ከተፈሪ ዓለሙ ልብ፥ አልከስም ያለ ንዝረት
“ግጥም እወዳለሁ። ገጣሚና ባለቅኔ አደንቃለሁ።
መልካም ግጥም ሳነብ ወይ ሳደምጥ ነፍሴ ሐሴት ታደርጋለች። ”
-ተፈሪ ዓለሙ
*የካፊያ ምች**
ሳልላክ ተልካ እንሂድ አለቺኝ
ካላጣችዉ ሰዓት ከቤት አስወጣቺኝ
ጥርቅም ዕቅፍ አርጋ በካፊያ ሳመቺኝ
የዕድሜ ልክ ልክፍቴን ያኔ አስለከፈቺኝ።
መብረቅ እየጮኸ ዝናብ እያካፋ
የኔ ልብ በሷ የሷ በኔ ጠፋ
የሰማዩ ባህር ቁልቁል ተንዶብን
ዉሃ ጠማኝ ዉሃ እየዘነበብን።
ጠፍቼ ስመለስ ከእቅፏ ስወጣ
በርዶኝ አተኮሰኝ እቤቴ ስመጣ
እያደር አደረ ከርሞ ከረመብኝ
የዘመን ሕመሜን ያን ዕለት ታመምኩኝ።
አሁን አሁን ታዲያ!
ደመናዉ ሲጠቁር ነጐድጓድ ሲያጓራ
ነፋስ ሲያስገመግም ክረምቱን ሊጣራ
ግንቦት ማለቂያ ላይ ይነሳል ህመሜ
ሲያቀብጠኝ በዝናብ በካፊያ ተስሜ፥
ምች ተሳልሜ።
ተዋናይ፥ ጋዜጠኛ፥ ገጣሚ ... ተፈሪ ዓለሙ በድምፁ በንባቡ የደራሲያንን ልቦለድ፥ ግጥምና ወግ ነፍስ ዘርቶባቸዋል። አዳም ረታ አንድ አጭር ልቦለዱን ዳግም ለመነካካት የተቀሰቀሰዉ ተፈሪ ካነበበዉ በኋላ፥ በድምፁ የሆነ ስውርነት በመዳሰሱ እንደሆነ ገልጧል። የግሉን መጽሐፍ እስከ ዛሬ ሳያሳትም መዘግየቱ ለጥበብ በደል ነዉ። “እንዲህ ካለፍ አገደም እፎይ ያልኩባቸዉንና በየጥጋጥጉ የሸጓጐጥኳቸዉን የሕይወት ጥያቄ ትንፋሾቼን ለቃቅመዉ ‘በል በል’ ብለዉ ገፍትረዉ ኅትመት አደባባይ ያሰጡኝ ውድ ወዳጆቼ ናቸዉ።” አብጅተዋል፤ በስድሳ ግጥሞች ለመደመም አብቅተውናል። ለመጽሐፉና ለሲዲ ርዕስ የተመረጠዉ ግጥም “የካፊያ ምች” ነዉ። ዝናብ እየተንጠባጠበ አካል ለብርድ ሳይሆን ትኩሳት ለመሰለ የህመም ግርፋት መነጠቅ ግልባጩ ያዉካል። ‘ጥርቅም እቅፍ አርጋ በካፊያ ሳመቺኝ / የዕድሜ ልክ ልክፍቴን ያኔ አስለከፈቺኝ።” በአፍላ እድሜ የሆነች ዉብ ሴት፥ አምረሽኛል ልላት የማልደፍር፣ በእሷ ብሶ አፈፍ ሳብ አድርጋ ጨማምቃኝ ከንፈሬን ስትመጠምጠዉ በፍትወት ፍላጐት ማባበጤ ብቻ ሳይሆን የመሳም ጣዕምና ጣፋጭነት የቀመመዉ ተጨማሪ ኅላዌ ይናደፋል። ያ ቅፅበት ከዘመን እየተሻማ የትዝታ ስንቅ ይሆናል። ልክ ደበበ ሰይፉ እንዳለው፤ “ዉጥኑ ግብ ይሁን፥ ጅማሬዉ ፍፃሜ / ቅፅበቷ ሙሉ እድሜሽ፥ ወቅቷ ዘላለሜ” በባህላችን እንስቷ ትሽኮረመማለች፤ ወይም አባብለው ጋብዘው ደጅ ጠንተው ነዉ ከከንፈሯ ማር የምንጐረጉረዉ። ሴቷም እኮ ትታዘበናለች፤ ልክ ዝነኛዋ ተዋናይ Marlyn Monroe እንዳለችዉ። “Hollywod is a place where they pay you a thousand dollars for a kiss and fifty cents for your soul” ለእሴትህ፥ ለነፍስህ ሀምሳ ሳንቲም እየወረወሩ፥ ለመሳሳም ግን ሺህ ብሮች ይከፍሉሃል የመሰለ ትዝብት። የተፈሪ ግጥም የሴቷን ብርቅ ድርጊት ተቀኘበት እንጂ ድምጿን አንሰማም። ግለሰብ ወናዉ ልቡ እየፈነደቀ ሲያቅማማ ያመለጡት መሳሳም - the kiss I miss - ዛሬም ይቆጫል። የተፈሪ ተራኪ ባንድ ወቅት ሴት ተጣብቃበት ከንፈሮቹን ስትጐርስ የመሳሳም ምትሀት እድሜ ልክ ነዘረዉ። “የዘመን ሕመሜን ያን እለት ታመምኩኝ” እያለ ያኔ፥ ትናንቶች ዉስጥ ፈሶ አልነጠፈም፤ ዛሬም ይፋጃል። “ግንቦት ማለቂያ ላይ ይነሳል ህመሜ / ሲያቀብጠኝ በዝናብ በካፍያ ተስሜ / ምች ተሳልሜ።” ሴት ደባብሳ አሻሽታ ስትስመዉ የተዘነጋ ክስተት ሳይሆን፥ የምንሳለመዉ ትኩሳት ሆነ እንጂ። መስቀልን፥ የቄስ እጅን፥ ቅዱስ መጽሐፍን በመሳም ለእግዜር ክብርና ምስጋና የምንገልጠበት ቃል መሳሳም ለለገስን ግለት እናዘወትረዋለን። የወንድና የሴት ግንኙነት አይነቱ ሳይለይ እንደ ደበዘዘ ሊቀር ሲችል፣መሳሳም እምርታዊ ለዉጥ ነዉ፤ ከተራነት መገላገል።
የተፈሪ ዓለሙ “የካፊያ ምች” የበኩር ፍቅርና የመጀመሪያ መሳሳም እሸቱ፣ ትዝታዉ እስከሚያዉከን ይነበባል። የመጀመሪያ መሳሳም እንደ አስማት፥ ሁለተኛዉ የመቀራረብ፥ ሶስተኛዉ የተቸከ -routine- እንዳይሆን ልብስ ማወላለቅ ሊያስፈልግ ነዉ። ልክ የአዳም ረታ “ሎሚ ሽታ” መንገድ ላይ መሳም ያምረኛል የምትለዉ ከአስናቀ ተዋውቃ ለካፊያዉ ምች ፈዉስ ፈለገች እንጂ በመሳሳም አልተገታችም። ”አስናቀ አንገቴን ይልሳል። በጆሮዬ የወንድ ቀረርቶዉን ይሰዳል። ዉስጤ የሚፋጅ ሐምሌ ነዉ። ምላሱ ቅባት የነካ መቀነት ነዉ ታጥቄዉ የማድር። ... የመንሸኳሸኩ ግለት ሊገለኝ ነዉ።” የተፈሪ ተራኪ፥ ሎሚ ሽታም ሁለቱም ግለዋል። “የሰማይ ባህር ቁልቁል ተንዶብን/ ዉሃ ጠማኝ ዉሃ ዘንቦብን።/ ጠፍቼ ስመለስ ከእቅፏ ስወጣ / በርዶኝ አተኮሰኝ እቤቴ ስመጣ” ተፈሪ በግጥሙ ከነገረን ይልቅ በምናባችን የምናስሰዉ ያደናግዛል። ከመሳሳም ማግስት ተለያይተዉ ቀሩ? የመጀመሪያዋ ከንፈር እንደ ኑሮ በሌላ ሁለት ሶስት ሴቶች ከንፈር እንዴት ሳትሻር ቀረች? የመጀመሪያ መሳሳም ከየልጅነት ፍቅር በልጦ ብኩርናዉን እንዴት አልተገሰሰም? ... ጥያቄዎች ተትጐልጉለዋል።
የአንድ ግጥም ጥበባዊ ብስለት ከመዘክዘክ ይልቅ በጡቀማ የሚያስተላልፈዉ መላቁ ነዉ። በያመቱ እንደ ዕንቁጣጣሽ ነፍስን የሚጐዘጉዙለት መሳሳም “የዘመን ሕመሜን ያን ዕለት ታመምኩኝ” ነዉና ግጥሙ አይለቀንም። የተፈሪ ዓለሙ ስድሳ ግጥሞች ከፍቅር ባሻገር የእለት በእለት ሩጫ ፥ የሀገር ጉዳይ፥ የሰዉ ዥንጉርጉሩነት፥ ለኅላዌ መገጣጠብ ... እሱ እንዳለዉ ”... በየጥጋጥጉ የሸጓጐጥኳቸዉን የሕይወት ... ትንፋሾቼ...” የተማሰለበት ነዉ። ለረባ ሂሳዊ ንባብ ወቅት ይጠብቃሉ። ከነገ ወድያ ሰኞ ግጥሞቹ - እንደ ፅላት ተደባብሰዉ- እስኪመረቁ የዚህ ነጠላ ግጥም ንባብ ለትዉዉቅ መቆያ ነዉ። ሰዉ እድሜው እየገፋ ሲመጣ ብርቅ የመሳሳም ክስተት ቢመነምንም፥ ተፈሪ ዓለሙ ዘመን አሻግሮታል።
Saturday, 08 August 2015 09:22
“የካፊያ ምች”
Written by አብደላ ዕዝራ
Published in
ጥበብ