Sunday, 28 May 2017 00:00

ሰሜን ኮርያ፤ ጃፓንና አሜሪካን መምታት የሚችል ሚሳኤል በገፍ ልታመርት ነው

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ሰሜን ኮርያ ጃፓንንና ዋና ዋና የአሜሪካ ወታደራዊ ካምፖችን የማጥቃት ብቃት ያለውን አዲስ የመካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ባለስቲክ ሚሳኤል በገፍ ለማምረት ዝግጅቷን ማጠናቀቋን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን ባለፈው ማክሰኞ አስታወቁ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ፑክጉሶንግ 2 የተባለውን ባለስቲክ ሚሳኤል በብዛት ለማምረትና በአገሪቱ ስትራቴጂካዊ የጦር ሰፈሮች በማስፈር፣ ለተልዕኮ ዝግጁ እንዲደረጉ ትዕዛዝ እንደሰጡ ማስታወቃቸውን የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት፣ ፕሬዚዳንት ኡንም አዲሱ ባለስቲክ ሚሳኤል ብቃቱ በሙከራ መረጋገጡንና ውጤታማ መሆኑን በመጥቀስ፣ ኢላማውን አነጣጥሮ ያለ አንዳች ስህተት መምታት የሚችለው የዚህ ሚሳኤል ባለቤት በመሆናችን ኩራት ይሰማናል ማለታቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡
የኒውክሌርና የሚሳኤል ፕሮግራሟን እንድታቋርጥ ቻይና እና አሜሪካን ጨምሮ ከተቀረው አለም በተደጋጋሚ እየቀረበላት ያለውን ጥሪ ላለመስማት የወሰነቺው ሰሜን ኮርያ፤ ከአሜሪካ የሚቃጣብኝን ወረራ ለመመከት በበቂ ሁኔታ መታጠቅ ግድ ይለኛልና አልሰማችሁም ብላለች፡፡
ሰሜን ኮርያ በዚህ አንድ ሳምንት ብቻ ሁለት የሚሳኤል ሙከራዎችን ማድረጓን ያስታወሰው ዘገባው፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትም አገሪቱ የተጣለባትን ማዕቀብ በመጣስ እያደረገቺው ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሰሞኑን ተሰብስቦ ውሳኔ ላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 4407 times