Monday, 31 August 2015 09:40

ፍቅር - ከብዕር እስከ አረር!

Written by  አለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(0 votes)

 የጦርነት መልክ ይሄ ነው፤ ተብላልቶ ሲሆመጥጥ የእብሪት ቡሆ ይሆናል፡፡ የጦርነት ፊት እንደ ጭርት መገኛው የሰው ፊት ነው፡፡ የሚያፈራርሰው ድልድይ፣ ህንጻ፣ ቤት …. አይደለም፤ የሰው ህይወት ነው፡፡ የሚያዳፍነው የአገር ጥሪት አይደለም፤ የግለሰብን ተስፋ ነው፡፡ በጦርነት ነገረ-ሥራው የተመሳቀለበት ሌላው ሩሲያዊ ባለቅኔ አሌክሳንደር ሚዝሒሮቭ ማለዘቢያ ቀለም አፍስሶበት ጦርነትን “ግሩም ሕብረዜማ” ያደርገዋል፡፡
                           
    የሁለተኛ ዓለም ጦርነትን ሰባኛ ዓመት ምክንያት አድርገን እንዲህ እናውጋ፡፡ ጦርነት መልኩ እንዴት ያለ ነው? የብረትና አረር ጋጋታ? ታላላቅ ፍንዳታ? የሰዎች ኡኡታ? ወይስ …?
… እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ሳነሳ ሩሲያዊው ደራሲ ሚኻኤል ሾሎክሆቭ ይታወሰኛል፡፡ በሩሲያ እርስ በርስ ጦርነትና ጀርመን ሩሲያን በወረረችበት ውጊያ በፊትና በኋላ የነበረው መልክ ፍፁም የተለያየ ነበር፡፡ ጦርነት የተካሄደበት መስክ ላይ ከጦርነቱ አስቀድሞ የነበረው ገፅታ ይገኛል? ልክ እንደዚያ የሾሎክሆቭ ፊት በፍርስራሽ የተሞላ የጦርነት ቅሪት መስሎ ነበር፡፡ ቀደም ሲል ፊቱ ላይ የሚነበቡ የዋህነትና ንፁህነትና እርህራሄ ፈፅሞ ወድመው በምትካቸው ጥላቻ፣ ተጠራጣሪነትና ተናቸፊነት ከትመው ነበር፡፡ ይሄን የሚነግረን “ኮምሶሞሊያ” የተሰኘ የወጣቶች መፅሄት ኤዲቶሪያል ፀሐፊ የነበረው ኢቫን ሞልቻየቭ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“ከእርስ በእርሱ ጦርነት አስቀድሞ አንድ ወጣት ወደ ቢሮዬ መጣ፣ ገና የ19 ዓመት አፍላ ነበር፡፡ ኪሱ ውስጥ አጣጥፎ የያዘውን ወረቀት በማውጣት ጠረጴዛዬ ላይ አስቀመጠው፡፡ የአጭር ልቦለድ ረቂቅ ነበር፡፡ የወረቀቱ ግርጌ ላይ አንድ በወቅቱ የማይታወቅ ደራሲ ሥም ሰፍሮ ነበር፡፡ ሚካኤል ሾሎኾቭ ይላል፡፡ ረቂቁን እኔና አሌክሳንደር ዚሐሮቭ አነበብነው፡፡ እጅግ አድርገን በመውደዳችን ወዲያው ወደ ህትመት ክፍል ላክነው፡፡ ለሾሎኾቭም የሚገባውን ክፍያ በቼክ አዘጋጀሁለት፡፡
“ሾሎኾቭን ለረጅም አመታት ዳግመኛ አላየሁትም፡፡ የመጀመሪያ ፅሁፉ ውስጤ ቀርቶ ስለነበር ፈፅሞ አልዘነጋሁትም፡፡ በኋላ እንደሰማሁት በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ነበር፡፡ በጀርመን ወረራ ወቅት (ሁለተኛ የዓለም ጦርነት) የፕራቭዳ ጋዜጣ ወኪል ሆኖ ውጊያው ላይ ተሳትፏል፡፡ ጦርነቶቹ ውስጥ የነበሩትን እንግዳ ነገሮች ሁሉ በአንክሮ እንዳጤናቸው የምንረዳው በልቦለድ ሥራዎቹ ነው፡፡ እናም ከብዙ ዓመታት በኋላ ስመለከተው፣ ወጣቱ ሾሎኾቭ ፊት ላይ የነበረው ደግነት ሁሉ ታጭዶ በምትኩ ሌላ ነገር አየሁ፡፡ ምን ልበላችሁ? ፊቱ ላይ ከሞላ ጐደል የደደረ እብሪት ተለጥፎ ይታይ ነበር (a look of almost stern arrogance on his face)
የጦርነት መልክ ይሄ ነው፤ ተብላልቶ ሲሆመጥጥ የእብሪት ቡሆ ይሆናል፡፡ የጦርነት ፊት እንደ ጭርት መገኛው የሰው ፊት ነው፡፡ የሚያፈራርሰው ድልድይ፣ ህንጻ፣ ቤት …. አይደለም፤ የሰው ህይወት ነው፡፡ የሚያዳፍነው የአገር ጥሪት አይደለም፤ የግለሰብን ተስፋ ነው፡፡ በጦርነት ነገረ-ሥራው የተመሳቀለበት ሌላው ሩሲያዊ ባለቅኔ አሌክሳንደር ሚዝሒሮቭ ማለዘቢያ ቀለም አፍስሶበት ጦርነትን “ግሩም ሕብረዜማ” ያደርገዋል፡፡
Such wonderful music it was!
Such wonderful music was playing
When our souls and bodies
Were trampled by the damened war.
Such music was
         in everything
for each and all
       indiscriminately
We shall overcome …. held out … and save …
ባለቅኔነትን የሚጠይቀው የግጥም ትርጉም ከሩሲያኛ ወደ እንግሊዝኛ እንዴት እንደተመለሰ ማመሳከሪያው የለንም፡፡ “በጥፋት ላይ ጥፋት” ካልተባለ እኛም የሙሉ ግጥሙን መንፈስ በቋንቋችን እንጥለፈው፡፡
እንዴት ያል ሙዚቃ
እንዴት ያል መሰንቆ
የሚቀነቀነው
ሥጋ በጦር ታንቆ
ነፍስ ተፈጥርቆ
ውጊያ ሁለመና
ጦሩ ሁለንተና
ህብረቃልነቱ ላለመቅረት መና
ላለመሆን ወና፡፡
ሚዝሒሮቭ ቅዠት ከሆነው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተርፎ ለሩሲያ የማሟጠጫ ባለ ቅኔ ሆኖ ነበር፡፡ አንዲት ቀዥቃዣ ሌጣ ጥይት በብሽሽቱ ተሽጣበት ቢሆን ኖሮስ? እንኳን ሩሲያ እኛም ኪሳራችን ምን ያህል ነበር? ማነው ይህ ከእንዲህ ብሎ የሚያወራርደው? በጦርነቱ የወደመው አልተገነባም? የጠፋው አልተገኘም? ባለቅኔውን የሚያካክሰው የትኛው የማወራረጃ ሥራ ነው?….
…“Soviet literature” የተሰኘ የቆየ መፅሄት ሳነብ፣ ጦርነቱ የጣለውን የገጣሚያን ኪሳራ ያትታል፡፡ በዓለም ዙሪያ ሃያ ሚሊዮን ህዝብ ያጣጣመው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት፣ በሩሲያ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣት ገጣሚያንን አሳጥቶናል ይላል፡፡ ተቅበዝባዥ ጥይት ተንሰራፍቶ አየር ላይ መረብ በሰራበት የጦር አውድማ ላይ ብዙ ቅኔ ያረገዙ ልቦች ያለወቅታቸው ተፈጥርቀዋል፡፡ የት መሸሸግ፣ የት መደበቅ ይቻል ነበር? ግጥም እንደ ጦር ነጋሪት በሚጎሰምበት ዓለም፣ ባለቅኔን “ለእራት” ማስተረፍ እንዴት ይቻለናል? ዤን ጊራውዶክስ እንዲህ ይላል፡-
“As soon as war is declared it will be impossible to hold the poets back. Rhyme is still the most effective drum” (ጦርነት እስከታወጀ ድረስ ባለቅኔውን ወደ ኋላ ማስቀረት አይቻልም፡፡ እስካሁንም የግጥም ምት ውጤታማ የጦርነት ነጋሪት ነውና፡፡)
እናም ከሥጦታ በላይ የሆነውን ስጦታ፣ ከሀብታት ሁሉ የሚልቀውን ሀብት ከአፈር ጋር ደባለቅን፡፡ ፍሬ ሳይሰጥ በአበባው ቀጠፍን፤ ጌጥ አልሆነን፣ ረሀብ አልከላልን፣ ጥበብ ማጣትን እስከ ቅዝቃዜው ታቀፍን፡፡
“Soviet Literature” በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጭዳ የሆኑት ገጣሚያን ዕድሜያቸው ከሃያ ሦስት እስከ ሃያ አምስት ዓመት የሚሆናቸው ተማሪዎች ነበሩ ይለናል፡፡ የጦርነቱን ጥሪ ተቀብለው መማሪያ ክፍላቸውን ለቀው የውጊያውን ፊተኛ ረድፍ ተቀላቀሉ፡፡ እነዚህ ባለቅኔዎች ሃያዎቹን ዕድሜ ሳያቆለቁሉ አፋፍ ላይ እንዳሸለቡ፣ ኪሳቸው ሲፈተሽ ነፍስ የሚመነጥቁ ግጥሞች ተገኙ፡፡ መፅሔቱ ስለነዚህ ገጣሚያን የምናውቀው ጥቂት ነው ይላል፡፡ ከጦርነቱ በፊት የት ነበሩ? ማንን አፈቀሩ? ስለ ምን ያልሙ ነበር? የት ለመድረስ አቅደው ነበር? … አይታወቅም፡፡ ግጥም ብቻ፣ ቅኔ ብቻ ….
ሌኒን ግራድን ሲከላከል የተሰዋው ጆርጂ ሱቮሮቭ፤ ካርታ ማስቀመጫ ኮሮጆው ውስጥ በግጥም የተሞላ ማስታወሻው ተገኘ፡፡ ከግጥሞቹ መካከል አንዱን አፀቅ መፅሔቱ ወደ እንግሊዝኛ መልሶ እንዲህ ያስነብበናል፡፡
The war still rages. But we
stubbornly believe
The day will come - and we’ll
drink the last
                       Pain to the last drop.
Again the wide world throw open
its door to us,
The quiet will rise from the new dawn
My dear friend oh how quickly,
How quickly our time flowed by!
In our recollections, we shall
not grieve
Why darken the brightness of
 the days with  
                                 sadness?
We lived through our good age
like people,
                            for the people.  
ወደ አማርኛ እንዲህ መለስነው፡-
የጦርነቱ ቁጣ ጉልበቱ ባይበርድም
በፅናት ማመኑ እኛን አይገደንም፡፡
ያ ቀን ይመጣል
የመጨረሻ መከራ የምንጨልጥበት
ያ ጠብታ ህመም ጠፈፍ የሚልበት
ፅንፍ አልባው ዓለም በሩ ይከፈታል
ፀጥተኛው ምድር ካዲሱ ጀንበር ጋር አብሮ ይወለዳል፡፡
ውዱ ጓደኛዬ፣ እንዴት ያል ፈጣን፣
እንዴት ያል ፈጣን ነበር ጊዜያችን?
ተክለፈለፈብኝ አጎራረፋችን፡፡
ቢሆንም
መዘከራችን ለመቃብር ላይተወን
ብራውን ቀናችንን በሀዘን ማጠየም
ለምኑ ሊበጀን?
መልካሚቷ ዕድሜያችን ውስጥ ተስለክልከን እንዳልኖርን
እንደ ህዝብ
ለህዝብ፡፡
ጦርነት እንዲህ ነው፡፡ የሚቀበቀብበትን ልብ አይለይም፡፡ ሰው ከሰው አያማርጥም፡፡ እንደ ጥንብ አንሳ የማይረባውን ብቻ አያጋብስም፡፡ ያገኘውን ይልሳል፣ ተስፋ ያቋርጣል፣ ጥሪት ያባክናል፡፡ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ያላገገምነው በፈራረሰው ገፅታ፣ በተድፋፋው ፀጥታ አይደለም፡፡ የማይጠግ ቁስል የሆነው ጥበብን ከግምት ከከተትን ነው፡፡ ኤድዋርድ ፖዳሬቭስኪ ሌላኛው በወጣትነቱ የተሰዋ ባለቅኔ ነው፡፡ እንደ እናት ጡት ሳይጠግባት ለተመነጨቃት ሞስኮ የገጠመውን ከውድ ህይወቱ ጋር አበርክቷል፡፡ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የተመለሰው እንዲህ ይነበባል፡-
ኦ - ሞስኮ -  ኦ ሞስኮ!
ማባሪያ የሌለው ውድ
ለእሷ የሚዥጎደጎድ
የብረት መንጠርጠር
ለሞስኮ ‘ሚዘከር
ፍቅራችን ሲያከንፈን ወፍ እንሆናለን
ናፍቆት ካሰገረን ዓሣነት አይገደን
ደም እናነባለን
እንባ እንራጫለን
ጥይት እንቀልባለን
ሩህ እንለቃለን
ትንፋሽ ምናባቱ
ለፍቅርሽ አፀፋ
በድን መሆን ከንቱ!!
የዚሁ ወጣት ባለቅኔ ሌላኛው ግጥም በሌላ ትርጉም እንዲህ ይነበባል፡-
የተጠለልንበት
ቤቱ ተደነባ
ሰማዩ አነባ
መሬቱ ተከፋ
ቅንጥብጣቢ ተስፋ?
የትም - ምንም ጠፋ፡፡
የቀረው ቅኔ ነው
እሳትና ብረት
    አጉራህ ጠናኝ ያለው፤
የአውሮፓን ትውስታ ፈጥርቆ የያዘው ሁለት የጦርነት ስርቅታ ነው፡፡ አየር አጥሯት በነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ጓጉራ ተረፈች፡፡ እኛስ? ስንት ጦርነት? ስንት ውጊያ? ስንት ከውስጥ? ስንት ከውጭ? ተቆጥሮ ይዘለቃል? አለቃ አጥሜ (አፅመጊዮርጊስ) ስለ አንድ የብዕር ሰው አሟሟት እንዲህ ይላሉ፡-
“ወዲያው በጥቅምት ወር (ንጉስ ምኒልክ) ብዙ ጦርነት አስከትተው፣ ብዙ ፋኖ አስከትለው ወደ ጉራጌ ዘመቱ፣ በጥቅምት 21 ቀን የንጉሡ ሰራዊት አለቀ፡፡ አለቃ ዘነብ የሚባል አዋቂ፣ መፅሐፈ ጨዋታ ብሎ የደረሰ የዚያኑ ዕለት ሞተ፤”
አለቃ ዘነብን በጦርነት ማጣት ከየትኛው ኪሳራ ጋር ይነፃፀራል? ቁስሉስ ይጠግጋል? ቁጭቱ ይበርዳል? ክፍተቱ ይደፈናል? ለመሆኑ በእነዚያ እልፍ አእላፋት ጦርነቶቻችን ውስጥ ስንት ባለቅኔዎች አጥተን ይሆን? እንደ ፀጋዬ ገብረመድህን ያለ፣ እንደ ደበበ ሰይፉ ያለ፣ እንደ በዕውቀቱ  ስዩም ያለ፣ እንደ ገብረክርስቶስ ደስታ ያለ፣ እንደ ኑረዲን ኢሣ ያለ ፣… እንደ፣ እንደ፣ እንደ …..፡፡

Read 2035 times