Saturday, 02 July 2016 12:37

‘Fikru’….‘ፍቅሩ’

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የሥዕል ትርዒት ዳሰሳ (Exhibition Review)
የትርዒቱ ርዕስ፡ ፍቅሩ
ሠዓሊ፡ ፍቅሩ ገ/ማርያም
የትርዒቱ አይነት፡ የግል፤ የቀለም ቅብ ስራዎች
ብዛት፡ 25 የቀለም ቅብ፤ ስራዎች
የቀረበበት ቦታ፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ጊዜያዊ የስዕል ማሳያ አዳራሽ አዲስ አበባ
ጊዜ፡ ሰኔ 06 - ሐምሌ 7: 2008 ዓ.ም
ዳሰሳ አቅራቢ፡ ሚፍታ ዘለቀ(የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)

“ፍቅሩ”
ለግል የሥዕል ትርዒት ስያሜነት ከሚውሉ አሰያየሞች መካከል መጠሪያ ስምን ለትርዒት ስያሜ ማድረግ ከተለመዱት መሃል አንደኛው ነው፡፡
ይህን ማድረግ ራሱን የቻለ መደንግግ ነው፡፡ ሠዓሊ ፍቅሩ ገብረማርያም ለዚህኛው ብቻ ሳይሆን በላጮቹንና አብዛኛዎቹን የግል የሥዕል ትርዒቶቹን መጠሪያ በስሙ ‘ፍቅሩ’ በሚል ነው ለህዝብ እይታ የሚያበቃው፡፡ ይህ ደግሞ መደንግግነቱን እንድናስተነትንና ‘ፍቅሩ’ የሚለውን ስያሜ በድግምግሞሽ እንዲጠቀም ያስቻለውን አመክንዮ ለመረዳት ቆፈር ቆፈር እያደረግን እንድንፈትሽው በር ከፋች ነው ባይ ነኝ፡፡ አሃዱ፡ ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም ‘ፍቅሩ’ ነቱ ላይ ችክ ያለ ሠዓሊ መሆኑን መረዳት እንድንችል እየነገረን ሊሆን ይችላል፡፡ ክልኤቱ፡ ሠዓሊው ገና የ’ፍቅሩ’ነቱን ፍቅር አጣጥሞ አለመጨረሱን እንድንጠረጥር በገቢርም ሆነ በነቢብ የማርያም መንገድ እየሰጠን ይሆናል፡፡ ሰልስቱ፡ ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም ራሱ ፍቅሩን ወይም የፍቅሩንነቱን ጥግ፣ልክ፣ጥልቀትና ርቅቀት ገና ዳሰሶ ወይም ፈልጎ አለመጨረሱንና አለማግኘቱን ለመጠቆም፤ ይልቅስ በፍለጋው ሂደት ያገኘውን ወይም የደረሰበትን ፍቅሩን እንካችሁ ማለቱ ሊሆን ይችላል፡፡ አርባዒቱ፡ ሠዓሊው በደረሰበት ወይም ባገኘው ፍቅሩነት እርግጠኛ ሆኖ፣ እነሆ ፍቅሩ መጥቷልና ከበረከቱ ትካፈሉ ዘንድ ትርዒቱን እንካችሁ እያለም ይሆናል፡፡ ሐምስቱ፡ መ ሁሉም መልስ ነው፣ አልተሰጠም ወይም መ መልስ የለውም የሚል መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን፡፡ ወደ ትርዒቱ፡-
በትርዒቱ ከቀረቡት ስራዎች ሰባ በመቶ የሚሆኑት በአውታረ መጠናቸው ብቻ የሚናገሩት ሃቅ አለ፡፡ የሥራዎቹ የጎን ስፋትና ቁመት ተቀራራቢነት ያላቸው፤ ወደ ስኩዌር ካሬነት የሚያዘነብሉና መሃከለኛና በብዛት ትልቅ መጠን ያላቸው የሥዕል ሰሌዳዎችን ነው የሚጠቀመው፡፡ እንዲህ አይነቱ አውታረ መጠን በተለምዶ ግዘፍ የሚነሳ፤ ዓይን የሚሞላና ደርፈጭ ያለ ወይም (bald) እንደሆነ ይነገራል፡፡ አንድ ሠዓሊ ይህን አይነት አውታረ መጠን ሲጠቀም ግዘፍ የሚነሱና ስለ ራሳቸው በልበ ሙሉነት የሚናገሩ ሀሳቦችን በማንሸራሸር እንዲያግዘው ሆን ብሎ የሚመርጠው እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህ ትርዒት የቀረቡ አብላጫዎቹ ስራዎች በዚህ አቀራረብ የተቃኙ እንደሆኑ ይስተዋላል፡፡ ሆኖም እንዲህ አይነት ዝንባሌ ያላቸው ስራዎች በአንድ ላይ ለዕይታ ሲቀርቡ፣ ሲደረደሩና ሲሰቀሉ ሰዓሊውም ሆነ የትርዒቱ አጋፋሪ (curator) በጥንቃቄ ማሰብና መከወን የሚገባውን ወሳኝ ነጥብ የሳተ አቀራረብ በዚህ ትርዒት ይስተዋላል፡፡ ይኸውም ትርዒቱ ከሚታይበት ህንፃ ውስጥ ፎቅ ላይ ባለው የመጨረሻውና ሰፊው የሥዕል ማሳያ አዳራሽ ውስጥ የተሰቀሉት ሳይሆን የተገጠገጡት ሊባል በሚያስችል ደረጃ እንደ ሱቅ በደረቴ በአንድነት ተቸምችመው ያሉት አምስት ስድስት ሰራዎች የግዙፍነታቸውን ብቻ ሳይሆን ያመቁትን የሃሳብና የስሜት  ጥቅጥቅነት (density) ከግምት ያላስገቡ ናቸው፡፡ ሠዓሊው ፍቅሩ ገ/ማርያም፤ በፍቅር የወደቀላቸውን ስራዎች ለማሳየት በጉጉት ሲጣደፍ አሰቃቀሉ ለዕይታ እንደሚጎረብጥ እንኳ ማስተዋል እንደነሳው ማየት እንችላለን፡፡ ለአንድ ነገር ፍቅር ብቻ ሲቸረው የሚያስከትለው ችግር ይኖራል፡፡ ምናልባትም በ’ፍቅሩ’ነቱ ጥግና ልክ እርግጠኛ የሆነ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ከመገጥገጥ ይልቅ አንድ ወይ ሁለት ስራዎቹን ብቻ “ገጭ” አድርጎ ሰቅሎ ሙሉ “ፍቅሩ”ነቱን በልበ-ሙሉነት መንፈስ ጀባ ሊለን ይቻለው ነበር የሚል ሙግት አመክንዮ እንዳነሳ የሚጋብዝ ፍንጭ በተለይ ከተጠቀሰው የሥራዎቹ አውታረ መጠናቸውን መሰረት በማድረግ፣ሥራዎቹ ከተሸከሙት የሀሳብና የስሜት ጥቅጥቅነት በመነሳት ለተመልካች እይታ ብሎም መረዳት ትግዳሮት (problem) የሚፈጥረውን የትርዒቱን ባህሪ ማየት ይቻላል፡፡ በመሰረቱ እንዲህ አይነት ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን ለአንድ የሥዕል ትርዒት ምሉዕነት ጉልህ ሚና ያላቸውን የአቀራረብ ባህሪያት ከግምት ውስጥ አስገብቶ የሚሰራ የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ ከሌላው ትርዒት የሚጠበቅ ህፀፅ ቢሆንም እንደ ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም በዓለም አቀፍ መድረኮች፣ በታላላቅ ሙዚየሞችና ጋለሪዎች ዓለማችን ካፈራቻቸው ምርጥ ሠዓሊያን ጎንና በአንድነት ስራውን ካቀረበ ሠዓሊ የማይጠበቅ በመሆኑም ነው ይህን ያህል ትኩረት ሰጥቼው የነካካሁት፡፡ በአንፃሩም የትርዒት ማሳያው አዳራሽ አስተዳደርም ቢሆን ለአዳራሹ ኪራይ አይሉት አበል ለፅዳትና ጥበቃ አንዳንዴም የአዳራሹን በርና መስኮት ከፍቶ ለሚዘጋው ሰው አበል በሚል ሰበብ ለሚሰበሰበው ገንዘብ ትኩረት ከመስጠት ውጪ ለእንዲህ አይነት ሙያዊ እገዛዎችም ሆነ የአዳራሹን ግድግዳዎች ለማደስ፣ የሥዕል አስቃቀልንና ዕይታን ለሚረብሹት እንዲያው እንደዘበት አቡጂዲ ጨርቅ በመስኮቶቹ ላይ ጣል ከማድረግ ውጪና አንድ የሥዕል የተሳካ ለሚያደርጉት የብርሃን አምፑሎች “በዕድላቸው” እንዲበሩ ከመተው የዘለለ መፍትሔ ከማቅረብ ሌላ ዳተኝነቱን በተከታታይ እየተዘጋጁ ካሉ ትርዒቶች ለመረዳት ችለናል፡፡ እናም ከዚህ ዓይነት የአዳራሹ አስተዳደር የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ (curator) መጠበቅ “እዬዬም ሲደላ ነው” ሊሆንብን ይችላል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ብሔራዊ … የሚል ሁለት ከባባድ መጠሪያዎችን ከተሸከመ የሥዕል ማሳያ አዳራሽ እንዴት “እዬዬም ሲዳላ” ይሆናል የሚል ሀሳብ ዘወትር ወደ አዳራሹ ጎራ ባልኩ ቁጥር የሚነዘንዘኝ ሃሳብ በመሆኑና መተቸት የሚገባው እንደሆነ ስለማምንበት ነው ያነሳሁት፡፡ አስተዳደሩ አዳራሹን ለተከታታይ ትርዒት ክፍት ከማድረጉ ባሻገር በዚህ በ “ፍቅሩ” ትርዒት ሙዚየሙና የአዳራሹ አስተዳደር ካሳየው አበረታች ጅምሮች መሃከል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አቶ ዮናስ ደስታ በትርዒቱ መክፈቻ ተገኝተው ስለ ትርዒቱና ስለ ሥነ-ጥበብ እንዲሁም ባለስልጣን መ/ቤቱ ለሥነ-ጥበብ ስለሚያደርገው ድጋፍ የሰጡት ጠንካራ የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡ በተለይ ባለስልጣን መ/ቤቱና የአዳራሽ አስተዳደር ከላይ የተጠቀሱት አይነት ችግሮችን በጊዜ ሂደት እየቀረፈ ቢሄድ ይበል የሚያስብል ማለፊያ ማበረታቻ ነው፡፡ ወደ “ፍቅሩ” እንመለስ፡-
ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም በ1987 ዓ.ም ነው ከአሁኑ የአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ  አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት  በቀለም ቅብ በዲፕሎማ የተመረቀው፡፡ ለዲፕሎማው አራት ዓመታትን፣ ከዚያ በፊት ት/ቤቱ ይሰጥ በነበረው የማታ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ለሁለት ዓመታት፣ እንደገና ከእነዚህ ሁለት ዓመታት በፊት ለአራት ዓመታት በተከታታይ የክረምት ትምህርት ክፍለ ጊዜ በት/ቤቱ ተከታትሏል- አስር ዓመታትን በድምሩ የሥዕል ትምህርት ሲማር ቆይቷል ማለት ነው፡፡ ተመርቆ ከወጣ በኋላ እስካሁን ባሉት ሀያ አንድ ዓመታት ውስጥ ደግሞ  በስቱዲዮ ሠዓሊነት ቆይቷል፡፡ ሥዕል የተማረበትና የሰራበት ዓመታት ሲደመሩ የአንድ ትውልድ እድሜ ይተካከላሉ ማለት ነው፡፡ የሥዕል ትምህርት መማር ሠዓሊ አያደርግም፤ምናልባት ሥዕል ለመስራት ያግዝ ይሆናል እንጂ፡፡ የሥዕል ትምህርት አለመማምርም ከሠዓሊነት አያግድም፡፡ በሀገራችን ብቸኛው የሥነ-ጥበብ ተቋም ሆኖ ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በላይ የዘለቀው የአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት፣ ሲያስተምርበት የቆየውንና አሁንም ከሞላ ጎደል እያስተማረበት የሚገኘውን የትምህርት አሰጣጥ ዘዬና ፍልስፍና እጅጉን ክሊሎት (skill) ላይ መሰረት ያደረገና ቆይታው ያዳበረው ልምድ ብቻቸውን ወደ አንድ ከዚህ ቀደም ሲሰራ ከቆየበት ወደ ተለየ የአሰራር አቅጣጫ እያመጡት እንደሆነ በዚህ ትርዒት ላይ መመልከት እንችላለን፡፡
 ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም አበድ፣ሰከር፣ቆፍጠንና ፈጠን ያለ ድፍረት በዚህ ትርዒት አሳይቶናል፡፡ እብደቱ ስካሩ ነፃነቱን፤ፍጥነቱና ቆፍጣናነቱ ደግሞ ሩቅ አላሚነቱን ያመለክታሉ፡፡ ጭልጥ አድርጎ ከመጠጣት ሳይሆን ቀስ በቀስ፣ ያውም የአስር ዓመታት ትምህርትንና ሃያ የሚሆኑ የሠዓሊነት ዓመታት ልምዶችን በዝግታ በማጣጣምና በማሰላሰል ከሚመነጭ ድፍረት ነው እብደቱና ስካሩ የተወለዱት፡፡ ቀጥ ብሎ ለመቆም፣አሻራውን ለመተው፣ምናልባትም ለመዝናናት፣ ፈታ ብሎ በስራዎቹ ሙከራ ለማድረግና እንደውም (ቀጣዩን ዓረፍተ ነገር ቡፍ ብሎ ከሚያመልጥ ሳቅ ጋር ነው ያሰብኩት)… እንደውም “ሥዕል ምናባቱ-የታባቱ አፈር ድሜ ማብላት ነው እንጂ” እያለ መስራ ከሚያስችል ድፍረት ውሰጥ የሚገኝ ሩቅ አላሚነት የከሰቱት ፍጥነትና ቆፍጣናነትም በስራው ማየት ይቻላል፡፡ በዚህ ትርዒት የቀረቡት ሥራዎች በሥነ-ጥበብና በሚሰራው ሥዕል ለመፈላሰፍና ለመዝናናት የሸሚዞቹን እጀታ ከክንዱ ከፍ አድርጎ የሰበሰበ ሰው የሚሰራቸው አይነት ስራዎቸ ይታዮኛል፡፡ ሥራዎቹ ቆፍጣናነትና ፍጥነት ካልተሞላባቸውም ለዘዝ ብለው ለዘመናት ሲመላለስበት ወደ ኖረበት ድግምግሞሽ ለመመለስ የፈራ የሚደፍረው ዓይነት ድፍረት ይስተዋላል፡፡ ይልቅስ ቆፍጠን ብሎ ፍጥነት በመጨመር ቢነጉድ አንድ ከፍታ ላይ ለመድረስ የሚያልም፣ነፍሱን የሳተ እብድና ሰካራም ጋላቢ ከሚደፍረው ድፍረት የመነጩ ስራዎች በትርዒቱ ይታያሉ፡፡
በትርዒቱ የቀረቡ አብዛኛዎቹ ሥራዎች ሙከራዊ (experimental) ቢሆኑም የአካዳሚክ (የሥዕል ትምህርት) ህግጋትን ለመጣስ የሚፍጨረጨሩ ናቸው፡፡ ከመማርም አልፎ በሥራ ያዳበረውን የአሳሳል መንገዶች ካላፈረስኩ ብሎ መታገል፣ እብደትና ስካር ካልታከለበት በቀር መድፈር አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ ሠዓሊያን ይህን ድፍረት አጥተው ለተማሩት ትምህርት ብቻ እስረኛ ሆነው ቀርተዋል፡፡ በሥነ-ጥበቡም ሆነ በፍልስፍናው እመርታ ለማሳየት ሙከራ ወሳኝ ነው፡፡ ሠዓሊ ፍቅሩ ይህንኑ ነው እያደረገ ያለው፡፡ እየሞከረ፡፡ ሙከራውም አያሌ የዓለማችን ሠዓሊያን ከሞከሩት የተለየ አይደለም፡፡ አሜሪካዊው ሠዓሊ ዊሊያም ደኩኒንግን ማንሳት እንችላለን፡፡
የፍቅሩ ሙከራ ማፍረስ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የሚሰራቸውን ምስሎች እያጠፋ አንዳች ሥነ-ጥበባዊ ፋይዳ ለማግኘት ነው እየተጋ ያለ የሚመስለው፡፡ በዚህ ከቀጠለም ያለፈባቸውንና በስራዎቹ ይስተዋሉ ከነበሩ ተፅዕኖዎች ከመላቀቅና ነፃ ከማውጣትም ባሻገር እንደ ድግምት ከሚደጋግመው “ፍቅሩ”ነቱ ሲጎነጩት እሚያረካ ጣዕም ሊቸረን ይችላል፡፡ ይህን ትጋት ወደ አንድ ጥበባዊና ሰብዓዊ አላማ የማዞር ኃላፊነት እንዳለበትም የሚዘነጋው አይመስለኝም፡፡ ጥበብ ሃቀኝነትን ትሻለች፡፡ በሃቀኝነት የሚከወን ጥበብ፣ከሠዓሊው ባሻገር ሃገርን፣ዓለምንና ሰብዓዊነትን ያገለግላል፡፡ በዚህ ትርዒት የቀረቡ ሥራዎች ይህን ታላቅ ኃላፊነትና ዓላማ ለማሳኪያ በር ከፋች አድርጌ ብወስዳቸው እመርጣለሁ፡፡ ሠዓሊው ጊዜውን፣አትኩሮቱንና እድሜውን ሙሉ ሲለፋለት በኖረለት ሥነ-ጥበብ ውስጥም አንዳች ፋይዳ ከመፈለጉና … ይህን ፍላጎት ክብር መስጠት አስፈላጊ ሆኑ በማግኘቴ ይበል ከማለት ውጪ መጨረሻውን ለመተንበይ እንኳንስ እኔ ሠዓሊውም የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡
 ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም ተማሪ በነበረበት ጊዜና ተመርቆ ከወጣም በኋላ የት/ቤቱ አስተማሪዎችም ሆኑ የሀገራችን ግንባር ቀደም ሠዓልያን ክሂሎት ላይ የተመረኮዘ የአሳሳል መንገድን ሲያቀነቅኑ ነው የኖሩት፡፡ ሠዓሊ ፍቅሩና በዚህ ትውልድ ውስጥ ያለፉ አብዛኞቹ ሠዓልያኖቻችን፣ይህን ዘፈን ሲያዜሙም ነው የኖሩት፡፡ በእርግጥ የዜማው ጥዑምነት ያማልላል ነፍስንም ይገዛል፡፡ ብዙ አቅም ያላቸው ነገር ግን የዜማውን ጥዑምነት ብቻ እያጣጣሙና እየነሆለሉ በዚያውም የዓለምና የዘመኑ የሥነ-ጥበብ ኮቴ እያሰማና እየፈጠረ ያለውን ንቅናቄ ማዳመጥ ተስኖአቸው በዚያው የጠፉና የቀሰሙ እንዲሁም በዚሁ አዘቅጥ ውስጥ ያሉ ሠዓሊያኖቻችንም አያሌ ናቸው፡፡ አዲሱን፣ዘመንኛውን፣ የዘመኑንና የአለምን የቅርብ ጊዜ ወይም ለእኛ አውድ “መጤ” የሆነውን የሥነ-ጥበብ ኮቴ ለመስማት ብለውም ለቀደመው ጥዑሙ ዜማ ጆሮና ሁለመናቸውን ደፍነው ያሉበት እስኪጠፋቸው እየተደናበሩ ያሉትንም  የስዕል ስቱዲዮ  ይቁጠራቸው፡፡ የወቅቱ የሀገራችን ሥነ-ጥበብ መመለስ ከሚገባው ጥያቄዎች አንዱም ይሄኛው ይመስለኛል፡፡ ሚዛን መጠበቅ አልያም ሚዛን መድፋት የሚችለውንም በጊዜ ሂደት የምናየው ይሆናል፡፡
ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም በሥነ-ጥበብ ት/ቤት ቆይታው ክሂሎቱን ሲያዳብር ለመቆየቱና በስቱዲዮ ሠዓሊነት ባሳለፋቸው ዓመታት የተማረውን ክሂሎት ሥዕል ለመስራት ሲጠቀምበት ለመቆየቱም አንዳች ጥርጣሬ የለኝም፡፡ የዳበረ ክሂሎቱን ብቻም ሳይሆን በት/ቤት ቆይታው በእሳት የተጠመቀባቸው እስኪመስል የተጣቡት የእነ ፒካሶና ጉጌይን ተፅዕኖዎች፤ በፍቅር ያንበረከከውና እንደ ድርሳን ለዓመታት ሲደጋግመው የኖረው የመምህሩና የሃገራችን ታላቁ ሠዓሊ የታደሰ መስፍን ተፅዕኖ በስራዎቹ ለዓመታት መታየታቸው የእርግጠኝነቴ መሰረቶች ናቸው፡፡ ተፅዕኖቹ በአካዳሚክ ህይወቱና በመስራት ልምዱ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ከመስራትም ደጋግሞ በመስራት፡፡ እነዚህ ሁለት ተፅዕኖዎች መልካም ጎኖች እንዳሏቸውም ልብ ማለት ይኖርብናል፡፡ የመጀመሪያው ገንዘብና እውቅና፡፡ የሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም የሥነ-ጥበብ ልምምድ (practice) በትጋት የተሞላ ነው፡፡ ያለማቋረጥ ይሰራል፤ከዚህም ባሻገር ልፋቱ ተገቢው ቦታ ክብርና ዋጋ እንዲያገኝም ይለፋል፡፡ መሳል ብቻ ሳይሆን ሥራውን ለማስተዋወቅ ይጥራል፡፡ በዚህም የሀገራችን የሥነ-ጥበብ እንቅስቃሴ “ሙት” እንደሆነ ገና ድሮ ገብቶት የሚያገኛቸውን እድሎች ሁሉ እንደ መሰላል እየተጠቀመ፣ ሥራዎቹን ሞቅ ያለ የሥነ-ጥበብ እንቅስቃሴ ባላቸው የዓለማችን ሀገራት ጋለሪዎች ሙዚየሞችና አጋፋሪዎች ዘንድ ለማድረስ ቀና ደፋ ሲል ብዙ ተንከራቶ ተሳክቶለትማል፡፡  ገንዘብንና እውቅናንም በዓለም አቀፍ ደረጃ አግኝቷል፡፡ ተፅዕኖዎቹ ጠንካራ መሰረት ባይኖራቸው ማንኛውም ጋለሪ ሙዚየምና ኪዩሬተር ፊት እንደነሱት ነበር የሚኖረው፡፡ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃም ላይበቃ ይችል ነበር፡፡ እነ ፒካሶና ጎጌይን የሰሩት ለዓለምና ለሃገራቸው አሁንም ድረስ ቤዛ እየሆነ ነው፡፡ ታደሰ መስፍንም ለሠዓሊ ፍቅሩ በቀጥተኛ መልኩ፣ ከሰላሳ ሶስት ዓመታት በላይ ለአስተማረበት ት/ቤትና ተማሪዎቹ በተለያየ መልኩ፣ለሀገራችን ሥነ-ጥበብ ደግሞ በጥቅሉ ቤዛ ነው፡፡
ሠዓሊ ታደሰ መስፍን እንደ “እድር አህያ” አንዴ በማስተማር፣ በሌላ ጊዜያት የስብሰባዎች ናዳ ሀገሪቱን ያሻሽሏት ይመስል እዚህም እዚያም በሚካሄዱት ስብሰባዎች ሲዶል በስቱዲዮው ጊዜ ለማሳለፍና ለመስራት መላ መምታት ተስኖት፣ በዘመናት ያዳበረውን ሥነ-ጥበባዊ እርምጃ አንድ ቦታ ማድረስ ቢሳነውም፤ ተማሪው የነበረው ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም ተፅዕኖው አርፎበት የተጀመረውን ለማስቀጠል እንኳን ባይሆን እንደ መሻገሪያ ተጠቅሞት ሊያተርፍበት ችሏል፡፡  ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም የተጠመቀባቸውና የተንበረከከባቸው እነዚህ ሁለት ተፅዕኖዎች፣ገንዘብና እውቅናን እንዲሸምትባቸው ከማስቻላቸውም በላይ አብዛኛው ሠዓሊ ስራውን ለመቀጠል ተግዳሮት ከሚሆንበት የገንዘብ  ጥያቄ ነፃነት አግኝቶ ስራውን በረጋና በነፃነት መንፈስ እንዲሰራ አስችሎታል ወይም ሊሰራ እንዲችል ምቹ ሁኔታ እየፈጠረለት ነው ባይ ነኝ፡፡
የተፅዕኖዎቹ ዳና በድግግሞሽ፤ አሊያም በመስልቸት፤ “አዲስ” ነገር ለመፈለግ እንዲነሳሳ፣ የተፅዕኖዎቹን ዳና ለማጥፋት የራሱ ብቻ ወደሆነ ዳና እንዲመጣ በማድረግ አቀጣጣይ፣ አነሳሽ ወይም ደግሞ አናዳጅ ሀይል መሆን ሁለተኛው ተፅዕኖቹ የተፈጠሩለት መልካም ጎን ይመስለኛል፡፡ ከላይ ስለዘረዘርኩት የአንደኛው ተፅዕኖ ምክንያታዊነት ሰዓሊው ፍቅሩ ገ/ማርያም ራሱ፣ሌሎች ሠዓሊያንና የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም አንባቢ ሊስማማበትም ሆነ ላይስማማበትም ይችላል፡፡ እንደው የቀደሙ ሥራዎቹ ከማንኛውም ተፅዕኖ የፀዱ ናቸው ተብሎ ቢካድ እንኳን ለዓመታት የተማረው ትምህርት በሠዓሊነቱ ላይ ተጽዕኖ ከማሳደሩም በላይ አሁንም ከተጽዕኖው ለመላቀቅ የሚያደርገው ጥረት ላይ ማነቆ እየሆነበት እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡
ትርዒቱን ታድሜ ከገጠሙኝና ልጠቅሳቸው ከምፈልጋቸው ሁነቶች መሃል እንካችሁ፡-
“እንትን ያለው ልጅ”፤ ትርዒቱን ታድመው የነበሩ አንድ ትልቅ ሰው ናቸው አሉ “ከእስክንድር በኋላ እንትን ያለው ሰዓሊ ተገኘ” ሲሉ የተደመጡት፡፡
አባባሉ “እንትን” ያላቸው ሠዓሊያንና እንትናቸው የሚያዝና ዘር የሚዘራ፤ እየዘራም ያለ ሠዓሊያን በሞሉባት ሀገር፣ ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም እኔ ብቻ ነኝ “እንትናም” ብሎ እንዲያስብ በር ከፋች ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን ሠዓሊው ፍቅሩ፤እኔ ብቻ ነኝ “እንትናም” ብሎ ያስብ… ግን እሳቸው የሌሎችን ሠዓሊያኖቻችንን እንትን ማየት አልቻሉምና ባለ እንትናም እሱ ብቻ ነው?
የተመልካች አስተያየቶች፡- የብሔራዊ ሙዝየም ታዳሚያን ብዙዎቹ ትርዒቱን ዘልፈውታል፣ ሰድበውታል፣ አነፃፅረውም ዋጋ ቢስ አድርገውታል፡፡ ሥዕል መመልከት፣ ልምምድ ዕውቀት ቢጠይቅም ከሚታየው ሥራ ጋር ስሜታዊና ሃሳባዊ ቁርኝት ይፈልጋል፡፡ የዕይታ ባህሉ ያልዳበረ የማህበረሰብ ክፍል ትርዒቱን ሲመለከት ምንም ስሜት ባይሰጠው፣ ሃሳብ ባይገለጥለትና የሆነ ዘባተሎ ነገር ቢሆንበት ሊገረም ወይም በሰዓሊው ሊናደድ አይገባም፡፡
ጎበዝ የሆነ ተመልካች ራሱን ይጠይቃል-፤ካልሆነም እርዳታ ይጠይቃል- ይህም ካልተሳካ አይተወውም? ምን አስጨነቀው? በእርግጥ አጥብቆ ጠያቂ፣ የእናቱን ሞት ሊረዳ ቢችልም መዳኗንም ሊበሰር ይችላል፡፡

Read 1328 times