Saturday, 03 October 2015 10:43

የእውለት ቅርፊቶች! ወግ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

   የልጅ ልጆቼ ስም ማን እና ማን ይባላል? ለሚለው ጥያቄ መልስ፣ እዚህ ወንበር ላይ ተቀምጬ ማግኘት አልችልም፡፡ ሁሉም ነገር ፍቺው በሂደት የሚገኝ ነው፡፡
እዚህ የካፌ ወንበር ላይ ተቀምጫለሁ፡፡ ከጐኔ በስተቀኝ ኮረዳዋ ተቀምጣለች፡፡ ቀጠሮ አለባት፡፡ የሆነ ሰውን እየጠበቀች ነው፡፡ እየጠበቀች እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ምክንያቱም እየጠበቀች ያለችው እኔኑ እራሴን ነው፡፡
እሷ አላወቀችኝም…የተዋወቅነው በአካል ሳይሆን በጽሑፍ ነበር፡፡ ብዙ ወራት በፌስቡክ ተፃፅፈናል፡፡ የመጨረሻው ጽሑፋችን መገናኘት እንዳለብን የተስማማንበት ነበር፡፡ ተስማማን ተቀጣጠርን፡፡ በመልክ ስለማንተዋወቅ ልዩ ምልክቶች ተለዋወጥን፡
የሷ ልዩ ምልክት ወፍራም የአይን መነፅር ማድረጓ ነው፡፡ የእኔ ልዩ ምልክት ቀይ ሹራብ ከላይ መደረቤ፡፡ አሁን ከጐኗ ተቀምጫለሁ፡፡ እሷ መነፅሯን ደንቅራለች፡፡ እኔ ግን በቀይ ሹራቤ ላይ ጥቁር ጃኬት ደርቤ ማንነቴን ደብቄአለሁ፡፡ እኔ እሷን አውቄያታለሁ፡፡ እሷ፤ ጐኗ ተቀምጬም አላወቀችኝም፡፡
ማንነቴን ወዲያው ልገልፅላት አልፈለኩም፡፡ ምክንያቱም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ከዚች ቅፅበት በኋላ… ከመጨባበጥ በኋላ… የሚመጡት ቅጽበቶች ይዘውን የሚጓዙበት ጐዳና አስፈርቶኛል፡፡ አንድ ቀን ስንት ሰከንዶች ነው፡፡ ለእሷ እና ለእኔ (ፌ.ቡ ስሜ) እና (ምናልባት የእሷም እንደኔው የፉገራ ስም) ቀኑ መቁጠር የሚጀምረው ከትውውቃችን በኋላ ነው፡፡ የእየግል ሰአቶቻችን በትውውቅ አንድ ላይ ከመዋሃዳቸው በፊት ትንሽ መወዛገብ አስፈለገኝ፡፡
ከበስተግራ ተቀምጬ ሰረቅ አድርጌ አያታለሁ፡፡ የምትጠብቀው ሰው እኔኑ ራሴን ቢሆንም እሷ ግን እኔን ራሴን እኔን ይሆናል ብላ ስላልጠረጠረች፣ ወደ ግራ እና ቀኝ እየተቅነዘነዘች ትጠብቃለች፡፡ ምናልባት እሷ የምትጠብቀው ጽሑፌን የመሰለውን አይነት “እኔ” ሳይሆን አይቀርም፡፡
ጽሑፌ በተክለ ሰውነት ሲተረጐም ምን ይመስል ይሆን? ምን መስሏት ይሆን እኔን አንዴም እንኳን ልብ ብላ ያላየችኝ? የሷ ቀና ብላ እኔን አለማየት ብቻ ሳይሆን፣ የእኔም ለመታየት አለመሞከር የበለጠ ግራ አጋብቶኛል፡፡ ምናልባት በራሴ ስለማልተማመን ይሆን? ብርክቲ በራሷ የተማመነችው ከውጭ በመምጣቷ ነው? ወይንስ ቆንጆ ነኝ ብላ ስለምታስብ ነው? ከውጭ የመጣ በግድም ይሁን በውድ ቆንጆ ይሆናል፡፡ ያን ያህልም ቆንጆ አይደለችም፡፡ ውስጣዊ ውበቷ ነው ይኼንን ያህል በራስ መተማመን የፈጠረባት፡፡ መነፅሯን ደጋግማ ታስተካክላለች፡፡ ለንባብ ብቻ ነው የምትጠቀምበት መሰለኝ፡፡ ለንባብ ብቻ እና እኔን ለመተዋወቂያ ምልክት እንዲሆንላት ብቻ፡፡ ከታክሲ ከመውረዴ በፊት ነበር ካፌው በራፍ ላይ ከቀጠሮዋ ቀደም ብላ መጥታ መቀመጧን ልብ ያልኩት፡፡ በታክሲው መስኮት እንደተመለከትኳት ወደድኳት፡፡ በቅጽበት ስለወደድኳት መሰለኝ የተሸማቀቅኩት፡፡ ፈጥኜ ማንነቴን መግለጽ አስፈራኝ፡፡ እንድትጠላኝ አልፈለኩም፡፡ ከላይ እንደ ሁልጊዜውም የምለብሰው ሹራብ ላይ በፌስታል የያዝኩትን ጥቁር ጃኬት ደረብኩበት፤ ቀስ ብዬ ከጐኗ መጥቼ ተቀመጥኩ፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ በአይኗ ገረፍ አደረገችኝ፡፡ የምትጠብቀው እኔ ከተቀመጠው ጋር አንድ እንዳልሆነ አረጋግጣ ችላ አለችኝ፡፡ እኔ ግን እሷ ብርክቲ መሆኗን አልተጠራጠርኩም፡፡
“ሰው የለውም አይደል?” አልኳት፡፡ እውነቱን እያወቅሁ፡፡
“ሰው እየጠበቅሁ ነው ግን ተቀመጥ” አለችኝ፡፡ የምትጠብቀው ሰው እኔው ራሴ ነኝ፡፡ ሳልግደረደር ተቀመጥኩ፡፡
በጽሑፍ ተግባብተናል፡፡ ፅሁፍ ውስጥን እንጂ ውጭን አይፈልግም፡፡ ጽሑፍ ግልፅ ነው፡፡ አይዋሽም፡፡ ተፃፅፈን ተግባብተናል፡፡ ተያይተን መግባባታችን ግን አጠራጥሮኛል፡፡ ለእኔ እሷ ተስማምታኛለች፡፡ የምወደው አይነት ያልጮኸ መልክ ነው ያላት፡፡ እድሜዋም ለጋ ነው፡፡ እኔ ግን ለእሷ እንዴት ነኝ?...
እስከዛው ከጐኗ ቁጭ ብዬ ትንሽ መወዛገብ ነበረብኝ፡፡ የወደፊት እጣ ፈንታ ከፊቴ ለጥ ብሎ ተዘርግቷል፡፡ “እኔ ታድኤል ነኝ” ካልኳት በኋላ ከዚህ ተነስተን የሆነ ቦታ መሄዳችን አይቀርም፡፡ ካፌ ያልሆነ ቦታ፡፡ ሁለታችንም በፀጥታ የምናወራበት ቦታ፡፡ እሷ ታሪኳን፣ እኔ ታሪኬን በአንደበታችን የምንገልፅበት ቦታ፡፡ ከጽሑፍ ውጭ ቅርፊት የሌለው እውነታ! ከዛ ቢራ ምናምን መባሉ አይቀርም፡፡ እጄ እጇን ጭምቅ አድርጐ መያዙ አይቀርም፡፡ የእጅ ሙቀት ከአቅም በላይ ከሆነብን ከንፈራችን መቀራረቡ እና በእሳት መያያዙ አይቀርም፡፡
ግን ከዚሁ ሁሉ በፊት፣ ጊዜ በዚህ የካፌ ወንበር ዙሪያ ቀጥ ብሎ ቆሟል፡፡ ለእሷ እና ለእኔ፡፡ እሷ በድፍረት የትውውቁን መጀመር እየጠበቀች ነው፡፡ እኔ በጥርጣሬ የማይታየውን የወደፊቱን ጊዜ በምናቤ እየለካሁት ነው፡፡
ፍርሀቴ ሰው እንደ ጽሑፉ አለመሆኑን ማወቄ ላይ ነው፡፡ ሰው በተክለ ሰውነት፣ በአካል አለም ሌላ ነው፡፡ እኔም ሌላ ነኝ፡፡ የጽሑፍ ድፍረቴ በካፌ ወንበሩ ዙሪያዬን ሆኖ ተሰውሯል፡፡ ምናልባት ብር በኪሴ ስለሌለ ይሆናል በራስ መተማመኔ የጠፋው፡፡ በኪሴ ብር ሳይኖር እቺን የመሰለች ልጅ መተዋወቅ ራሴን ለማስናቅ ነው፡፡
ብር ተበድሬ ልብስም ተውሼ ጠንካራ ቅርፊት አበጅቼ መምጣት ነበረብኝ፡፡ ግን በጥርጣሬ ውስጥ ተጠቅልዬ እዛው ቁጭ ብያለሁ፡፡ ቅጽበት ባለበት ቀጥ ብሎ ቆሟል፡፡ አንድ ሰከንድ ስንት ቀን እንደሆነ ማወቅ ነው ያለብኝ እንጂ ቀን ከስንት ሰከንዶች ብዛት እንደሚፈጠር መቀመር አይደለም ለእኔ ትርጉም ያለው ጥያቄ፡፡
መነፅሯን አውልቃ ወለወለችው፡፡ ወልውላ የሆነ ደረቅ ቅርፊት ያለው ማስቀመጫ ውስጥ ከታ ጠረጴዛው ላይ ተወችው፡፡ መበሳጨት ጀምራለች፡፡ ዘግይቼባታለሁ፡፡ እዛው ጐኗ ተቀምጬ አርፍጄባታለሁ፡፡ አይኗ በመንገዱ ላይ እየተንከራተተ ነው፡፡ የእኔ አይን ግን መጪው ጊዜ ላይ ነው በጥርጣሬ ግራ ተጋብቶ የቀረው፡፡ እዚህ እና አሁን ከአጠገቤ ርቋል፡፡
ስልኳን አውጥታ ወደኔ ቁጥር ልትደውል መሆኑ ሲገባኝ፣ ተንቀሳቃሽ ስልኬን በፍጥነት አውጥቼ አጠፋሁት፡፡ “የደወሉለት ሰው ስልክ ዝግ ነው” ሲላት ሁለታችንም ተሰምቶናል፡፡ አሁን ነገሩ በጣም እየተበላሸ መሆኑ ገባኝ፡፡ ስልኳም እንደ ተክለ ቁመናዋ ከእኔ በተጨባጭ የበለጠ ነው፡፡ በቃ እሷ ሀብታም ፀሐፊ ናት፡፡ እኔ ደሀ ህልመኛ ነኝ፡፡
አሁን ተነስቼ “እኔ ነኝ ታድኤል” ብላት ሳትቀየመኝ አትቀርም፡፡ “አላወቅሁሽም ነበር” ብላትም ይቅር አትለኝም፡፡ ነጥብ ጥያለሁ፡፡ ቀስ ብዬ ተነስቼ ነው መሄድ ያለብኝ፡፡ ቤት ደርሼ ስልኬን አብርቼ ብደውልላት እና ይቅርታ ብጠይቃት ይሻላል፡፡ ምናልባት የሚቀጥለው ሳምንት የተክለ ቁመና አቀራረቤን አሻሽዬ፣ ልብስ እና ገንዘብ ተበድሬ በአዲስ አቀራረብ፣ አዲስ ካፌ ብቀጥራት ይሻላል…ብዬ ወሰንኩ፡፡
ወሰንኩ ግን ከተቀመጥኩበት አልተነሳሁም፡፡ እሷም አልተንቀሳቀሰችም፡፡ ያዘዘችው ማኪያቶ ቀዝቅዟል፡፡ ቅዝቃዜውን ሳልቀምሰውም አውቄዋለሁ፡፡ ስልኩን ሞክራ ሞክራ ቁርጧን አወቀች፡፡ በረጅሙ ተንፍሳ የማኪያቶውን ብር ጠረጴዛው ላይ ጥላ፣ ቦርሳዋን በክንዷ ላይ አንግታ ተነሳች፡፡ ተነስታ በሚያመነታ እርምጃ ማዝገም ጀመረች፡፡ አንድ ጊዜም ዞራ አላየችኝም፡፡ እኔ ግን በአይኔ ተከተልኳት፣ ከአይኔ ልትጠፋብኝም ስትል ከወንበሩ ተነስቼ በእግሬ ሸኘኋት፡፡ ኮንትራት ታክሲ ስትነጋገርም ከጀርባዋ እንደ ውቃቤ ቆሜ ነበር፡፡ ታክሲው ተነስቶ ከሄደ በኋላም እግሬ አልተንቀሳቀሰም፡፡ ወደፊት መሄድ የሚፈራ ሰው የሚራመድበት መንገድ የለውም፡፡ እኔ ህይወት ውስጥ በተጨባጭ ያለሁ ሰው ስለመሆኔ ተጠራጠርኩ፡፡ ወደ ካፌው ተመለስኩኝ፡፡
ወንበሩ ላይ ተቀመጥኩኝ፡፡ የደረብኩትን ጥቁር ጃት አወለቅሁኝ፡፡ እሷ (ብርክቲ) ቅድም እኔን ስትጠብቅ ትመስል እንደነበረው መሰልኩኝ፡፡
 የመሰልኩትን የሚያምንልኝ ግን አላገኘሁም፡፡ የጠበቅሁዋት ሴት የቀረችብኝ መሆኔን የሚያሳምን ኩርፊያ፣ በገጽታዬ ላይ አኮሳትሬ አንገቴን ደፍቼ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡
 ተመልሼ አልጋዬ ላይ ቁጭ አልኩ፡፡ እውነተኛ ታሪክ መፃፍ ሲያቅተኝ ነው ለካ የፈጠራ ታሪክ ድርሰት እያልኩ የምጽፈው፡፡ መኖርን እንደፈራሁት መፃፍ ደግሞ አስጠላኝ፡፡ ስልኬን ብቻ አበራሁት፡፡

Read 1703 times