Saturday, 03 October 2015 10:41

ሶስቱ ጥያቄዎች (Three Questions)

Written by  ደራሲ፡- ሊዮ ቶልስቶይ ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(0 votes)

  (ሊዮ ቶልስቶይ ከ1828 እስከ 1910 ዓ.ም የኖረ ሩሲያዊ ደራሲ፣ ወግ ፀሐፊ እና ፈላስፋ ነበር፡፡ ከደርዘን በላይ ከሆኑት ረዣዥም ልብ ወለዶቹ መሐል War And Peace እና Anna Karenina የሚባሉ ስራዎቹ በብዙዎች ይታወቃሉ፡፡ እኩያ የሌለው የረዥም ልብወለድ ፀሐፊ ነው ተብሎ ይሞካሻል፡፡ አጫጭር ልብ ወለዶቹም ድንቆች ናቸው፡፡)

     በአንድ ወቅት አንድ ንጉስ እንዲህ ሲል አሰበ፤ ሁሌም እያንዳንዱ ሥራ የሚሰራበትን እቅጩን ጊዜ ባውቅ፤ ቀጥሎ የየትኞቹን ሰዎች ምክር መስማት እንዳለብኝ ባውቅ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በጣም አስፈላጊውን ስራ ለይቼ መስራት ብችል፤ አንድም ቀን በየትኛውም የስራ መስክ አልፎርሽም፤ በየትኛውም፡፡
ሀሳቡ እንደመጣለት በግዛቱ እንዲህ ሲል ማስታወቂያ አስነገረ፡- ለእያንዳንዱ ድርጊት ትክክለኛው ጊዜ መቼ እንደሆነ ለሚነግረኝ፣ ምክራቸውን መስማት ያለብኝ ምርጦች ሰዎች እነማን እንደሆኑ አውቆ እውቀቱን ለሚያጋራኝ፣ እሰራው ይገባኝ ዘንድ ቀዳሚ እና ዋነኛ ሥራ የቱ እንደሆነ ለሚያስታውቀኝ ልዩ ሽልማት አዘጋጅቻለሁ፡፡ ልዩ፡፡
የግዛቱ ጠቢባን ሁሉ ወደ ቤተ - መንግስት ተመሙ፡፡ ንጉሱ ፊትም አለኝ የሚሉትን መልስ ይዘው ተሰበሰቡ፡፡ ለሶስቱም ጥያቄዎች ግን ጠቢባኑ የሰጡት መልስ የተለያየ ነበር፡፡
አንደኛውን ጥያቄ አንዳንዶቹ አዋቂዎች እንዲህ ሲሉ መለሱ፡- የትኛው ሥራ መቼ መሰራት እንዳለበት ለማወቅ የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀት ነው፡፡ እናም ያንን ጊዜ በቀናት፣ በወራት እና በአመታት መሰባበር፤ በዚህም መሰረት እቅድ ማዘጋጀት፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ያለ አንዳች ማዛነፍ ይህን የጊዜ ሰሌዳ መከተል አለብን፡፡ ያኔ ብቻ ነው ማንኛውም ስራ በትክክለኛው ሰዓት ሊሰራ የሚችለው፡፡ ሌሎች ደግሞ እንዲህ አሉ፡- የለም፣ የለም አንድን ሥራ መቼ መስራት እንዳለብን ቀድመን ልናውቅ ፈጽሞ አንችልም፤ ይህ ምን ማለት ነው? እቅድ ማውጣት ረብ የለውም ማለት ነው፡፡
ይህን ማድረግ ግን እንችላለን፡፡ ዝም ብለን አጉል እቅድ ከማቀድ ወይም ለሁሉም በቂ ጊዜ አለኝ ብሎ በስንፍና እና በከንቱ ነገር ሁሉ ጊዜን ከማባከን አካባቢያችንን በንቃት መከታተል፡፡ ያኔ “እኔ ነኝ ተረኛ” የሚለውን ሥራ አፍጥጦ እናየዋለን፤ ያኔ ምን ጥያቄ አለው? እሱን መስራት ነዋ፡፡ የቀሩት ሌሎች ደግሞ ይህንን አሉ፡- ይህንን ለማድረግ ለአንድ ሰው ይከብደዋል፡፡ ምንም ያህል ንጉሳችን አካባቢውን በአንክሮ ቢያጤን፣ አንድ ነውና ለእያንዳንዱ ድርጊት ትክክለኛው ሰዓት የቱ እንደሆነ ሊያውቀው አይችልም፡፡ ስለዚህም ንጉሱ ያወቁ፣ የነቁ እና የበቁ አማካሪዎች በዙሪያው ሊሰበስብ ይገባል፡፡ ከነዚህ ጠቢባን ከአንዳቸው አንዳቸው ለእያንዳንዲቷ ነገር ትክክለኛውን የድርጊት ጊዜ ማወቅ አይሳናቸውም፤ ይህንንም ለንጉሱ ይነግራሉ፡፡ ግን፣ ግን፣ ተባለ፡- ነገርየው የተባሉት አማካሪዎች ጋር እስኪደርስ፣ እነሱ ተሰብስበው እስኪመክሩ፣ መክረው እስኪወስኑ ፋታ የማይሰጡ ጉዳዮች አሉ፡፡ እንዲህ አይነት ጉዳዮች እዚያው፣ እና ወዲያው ውሳኔ ይፈልጋሉ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ መቼ፣ ምን እንደሚከሰት አስቀድሞ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ነገሮች ከመከሰታቸው በፊት፣ ማወቅ የሚችሉት ደግሞ አስማተኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ በትክክለኛው ሰዓት ሥራውን ለመከወን ንጉሳችን አስማተኞችን ማማከር ይኖርበታል፡፡ ለሁለተኛው ጥያቄ ጠቢባኑ ያቀረቡት መልስ ለአንደኛው ጥያቄ እንደሰጡት መልስ የተለያየ ነበር፡፡ ንጉሱ ከሁሉም በላይ የሚያስፈልጉት ሁነኛ ሰዎች አማካሪዎቹ ናቸው ተባለ፡፡ የለም ቀሳውስቱ ናቸው፡፡ የለም፣ የለም ህክምና አዋቂዎችን ነው ከሌሎች አብልጦ ንጉሱ መስማት ያለበት፡፡ ከሁሉም በላይ እጅግ አስፈላጊዎቹ ጦረኞች ናቸው ያሉም ነበሩ፡፡
ሶስተኛው ጥያቄ ለጠቀ፡፡ በምድር ላይ ምርጡ ስራ የቱ እንደሆነ ጠቢባኑም መለሱ፡፡ ሳይንስ፡፡ ጦረኝነት ነውም ተባለ፡፡ ሃይማኖተኛ መሆንን የሚያክል አንዳችም ስራ የለም፡፡ አራት ነጥብ፡፡ ተባለ፡፡
የጠቢባኑ መልሶች የተለያዩ፣ ምን የተለያዩ ብቻ የተበታተኑም ነበሩ፡፡ ንጉሱ ከአንዳቸውም አልተስማማም፡፡ የየትኛቸውም መልስ አላረካውም፡፡ ቃል የተገባው ሽልማት ለየትኛውም ጠቢብ አልተሰጠም፡፡ ንጉሱ ግን ከዚህም ወዲያ ጥያቄዎቹን መጠየቅም ሆነ መልሶች መፈለጉን አልተወም፡፡ አንድ መነኩሴ ታወሱት፡፡ ዘመን በፈተነው እውቀታቸው ይታወቃሉ፡፡
መናኙ ጫካ ውስጥ ነው የሚኖሩት፤ የእንጨት ቤት ሰርተው፡፡ ከእለተ - ምነናቸው ጀምሮ አንድም ቀን ከጫካው ወጥተው አያውቁም፡፡ እንግዶችን ግን ተቀብለው ያነጋግራሉ፡፡ ተቀብለው የሚያናግሩት ተራ ሰዎችን ነው፤ ጥበባቸውንም የሚያካፍሉት ለምስኪን ገበሬዎች ብቻ ነው፤ ሌሎች እንግዶች አይቀበሉም፡፡ ይህንን የሚያውቀው ንጉሱ ዘባተሎ ለበሰ፡፡ ወደ መናኙም ሄደ፡፡ እንጨቷ ቤት ለመድረስ ጥቂት የማይባሉ ደቂቃዎች መንገድ ሲቀረው ከፈረሱ ወረደ፡፡ አጃቢዎቹን ከነፈረሱ ያሉበት ትቶ ቀሪውን መንገድ በእግሩ አዘገመ፡፡ ንጉሱ፣ መነኩሴው ከጐጆዋቸው ፊት ለፊት ያለች የእርሻ መደብ ሲቆፍሩ ደረሰ፡፡ መነኩሴው፣ ንጉሱን ሲያዩ ሰላም ብለውት ቁፋሮዋቸውን ቀጠሉ፡፡ ቀጭን እና ደካማ ናቸው፡፡ ያለ የሌለ አቅማቸውን ይሰበስቡና በዶማው የእርሻውን መደብ ይመታሉ፤ ትንሽዬ ቦታ ትቆረሳለች፡፡ ይህችውም ቁና፣ ቁና ታስተንፍሳቸዋለች፡፡
ንጉሱ ወደ መነኩሴው ቀረበ፡- “ክቡር ሆይ የመጣሁት ምክርዎትን ለመጠየቅ ነው፡፡ ለሶስት ጥያቄዎቼ ከእርሶ ዘንድ መልስ ፍለጋ መጣሁኝ፡፡ እኒውና ጥያቄዎቹ፡- የምሰራቸውን ነገሮች መቼ መስራት እንዳለብኝ እንዴት ማወቅ እችላለሁ? የትኞቹ ጠቢባኖች ናቸው ከሌሎች የላቁት እና “እህ” ብዬ ልሰማቸው የሚገባኝ? የትኛው የሥራ መስክ ነው ምርጡ እና እኔ ልሰራው የሚገባኝ?” መናኙ በፅሞና ጥያቄዎቹን ሰሙ፡፡ አንዳችም ነገር አልተናገሩም፡፡ እጆቻቸው ላይ ተፉ እና እርስ በርሳቸው አሻሿቸው፡፡ ዶማቸውን አንስተው ቁፋሮዋቸውን ቀጠሉ፡፡
“እንደደከሞት በጣም ያስታውቃል፡፡” አለ ንጉሱ፡- “እባክዎትን ዶማውን ያቀብሉኝ እና ቁፋሮውን ትንሽ ላግዞት፡፡” ብሎ አከለበት፡፡
“መልካም፡፡” አሉ መነኩሴው፡፡ ዶማውን ለንጉሱ አቀበሉና መሬቱ ላይ ተቀመጡ፡፡ ንጉሱ፣ ሁለት የእርሻ መደቦችን ከቆፈረ በኋላ ፋታ ወሰደ፡፡ ሶስቱን ጥያቄዎች ለመነኩሴው ደገመላቸው፡፡ መልስ የለም፡፡
“እስኪ አሁን ደግሞ አንተ አረፍ በልና እኔ ልቆፍር፡፡” አሉ መነኩሴው፡፡ ንጉሱ ዶማውን ለመነኩሴው አላቀበላቸውም፤ ቁፋሮውን ቀጠለ፡፡ በዚህ ሁኔታ አንድ ሰዓት አለፈ፡፡ ሌላም አንድ ሰዓት ተከተለ፡፡ ፀሐይዋ ከዛፎቹ ጀርባ እየሰጠመች ነው፡፡ ንጉሱ በሀይል ዶማውን መሬት ውስጥ ቀረቀረው፡፡ ቁፋሮውን አቆመ፡፡ እንዲህም ሲል ተናገረ፡-
“እንዴት ነው ነገሩ? እዚህ የመጣሁት ለጥያቄዎቼ ከእርስዎ መልስ አገኛለሁ ብዬ ነው፡፡ ጥያቄዎቹ መልስ ከሌላቸው እንዲያ ብለው ሀቁን ይንገሩኝና ወደ መጣሁበት ልሂድ፡፡”  
“ተመልከት፡፡ ተመልከት፡፡ የሆነ ሰው እየሮጠ ወደ እኛ እየመጣ ነው፡፡” አሉ መነኩሴው፡- “እስኪ ማን እንደሆነ እንየው፡፡”
ንጉሱ ዞር አለ፡፡ ፊቱ በፂም የተሸፈነ ሰው ከጫካው ውስጥ እየሮጠ ወደ እነሱ ሲመጣ ተመለከተ፡፡ ፂማሙ ሰው ሆዱን በሁለት እጆቹ ግጥም አድርጐ ይዟል፡፡
 ደም ከእጆቹ እና ከሆዱ መሀል እየፈሰሰ ነው፡፡ ንጉሱ ጋ ሲደርስ መሬት ላይ ተዘረጋ፡፡ እራሱን ሳተ፡፡ በቀስታ ሲያቃስት ይሰማል፡፡
 ንጉሱ እና መነኩሴው፣ ሰውዬው ከወገቡ በላይ የለበሰውን ልብስ አወለቁ፡፡ ትልቅ እና ትኩስ ቁስል ሆዱ ላይ አለ፡፡ በስለት እንደተወጋ ያስታውቃል፡፡ ንጉሱ እስኪደክመው ድረስ ቁስሉን አጠበ፡፡ ቁስሉን በመሃረቡ ሸፈነ እና መነኩሴው በሰጡት ፎጣ አሰረው፡፡ ደሙ ቶሎ አልቆመም፡፡ ንጉሱ በተደጋጋሚ ቁስሉን እያጠበ፣ በንፁህ ጨርቆች ሲሸፍናቸው ቆየ፡፡ ደሙ መፍሰስ አቆመ፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ቁስለኛው እራሱን አወቀ፡፡
“እባካችሁ የሚጠጣ ነገር፡፡” አለ፡፡ ንጉሱ ንፁህ ውሃ አቀበለው፡፡
ፀሀይ ጠለቀች፡፡ አየሩ መቀዝቀዝ ጀመረ፡፡ ንጉሱ እና መነኩሴው ተጋግዘው ቁሰለኛውን ተሸክመው ወደ ጐጆዋ አስገቡት፡፡ የመነኩሴው አልጋም ላይ አስተኙት፡፡ አይኖቹን በእፎይታ ከደነ፡፡ አንዳችም አልተናገረም፡፡
ንጉሱ ጉዞው፣ ቁፋሮው እና ቁስለኛውን መንከባከቡ እጅግ አድክሞት ሰለነበር ከአልጋው ስር የነበረው መሬት ላይ ዘፍ አለ፡፡ ወዲያው እንቅልፍ ወሰደው፡፡ እንዲህ አይነት ጥልቅ እንቅልፍ ተኝቶ አያውቅም፡፡ እስኪነጋም ድረስ አልነቃም ነበር፡፡ ለነገሩ ወቅቱም በጋ ስለነበር ሌሊቱ አጭር ነው፡፡ ንጋት ላይ ከእንቅልፉ ሲነቃ የት እንዳለ ግራ ገባው፡፡ በዚያም ላይ እንግዳ የሆነ ፂማም ሰው በሚያበሩ አይኖቹ እያየው ነው፡፡ ቀስ እያለ የት እንዳለ እየታወቀው መጣ፡፡
“እባክህ ይቅር በለኝ” አለ ፂማሙ ሰው በሳሳ ድምፅ፤ ንጉሱ መንቃቱን ሲየውቅ እና እያየው እንደሆነ ካስተዋለ በኋላ፡፡
“ጉድ መጣ፡፡ አላውቅህም፡፡ የበደልከኝ ነገር የለም፤ ይቅር የምልህም ነገር የለኝም” አለ ንጉሱ፡
“አንተ አታውቀኝም፡፡ እኔ ከምንም በላይ አውቅሃለሁ፡፡ ወንድሜን የስቅላት ፍርድ ፈርደህበት አሰቅለኸዋል፡፡ ንብረቱን ሁሉም ወርሰሀል፡፡ ከወንድሜ ሞት በኋላ የኖርኩት ለበቀል ነው፤ አንተን ለመግደል ስከታተልህ ነው ዘመኔን ያሳለፈኩት፡፡ መነኩሴውን ልትጐበኛቸው ስትመጣ እንዴት ደስ እንዳለኝ ልነግርህ አልችልም፡፡ ተከተልኩህ፡፡ አጃቢዎችህን ወዲያ ማዶ አቁመህ ብቻህን በእግርህ መጣህ፡፡ ስትመለስ ልገድልህ ወስኜ አጃቢዎችህ ካሉበት ትንሽ ራቅ ብዬ ጫካው ውስጥ ተደበቅኩ፡፡ ብጠብቅ፣ ብጠብቅ፣ ብጠብቅ አልመጣ አልህ፡፡ ትእግስቴ አለቀ፡፡ ከተደበቅኩበት ወጥቼ ወደዚህ ልመጣ ወሰንኩ፡፡ ታዲያ ምን ዋጋ አለው? አጃቢዎችህ ንቁዎች ናቸው፡፡ እንቅስቃሴዬ የፈጠረውን ድምፅ ሰምተው ተከተሉኝ፣ ያዙኝ፡፡
ማን እንደሆንኩ፣ ለምን እዚያ ቦታ እንደተገኘሁ ሳልናገር ገባቸው፡፡ አንተ ነህ እንጂ አነሱ ያውቁኛል፡፡
 እንደምታየው ሆዴን በጐራዴ ሰነጠቁት፡፡ እንደምንም አምልጬአቸው ስሮጥ ወደዚህ መጣሁ፡፡ አንተ ቁስሌን አጥበህ፣ የተቻለውን ያህል ባታክመኝ ኖሮ ማምለጤ ምንም ዋጋ አይኖረውም ነበር፡፡ በደም መፍሰስ ብዛት እሞት ነበር፡፡ ልገድለው የነበረው ሰው፣ ህይወቴን አዳናት፤ ይገርማል፡፡ አሁንም ምህረት የምታደርግልኝና የማትገለኝ ከሆነ እድሜ ልኬን ታማኝ አገልጋይ ባሪያህ ለመሆን ቃል እገባለሁ፡፡ ምን እኔ ብቻ ልጆቼም እንዲያ እንዲያደርጉ አደርጋለሁ፡፡ ይቅር በለኝ፡፡”
እንዲህ በቀላሉ ከፉኛ ጠላቱ ወዳጁ ሲሆን ንጉሱ ደስታ ወረረው፡፡ ውርርር አደረገው፡፡
“ይቅር ብዬሃለሁ፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፤ እንዲንከባከቡህ አገልጋዮቼን፣ እንዲያክምህ ደግሞ የግል ሀኪሜን እልክልሃለሁ፡፡ ከወንድምህ የወረስኩት ንብረት ሁላ ላንተ ይመለሳል፡፡” አለ ንጉሱ፡፡ ይህን ብሎም መነኩሴውን ፍለጋ ወደ ጐጆዋ በረንዳ ወጣ፡፡ መነኩሴውን የፈለጋቸው ለመጨረሻ ጊዜ ለጥያቄዎቹ መልስ ለመጠየቅ ነው፡፡ መነኩሴው በርከክ ብለው ትናንት የቆፈሩዋቸው የእርሻ መደቦች ላይ ዘር እየዘሩ ነበር፡፡
ወደ መነኩሴው ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፡-
“ለመጨረሻ ጊዜ ልለምንዎት፤ እባክሆን ለጥያቄዎቼ መልስ ይስጡኝ፡፡”
“ተመልሶልሃል” አሉ መነኩሴው በእንብርክካቸው እንዳሉ፣ ቀና ብለው እያዩት፡፡
“ምን? ተመልሶልሃል? የምን መልስ? ምን እያሉኝ ነው?” ጠየቀ ንጉሱ፡፡
“አላስተዋልክምን?” አሉ መነኩሴው፡- “አንዴ ብቻ አይደለም ለጥያቄዎችህ መልስ የተሰጠህ፤ ከአንዴም ሁለቴ ነው፡፡ በመጀመሪያ ትናንት ድካሜን አይተህ ዶማውን ከኔ ተቀብለህ የእርሻ መደቦችን መቆፈር ያዝህ፣ ሄደህ ቢሆን ኖሮ ይህ ሰው መንገድ አግኝቶ አደጋ ይጥልብህ ነበር፡፡
እግዚሀር ብሎ በህይወት ብትተርፍ “ምነው መነኩሴው ጋር በቆየሁ!” ብለህ ትፀፀት ነበር፡፡ ቆየህ፤ ከአደጋም ዳንክ፤ ህይወትህም ተረፈ፡፡ እናም የእርሻ መደቦቹን ስትቆፍር የነበረበት ሰዓት በህይወትህ በጣም ወሳኙ ሰዓት ነበር፡፡ በዛች ቅፅበት በህይወትህ በጣም አስፈላጊው ሰው እኔ ነበርኩ፤ በኔ ሰበብ ነዋ ወደ መጣህበት ያልተመለስከው፡፡
እኔን በእርሻው ሥራ ማገዝህ ደግሞ ለአንተ በአለም ላይ ምርጡ ሥራ ነበር፤ ህይወትህን አትርፎታል፡፡ አንድ በል፡፡
ሁለት ደግሞ፡- ሰውየው ወደ እኛ ቆስሎ እየሮጠ መጣ፤ ቁስሉንም አፀዳህለት፡፡ ያቺ ሰዓት ወሳኟ ጊዜ ናት፡፡ ያንን ባታደርግ ኖሮ ካንተ ሳይታረቅ፣ የአእምሮ ሰላም ሳያገኝ ይሞት ነበር፤ በደም መፍሰስ ብዛት፡፡ በዚያን ወቅት እጅግ አስፈላጊው ሰው ባላንጣህ ነበረ፡፡
ለሰውየው ያደረከው እርዳታ ደግሞ በምድር ላይ ልታደርገው የምትችለው የምርጦች ምርጥ ሥራ ነበር፡፡ በመጨረሻም ይህንን አስታውስ፡- ከጊዜያት ሁሉ ለእኛ ታላቁ እና አስፈላጊው ጊዜ አሁን የሚባለው ጊዜ ነው፡፡ ባለፈውም ሆነ በመጪው ጊዜ ላይ አንዳችም ስልጣን የለንም፡፡
በእጃችን ላይ ሁሌም ያለው ልንወስንበት የምንችለው የጊዜ ክፋይ አሁን ነው፡፡ አሁን፡፡ ከምንም በላይ ልናከብረው እና ልናዳምጠው የሚገባው ሰው ደግሞ በሆነው ቅፅበት አብሮን ያለውን ሰው ነው፡፡ እዚህች ምድር ላይ ልንሰራው የምንችለው ምርጡ ስራ ደግሞ አብሮን ላለው ሰው መልካም ነገር ማድረግ ነው፤ ወደዚህ ምድር የተላክነውም ለዚህ ነው፡፡”  

Read 1440 times