Saturday, 03 October 2015 10:39

“ከመኖር ብዙ አለ፤ ካለመኖር ምንም”

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(1 Vote)

 ቀኑ መስከረም 10 ነው፡፡ ለሰው ያዋስኩትን መፅሐፍ ተቀብዬ ፒያሳ አንድ ካፌ ውስጥ አረፍ ብያለሁ፡፡ “Bloom’s Biocritiques” የተሰኘ ተለጣጣቂ ሕትመት ያለው ድንቅ ሥራ ነው፡፡ በዚህኛው መጽሐፍ ላይ የሩሲያው ደራሲ ፊዮዶር ዶስተየቭስኪ ሥራውና ሕይወቱ ተዳስሷል፡፡ ደጋግሜ ያነበብኩት ቢሆንም ማገላበጤን ቀጠልኩ፡፡ የደራሲውን የውልደት፣ የልጅነት፣ የጉርምስናና የእርጅና ዘመን የሚያጐሉ መረጃዎች (እንደ አገላለጤ) ቅደም ተከተላቸው ተፋልሶ እየደረሰኝ ነው፡፡ አገላለጤን ፈጣን፣ ረገብ እያደረኩ ስዳስስ አንድ ጉዳይ ትኩረቴን ሳበው፡፡ ደስተየቭስኪ በመንግሥት ላይ በመዶለት ከተወነጀለው Palm - Durov የተሰኘ ቡድን ጋር ታፍሶ ከታሰረ በኋላ ነው፡፡
በዚች ዕለት (አሁን እኔ ካፌ በተቀመጥኩባት ቀን) 1849 ዓ.ም ጉዳዩን እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚሽን (Commission of Inquiry investigative the accused Conspirators) ለዛር ኒኮላ የመጨረሻውን ሪፖርት ያቀረበበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ሪፖርት ላይ የተመሰረተው ዛር (Tsar) በቡድኑ አባላት ላይ ሞት ፈረደ፡፡
ያ - ዘመን እንደዚያ ነበር፡፡ በተለይ የወቅቱ ምሁራን መተንፈስ እስኪያቅታቸው የታፈኑበት፡፡ ከአንድ ሰው በላይ ሆኖ በፖለቲካ፣ በሃይማኖትና በኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ መወያየት ፈጽሞ የተከለከለ አደገኛ ጉዳይ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ሥነ - ፅሁፍን ርዕስ አድርጐ መወያየትም አይፈቀድም፡፡ ይሁንና አንዳንድ የምስጢር ቡድኖች በመሹለክለክ በመጠነኛ አባላት በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከመወያየት አልተገቱም ነበር፡፡ ደስተየቭስኪ መጀመሪያ ፔትራሼቭትሲ (Petrashevtsy) ከተሰኘ የምስጢር ቡድን ጋር ተቀላቀለ፡፡ ቡድኑ የውይይት ክበብነቱ የሥነ - ፅሁፍ ብቻ በመሆኑ ከመካከል የፖለቲካ ዝንባሌ ያላቸው ብቻ ተገንጥለው “ፓልም ዱሮቭ”ን መሰረቱ፡፡ ጥቂት እንደቆዩ በምስጢር ሰራተኞች ተደርሶባቸው ተያዙ፡፡
የሞት ፍርዱ ገና ሲያዙ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በዛሩ በኩል የተለወጠ ነገር አልተፈጠረም፡፡ ሞት ፍርዱ ይፋ ተደረገ፡፡ ቀጣዩ ደግሞ የሞት ፍርዱ የሚፈፀምበት ዕለት መርዘምና ማጠር ላይ ተስፋ ተደረገ፡፡
ደስተየቭስኪ ለወንድሙ በፃፈው ደብዳቤ ላይ፤ “ምንጊዜም ተስፋ ታደርጋለህ” ብሏል፡፡ “በመጨረሻዋ ዕለት እንኳን ገዳዮችህ ረድፍ ይዘውና ጠበንጃቸውን ደረትህ ላይ ደቅነው ቃታ እስኪስቡ ተስፋ ታደርጋለህ፡፡” ሰው መሆን ይሄ ነው፤ ተስፋ በሌለበት ቅጽበት እንኳን ተስፋ ማድረግ፡፡
ከዶስተየቭስኪ ጋር አምስት የሞት ፍርደኞች ነበሩ፡፡ ገዳዮች ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ ተገዳዮች ለሁለት ቡድን ተከፈሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ረድፎች ውስጥ ደራሲው አለመኖሩ እንዴት ተስፋውን ከፍ እንዳደረገው እዚያው ደብዳቤው ላይ ይገልፃል፡፡ “እኔ መካከል ነኝ፤ ፕሌስትቼቭኝ እና ዱሮቭን አቅፌ የመሰናበት ዕድል ስለገጠመኝ ተደሰትኩ” ይላል፡፡ ሆኖም ጭንቀቱ የትየለሌ እንደሆነ ደግሞ አልደበቀም፡፡
“ከፍተኛ ጭንቀት ወረደብኝ፡፡ ገዳዮችህ ፊት ለፊት ተሰይመዋል፡፡ በሆነ ደቂቃ ውስጥ ቃታ ሊስቡ ይችላሉ፡፡ በፍርድ ከመገደል በላይ ምን አስከፊ ሞት አለ? ጨካኝ ሞት ፊት ለፊታችን አለ፡፡ በወንበዴዎች መገደል እንኳን የዚህን ያህል አይከፋም፡፡ ከበስተኋላህ መጥተው፣ ወይም ጨለማ ተላብሰው፣ ወይም ማሳበሪያ ቦታ ተገን አድርገው አንገትህን ቢቆርጡህም የፍርድ ሞትን ያህል አይከፋም፡፡ ሳንጃ ለሳንጃ የምትሞሻለቅበት የተጧጧፈ ጦርነት ውስጥ ሆነህ እንኳን የመትረፍ ተስፋ አለ፤ በወንበዴዎች ጉሮሮህ ተቆርጦ እንኳን ጥለውህ ሄደዋልና የመዳን ዕድል አለህ፡፡ ነገር ግን ሆን ብሎ መሞትህን እስኪያረጋግጥ ድረስ ከማይለቅህ የፍርድ ሞት ፊት ምን ተስፋ አለ? በፍፁም! በፍፁም፣ በእንዲህ ያለ ሞት ፊት ማንም ሰው መቆም የለበትም፤ በፍፁም! በፍፁም!” ደስተየቭስኪ ይሄን እውነታ የገለፀው “The Idiot” የተሰኘ ልቦለዱ ውስጥ ነው፡፡
ዶስተየቭስኪ በሰቀቀን ከሚጠብቀው የአፈሙዝ እሳት በፊት የንጉሰ ነገስቱ ምህረት ደረሰ፡፡ ለሞት ፍርደኞቹ በጽሑፍ ሲነበብላቸው የማይታመን መዳን እንደሆነላቸው አረጋገጡ፡፡ በሞት ፋንታ የአራት አመት የጉልበት ሥራና የአራት አመት የውትድርና አገልግሎት ደራሲው ላይ ተበየነ፡፡ ለጉልበት ሥራው ወደ ሳይቤሪያ ተላከ፡፡ በ1854 ዓ.ም ለወንድሙ የፃፈው ደብዳቤ ላይ እንደገለፀው፤ የሳይቤሪያ ቅጣቱ የውትድርና አገልግሎቱን ያህል የከፋ አልነበረም፡፡
“…Men every where are Just – men. Even among the robber - merders in the prison. I came to know some men in those four years. Believe me there were among them deep, strong, and beautiful natures. And it often gave me great joy to find gold under a rough exterior.”
(“…የትም ይሁን የትም፣ ሰዎች ምንጊዜም ሰዎች ናቸው፤ የቤት ሰባሪ ነብሰገዳዮች ባሉበት ዘብጥያ ውስጥ ቢሆንም ማለቴ ነው፡፡ በእነዚያ አራት አመታት ውስጥ ጥቂት ሰዎችን አውቄአለሁ፡፡ እመነኝ፣ እነርሱ ዘንድ ጥልቅ፣ ጠንካራና ውብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ላይ ላዩን የሚታየውን አስቀያሚ ነገር አልፌ በማገኘው እንደወርቅ የከበረ ነገር ስንት ጊዜ እንደተደሰትኩ አትጠይቀኝ”)
የውትድርና አገልግሎቱ ግን ለዶስተየቭስኪ የሞት ያህል የከበደ እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ የታሊያ ፎንቪዚና ለተባለች አንዲት ሴት በፃፈው ደብዳቤ ላይ፤ “In the overcoat of a soldier, I am just as much of a prisoner as before” (በወታደሮች ካፖርት ውስጥ ያው እንደቀደመው በእስረኝነት እንዳለሁት ያለ እስረኝነት ኑሮ እገፋለሁ) ብሏል፡፡
ከመፅሐፉ ላይ ቀና አልኩ፡፡ የሰዎች፣ የብርጭቆዎች፣ የማሽኖች ቱማታ ከብቦኛል፡፡ የዶስተየቭስኪ የሞት ፍርድ በአንድ ሰው ዕጣ - ፈንታ ላይ ብቻ የሚተገበር ይሆን ነበር? ምህረቱስ? የአንድ ሰው የመኖር ፈቃድ ብቻ ነበር? አይደለም፡፡ ያኔ የዛሩ ልቡና ደንድኖ የሞት ፍርዱ ተፈፃሚ ቢሆን ኖሮስ? እርሱ (ዶስተየቭስኪ) ከሚያጣው የእኛ ጉዳት አይልቅም ነበር? ደስተየቭስኪ የአፈሙዝ ባነጣጠረበት ወቅት የነበረው አንድ ትርጉም (የባልዛክ) እና ሁለት ቤሳ ልቦለዶች (Poor Folk, White Nights) እንዲሁም አንድ ልቦለድ (The Double) እና ጥቂት አጫጭር ልቦለዶች ብቻ ነበሩ፡፡ በሞት ፍርሃት፣ በጉልበት ቅጣትና በውትድርና አገልግሎት ሳምንት… አመታት ከቆየ በኋላ ከ1857 እስከ 1880 ሃያ ሦስት ታላላቅ ልቦለዶችን አበርክቶልናል፡፡ እነዚህን ማጣት ከምን ማጣት ጋር ይነፃፀርልን ይሆን? The Brothers Karamazov, Crime and Punishment, The Idiot, Notes From Underground, The Gambler, The possessed, The Insulted and Injured… ከዛር ኒኮላ በላይ አልኖሩም? በጊዜአዊ ዘላለማዊ ይለወጣል? ለመሆኑ የዛር ኒኮላ መንግሥት ለእኛ ምናችን ነው?...
ከካፌው ወጣሁ፡፡ ውስጤ ተረብሿል፡፡ ዶስተየቭስኪ የሞት ቅጣቱን ተቀብሎ እነዚህን ሁሉ ሥራዎች ያጣናቸው ያህል ተሰምቶኛል፡፡ እናም እኔ በተአምር የቀሩብንን ልቦለዶች ከመፀነሳቸው በፊት እዚያው የመከኑበት ድረስ ሄጄ የምጐበኝ፡፡ እንዲያ ነው የተሰማኝ፡፡ ጉዳዩ “ከመኖር ብዙ አለ፤ ካለመኖር ምንም” እንደተባለው ነው፡፡
እንዲያ…. በሃሳብና በእግሬ እየተወዘወዝኩ የመኖሪያ አቅጣጫዬን ስቼ ተጓዝኩ፡፡ የምሄደው ወደ ሰፈሬ የሚወስደኝ ታክሲ የሚገኝበት ቦታ አይደለም፡፡ በተቃራኒው ወደ አትክልት ተራ ነው፡፡ ወዴት እንደምሄድ እግሬ ሳያውቅ የቀረ አይመስለኝም፡፡ የአራዳ ህንፃ ያጠላበትን ስፍራ እንደጨረስኩ ተሻግሬ ቀጥታ ቁልቁል ወረድኩ፡፡ እዚያ የደስተየቭስኪ አምባ የሩሲያ ባህል ማዕከል አለ፡፡ እርሱን ለማሰብ አንድ የሩሲያ መልክ ወይም ስዕል አይቼ ብመለስ በቂዬ ነው፡፡ ጉዳይ እንዳለው ሰው እየተከታለፍኩ ወደ ምድረ ግቢው ዘለቅሁ፡፡ በድርድር መወጣጫው ላይ አሻቅቤ የህንፃውን አንደኛ ደርስ ተቆናጠጥኩ፡፡ እናም እዚያ ብዙ የሩሲያ መልክ የታተመባቸው ወረቀቶች አሉ፡፡ ጠጋ ብዬ አነበብኩ፡፡ በተለያየ ዘርፍ የኖቬል ሽልማት አሸናፊ ሩሲያውያን ፎቶና ታሪክ ነበር፡፡ ከእነሱ ሁሉ በላይ አንድ ማስታወቂያ አይኔን ሳበው፡፡ በአማርኛ የተፃፈ ነበር፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“ደስተየቭስኪን፣ ቶልስቶይንና፣ ቼኾቭንና ጐርኪን በእናት ቋንቋቸው ለማንበብ ሩሲያኛ ተማሩ፡፡”
ይኸው፤ የምህረት ውጤት፤ ከፍታውን በደስተየቭስኪ ሥራዎች አየን፡፡ የመላው ሩሲያ ቋንቋ ዋስትና እስከመሆን ሽቅብ ሲመነጠቅ፣ እኛ በበአሉ ግርማ፣ በአቤ ጉበኛ፣ በዮፍታሄ ንጉሴ… ምህረት አልባ መገደል ያጣነው ይሄንን ከፍታ ነው፡፡ አዲዮስ!! 

Read 1705 times