ ተደብቀው በዓመት አንዴ እንኳ ወግ ማውጣት ያቅታቸው ነበር!
ሃሳቤ አንቅፎት ወደ ሌላ እንዳይሄድ ልጓም ላግባለትና ወደ ዛሬው ጉዳዬ ልግባ፡፡ የዛሬው ፅሁፌ ሰበብ ደግሞ የዓለማየሁ ገላጋይ አዲስ ልብወለድ፣ “ወሪሳ” ነው፡፡ ዓለማየሁ ለምን ቶሎ ትርጓሜው የሚገባ ርዕስ እንደማይመርጥ ባይገባኝም፣ (“ኩርቢት” የሚለውን የአጭር ልብወለድ መድበሉን ጨምሮ) ወሪሳ የሚለው ቃል ግን ዘረፈ፣ በዘበዘ … ወረረ ማለት ነው፡፡ አሁን ወደ መጽሐፉ እንዝለቅ!
ዓለማየሁ ገላጋይ በዘመናችን ከሚጠቀሱ በሣል የሥነጽሁፍ አንባቢያን፣ ደራሲያን፣ ሃያሲያንና ተንታኞች ተርታ በቀዳሚነት የሚሰለፍ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም “አጥቢያ” በተሰኘ ልቦለድ መጽሐፉ፤ አራት ኪሎን ልብስዋን አውልቆ፣ ነውርና ቁንጅናዋን፣ ክርፋትና መዐዛዋን ያሳየን ዓለማየሁ፤ በ “ወሪሳ” ደግሞ ባልታየ ዓይን፣ ማሕበረሰባዊ መዋቅሮችንና ድንኳኖችን ገልብጦ በከተማ ላይ ከተማ፣ በማህበረሰብ ዓይን ውስጥ ሌላ ዓይን ፈጥሮ ብቅ ብሏል፡፡ ምናልባትም አጠቃላይ መዋቅሩ ሲታይ የድህረ ዘመናዊነት ፍልስምና አዝሎ፣ ዘመናዊ የአፃፃፍ ስልትን ሳይለቅ፣ በስላቅ (Satire) የሚተርክ ነው ማለት ይቻላል፡፡
“ወሪሳ” መበዝበዝ፣ መውረር ከሆነ ወሪሳዊያን ደግሞ በዚያ ፈረስ ተቀምጠው ሕይወትን የሚጋልቡ ተዋናዮች ናቸው፡፡ ትወናውና መድረኩ ደግሞ ለኛ በተለይ ኦሪትን ለተቀበልን ኢትዮጵያዊያን አሊያም በቁርዐን ለምንመራ ሰዎች እጅጉን እንግዳ ባህልና እምነት ነው፡፡ ግና እነ ፎከልት እንደሚሉት፤ ዘመኑ የዕውቀት ሳይሆን የትርጓሜ (Interpretation) ነው፡፡ አጠቃላይ የሆነ የጋራ ዕውቀት ሳይሆን፣ እንደ ወሪሳዊያን አካባቢያዊ የሆነ እምነትና ግብ እንዳይኖር የሚከለክል ድንበር የለም፡፡  
ዓለማየሁ በሕይወትና በማሕበረሰብ ላይ የተሣለቀበት መንገድ (Satire) ከሁለቱ ዐበይት መንገዶች አንዱን ነው፤ “Horatian” የተሰኘውን፡፡ ይህ አፃፃፍ እንባ ያጠቀሰውን የሕይወት መልክ እንኳ በሣቅ ቅባት ያሳምረዋል፡፡ የገረጣውን የሕይወት ፊት በሣቅ ቬሎ ይሞሽረዋል! “ወሪሳም” እንዲያ ነው…እሾህ በተነጠፈበት የቀራንዮ መንገድ፣ የትንሣኤን ብርሃን የሚፈጥር! በዮፍታሔ ልጅ የሥዕለት ጭዳነት፣ የአንድ ወርዋን ዘፈን ከበሮ የሚደበድብ አታላይ ዓለም!
በጥቅሉ የፃፈበት መንገድ መነሻ ከግሪክ ጓዳ የተገኘ፣ በሮማ አደባባይ ያደገና በነሞሊየር የጥበብ ፍም የተወለወለ ነው፡፡ ከገጣሚዎቹም እነ ድራይደን በመንቶ ግጥሞች የተራቀቁበት፣ እነ ቮልቴር ዘውድ የጫኑበት ነው፡፡ በተለይ እንግሊዝ በ18ኛው ክፍለ ዘመን አይኖችዋን ተኩላበታለች፡፡ አሜሪካም ያንን ቀለም፤ ጥበብዋን ሞሽራበታለች፡፡ ምናልባትም የዚህ ዓይነቱ ጥበብ እንባ በተጣባ ጊዜ፣ ሰማይ ለንጋት ሳይቀላ በደመና ፊቱን ባጠቆረ ጊዜ፣ የውሃ መንገድ ይመስለኛል፡፡ አሜሪካም በነፃነትዋ ብርሃን ዋዜማ፣ በዚህ ችቦ ጭላንጭል የተሣከረችው በዚሁ ስሜት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ለነገሩ “ሳታየር” ማለትስ የያይነቱ ፍራፍሬ ቅምር ማለት አይደል… (ፍሩት ፓንች እንበለው!...)
ሆኖም ግን በኛ ሀገር ሥነ - ጽሑፍ ታሪክ፣ ይህንን መንገድ የተከተለ የልቦለድ ደራሲ ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ስለዚህም በዚህ አሠልቺና ግልብ ሥራዎች በንፋስ ተንጠልጥለው አየሩን በከደኑባት የሥነፅሁፍ ሰማይ ሥር፣ ሌላ ደጅ አንኳኩቶ አዲስ እንግዳ ይዞ ብቅ ማለት ዓለማየሁን የሚያስወድሰው ይመስለኛል፡፡
የዘመናዊውን ሥነ ጽሑፍ መንገድ የተከተለው ይህ ድርሰት ባዋቀረው ማሕበረሰባዊ ሕይወት ዐውድ ውስጥ የተለያየ መልክና አስተሳሰብ ያላቸው፤ ግን ደግሞ ባንድ ሳንባ የሚተነፍሱበት የጋራ እሴቶችን ያረቀቁና ያፀደቁ ሰዎች በአንድ አዳራሽ ታድመዋል። አዳራሹም የጋራ መልካቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የአማርኛ መምህር የሆነው መሪ ገፀባህሪ፤ ወሪሳ ወደሚገኘው የአክስቱ ልጅ ቤት ገብቶ ሲኖር፣ ያጋጠመውን አዲስ ባህል፣ አዲስ አስተሳሰብና ሕይወት፣ ከሥሩ እየተተረተረ ይተረክለታል፡፡
ታዲያ ሕይወት በ“ወሪሳ” የግሪንቢጥ ነው። “ወሪሳ” ውስጥ የማሕበራዊ ሣይንስ ምሁራን ካስቀመጧቸው ስድስት ያህል የትክክለኝነት መለኪያ ደንቦች አንዱን የሚከተል ይመስላል፡፡ “Antinomianism” የሚለውን፡፡ ይህ የፍስልስፍና ቀንበጥ፣ “There is no moral laws” ወደሚለው ያዘነብላል፡፡ የዚህ ፍልስፍና አቀንቃኞች ለምሳሌ መዋሸትን “ትክክልም ሀሰትም አይደለም” ይላሉ። ለወሪሳዊያንም ይህ እውነት ይመስላል፡፡ መሥረቅ ነውር አይደለም፡፡ ሥራ ነው፡፡ ከጉብዝና ይቆጠራል፡፡ እንደውም ያለመስረቅ ጣጣ ያለው ነው የሚመስለው፡፡
ዋናው ገፀ ባህሪ በዚህ ገንዳ ውስጥ ገብቶ፣ የቀደመው አስተሳሰቡ እንዲታጠብ መዐት ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ ከባልቴትዋ ወ/ሮ ገዶ፣ አቶ ጆቢራ፣ አቶ አንጰርጵር ለርሱ የሰጡት ግብዐት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ወሪሳ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የራስዋን የሕይወት መልክ ይዛ፣ ደጅዋ ላይ የራስዋን ፍልስፍና ሻማ የለኮሰች ሉዐላዊት ደሴት ናት፡፡ የአማርኛ መምህሩ ዓይነት የማዕበል ሰይፎች ቢላኩም ድምፃቸው ተውጦ፣ ሥነ ልቡናቸው ቀልጦ እንደገና ይፈጠሩባታል፡፡ ወ…ሪ…ሳ!
“ወሪሳ” ውስጥ አውራ ጣት የሚያክሉት አቶ አንጰርጵር ሠፊ ድርሻ አላቸው፡፡ ቁመናቸው እንደ ናፖሊዮን ነው፤ ልባቸውም የእርሱን ያህል ተከምሯል፤ ልዩነታቸው የፍልስፍና ነው፡፡ ምናልባት በገፀ ባህሪያት አሣሣል መለኪያ በሥነ ልቡናዊው ቀረፃ፣ ዓለማየሁ የተሻለ ተግቶበታል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ለ “Compensation” ወይም ማካካሻ ሲሉ ሰዎች በውስጣቸው ለሚፈጥሩት ሞገደኝነት ብርታት እንደ ማስረጃ ይሆናሉና!
እዚህ መጽሐፍ ውስጥ መሪ ገፀባህሪው የቅርጫት ኳስ ዓይነት ሚና ያለው ይመስላል፡፡ ሁሉም የራሱን ግብ ሊያስቆጥር ነውና የወረወረው። አምጰርጵር በታሠረው የአክስቱ ልጅ ሰበብና “ሰው ገድሎ የመጣ መምህር ነው” በሚለው ወሬ ሊፈሩበትና ሊታፈሩበት፣ ቀድሞ በነበራቸው ግርማ ሞገስ ላይ ሌላ ሊደርቡ ሲባትሉ እናያለን፡፡ ዕውቀት ለማጋራት ጠመኔ የጨበጠውን የመምህር እጅ፣ ዱላ አስጨብጠው የራሳቸውን ስም ሊያደምቁበት ይባትታሉ፡፡ በዚህ ሰበብም ነገር ለቅመው ሕግ አዋቂነታቸውን ሰበብ አድርገው ቤተሰብ ሊያደርጉት ተራራ የምታክለውን ልጃቸውን ሺትረግጥን ድረውታል፡፡ ያልወለዳቸውን ልጆች እንዲያሳድግ፣ የሞዴል 6 እሥረኛና ደንበኛ አድርገው ሰማይን ደፍተውበታል፡፡ እርግጥም መምህሩ የቅርጫት ኳስዋን ሆኖ ተንከባልሏል፡፡ መሬት ደብድቦታል፤ ብዙ መዳፎች ጨምድደውታል፡፡ ባልወደዳቸው ፓርቲዎች ገብቶ ሠልፈኛ ሆኖዋል፡፡ “ወሪሳ” የሲዖል ስባሪ! የገነት ቅርፊት!
ህፃኑ ልጅ በማህበረሰቡ አስተሳሰብ የተቀኘ ሲናገር፣ ሲራመድ፣ ሲበላ፣ ሲጠጣ፣ የተሰራበትን አፈር ፍልስፍና የሚከተል ነው፡፡ “አባባ” ብሎ በተኮላተፈ አንደበት ሆድ ካባባ በኋላ፣ ሲታቀፉት የኪስ ቦርሣ የሚመዠርጥትበት ዓለም ናት - ወሪሳ! ጭፍኔ ደግሞ የመጽሐፉ ፅጌረዳ አበባ ትመስላለች። የጠወለገች ፅጌረዳ … ነገር ግን ነፍስዋ ከዚያ ሁሉ ጭቅቅት፣ ከዚያ ሁሉ ሚጥሚጣ አምልጣ እንደ ማር ስትላስ የምትጣፍጥ! … ህይወት ችክ ላለበት፣ ግራ ለተጋባው የአማርኛ መምህር፣ አዲስ ጀንበር ሆና፣ በጨለማ ቤቱ ብቅ የምትል!
ሲጋራ አጢያሽ፤ ጂን ጠጪ፣ የተበላሸ ህይወት ያላት፡፡ ግን ለሌላ ሰው የሚሆን ትኩስ የፍቅር ምድጃ ያላጣች፡፡ እንባ ረግጣ መሄድ የለመደች፣ ግን ደግሞ ስለ ፍቅር ከልብ የተጨመቀ እንባ የሚፈስሳት እንስት ናት - ጭፍኔ፡፡ ቋንቋዋ የተለየ፣ ቃላትዋ የተገነጠሉ፣ ነገር ግን ለሚሰማት የነፍስዋን ግማሽ የምታካፍል እንስት፡፡
ይህንን ውበት የአማርኛ መምህሩ ቀምሶታል፡፡ ዋናው ገፀ ባህሪው ይህንን ውበት ባይቀምስ ኖሮ፣ በዚያ ሸረሪት ባደራበት ቤት፣ በዚያ ለውጥ በናፈቀው ዓለም እንዴት ሆኖ ይኖር ይሆን! … ወይም ሳይደግስ አይጣላም እንደሚባለው ይሆን?!
የዓለማየሁ መጽሐፍ የምሳሌያዊ አነጋገሮች ጥራዝ ይመስል የማንሰማው ነገር የለም፡፡ የተረት ስብስብም ይመስላል፡፡ (ምናልባት ትንሽ ሳይበዛም የቀረ አይመስለኝም) ግን ይህንን በቦታ በቦታው መሰደር ሌላ የምንደነቅበት ስራ ነው፡፡
የሺትርገጥ አባት አምጰርጵርን ገና መጀመሪያ ያያቸው ቀን፣ገፅ 40 ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “አምጰርጵር ሁከተኛ ሳይሆኑ አይቀሩም፤ በአንድ ጊዜ ከቀጂውና ከጠጪ ጋር ሲጣሉ ነው ያገኘናቸው ይላል፡፡ የመጽሐፉን መሪ ገፀ ባህሪ እንዳስጨነቁት ሙሉ መጽሐፉን ማንበብ ግድ ቢልም የአማርኛ መምህሩ ከባለቅኔዎች አንደበት ተዋስኩኝ ብሎ የቋጠራቸው፣ ስንኞች ይህንን ያሳያሉ፡፡
እግዜር ይይልዎ አምጰርጵር
ከዚህ ሌላ ትዝብት ውረሱ
ሳይነጋ እንዳስመሹብኝ
ጊዜና ትውልድ ይፍረደን
ስነቃል እንዳስፈረዱብኝ፡፡
መራራ አጠጥተውታል፣ የሌለውን ልብ፣ ልባም ነው ብለው በትር አስይዘው ለጠብ ጋብዘውታል፤ እንቅልፍ ነስተውታል፡፡ ይሁን እንጂ በማህበረሰቡ እምነትና የአክብሮት መለኪያ ከፍ ብሎ እንዲታይ በማድረግ፣ ከምንም የማይቆጥረው ርዕሰ መምህር ሽር-ጉድ እንዲልለት፣ እንደ ምንጣፍ ዘርግተውለታል፡፡ “ጀግና እወዳለሁ” የሚሉት እነ ሳጂን መርጌም ተዐምር ሆነውበታል፡፡ የወሪሳ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅትም የህዝቡን ነፃነትና ክብር በማስጠበቅ የተጫወተውን ሚና በአካባቢው ዐውድ ሲያሳየን “ወቸ ጉድ” ብለን መሳቃችን የግድ ነው፡፡ ለካ ህዝብ እርኩሱን ቅዱስ፣ ቅዱሱን እርኩስ ብሎ በራሱ አደባባይ ላይ ሥያሜ መስጠት ይችላል? … ለካስ አሁን በአካባቢያችን ላለና ተቀብለነው ለምንኖር መስመር ሁሉ ማህበረሰብ አለቃ ነው? … ብለን ልናስብ እንችላለን፡፡ ለነገሩ እውነታችን ለሌሎች እውነት እንዲሆንና እንዲመሥል የምንባትለውስ ይህን አውቀን አይደል? … ሂትለርም‘ኮ እኔና የሀገሬ የጀርመን ህዝብ ሌሎችን ለመጉዳት የሰራነው ምንም ክፉ ሥራ የለም ብሏል፡፡ ብቻ በጥቅሉ የዓለማየሁ ገላጋይ “ወሪሳ” የሚያስቅም የሚያሳቅቅም ነገር አለውና ማለፊያ ነው፡፡ ሕይወትን በሌላ መነፅርና መንገድ ማየትም ደስ ይላል፡፡
የዓለማየሁ ገላጋይን መጽሐፍ ጠቅልዬ ሳየው፣ በርካታ መልኮችና ዥንጉርጉርነቶችን አስተውዬበታለሁ፡፡ በዘመን አንጓ መለኪያና መልክ እንኳ ከፊል ዘመናዊነት፣ የተወሰነ የድህረ ዘመናዊነት ቀለምና ባህርይ አለው፡፡ የገጸ ባህርያት አሳሳሉ እውነታዊ ሥነ ጽሑፍ ሊያሟላቸው በሚገባ አላባዊያን የተገጠገጠና ምክንያታዊነትን የጠበቀ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ደራሲ አዳም ረታ እንደሚያደርገውና የድህረ ዘመናዊነት ደራሲያንና ገጣሚያን እንደሚሉት፤ ዥንጉርጉርና ቅንጥብጥብ ሁነቶች የታዘሉበት አይደለም፡
ግን ደግሞ በዚህ ግራ መጋባት ውስጥ ወደ አንድ ሀሳብ ጥላ ስር ሊመራን የሚችል ምሁራዊ ጥቆማና አተያይ ያላቸው ሰዎች ነገር ውልብ አለብኝ፡፡ እንዲህ ነው ያሉት፡ Some post modern authors have brought together traditional forms in displaced ways in order to provide ironic treatments of otherwise perennial themes. ይህ ደግሞ ወስዶ ወደ ድህረ ዘመናይነቱ ፍሬዴሪኮ ዴ - ኦኒስ ዘፍጥረት ያደርሰናል፡፡
ታዲያ የዓለማየሁ ገላጋይ “ወሪሳ” ወደዚህ ካምፕ የሚተከል ድንኳን፣ የሚቀለስ ጎጆ አይደለም ትላላችሁ? አንብቡትና ሃሳባችሁን አጋሩን፡፡  

Read 1553 times