Saturday, 01 August 2015 14:44

የንባብ - አደባባይ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ቴክኖሎጂ ሲቀብጥ ትውልድም መልኩን ለቅቆ፣ ጨርቁን ጥሎ እንዳያብድ፣ በትይዩ ቦይ እንዳንለቀው፣ የሚተልምልን መሪ፤ መረን እንዳይወጣ የሚገታ የፍቅር ልጓም ያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ዕውቀትን በቅጡና በወጉ ለመጠቀም፣ በሥርዐት ለህይወት ጉልበት መስጫ ለማድረግ መማር አንዱ መንገድ ቢሆንም ቅርፅ ለመስጠት፣ ውበት ለማምጣት ደግሞ ንባብ ሻካራችንን እያለሰለሰ፣ ለማህበረሰቡ ምቹ እንደሚያደርገን ይታመናል፡፡  
ከሀገር ውጭም ሆነ በሀገራችን ውስጥ አያሌዎች እሳት የላሱ ጠቢባን ይሆኑ ዘንድ አእምሮዋቸውን ገርቶ፣ ላባቸውን አቅንቶ፣ዘመን የማያቆመው ድምቀት የሰጣቸው ንባብ እንደሆነ ደጋግመን ያወሳነው ጉዳይ ነው፡፡
በእኛም ሀገር የንባብ ባህል እንዲያድግና እንዲጎለብት የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ታላቅ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ ለዚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሀዋሳና የዲላ ዩኒቨርሲቲ በየራሳቸው ያደረጉትን ጥረት ልንዘነጋው የምንችል አይመስለኝም፡፡ ይበልጥ የሚመለከተው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርም ከነዚሁ ጎራ የሚመደብ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ደራሲ ዳንኤል ወርቁ “አዲስ አበባ ታንብብ”ን በመሳሰሉ ፕሮግራሞቹ የተቻለውን ያህል ተግቷል፡፡  በጥቅሉ ሲታይ በሀገራችን የንባብ ባህልን ለማበረታታት የሚደረገው ጥረት በእጅጉ እየበረታና እየደመቀ የመጣ ይመስላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ብቻ የተካሄዱትን የመጻህፍት አውደ ርዕዮች ስናይ ጉዳዩ ምን ያህል የልብ ትርታ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡
በተለይ ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ፣በማስተር ፊልምና ኮሙኒኬሽን አዘጋጅነት ከትላንት በስቲያ የተጀመረውና እስከ ነገ (»ሐምሌ 23-26 2007 ዓ.ም) የሚቆየው “ንባብ ለህይወት” የመፃህፍት አውደ-ርዕይ፤በዓይነቱና በይዘቱ ግዙፍና ታላቅ ነው፡፡ ምናልባትም ከዚህ ቀደም ከለመድናቸው የሚለዩ በርካታ አላባዎችን አጭቆ የያዘ ዝግጅት ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱና ዋነኛ ጠባዩ፣  አውደ ርዕዩ በየዓመቱ በቀጣይነት የሚካሄድ መሆኑ ነው። ከዚህም ሌላ በየክልሉ እንዲላመድ በማድረግ ሀዲዱን ቆንጥጦ ይቀጥላል፡፡
ብዙ ጊዜ ስለ ንባብ ስናወራ፣ ስለ ንባብ ስንሰብክ፣ በእዝነ ህሊናችን የሚመጡት ፊታቸው በጢም የተሞላ፣ ምናልባት ሽበት ጣል ጣል ያደረገባቸው አዛውንትና ጎልማሶች ናቸው፡፡ ንባብ ለህይወት ዓይኖቹን ወደ ችግኞቹም ላይ ጥሏል። ሕፃናት ከሥር ጀምረው እንዲኮተኮቱ፣ እኩይ መልኮችን እንዲዘልሉ ከአሁኑኑ ክትባት ያገኙ ዘንድ ለእነርሱም በቂ ዝግጅት አድርጓል፡፡ የሚመጥኗቸው መፃህፍት፣ የሚያጫውቷቸው አሻንጉሊቶችም ተዘጋጅተዋል፡፡
በዚህ አውደ ርዕይ፣120 ያህል የመፃህፍት አሳታሚዎችና የትምህርት ተቋማት በአንድ ዓላማና ድንኳን ስር ይተሳሰራሉ፡፡ እውነት ለመናገር የትምህርት ተቋማት ተሰባስበው በአንድ ሰፈር መች ተገኝተው ያውቃሉ! … ይኸው አሁን በንባብ ለህይወት ችቦዋቸውን እየለኮሱ ደመራውን ሊያደምቁት ታድመዋል፡፡
በንባብ ለህይወት፣ መጻሕፍት ቢያንስ በ10 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ለገበያ የሚቀርቡ ሲሆን ቅናሹ  እስከ 50 በመቶ ሊዘልቅ እንደሚችል አዘጋጆቹ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ መጻሕፍት ለመሸመትም ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በፈጠረው ዕድል ጎብኚዎች ከ100,000 ሺህ በላይ በመረጡት ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተፃፉ መፃህፍትን ሶፍት ኮፒ በነፃ ያገኛሉ ተብሏል፡፡  
በዚህ ዐውደ-ርዕይ ባልተለመደ መልኩ አዳዲስ መጻህፍት ቬሎዋቸውን ለብሰው ብቅ እንደሚሉም ታውቋል፡፡ ከአዘጋጆቹ በተገኘው መረጃ መሰረት፤12 አዳዲስ መፃህፍት እዚያው ተመርቀው፣የደራስያኑ ፊርማ አርፎባቸው፣በትኩሱ ወደ ተደራሲያን እጅ ይገባሉ፡፡
ሌሎቹ ሁለት ታላላቅ የበዓሉ ድምቀቶችም እንደዚሁ ያልተለመዱ ናቸው፡፡ ከነዚህ አንዱ በየሙያ ዘርፉ “አንቱ” የተባሉና በአንባቢነታቸው የተመሰከረላቸው ሰዎች  የንባብ አምባሳደር ተብለው ዕውቅና የሚያገኙበት ሲሆን በቀጣዩ ጊዜ በየትምህርት ቤቱና በሌሎች ክበባት በመገኘት አንብበው የሚያስነብቡበት የኃላፊነት ሹመት ነው። ይህ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ለሚካሄደው የንባብ ልምድ ማበልፀጊያ ጉዞ ትልቁን ድርሻ ሊጫወት እንደሚችል እሙን ነው፡፡  ታዲያ ይህ ሁሉ ዘመቻ፣ ዕውቀትን ጓዳችን ለማስገባት፣ እንደ ሰው አውቀን፣ እንደ ሰው አስበንና የተሻለውን መርጠን እንድንኖር ነው። ማወቅን ካለማወቅ የሚለየው አንዱ፣ ህይወትን የምናጣጥምበትን ምላስ መንጠቁ ሲሆን ሌላኛው ህይወትን የምናጣጥምበትን አቅም መስጠቱ ነወ፡፡ ይህንንም እንድናውቅ የሚያደርገን በልብ አይኖቻችን ላይ የተጋረደው መጋረጃ መነሳቱ ነው፡፡ ይህ አውደርይ የማንበብ ጥቅምንና ወደዚህ የጥቅም እልፍኝ የምንገባበትን መንገድ ለመጥረግ ያዘጋጀው ሌላም ነገር አለ፡፡ በአንድ ወገን የተወዳጅ ደራስያንን ወግ እያነበቡ በማዝናናት፣ በሌላ ወገን ደግሞ የንባብን ጥቅምና ፋይዳ ወደ ኋላ እየፈተሹ፣ ታሪክ በማጣቀስ መወያየትም አለ፡፡
 ሙዚቃ የነፍስ ጥበብ ናት! … በጥበብ እልፍኝ ውስጥ ሽር ብትን እያለች የዓውደ ርዕዩን እልፍኝ ታድምቀው በሚል ጥንታዊውን የሙዚቃ ዓለም በቀደመው ዘመን ከያንያን ዜማ - ታንቆረቁረዋለች ይላሉ - የንባብ ለህይወት አዘጋጆች፡፡ ታዲያ ይህ ቀን አይናፍቅም? … ንባቡስ አይርብም? … የነፍሳችን ከንፈር እስኪላጥ እያፏጨን ብንጠራውስ? … እልልል!  

Read 1891 times