ዳሰሳ - ዘነበ ወላ
ደራሲ - መኮንን ከተማ ይፍሩ
የመጽሐፍ ርእስ - ከተማ ይፍሩ
ገጽ - 280
ዋጋ - 480 ብር
አሳታሚ - ሻማ ቡክስ
የድሮውን ድንቅ ዲፕሎማት አቶ ከተማ ይፍሩን አውቃቸዋለሁ። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት በደግ የሚነሱ ሚኒስትር ነበሩ። እኛ ቤት ሬዲዮ ስለነበር በዚያን ዘመን በአየር ላይ ይለቀቅ የነበረውን ዜና እሰማለሁ፡፡ የሰማሁት ሁሉ ይገባኝ ማለት ግን አይደለም፡፡ አዋቂ ሰዎች ስለ ሚኒስትሩ የሚለቀቁ ዜናዎችን እያደመጡ አድንቀው ሲነጋገሩባቸው እሰማ ነበር፡፡ ከተማ ይፍሩ በርትተው በመማራቸው ጃንሆይ ትልቅ ቦታ እንዳደረሷቸው ደጋግመው ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡
ሬዲዮ እኛ ቤት ነበር ስል የዚህ ዘመን አንባቢ “ቢኖርስ ብርቅ ነው እንዴ ?” ይል ይሆናል። ከሃምሳ አመት በፊት በነበረች ኢትዮጵያ ውስጥ ሬዲዮ አንድ ቤተሰብ ውስጥ መገኘት አዎን ብርቅ ነበር። በመቶ ቤት አልፈህ የሬዲዮ ድምጽ ከሰማህ አንድም የነጋዴ ቤት አሊያም ኮርያ ዘምቶ የመጣ ወታደር ቤት ነው። ወይም ደግሞ የዘመኑ መኳንንት ቤት ሊሆን ይችላል። ሸማኔው አቶ ወላ ወጋ እቁብ ጠጥቶ እጣው ሲደርሰው የገዛው ኦርጂናሌ ሬዲዮ ነበረው፡፡
በዚህም የተነሳ ስለ ጃንሆይ፣ ስለ ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ አቶ ከተማ ይፍሩ ወዘተ እየሰማሁ ነው ያደኩት። የጋዜጠኝነት ዓለም ውስጥ ከገባሁ በኋላ አንድ ቀን ከጋሼ ማሞ ውድነህ ጋር ስንወያይ፤ “የህይወት ታሪካቸው መጻፍ ነበረበት ብለው ሳይጻፍ በመቅረቱ የሚቆጭዎት ባለታሪክ አለ ወይ?” ብዬ ጠይቄአቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ሲመልሱ፤ “ጋሼ ከተማ የህይወት ታሪኩን ባለመጻፉ በጣም እቆጫለሁ። እንቀራረብ ስለነበር እንዲጽፍ አደራ ብዬው ነበር፤ ነገር ግን ሳይጽፍ አረፈ። ይህ በመሆኑ አዝኛለሁ፡፡!” ብለውኛል፡፡
ይህ ከተማ ይፍሩ የተሰኘው መጽሐፍ፣ ጋሼ ማሞ አፈር ከቀመሱ 11 ዓመታት በኋላ ነው ለንባብ የበቃው፡፡
ከግማሽ ምእተ አመት በኋላ የሆነውን ታሪክ ሳስታውስ፣ አቶ ከተማ የታሰሩት ላጭር ጊዜ ይመስለኝ ነበር፡፡ ጋሼ ማሞን እያሰብኩ መጽሐፉን ሳነበው ለዘጠኝ ዓመታት ታስረዋል። አልደነቀኝም፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን “ለአምስት ደቂቃ እንፈልግሃለን” ብለው ወስደዋቸው አምስት አመት አስረዋቸዋል፡፡ አቶ ከተማንም “ለዘጠኝ ደቂቃ እንፈልግሃለን “ ብለዋቸው ይሆናል የወሰዷቸው፣ ስል አስባለሁ። ለምን? ፕሮፌሰሩ ህይወት ላይ አንድ ደቂቃ አንድ አመት ወክላ አስተውያለሁ።
አቶ ከተማ የአፍሪካ አንድነት እንዲመሰረት፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ከተማ እንድትሆን ታላቅ ሚና ተጫውተዋል። የኤርትራ ችግርን የሚፈታ ድንቅ ጽሁፍ አዘጋጅተዋል። በእኔ እምነት፣ ይህ ወረቀት በወቅቱ ያለው መንግስት አምኖበት ከአማጺያኑ ጋር ተወያይቶበት ቢሆን ኖሮ፣ ያ ሁሉ ደም ሳይፈስ፣ ያ ሁሉ ገንዘብ፣ ንብረት ወዘተ ሳይወድም የተሻለች አገር በኖረን ነበር።
ከታህሳስ ግርግር መሪዎች ጋር አቶ ከተማ ሲወያዩ ስለ ሥር ነቀል ለውጥ አደገኝነት አንስተው ነበር፡፡ “ሥር ነቀል ለውጥ በአፍሪካ ፣በእስያ ፣ በመካከለኛውና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ፡- አገራቱን የከፋ ችግር ውስጥ ጥሏቸዋል” ሲሉ ነግረዋቸው ነበር፡፡ እነ ገርማሜ “ጆሮ ዳባ ልበስ” በማለታቸው፣ መጨረሻው በታሪክ የሆነው ሆነ።
በወቅቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ኮሪ፣ ለምእራባውያን ፖሊሲ ታላቅ እንቅፋት አድርገው ይቆጥሯቸው የነበረው አቶ ከተማ ይፍሩን ነው። የተበታተነች አፍሪካን እንዳሻቸው እንዳያደርጓት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሰረቱ፣ ወደፊት ፓን አፍሪካኒዝም መመሥረት አላማቸው ነው። ንጉሰ ነገሥቱን ተናግሮ ምንም ከማይሆኑት አንዱ ናቸው። የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ከንጉሡ እጅ ወጥቶ ከተማ እጅ ገብቷል። ወዘተ እያሉ ይብከነከናሉ።
አሜሪካ የጦር መሳሪያ ለኢትዮጵያ መቸሩን ስታቆም፣ አቶ ከተማ በምስጢር ከእስራኤል ጋር ተነጋግረው ሠራዊቱን አስታጥቀዋል። ይህ ሁሉ ምእራባውያንን ያበሳጫቸዋል። የእነሱ ፍላጎት ቀጥ ለጥ ብላ ለምእራቡ ዓለም ፖሊሲ የምትገዛ አገር መፍጠር ነው። ይህንን በ1960ዎቹ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትን ሄኒሪ ኪሲንጀር ወጥነው የጊዜው ፕሬዚዳንት የነበሩት ሪቻርድ ኒክሰን ይሁንታ አግኝቶ የሄዱበትን መንገድ ማስተዋል ነው። ውጥኑ አገራችንን በዘር፣ በሃይማኖት ማእበል በማተራመስ ... ደካማ ኢትዮጵያ መፍጠር ነበር ... ከዚያ መሪዎቻችን ሲጠሩ አቤት፣ ሲላኩ ወዴት? እንዲሉ ማድረግ ነበር። ትርምሱንም አብዮተኞቹ አሳምረው ሰሩላቸው።
አቶ ከተማ በሪፎርም ነው የሚያምነኑት። ይህ ደግሞ ለአብዮተኞች አይጥማቸውም። እነርሱ ስር ነቀል ነው የሚፈልጉት፡፡ አብረናቸው ከአብዮተኞቹ ጋር ኖረን እንዳስተዋልነው ስር ነቅለው የሚተክሉት ስር የላቸውም። ባለፉት ሃምሣ አመታት የሄድነውን ታሪካዊ ሂደት ብቻ ማስተዋል ይበቃል። አንድ ምሳሌ በመስጠት ጉዳዩን ላስረዳ፡፡ በ1966 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ሥርዓትን እንዲናድ ያደረገው 250ሺ የወሎን ህዝብ አስራባችሁ ተብሎ ነው። ይሁን እንጂ አብዮተኞቹ ለረሃቡ መፍትሄ ሳያገኙለት ቀርቶ በደርግ ዘመነ መንግስት 8 ሚሊዮን ሕዝብ ሲራብ፣ ”የአየር መዛባት !” የሚል ስም ወጣለት። ከኢሠፓ ምስረታም ጋር ተገጣጥሞ እንዲደበቅ ተደረገ። የሚገርመው ታላቁ ቤተ መንግስት ዋናው በር ላይ “አድሀሪን ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮንም በቁጥጥራችን ሥር እናደርጋለን !” የሚል መፈክር ተሰቅሎ ይታይ ነበር። ሥርአቱ እስኪገረሰስ ድረስም እንደተሰቀለ ነበር። አሁን ደግሞ በስለን አንብበን ተፈጥሮን ስናስተውላት፣ አይደለም የኢትዮጵያ አቅም፣ የአሜሪካንም አቅም “ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር ማድረግ” እንደማይችል ተረድተናል።
ዘመነ ኢህአዴግ ላይ ስንመጣ ረሃብተኛው 11 ሚሊዮን ደረሰ። ይህንን ዘግናኝ ዜና መንግስት በፍጥነት ለመጽዋቾቻችን በማስታወቁ ረሃብተኛው ተረፈ። በዚህ ዘመን ባለፉት ወራት ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንዳነበብኩት፣ ረሃብተኛው 20 ሚ. 400 ሺ ደርሷል። በሌላ አባባል፣ ከአምስት ኢትዮጵያዊያን አንዱ የምር ይርበዋል ማለት ነው። ስለዚህ የአብዮተኞቹ ስር ነቀል ለውጥ መፍትሄ አልሆነም።
በአንድ ወቅት የአሜሪካ የወቅቱ አምባሳደር ኮሪ፣ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ጀነራል መርእድ መንገሻ ጋር ሲነጋገሩ፤ “እናንተን (ኢትዮጵያን) በካርታው ላይ ያስቀመጥናችሁ እኛ ነን፤ ከካርታው ላይ ልናስወግዳችሁ እንችል!” ነበር ብለዋቸዋል።(ገጽ 182)
አዎን በፋሽት ወረራ ወቅት በመጨረሻው ሰአት ታላቋ ብሪታንያ አግዛን ፋሽስት ኢጣሊያን ከአገራችን አስወጥተንናል። በነገራችን ላይ እንግሊዝ ባታግዘንም አባቶቻችን ጥሊያንን ይዘግይ እንጂ ያሽንፉት ነበር። ምክንያቱም የቤኒቶ ሞሶሎኒ መሰረት ተናግቷል። በ1933 ዓ.ም ከአባቶቻችን እናቶቻችን ጋር በድል አድራጊነት ወደ መናገሻ ከተማችን አብሯቸው ገብቶ የነበረው የእንግሊዝ ጦር፣ በሞግዚትነት እያስተዳደረ 14 ዓመታት ቆየ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዲ. ሩዝቬልት ጋር ቀይ ባህር ላይ ተገናኝተው ለ15 ደቂቃ በፈረንሳይኛ ተነጋገሩና ብረት የሆነውን የእንግሊዝ እጅ ገለል አደረጉልን። ይህንን ወቅት አስበው ይሆናል ከላይ የጠቀስኳቸው ሚስተር አምባሳደር ኮሪ የተናገሩት። ይሁን እንጂ እንደ እኔ እምነት፣ ኢትዮጵያዊያንን አያውቋቸውም እና ይቅር ብያቸዋለሁ፡፡
አቶ ከተማ የምእራባውያንን መንገድ ሲያደናቅፉ፣ እነ ፓትሪስ ሉሙባ ላይ ምን አይነት ጭካኔ እንደደረሰ ያውቁትል። ይሁን እንጂ የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ስለሚያደላ፣ አቶ ከተማም በአገራቸው ጉዳይ አይደራደሩም። በጣም የሚያዝኑበት ነገር ቢኖር፣ ካቢኔው ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተሰብስበው የተወያዩበትን ጉዳይ ሳይውል ሳያድር የአሜሪካ አምባሳደር ሰምተውት ያድሩ ነበር። በዚህ እጅግ በጣም ያዝኑ ነበር። ከአገሩ ይልቅ ለባእድ ያደረ ምኒስትር መካከላቸው ነበር፡፡ ማነው ይህ ባንዳ?! አይታወቅም።
ጄኔራል መርእድ መንገሻ አቶ ከተማን የሚያውቋቸው በወጣትነታቸው ነው። ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ ጀኔራሉ ረድተዋቸዋል። ከተማም ምስጉን ተማሪ ሆነው የአገር ውስጡን አጠናቀው፣ ባህር ማዶ ተጉዘው በቅጡ ተምረዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን አንድም የአሜሪካ ተጽእኖ የለባቸውም። ከጀነራል መርድ መንገሻ ጋር ይህ አጋጣሚ አወዳጅቷቸው የሥራ ባልደረባም ሆነው ሲገናኙ የሆድ የሆዳቸውን ያወራሉ። በመጨረሻዋ እለት መኮንንኖች ክበብ ተገናኙ። ስለ “ሪፎርም” አወሩ። ማምሻውን ቤተ መንግሥት የካቢኔ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አቶ ከተማ ዘለቁ። ጃንሆይን እንዳገኙዋቸው “መርእድ ሞተ !” ሲሉ አረዷቸው። ይህንን ድራማ መስራት የሚችል መንግስት እንዴት የአሜሪካ ኤምባሲን ሰላይ ሳያውቀው ቀረ? ስል እጠይቃለሁ፡፡ ወይንስ ጀነራል መርድ የሞቱት የእግዜር ሞት ነው ? አሟሟታቸው ያመራምራል።
አቶ ከተማ ሪፎርመር መሆናቸውን ተናግሬያለሁ። ይህ ማሻሻል መገንባት ፈላጊነታቸው አንድ ወሳኝ ደብዳቤ ጽፈው ለንጉሠ ነገሥቱ እንዲያቀርቡ አስገደዳቸው፡፡ ለውጥ ፈላጊነታቸው ግን ጃንሆይን አላስደሰታቸውም። አቶ ከተማን ከሚወዱት ሥራቸው ላይ በማንሳት የንግድና ኢንዱስትሪ ቱሪዝም ሚኒስትር አደረጓቸው። ይህ ስልጣንን የሙጥኝ ማለት ራስን “ብርሃንም መንገድም!” ነኝ ብሎ ማሰብ ጃንሆይ ትልቁ ህመማቸው ነበር። በዘመኑ ጎልማሳ የነበሩት አቶ ሀዲስ አለማየሁ የመታደስን አስፈላጊነት ጽፈውላቸው ነበር። አልሰሙዋቸውም። መስፍኑ ራስ ካሳ እግራቸው ላይ ወድቀው ለመኑዋቸው፤ አልሰሙም። በ1966 ዓ፣ም ህገ መንግስት አርቃቂው ይህንን አጀንዳ አካቶት ነበር። ጃንሆይ ይህ በጣም አስጨንቋቸው የአርቃቂውን ሰብሳቢ አቶ ተክለጻድቅ መኩሪያን (ዘላለማዊነትን እንዳይነፍጓቸው ) የግቢ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋቸው ነበር። ተክለጻዲቅ ሹመቱን ሳይቀበሉ ቀሩ። እዚህ ጋ ጃንሆይን የምናደንቀው ተሿሚው አልፈልግም ካለ አያስገድዱም፣ አያስፈራሩም ። ... ብዙ አሪፍ የምንልላቸው ባህሪ ቢኖራቸውም፣ “ሥልጣን መልቀቅ” ታላቁ ህመማቸው ነው። በ1950ዎቹ የነበሩ ጎረምሶች ይህንን ህመማቸውን በቀልድ ሲገልጹት፤ “ጃንሆይ ቢሾፍቱን ደብረዘይት አልዋት። አዳማንም ናዝሬት። ከፈለጋችሁ እንወራረድ የተወለዱበትን ኤጀርሳ ጓሮ ቤተልሄም ይሉታል” ይሉ ነበር።
ጀኔራል ደጎል ስመጥር የፈረሳይ መሪ ነበሩ። ስልጣን ላይ እያሉ ሁለት ጊዜ የመግደል ሙከራ ተካሄደባቸው። ይህንን ያስተዋሉት ደጎል፤ “ ....ልብ ብላችሁ እዩኝ የሰማይ ስባሪ ነው የማክለው። እኔን ለመግደል የላካችሁት ወመኔ ሲርበተበት ሁለት ጊዜ ሳተኝ። ለምንድነው እንድገደል የሞከራችሁት ? ምን አጠፋሁ?” ሲሉ ጠየቁ። ህዝቡም ሲመልስ፤” የተከበሩ ጀኔራል ልክ ነው ፍራንስን ከደረሰባት ውድቀት አንስተው በፊት ወደነበረችበት ታላቅነት አብቅተዋታል። የዳበረ ኢኮኖሚ የተረጋጋ ኃያል መንግስት ፈጥረውልናል፡፡ ነገር ግን ረዥም ጊዜ ስልጣን ላይ ስለቆዩ ሰለቹን፤ አዲስ ፊት ማየት እንናፍቃለን !” ሲሉ መለሱ ይባላል። ጃንሆይ ይህንን ቀልድ ቢሰሙም አልገባቸውም፤ ስለዚህ ከዘለአለማዊነት ጋር ለዘለአለም ተለያዩ። ቀጣይ የህይወት አቅጣጫቸውን አቶ ከተማ ሲተነብዩ፣ ጃንሆይ እሺ ብለው ስልጣን ከለቀቁ እንደ ከማል አታቱርክ (በቱርክኛ የቱርኮች አባት ማለት ነው) ዘልአለም በትውልዱ እንደሚከበሩ፤ ያንን አላድርግም ብለው በስልጣን ላይ ችክ ካሉ እንደ ጆሴፍ ስታሊን ከህልፈት በኋላ መታሰቢያቸው ሁሉ እንደሚፈራርስ ነግረዋቸው ነበር። ግን በጄ ባለማለታቸው አብዮተኞች አጠናቀቋቸው። እንደ ሙሴ መቃብራቸውም ጠፋ።
ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ጃንሆይ በስልጣን ዘመን ማብቂያቸው ላይ ያደረጉትን የ13 ደቂቃ ከ12 ሰከንድ ንግግራቸውን ልኮልኝ አደመጥኩት። “ሪፎርሙን” ተቀብለውት ነበር። ይሁን እንጂ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” እንዲሉት ሆነ። በጣም በመዘግየታቸው ያንን ከልብ የሚሳሱለትን ሥልጣንና ሥም ለዘለዓለሙ አጡት።
አቶ ከተማ ይፍሩ በነበሩበት ሥርአት ድንቅ የወደፊቱን አመላካች ነብይ ነበሩ፣ ጃንሆይም ሆኑ ደርግ ይህንን አርቆ አሳቢነታቸውን፣ አቅማቸውን፣ እውቀታቸውን አልተጠቀሙበትም። አላወቁትም፡፡ እንዲህ አይነቱን ህሊና ለመረዳት ራስን ማብቃት ወሳኝ ነው። ስለዚህም ጃንሆይ ፈጥነው ደርግም ዘግይተው ወደቁ።
አቶ መኮንን የወላጅ አባቱን ታሪክ የገባውና የተረዳውን ያህል ጽፎ በማስነበቡ ሊመሰገን ይገባዋል። እንደ ማንኛውም ጀማሪ ደራሲ አጻጻፉ ላይ የራሱ የሆነ ችግር አለበት። ቋንቋው ተራ ነው። በዘይቤያዊ አባባል ሊያሳምረው፣ ሊያስውበው አልሞከረም። ምእራፎቹን እንዴት ጀምሮ ማጠናቀቅ እንዳለበት በቅጡ አላሰበበትም። እንደመጣለት ነው የጻፋቸው። ይሁን እንጂ አባቱን እንደገባው ሊያሳየን ጥሯል። ኪነታዊ ጸጋው የለውም እንዳልል፣ አባቱን ወታደሮች ሊያስሯቸው ሲመጡ በልጅ ልብ ዲንጋይ አንስቶ ሊወረውር ሲል ታላቅ ወንድሙ አንቆ ሲያስጥለውና፣ ይህንን ሊያደርግ ሲል ያየው ወታደር እንባው ባይኑ ቀሮ ያየበት ቅጽበት ጸጋው እንዳለው አሳይቶኛል።
እናቱ ወይዘሮ ራሄል በእዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጋብቻቸው ሲፈጸም እንተዋወቃቸውና መጽሐፉ ሊጠናቀቅ ሲል ነው የምናገኛቸው። አባታቸው እስር ቤት ሆነው ጥየቃው ሳይጓደልባቸው አራት ወንድ ልጆችን ገርቶ ሰው ማድረግ ራሱን የቻለ ታላቅ ፈተና ነውና፣ ለውጤትም ስለበቁ ታላቅ ድል ነው። እኝህን እመቤት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በምንጭነት አለመጠቀም ትልቅ ስህተት ነው። ደራሲው ቢያንስ “እማዬ ስለ አባዬ እንዲህ ብላኝ!” ነበር ብሎ ሊነግረን የሚገባውን ቁም ነገር አጓድሎብናል። በነገራችን ላይ በአቶ መኮንን ወላጆች መካከል የመደብ ጉዳይ አለ። እናት የመኳንንቱ ዘር ሲሆኑ፤ አባት የተገኙት ከሰፊው ሕዝብ ነው። ፊውዳል ደግሞ በአደባባይ የማያኮራ ባል ከሆነ ልጃቸውን እቤት ጠርተው፣ ባል ሚስቴን ብሎ ቢመጣ “ፈተንሃል” ነው የሚባለው።
ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እቴጌ መነን ሁለተኛ ባለቤታቸው ናቸው። ጃንሆይን እቴጌ መነን ስድስት አመት ይበልጧቸዋል። እቴጌ ከመጀመሪያ ባላቸው አራት ልጆችን ወልደው ነው ከጃንሆይ ጋር የተጋቡት። ልጅ እያሱ አፋትተው ለደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ዳሩላቸው። ባላቸው ራስ ልዑል ሰገድ “ባለቤቴስ ?” ብለው ሲመጡ፣ “ፈተንሃል!” ብለዋቸዋል።
የአቶ ከተማ ትዳራቸው እንዲቀጥል የሆነው የከተማን ራስ ዳሸን ተራራ የሚያክል ማንነት በመፍጠራቸው ነው፡፡ አማቾቻቸው ይህንን አስተውለዋል። ስገምት በአደባባይ የሚያኮሩ አማች ናቸው። አቶ መኮንን የአባቱን “ድህነት!” ደጋግሞ ማንሳቱ ተገቢ አልነበረም። እርሱ ግን እጅ እጅ እስኪል ይደጋግመዋል። በጽሁፍ ያገኘው ብቻ ሳይሆን አቶ መኮንን ልጅም ሆኖ “የድሃ ልጅ!” ተብሎ ተሰድቦበት ይሆን ? ብዬ እስከ ማሰብ ደርሻለሁ። ለሃሳቤ መነሻ ምክንያት አለኝ። ያንን የጃጀ ዘመን ሳስበው የፊውዳሉ አንዱ ቅስም መስበሪያ ስድብ “ሂድ የድሃ ልጅ!” ስትሆን በአብዮቱ ወቅት አንዷ ነገር ማቀጣጠያ ነዳጅ እንደነበረች አስታውሳለሁ። አሁን ደግሞ ከጉልምስና ጋር ሳስተውለው ኢትዮጵያ ውስጥ ማነው ደሃ ያልሆነው። አገሪቱ ራሷ ድሃ አይደለችም እንዴ ? ህዝቧስ ? በድሃ አይን ሃብታም የምንለው ሰንጋውን አርዶ፣ ጠጁን አስጥሎ ያስጠጣን ያበላንን አልነበረም? እውነተኛ ሃብታም ያየነው ባለፉት ሰላሳ አመታት አይደለም እንዴ ?! ከድህነት ሁሉ የከፋው ድህነት የመንፈስ ድህነት ነው። አባቱ መንፈሳቸው ሙሉ ሆኖ በThinker ደረጃ እያሰቡ ሊያያቸው ባለመቻሉ ከልብ አዝኛለሁ።
አቶ ከተማ ይፍሩ እስር ላይ እያሉ ከያዙት ማስታወሻ ዉጪ ምንም መረጃ ደራሲው አይነግረንም። ይህ ትልቅ አስተሳሰብ ግን በማንበብ እንደሚያጎለብት አውቃለሁ(እገምታለሁ)፡፡ ይህንን ልምዳቸውን ደራሲው ትንፍሽ አላለም። በእስር ላይ በነበሩ ጊዜ ወደ ኋላ ጊዜ መጻሕፍት ማስገባት ተፈቅዶ ስለነበር ብዙ ያነበቡ እንደነበሩ አስታውሳለሁ። በአንድ ወቅት አምባሳደር አሀዱ ሳቡሬን አነጋግሬአቸው (እስር ቤት አንድ ላይ ነበሩ) ይህንን ወቅት በፍቅር እንደሚያስቡት አጫውተውኛል። አቶ ከተማ ምን አነበቡ ? እቤት ውስጥስ ቤተ መጻሕፍት ነበራቸው ?...
በታሪክ አጠቃቀስ ላይ ግድፈት አጋጥሞኛል፡፡ በ1953 ዓም የተከናወነውን መፈንቅለ መንግስት 1952 ዓ.ም ሲል ደጋግሞ ይጠቅሳል። ይህ ደጋግሞ የማንበብ ልምድ ማጣት፣ አልያም የአርታኢው አለመያዝ ብዬ እንዳላስብ፣ ኃይለ መለኮት መዋእልን ስለማውቀው ይህንን አይነት ግድፈት አውቃለሁ።
ይህ ሥራ የአቶ ከተማ ይፍሩ ዘለአለማዊ ሀውልት መሆኑን አቶ መኮንን ተረድቶ ዳግም እንዲያየውና አሻሽሎና አስፍቶ ፣ በቅጡም በፖለቲካው ፣ በዲፕሎማሲያዊ ላይ በማንበብ እያንዳንዷን ምእራፍ ምን ጎደለው እንዴት ላሟላው ብሎ እንዲጽፈው ማሳሰቡን እወዳለሁ። ልብ አድርጉልኝ፤ የእኔ ትውልድ ምኒስትሩን ያውቃቸዋል። ይህና ቀጣዩ ትውልድ ግን ማነው ከተማ ይፍሩ? ብሎ ሳይጠይቅ ወለል ብሎ እንዲያስሰው መጽሐፍ ታላቅ መነጽር ነው።
መታከል ያለባቸውን ለመጠቆም
አቶ ከተማ በዚህ ከፍተኛ ሀላፊነት ላይ እያሉ፣ በጅቡቲ ጉዳይ ላይ ምን ተነጋግረው ነበር ? ... የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሚስተር ሄኒሪ ኪሲንጀር አገራችንን የሚያዩበት መንገድ የተለየ ነው። ስለ እኚህ ሰው ከተማ አቋማቸው ምን ነበር ? ከኪሲንጀር ጋር አይተዋወቁም እንዳልል በስም ሲጠቅሷቸው አጋጥሞኛል። ስለዚህ አንድ የተባባሉት ጭብጥ አይጠፋም እና ጉዳዩን ሥራዬ ብሎ ቢመረምረው ማለፊያ ነው። ይህንን ስል ያለህበትን አገር ባህልና ወግ በንባብ አሳምሬ የማውቅ ይመስለኛል። መንከውከው የሚበዛበት፣ ምራቅ ለመዋጥ ፋታ የሌለበት እንደሆነ እገምታለሁ። ይሁን እንጂ የጀመርከው ሥራ አይደለም ጊዜ፣ ህይወትም ሊከፈልበት የሚያስችል ስለሆነ ትንሽ ጊዜ ሰጥተኸው ድጋሚ ብትጥር ድንቅ መታሰቢያ ለአባትህ ማኖር ትችላለህ።
የመጽሐፉ ሽፋን ድንቅ ነው። በርግጥም አቶ ከተማን አሳምሮ የገለጠ ስለሆነ ዘመዴ ማሊ ኃይሉን ልናመሰግነው ይገባል። በእኔ እምነት ፎቶግራፎቹ ተበታትነው ከሚቀመጡ እንደ አልበም ማሀል ላይ አንድ ላይ ቢቀመጡ ኖሮ ለተደራሲያኑ ጥሩ ፋታ ማግኛ በሆኑ ነበር። ይህ በወደፊት ህትመት ላይ ቢታሰብበት። ደራሲው በመጽሐፉ ማጠቃለያ ላይ አንባቢያንን እንደመምከር ይቃጣዋል፣ ይህ ቢቀር ማለፊያ ነበር።
የዘመኑ አንባቢ ታሪኩን በማለፊያ ብዕር ከትብና ስጠው እንጂ ሞራሉን እራሱ ያውቅበታል፤ አቶ መኮንን ጥቅስ ሲጠቅስ ለመጽሐፍ ጉዳይ ስለሆነ እርግጠኛ መሆን ይኖርበታል፤ እርሱ ግን ሰምቻለሁ በሚል ጠቅሶ ያወጋናል።
አቶ ከተማ ይፍሩ ዘላለማዊ መታሰቢያ የሚያገኙበትን መንገድ ልጠቁም። ለድንቁ ዲፕሎማት ማለፊያ መታሰቢያ የሚሆኗቸው ሽልማቶቻቸው ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ሽልማቶች ትክክለኛ መቀመጫ ቦታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሙዚየም ውስጥ ነው። እዚህ ሙዚየም ውስጥ የደራሲያኑ የመንግስቱ ለማ ፣ ሀዲስ አለማየሁ፣ የማሞ ውድነህ፣ የአያልነህ ሙላት፣ አቤ ጉበኛ እና የስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ቁሶች ሽልማቶች በወግ ተቀምጠው በመጎብኘት ላይ ናቸው። የከተማ ይፍሩን ቁሶች (ልብስ፣ጫማ፣መነጽር፣ የተጠቀሙባቸው የማእረግ ልብስ ካለ) እናም ሽልማቶቻቸው በአንድ ሰው ቁመት በተሰራ የመስታወት ቁም ሳጥን ደርድረህ ታስረክባለህ። በወግ ተገቢው ስፍራ ላይ ተቀምጦ መጪው ትውልድ ለዘላለም እያያ እየጎበኘ ይማርበታል። የዚያኔ ነው እፎይ! የምትለው እንጂ በጅምር እፎይታ የለም። በነገራችን ላይ እኔ የጋሼ ስብሐትን ቁሶች ሳስረክብ፣ “ከፈለክ ያንተንም ቁሶች ብትሰጠን በአግባቡ ተረክበን ሙዚየም ውስጥ እናስቀምጥልሀለን” ተብዬ ነበር። አመስግኛቸው ለዚህ ማእረግ የሚያበቃ ሥራ እንደሌለኝ በሆዴ አስቤ ነው የተውኩት። እርግጠኛ ነኝ ይህ በር ለአቶ ከተማ ክፍት ነው።
አቶ ከተማ የሚከተሉትን ሽልማቶች ከአገር ውስጥ እና ክውጪ አገር አግኝተዋል። 1ኛ. የኢትዮጵያ የክብር ኒሻን ፣ 2ኛ. የዳግማዊ ምኒልክ ኒሻን፣ 3ኛ የክብር ኒሻን ከእንግሊዝ ፣ ከፈረንሳይ፣ ከሜክሲኮ፣ ከፖላንድ፣ ከሶቪየት ህብረት፣ ከቤልጅየም፣ ከጣሊያን፣ ከኔዘርላንድ፣ ከሀንጋሪ፣ ከጃፓን፣ ከካምቦዲያ፣ ከደቡብ ኮርያ ፣ ከኢንዶኔዥያ ፣ ከማሌዢያ ፣ ከቡልጋሪያ ፣ ከምእራብ ጀርመን፣ ከሴኔጋል ፣ ከጊኒ ፣ ከናይጄሪያ ፣ ከሱዳን ፣ ከቼኮዝላቫኪያ ፣ ከዴንማርክ፣ ከኖርዌይ፣ ከታይላንድ፣ ከኬንያ ፣ ከአልጄሪያና ከሌሎች አገሮች ተሸልመዋል፡፡ አሜሪካ ምንም ባትሸልማቸውም የተማሩበት ሆፕ ዩኒቨርስቲ ጠርቶ አክብሮ “አንቱ!” ሲላቸው ነው፣ ልጃቸው መኮንን የአባቱ ታላቅነት የተገለጠለት። ይህንን መጽሐፍ እኔም በዓለም የመጽሐፍት ቀን ምርጥ ብዬ ስመርጠው ከላይ የጠቀስኳቸውን ህፀፆች በመንፈሴ እያሟለሁ፣ ከጭብጥ አንፃር ከልብ እያደነቅሁ፣ እኔ የገበየሁትን ፍሰሀ ከልብ እየጋበዝኩ ነው።
ከአዘጋጁ፡- ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ከ6 በላይ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡ ከጥበባዊና ወጋዊ ጸሃፊነቱ ባሻገርም የህይወት ታሪኮችን (ባዮግራፊስ) በመጻፍም ይታወቃል፡፡ ዘነበ ወላ አርታኢም ነው፡፡ ደራሲውን በኢሜይል አድራሻው፡
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይቻላል፡፡