Monday, 03 July 2023 09:25

እኔ፣ እሷና የቃላት ፍቅር

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(9 votes)


ታሪኩ እንደዚህ ነው። በትናንሽ ህይወት መሳይ የቃላት ቅብብሎሽ… በትናንሽ ቅፅበቶች… በአይኖች ውስጥ ጨዋታ አምለሰትን ተዋወቅኳት። እውቀት በማያሻው የመግባባት አለም ውስጥ ፍቅር ተፀነሰ። የምሯን ወዳኝ እኔ በተራዬ እስክናፍቃት ድረስ አቆየችኝ። አስተውላ እያዳመጠችኝ ደካማውንም ጠንካራውንም ጎኔን መርምራ ደረሰችባቸው። ስተነፍስ እንዳስታውሳት አድርጋ ራሷን ራሴ ውስጥ ፈጠረችው።
አንድ ቀን።
አልጋ ውስጥ ሆና…
ሁሌም እንደምናደርገው ከእኔ ጋር አድራ በበነጋታው ልሸኛት ከአልጋ ልነሳ ስል ፊቷን ትራሱ ውስጥ ቀብራ ይህን አለች…
“አትነሳ?”
ትዝ ይለኛል ግራ ስጋባ። ትዝ ይለኛል በትራሱ መሀል ጭንቅላትዋን ቀብራ ሀፍረቷን ሸሽጋ እውነቷንስ ትናገር። ትዝ ይለኛል አንድ ቃል አንድ ሙሉ ህይወት መስራት እንደሚችል እርግጠኛ ስታደርገኝ። አሁን እዛው ቦታ ላይ ነኝ። ከጎኔ የአምለሰትን የዛን ቀን የፍቅር ትንፋሽ ሰግስጎ የያዘውን ትራስ እያየሁ… ለራሴ ምንም ሳልለው።
አትነሳ አለች።
“ለምን?” አላልኳትም።
አምለሰት ጥያቄ አትወድም። መውደድ እና ፀጥ ማለት ነው የሚቀናት።
ከቆይታ በኋላ ከትራሱ ውስጥ ወጥታ በፀጥታ ስታየኝ ከቆየች በኋላ አሁንም ይህን ተናገረች…
“ከዚህ በኋላ ከዚህ ቤት መውጣ አልፈልግም። ከፈለክ እቃዎቼን እራስህ ከቤቴ አምጣልኝ ከዚህ በኋላ ካንተ ርቆ መቀመጡን፣ መተኛቱን፣ መብላቱን፣ መኖሩን አልፈልገውም።”
ቃልኪዳን በሚገቡ አይኖቿ ቃል ገባችልኝ። አሁንም እኔ እዛ አልጋ ውስጥ ነው ያለሁት። አምለሰት ግን የለችም።
* * *
ደራሲ ነኝ። አምለሰትን የመሰለች ውበት፣… ፈጣሪ ቃላት ሳይጠቀም በፀጥታው ውስጥ ያገኛት፣ ከሰው ነፍስ ፈቀቅ አድርጎ መለኮታዊ ድባብ የደረበባት… እንዲያውም ስለውበቷ እናገራለሁ ብዬ አምላኬን ከማስቆጣ ቢቀርብኝ ይሻላል። ደራሲ ነኝ። አምለሰትን የመሰለች ሴት እንዳሻት የፈለገችውን እየገዛሁና እያበቀልኩ የማኖርበት አቅም እንደሌለኝ እኔም እሷም እናውቀዋለን። እናም አንድ ቀን ላስጠነቅቃት አስቤ…
አቤት ያ ቀን…
ከምንወደው የየካ ተራራ ጫካ ውስጥ ጸጥታን ልናደምጥ በተቀመጥንበት በአንዱ ቀን። አምለሰት ከጎኔ ተነስታ በርቀት የሚተራመሰውን ህዝብ እያየች አሁንም ይህን ተናገረች…
“መች ይሆን ከዚህ ሁሉ ትርምስ ነፍሳችን አርፋ ያለምንም ንትርክ በሰላምና በፀጥታ መኖር የምንችለው፣ እኔና አንተ ብቻ?”
ዞራ ስታየኝ ሁሌም የምደነግጠው ነገር እስካሁን አይገባኝም። መልስ ከኔ እየጠበቀች አልነበረም። መልሶቼ ሁሌም አይኖቼ ላይ ናቸው። አምለሰት ተመልክታኝ ሀዘን ባጠላበት ስሜት ውስጥ ሆና…
“ለምንድነው ሁሌ አብረን መኖር እንደማንችል አድርገህ የምታስበው? የትኛው ድፍረትህ ነው እሷን ካዳትና ወደ ጫጫታው አለም ካልተቀላቀልክ የሚልህ?”
“አምለሰት?” አልኳት። ሁሌም ስሟን ስጠራት ደስ ይላታል።
“ስሜ ከድምፅህ ጋር አብሮ ተሰፍቶ የተወለደ ነው የሚመስለኝ” ትለኛለች።
“አምለሰት… አሁን የማስበውን የሚያሳስበኝ ድረስ ተጉዘሽ ማሳካት አለብሽ። መሳቅ አለብሽ። በሀሳብሽ ያሰብሽውን እንደምታደርጊው እርግጠኛ መሆን አለብሽ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች መልክ መያዝ የሚችሉት የተሻለ ቦታ ላይ ራስሽን ስታገኚው ነው።… ብዙ ብዙ ነገሮች በምድር ላይ ላንቺ ተፈጥረዋል። ሁሉም የሚገቡሽ ሆነው ነው የተፈጠሩልሽ… እኔ ደግሞ…”
አቋረጠችኝ።
ፊቷን አዞረችብኝ።
ምን ልላት እንደፈለኩ ገብቷታል።
እንዴት አድርጌ ልወዳት እና ልርቃት እንደፈለኩ ተረድታለች። እኔን ሆናችሁ ፍረዱኝ። የምትወዱትን ሰው ማሰቃየት ይሆንላችኋል? ታዲያ እንዴት አምለሰትን ትተዋታለህ ትሉኛላችሁ? አዎ ውብ እና ውብ ብቻ ናት… አዎ ነፍስ ያላት ሆና ነፍሳቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ቀዳደው ለጣሉት መልስ ሆና የመጣች ናት…
አዎ ሳልናገር ታደምጠኛለች። አዎ ሳትናገር የአይኖችዋን የሽፋሽፍት እንቅስቃሴ ብቻ ተመልክቼ ምን ልትለኝ እንደሆነ አውቅባታለሁ። አዎ ይህን ሁላ እና ብዙ ህይወቶች ናት - አምለሰት።
እና የዛን ቀን አብረን መኖር ያልቻልነው ደራሲ ብቻ እና ብር የሌለኝ መናጢ ደሃ በመሆኔ እንደሆነ ልነግራት ነበር ከዛ ውብ ስፍራ የወሰድኳት። ሆኖም አምለሰት ለወራት ስዘጋጅባቸው የነበሩትን ቃላት አይኖቼ ላይ ተስለው ስትመለከት ሁሉም ነገር በቅፅበት ውስጥ ገባት። ሲገባት ደግሞ እንዴት እንደምታምር አልናገር።
የዛን ቀን ምንም ሳንነጋገር ቤት ሄድን። ምንም ሳንነጋገር አልጋችን ውስጥ ገባን። ምንም ሳንነጋገር በከንፈሮቻችን መሳሳም ሀዘናችንን ተነጋገርን። ብዙ የከንፈር ወጎች አወጋን። እንደምንዋደድ ሁለታችንም እናውቃለን። አብረን መኖር ግን እንደማንችል የገባኝ እኔ ብቻ ነበርኩ።
ጠዋት ስነቃ አምለሰት ካጠገቤ የለችም። ልብሶቿ ግን በሙሉ አሉ። ምሽት ላይ ሰክሬ ወደ ቤቴ በገባሁ ቁጥር እነዛን ልብሶች አልጋዬ ላይ በታትኜ እተኛባቸዋለሁ። ይህን እና ሌሎች ብዙ እብደቶችን ማበድ ከጀመርኩ አሁን ሶስት አመታት ተቆጥረዋል። በነዚህ ሶስት አመታት ውስጥ ከሶስት ጋዜጦች ውጭ ፅሁፌ የትም አላደረሰኝም። የቃላቴን ቅኝት የተረዳልኝ የሰው ዘርም በአጠገቤ የለም።
የቃላት ጫካ ውስጥ ብቻዬን የምሳከር ተራ የነፍስ መናኝ ደራሲ መሆኔን… የሰውን ስሜትና ታሪክ በአይኔና በጆሮዬ እየሰገሰግኩ እንዲሁ የምባክን ተራ ግለሰብ መሆኔን... እኔ የማስበው የፋንታሲ አለም እና ፊት ለፊቴ ያለው ደረቁ አለም በምንም ስሌት አብረው መሄድ እንደማይችሉ እና በገዛ ሀሳቤ ውስጥ ተዘፍቄ በእውቀት ትንፋሽ ውስጥ ብቻ የምመላለስ የህልም አድባር ብቻ መሆኔን የተረዳሁት አሁን እናንተ ይህን ፅሁፍ ማንበብ የጀመራችሁበት ሰዓት ላይ ነው።
አሁን…
ይሄ ያለንበት ቅፅበት ላይ…
ከፊት ለፊቴ ለአምስት አመታት ሳላቋርጥ የፃፍኳቸው ፅሁፎች በስነ ስርዓት ተደርድረው ተቀምጠዋል።
ዛሬ…
አሁን…
አንስቼ ከቦርሳዬ ውስጥ ከትተኳቸው።
እያንዳንዱ የጥራዝ ቅጠልና ገፅ አምለሰትን ሳላያት ያሳለፍኩዋቸውን ቀናት በቁጥር ይነግሩኛል። አብረው ሆነው ወፍረው ሳያቸው ስሜት ወደ ማይሽረው ፍቅር እንዳልደርስ ተጭነውኝ የከረሙ አለቶች ይታዩኛል። ውሉ ቅጡ የማይታወቅ ህይወት ውስጥ ሰቅዘው የከተቱኝ ድካሞቼ ናቸው። እነሱ ካልጠፉ አምለሰትን ላገኛት አልችልም። ወይ እነሱ ወይ እኔ አንዳችን እንጠፋለን።
አዎ አልተሳሳትኩም። በቃላት የሰበርኩትን ልብ መልሼ በቃላት ማከም አለብኝ። አሁን ግን ቃላት ዘርቼባት ህይወት እንደሰጠኃት ቃላቴን ገድዬ እንደገና የኔ አደርጋታለሁ። በደንብ ነው የሰማችሁኝ …ቃላቴን ገድዬ መልሼ የኔ አደርጋታለሁ ነው እያልኩ ያለሁት።
የምትኖርበትን ቤት አውቀዋለሁ። እኔ ነኝ ቤት ቀይሬ የጠፋሁባት። እንደምትወደኝ አውቃለሁ። እኔ ነኝ መውደዷን እንደ ባለመብት ከህሊናዋ ውስጥ የሰወርኩባት።
በቃላት የደለበውን ወረቀት ዋጋውን ሰጥቼው የኔ የምላትን… አምለሰቴን እመልሳታለሁ።
መለያየት እንዳለብን በአይኔ ብቻ የነገርኳት ቦታ ጋ ቆሜ ወረቀቶቹን ከፊቴ ከመርኳቸው። ከኪሴ ውስጥ …
ምንም ከማድረጌ በፊት ግን አንድ ጊዜ እናንተን… የመጨረሻዎቹ አንባቢዎቼን ልጠይቃችሁ። ከዚህ የቃላት ወረርሽኝ ማምለጥ የለብኝም ትላላችሁ? ሰው እና ህይወት አያስፈልገኝም ትላላችሁ? ፍቅር ብቻ የሚሰብክ ትንፋሽ ከተኛሁበት እንዲያነቃኝ ሆኜ የተፈጠርኩ ሰው አይደለሁምን? ከመለኮሴ እና ቃላቴን ከመማገዴ በፊት ንገሩኝ?
ጭንቅላቱ በኑሮ… ህሊናው በማይዳሰስ ተስፋ… ፈገግታው የተውሶ የሆነ… ጥሙ ዝሙትና ሱሱ ብቻ የሆኑበት… አላማው የሰዎች አላማ ውስጥ ተሰውሮበት የማንነት ቀውስ ውስጥ ያለ ምስኪን ማህበረሰብ ውስጥ ሰበካዬን እና እብደቴን ካልሰማህ ብዬ እድሜዬን አብሬያቸው ባወድም ይሻለኛል ወይስ ከአምለሰት ጋር… ገብቶኛል።
እኔም ቀጥሎ ያለውን ሳልናገር በዝግታ ለኩሼ ወረቀቶቼ ላይ ወረወርኩት። የእድሜ ዘመን ሀሳቤን… በአምለሰት መገፋት ምክንያት ለአመታት ስተረትራቸው የነበሩት ቃላት በወላፈን ሲጨሱ ሲከስሉ አመድ ሲሆኑ አየሁ። የተፈጠረብኝ ህመም ለመናገር የሚችል አቅም ላይ አይደለሁም። ሆኖም አሁን ላይ ቆሜ ማንነቴን ነው ያቃጠልኩት ማለት እችላለሁ።
አምለሰት ገና ስንተዋወቅ ደራሲ መሆኔን አምናልኝ ለልደቴ ብዕር ሰጥታኝ ነበር - በሚያምር ሳጥ ውስጥ። ብዕር አዝሎ የመጣው የሚያምር ሳጥን ውስጥ የተቃጠለውን ወረቀት፣ የቃላት ቅሪት አመዱን ከትቼ፤ ከሚያምረው የቤተሰቦቿ ቤት ፊት ለፊት ቆሚያለሁ። በሩን እንዴት ማንኳኳት እንዳለብኝ አላወቅኩም። ሆኖም ማንኳኳት አለብኝ። በሩን ደግሞ አምለሰት ትከፍተዋለች። አይኖቿን ሳያቸው መናገር ያቅተኝና እግሮቿ ስር እወድቃለሁ። የሰበሰብኩትን አመድ ስሰጣት፣ ከእስሬ እንደተፈታሁ ትነግረኛለች። ይህን ለማድረግ ብዙ ተጉዣለሁ። አሁን አሁንን ወልዶ አሁን ላይ አድርሶኛል።
በሩን አንኳኳሁ…
ደገምኩት…
ደገምኩት…
ከቆይታ በኋላ አንዲት ቆንጂዬ ህፃን ልጅ መጥታ በሩን ከፈተችልኝ።
“ሚጣዬ አምለሰት አለች?” ብዬ ጠየኳት።
መልስ ሳትሰጠኝ አተኩራ ተመለከተችኝ። ደግሜ ልጠይቃት ስል አንድ ፈርጠም ያለ …በእድሜ ጠና ያለ መልከመልካም… አይቼው የማላውቅ ወንድ መጥቶ ህፃኗን ልጅ ከበሩ ነጥሎ ወደ እሱ እየሰበሰባት፣ እኔን ግራ በመጋባት እያየ ጠየቀኝ።
“ማንን ፈልገህ ነው?”
ድንገት መናገር አቃተኝ። አይኖቼን ብቻ አይቶ አምለሰትን እንደምፈልግ ማወቅ ነበረበት።
“አምለሰት ትኖራለች?”
ምንም እንዳላማርኩት እንዲሁ ይታወቀኛል።
ሆኖም ጠራልኝ… ድምፁን ከፍ አድርጎ ያንን ስም ተጣራ…
“አምለሰት”… ብሎ።
አምለሰት ገርበብ ያለውን በር ከፍታ ወጣች። እንዳየችኝ… እንዳየችኝ…
“ኢዛና…” ብላ በሀይል ተጣራች። ፊቷ ላይ ፍርሀት… ደስታ… አድናቆት… ፍርሀት… ጥበቃ… እነዚህ ሁሉ የፊቷ ገፅ ላይ በአንድ ጊዜ መነበብ ጀመሩ። ኢዛና የተባለው ሰው በቅርብ ርቀት ቆሞ ስለነበር በር የከፈተችልኝን ህፃን አቅፎ ከተፍ አለ። አምለሰት ተናገረች።
“ስልህ የነበረው ልጅ እሱ ነው”
ኢዛና ከላይ እስከታች አይቶኝ… “ደራሲው ያልሺኝ ልጅ ነው?”
አምለሰት እኔን ሳይሆን እሱን በጉጉት እያየችው መለሰችለት።
“አዎ እሱ ራሱ ነው”
እሷ ሳትሆን እሱ… ኢዛና ይህን ተናገረኝ…
“እንዲሁ ሳይህ ደራሲ ነበር የመሰልከኝ ለነገሩ።
“ይሄው አምለሰት ከተዋወቅን ጀምሮ አንድ ደራሲ አለ፤ በጣም እውቀት ያለው፤ መፅሀፉን ማንም ሳይቀድመን እኛ ነን ማሳተም ያለብን ብላ ስትጨቀጭቀኝ ነው የከረመችው። እንኳን መጣህላት።”
ዞሬ አምለሰትን አየኋት። አይኖቿ ሞተዋል… ዝቅ ብዬ ጣቶቿን ተመለከትኩ… ቀለበት አስራለች። ሁለታችንም ግዳያችንን በጣቶቻችን ይዘን ተገናኘን። ነፍሴ ውስጥ የአምለሰት ነፍስ ስትሞት ሰማኋት። እዛች ቅፅበት ላይ።
መፅሀፌን ልታሳትምልኝ ስታፈላልገኝ ነበር።
እኔ ደግሞ መፅሀፌን ገድዬ ከነፍሷ ላይ ልታተም ነበር የመጣሁት።
ሙሉ ቤተሰብ ሆና ጠበቀችኝ።
ሙሉ።
እየሳቀች…
ለካ አምለሰት እዚህ ድረስ ቃላቴን ታምናቸው ነበር። ለካ ቃላት አይሞቱም። ማደሪያቸውም የሰው አዕምሮ ውስጥ ብቻ ነው።
* * *
የዛን ቀን ለሁለቱም መልስ ሳልሰጥ እንደአበደ ሰው እየጠሩኝ ሮጬ አመለጥኳቸው።
ሆኖም አሁን ሳስበው ይህ ቅፅበት አሁን ላለሁበት የመነቃቃት መንፈስ መፍትሄ ሆኖኛል። እፅፋለሁ… እንደአምለሰት እምነት እና እንዲህ አድርጎ እንደፈጠረኝ ፈጣሪዬ ለማሰብ እየሞከርኩ እፅፋለሁ። አንድ ቃል አንድ ሙሉ ህይወት ይሰራል። አንድ ቃል…

Read 922 times