Monday, 08 December 2014 14:02

እውነትና ሃይማኖት፣ ሰውና አገር በፕ/ር መስፍን መፅሐፍ

Written by  ዩሃንስ ሰ.
Rate this item
(9 votes)

         የአውሮፓና የአሜሪካ ምሁራን የኢትዮጵያን ታሪክ በትክክል ሊፅፉ እንደማይችሉ ይገልፃሉ ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም። ለምን? ብዙዎቹ ምዕራባዊያን ስለኢትዮጵያ ሲፅፉ፣ በቋንቋና በብሔረሰብ ወይም በሃይማኖትና በባህል ልዩነት እና ግጭት ላይ ያተኩራሉ ብለው የሚያምኑት ፕ/ር መስፍን፣ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን የታሪክ ፀሐፊዎችም የአውሮፓውያን ግርፍ ናቸው በማለት ያጣጥሏቸዋል። የንዴታቸው ምክንያት ይገባኛል። በሃይማኖት ልዩነት ወይም በብሔረሰብ ልዩነት የተቧደነ ግጭት ላይ ማተኮር ጉዳት እንጂ ጥቅም እንደሌለው ይገነዘባሉ። የአገሪቱን ህልውና (ማለትም፣ በአገሪቱ የሚኖሩ ሰዎችን ኑሮ) እንደሚያናጋ ይገባቸዋል። እናም ይጠሉታል፤ ይፈሩታል፤ ይናደዱበታል። ይህንን ለመከላከል ያገኙት ዘዴ ግን፤ “ባዕዳን” ወይም “የባዕዳን ግርፍ” በሚል እነዚያን ምሁራኑና አስተሳሰባቸውን ማጣጣል ነው - ለኢትዮጵያ ታሪክና ህልውና ሲባል። በድሮው አጠራር፣ እንዲህ0 “ባዕድና ወገን” በሚል እውቀትን መፈረጅ... ብሔረተኝነት (ናሽናሊዝም) ይባላል። የውጭ ሃይሎችን በማጥላላት፣ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ለመፍጠር ያግዛል ብለው የሚያስቡም ይመስላል።
ግን ምን ዋጋ አለው? እሳቸው በተከተሉት አቅጣጫ ስንሄድ ብዙም ሳይቆይ የት እንደምንደርስ አይተነዋል፤ እሳቸውም አይተውታል። “የአማራ ምሁራን የፃፉት የኦሮሞ ታሪክ”፣ “ትግሬ የፃፈው የአማራ ታሪክ”፣ “ኦሮሞ የፃፈው የወላይታ ታሪክ”፣ ከዚህም አልፈን... “ጎጃሜ የፃፈው የወሎ ታሪክ፣ የነቀምት ምሁር የፃፈው የቦረና ታሪክ፣ የአድዋ ምሁር የፃፈው የተንቤን ታሪክ... ተቀባይነት የለውም፤ ባዕድ ነው” ወደ ሚል የጎሳ አስተሳሰብና የብሔረሰብ ፖለቲካ ይመጣል። ዛሬ ዛሬ በኢትዮጵያ ይሄ አስተሳሰብ ነው “ብሔረተኝነት” ተብሎ የሚታወቀው። በብሔረሰብ ተወላጅነት መቧደን የሚፈልግ ሰው፤ አላማውን ለማሳካት የሚጠቀምበት አንዱ ዘዴ “የአማራ እውነት፣ የትግሬ እውነት፣ የኦሮሞ እውነት...” የተለያዩ እንደሆኑ መስበክና፤ የማይጥመው አስተሳሰብ ሲያጋጥመው “የባዕዳን አስተሳሰብ”፣ “የባዕዳን ግርፎች አስተሳሰብ” ብሎ ማጣጣል ነው። ከዚሁ ጋርም፤ “እኛ” እና “ሌሎች” በሚል ቅራኔ በመፍጠር፣ ኦሮሞነትን፣ ሶማሌነትን፣ ትግሬነትን፣ ሲዳማነትን፣ አማራነትን እያለ በተወላጅነት መቧደንን ያስፋፋል።
“ባዕድ” እና “ወገን” በሚል የፍረጃ ዘዴ ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር የሚሞክሩ እንደ ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም የመሳሰሉ ምሁራን፣ እነሱ በሚጠቀሙበት የፍረጃ ዘዴ “አማራ”፣ “ጉራጌ”፣ “አፋር”... የሚሉ ስሜቶች እየገነኑ ሲመጡ ምንም መከራከሪያና ምላሽ የላቸውም። ከመነሻው የስህተቱ ምንጭ እነሱ ናቸውና።
የፊዚክስ ፎርሙላ፣ ታሪካዊ የአርኪኦሎጂ ግኝት፣ የቫይረስ ምርመራና የክትባት ፈጠራ፣ የአውሮፕላን ወይም የኢንተርኔት ፈጠራ፣ የፋብሪካ ምርትና የሃብት ፈጠራ... በአጠቃላይ የአንድ ሰው ሃሳብና መርህ፣ ተግባርና አኗኗር፣ ባሕርይና ሰብእና ከማንኛውም ሰው በኩል ቢመጣ፣ ትክክለኛነቱ፣ ጠቃሚነቱ፣ ቅዱስነቱ የሚለካው የወገን ወይም የባዕድ በሚል አይደለም። የኢትዮጵያዊ ግኝት ከሆነ ትክክል፣ የአውሮፓዊ ከሆነ ስህተት፣ የኢትዮጵያዊ ፈጠራ ከሆነ ጠቃሚ፣ የአሜሪካዊ ከሆነ ጎጂ፣ ኢትዮጵያ ከሆነ ቅዱስ፣ ጃፓናዊ ከሆነ እኩይ ነው እንድንል ሲገፋፉን የኋላ ኋላ የት እንደርሳለን? የእገሌ ብሔር፣ የእንትና ብሔረሰብ ተወላጅ ወደሚል መውረዱ የማይቀር ነው። በዚህም አይቆምም። የእገሌ ጎሳና ነገድ ወገን፣ የእገሌ ዞንና ወረዳ ሰው... ወደሚል ሲቀየር ማምለጫ አይኖርም።
ፕ/ር መስፍን ይህንን ሲያዩ ምላሻቸው ምንድነው? ጥያቄው ቢያሳስባቸውም፣ በዚያው በያዙት አቅጣጫ ለመጓዝ ለበርካታ አመታት ሲሞክሩ እንደነበር “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ከሚለው መፅሐፋቸው መረዳት ይቻላል። ከ35 ዓመት በፊት ስለነበረው ሁኔታ የኢትዮጵያ ታሪክና ቄሳራዊን ምሁራን በሚል ርዕስ መፅሐፉ ውስጥ ያቀረቡትን ሃሳብ ተመልከቱ። (ቄሳራዊያን ምሁራን የሚለውን ሐረግ፣ ባዕዳን፣ ምዕራባዊያን ወይም፣ የአውሮፓና የአሜሪካ ምሁራን፣ እንዲሁም በምዕራባዊያን አቅጣጫ የሰለጠኑ ምሁራንን የሚያካትት አድርገው ይጠቀሙበታል - ፕ/ር መስፍን)። እናስ ምን አሉ?
የባዕድ አስተሳሰብ የአገርን ታሪክን እንደሚያበላሽ የገለፁት ፕ/ር መስፍን፤ “በተለይ በእኛ አገር ታሪክ ላይ ከባድና ክፉ ተፅእኖ ያደረገ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ አስተማሪዎቹም፣ የመማሪያውን መፅሐፍ የሚያዘጋጁትም አውሮፓውያንና አሜሪካኖች ናቸው። የኢትዮጵያም የታሪክ ሊቃውንት የሚሰለጥኑት በነዚሁ የውጭ አገር ሰዎች ነው” ብለዋል (ገፅ 44)። የተፃፈውን ታሪክ ከማንበባችን በፊት፣ ታሪክ ፀሐፊው የየት አገር ሰው ነው ብለን መጠየቅ እንዳለብንም ፕ/ር መስፍን ያሳስባሉ (ገፅ 49)።
ፕ/ር መስፍን ከዚህ በመቀጠል፤ አንድ ጥያቄ ያቀርባሉ። “ስለቋንቋዎች፣ ስለዘር፣ ስለባህል፣ ስለታሪክ... በአጠቃላይ በሕዝቡ መሀከል ስላለው የሃይማኖትና ቋንቋ፣ የኑሮና ሌላም ልዩነት ላይ የውጭ አገር ሊቃውንት የሚያተኩሩት ለምንድን ነው?” ብለው በገፅ በ56 ላይ ላቀረቡት ለዚሁ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። ከባዕዳን ምሁራን ዋና ዋና ስራዎች አንዱ፤ “በሕዝቡ መሀከል ያለውን የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የኑሮና ሌላም ልዩነት እየተነተኑ በሕዝሙ መሀከል ቅራኔ ለመፍጠር የሚቻልበትን ዘዴ ማመልከት” እንደሆነ ገልፀዋል ፕ/ር መስፍን (ገፅ 57)። ለቅኝ ግዛት አጋልጠውናል ማለታቸው ነው። ግን በዚህ አላበቁም። “በኢትዮጵያና በሶማልያ መሀከል ያለውን ጠብም ሆነ፣ በውስጥ የሚታገሉትን ተገንጣይ ቡድኖች ጠለቅ ብለን ስንመለከታቸው በስተጀርባ ሆነው አስፈላጊውን ፕሮፓጋንዳ ሁሉ የሚደግሱ እነዚሁ በሃይማኖትና በእውቀት ፍለጋ ስም ኢትዮጵያን እንጀራ መብያቸው ያደረጉ የውጭ አገር ሰዎች ናቸው” ብለዋል ፕሮፌሰሩ (ገፅ 59)።
የኢትዮጵያ ታሪክ ማለት፣ የኦጋዴን ሶማሌ እና የደገኛው ቅራኔ እንደሆነ፣ ወይም የብሔረሰቦችና የጎሳዎች የቅራኔ ታሪክ እንደሆነ አድርገው በሚፅፉ ምሁራን ፕ/ር መስፍን ቢናደዱ አይገርምም። ነገር ግን እነዚህን ምሁራን ለማጣጣል የተጠቀሙበት ዘደዜ፣ በደፈናው “ባዕዳን”፣ “የውጭ አገር ሰዎች” የሚል ፍረጃ ነው። ነገር ግን እንዲህ አይነቱ በተወላጅነት ላይ የተመሰረተ ፍረጃ፣ ብዙም እንደማያዛልቅ በቀላሉ መረዳት የሚያቅታቸው አይመስለኝም። አንደኛ ነገር፤ “ባዕድ ምሁር” እና “ወገን ምሁር” በሚል የተጀመረው ፍረጃ፣ “የእገሌ ብሄር ምሁር፣ የእንትና ብሔረሰብ ምሁር” ወደሚል ፍረጃ መዝለቁ አይቀሬ ነው። ሁለተኛ ነገር፣ “ባዕድ” እና “ወገን” በሚል የሚጠቀሙበትን ፍረጃ ራሳቸው ፕ/ር መስፍን እዚያው መፅሃፋቸው ውስጥ ያፈርሱታል።   
ስለ ኢጣሊያ ወረራና ስለተፈፀመው ግፍ በዝርዝር የፃፈ ኢትዮጵያዊ ምሁር እንደሌለ ፕ/ር መስፍን ጠቅሰው፣ “አንድም ኢትዮጵያዊ ባለሙያ ተቆርቁሮ ለመፃፍ ያልተነሳሳበትን፣ ቢያንስ ሁለት የኢጣልያ ባለሙያዎች ፅፈዋል” ብለዋል (ገፅ 51)። በምዕራባዊያን ምሁራን የተቃኙ ናቸው በሚል ሶስት ኢትዮጵያዊያን ምሁራንን በተቹበት ባለ 25 ገፅ ምዕራፍ ላይ፣ ከአንድ የውጭ አገር ምሁር ጋር ማነፃፀር ጠቃሚ እንደሆነ ለማሳየት እንዲህ ይላሉ። “ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰው፣ ከኢትዮጵያዊው የተሻለ ኢትዮጵያዊ አመለካከት ሊኖረው እንደሚችልም ጥሩ ማስረጃ ስለሚሆን ነው” ገፅ 100።
ሶስተኛ ነገር፣ “ባዕድ” እና “ወገን” በሚል የሚጠቀሙበት ፍረጃ ተገቢ እንደሆነ ለማሳመን ፕ/ር መስፍን ያቀረቡት ማስረጃ፣ የውጭ አገር ምሁራን ሃሳብን ነው። የውጭ አገር ሰዎች ስለሌላ አገር ታሪክ በትክክል መፃፍ እንደማይችሉ ፕ/ር መስፍን ሲያስረዱ አለን ኔቪንስ የተባለ አንድ ምሁር ከሃምሳ አመት በፊት ባሳተመው መፅሃፍ፣ ምዕራባዊያን በቻይና ስለሚኖሩት ትቤታዊያን በትክክል ታሪክ ማጥናትና መፃፍ እንደማይችሉ ገልጿል የሚል ነው (ገፅ 44፣ 74፣ 75)። ለነገሩ ስለ ታሪክ ምንነት ለማስረዳት በቀዳሚነት ዋቢ ያደረጉትና በሰፊው የጠቀሱት መፅሐፍ የስፔናዊ ምሁር መፅሐፍ ነው (ገፅ 35፣ 36፣ 37)።
በእነዚህ በርካታ ምክንያቶች የተነሳ፤ “ባዕድ” እና “ወገን” የሚለውን ፍረጃ ይዘው መቀጠል የከበዳቸው ይመስላል - ፕ/ር መስፍን። እናም ሁሉንም ችግር “በባዕዳን” ላይ ሲያሳብቡ የቆዩት ፕ/ር መስፍን፤ ከጊዜ በኋላ ዋናው ችግር እዚሁ እኛው ጋር እንደሆነ መገንዘባቸውን ከመፅሃፋቸው መረዳት ይቻላል። በኢትዮጵያ ጎልተው የሚታዩ አስተሳሰቦችንና ባህሎችንል እንዲህ ሲሉ ተችተዋል - “ባህላችን የቆመበትን ጓሮ ፍልስፍና ሁሉ ብንመረምረው ለእድገትና ለመሻሻል የሚመች አይደልም። የእድገትና የመሻሻል እንቅፋቶች፣ አእምሮ ውስጥ ተመርገው ሰው የተሻለ ነገር እንዳይመኝ የሚያደርጉ ... ሌላው ቀርቶ በሕልም እንኳን ሰው ደስ እንዳይለው ልፋ ያለው በሕልሙ ዳውላ ይሸከማል እየተባለ እንዳይጥርና እንዳይተጋ ጋሬጣ ይደነቅሩበታል” ገፅ 21።
ሃይማኖትንም ተችተዋል - “ለኢትዮጵያውያን፣ ታሪክ ሁልጊዜም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ... ጋር የተያያዘ ነው። በሃይማኖተኛ ማህበረሰብ ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር ጎልቶ መውጣቱ አያስደንቅም። የሚያስደንቀው የሰው ልጅ ገና ከሕፃንነት አለመውጣቱ ነው። ከሕፃንነት አልወጣም ማለት፣ ራሱ ለሚሰራው ሁሉ ገና ሃላፊነትን መውሰድ አልጀመረም ማለት ነው” ገፅ 34።
ከዚህ በኋላ ነው፤ መፅሐፉ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ፣ የኢትዮጵያ ሶስት ዋና ዋና ችግሮችን የሚገልፁት - ባዕዳን እና ወገን በሚለው ፍረጃ ምትክ አስተሳሰባቸው እንዴት እንደተቀየረ የሚጠቁም ይመስለኛል። “በረጅም ታሪካችን ያልደረስንበትና ያቃተን አንዱ ዋና ነገር፣ በተረጋገጠ እውነት እየተመራን፣ ልማትን፣ እድገትንና ብልፅግናን ለማምጣት አለመቻላችን ነው” ገፅ 195።
በረጅም የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፣ እውነትና እውቀት፣ እንዲሁም ስራና ምርታማነት ክብር ባለማግኘታቸው ኋላቀርነትና ድህነት መለያ ባህሪያችን እንደሆነ የሚገልፁት ፕ/ር መስፍን፣ ለረጅም ዘመናት “ኢትዮጵያ የእውነት አገር ሆና አታውቅም” ይላሉ። እዚህ ላይ እውነት ሲሉ “የተረጋገጠ እውነት” ማለታቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ጠቅሰዋል - በመረጃ ላይ የተመሰረተና በሳይንሳዊ ዘዴ የተረጋገጠ እውነት። ይሄ “እውነት” ፣ ለምርምርና ለክርክር ክፍት ስለሆነ፣ ከሃሳብ ነፃነት ጋር ይጣጣማል። በዚያ ላይ፤ የእውቀት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራና የፋብሪካ፣ የምርታማነትና የብልፅግና መሰረት ነው። ነፃነትን የሚቀዳጅ የሰለጠነና የበለፀገ ማህበረሰብ የሚገነባው በዚህ መንገድ እንደሆነ ሲጠቁሙም፣ ሳይንሳዊ ማህበረሰብ ሲሉ ይሰይሙታል።
በተቃራኒው፣ በእምነት ወይም በጥንታዊ ልማድ ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብን ደግሞ፣ “ባህላዊ ማህበረሰብ” ሲሉ ይጠሩታል። የዚህ ማህበረሰብ “እውነት”፣ ከሃይማኖት፣ ከጥንታዊ ልማድ፣ ከጉልበት ወይም ከስልጣን የሚፈልቅ “እውነት” እንደሆነ ፕ/ር መስፍን ይተነትናሉ(ገፅ 194፣ 195)።  
በእርግጥም፤ ለረዥም አመታት፣ ኢትዮጵያ እውቀት የሰፈነባት አገር ሳትሆን፤ እምነትና ስብከት፣ ልማድና ተወላጅነት፣ ትእዛዝና ፕሮፖጋንዳ የገነነባት አገር ሆና ቆይታለች ልንለው እንችላለን። እናም “በረጅም ታሪካችን ያልደረስንበትና ያቃተን አንዱ ዋና ነገር፣ በተረጋገጠ እውነት እየተመራን ልማትን፣ እድገትንና ብልፅግናን ለማምጣት አለመቻላችን ነው” በማለት መፃፋቸው፣ ለፕ/ር መስፍን ይሄ ለፕሮፌሰር መስፍን ጥሩ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው፤ ቀደም ሲል “እውነት”ን ቢያንስ ቢያንስ ከተወላጅነት ጋር ሲያያይዙት ነበር - የባንዳ ልጆች፣ የባዕድ ሰዎች... የሚሉ ቃላትን በመጠቀም። ስለ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ፣ አፄ ምኒልክና አፄ ሃይለስላሴ ያቀረቧቸው በርካታ አስተያየቶችም ከዚህ ስህተት ጋር ዝምድና ነበራቸው።  
ሁለተኛው... ያቃተን ነገር፣ ስልጣንን መግራት ነው። “ስልጣንን መግራት ያልቻልንበት አንዱ ምክንያት፣ ስልጣን በፀጋ ከተገለጠ እውነት ጋር መያያዙ ነው” የሚሉት ፕ/ር መስፍን፤ “እግዚአብሔር ለፈቀደለት ተገዙ” የሚል ስብከትን ይጠቅሳሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ያልጠቀሱት ነገር መኖሩን ላስታውሳችሁ። “ለአገር ወዳድና ለባህል ወዳድ ተገዙ፤ ለብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ተገዙ፤ ለድሆች ተወካይና በሕዝቡ ለተመረጠ ተገዙ” የሚሉ ስብከቶችስ? የትኛውም አይነት መንግስት ቢሆን፣ የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት፣ ንብረትና ክብር መጠበቅ እንጂ መግዛት አለበት እንዴ?
በሃይማኖት ስም ብቻ ሳይሆን፣ በአገርና በባህል ስም፣ በብሔረሰብና በቋንቋ ስም፣ በድሆችና በሕዝብ ስም፣ “መግዛት” እንዳይችል ማድረግ ነው - ስልጣንን መግራት ማለት። በሌላ አነጋገር፣ የመንግስት ስልጣን የእያንዳንዱን ሰው ነፃነትና መብት ከማስከበር ውጭ ምንም ስልጣን እንዳይኖረው ማድረግ ያስፈልጋል። ቀደም ሲል፣ መንግስት በታሪክ ትምህርት ላይ ጣልቃ መግባትና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት በሚጠቁም መንገድ መፃፋቸውን ስናስታውስ፣ ይህንን አስተሳሰብ በቀጥታ ባያስተካክሉትም የመንግስትን ስልጣን መግራት እንደሚያስፈልግና ለዘመናት እውን ሊሆን ያልቻለ ዋና ጉዳይ መሆኑን መግለፃቸው መልካም ነው።
ሶስተኛው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቃተ ነገር “መተባበር” መሆኑን ፕ/ር መስፍን ሲገልፁ፤ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ትብብር ሳይሆን፣ ማስገደድን ዋነኛ መሳሪያ አድርገነዋል ይላሉ። ይህንንም ማህበረሰቡ የሳይንስን አቅጣጫ ሳይሆን የእምነት አቅጣጫን ከመከተሉ ጋር ያያይዙታል - የእምነት አቅጣጫ ለምርምርና ለክርክር ክፍት ስላልሆነ፣ በጉልበት ማስገደድን እንደ መፍትሄ እንጠቀምበታለን። ብልፅግናና ክብር ከእውቀትና ከስራ መገኘት ይኖርበታል የሚል አስተሳሰብ ስለሌለም፤ በግድ ማሳመንንና ንብረት በግድ መዝረፍን እንደዋነኛ መሳሪያ መጠቀም ይለመዳል። ለዚህ ደግሞ፣ አስተማማኙ ዘዴ የመንግስት ስልጣንን መያዝ ይሆናል - ብዙ የማስገደጃ ጉልበት ለማግኘት። እዚህ ላይ ፕ/ር መስፍን ትክክል ናቸው። ቀደም ሲል፣ “ማህበራዊ ፍትህ” በማለት በተደጋጋሚ ከሚያነሱት አስተሳሰብም ይለያል።
“ማህበራዊ ፍትህ” ማለት፣ እንዲያው ብዙዎች ያድበሰብሱታል እንጂ፣ መንግስት ከተወሰኑ ምርታማ የስራ ሰዎች ላይ ሃብት እየወሰደ፣ ምርታማ ላልሆኑ ሰዎች መስጠት ማለት ነው - በውዴታ ሳይሆን በግድ። “ማህበራዊ ፍትህ”፣ ማህበራዊም ፍትህም አይደለም። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ድርሻና ጥቅም የሚያስከብርበት የፈቃደኝነትና የትብብር ግንኙነት ስላልሆነ፣ ማህበራዊ ሊሆን አይችልም። የሰውን ምርት አስገድዶ መውሰድ፣ መንጠቅ ወይም መዝረፍ፣ በየትኛውም የእውነት መመዘኛ “ፍትህ” አይደለም - በድሆች ስም፣ በአገር ስም፣ በብሄር ብሄረሰብ ስም የሚፈፀም ቢሆን እንኳ ልዩነት የለውም። ፍትህን የሚያጠፋ ነው።
እና፣ ፕ/ር መስፍን፣ “የማስገደድ” ግንኙነት ከኢትዮጵያ ሶስት ዋና ዋና ጉድለቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የገለፁት፤ ቀደም ሲል የያዙትን የ“ማህበራዊ ፍትህ” አስተሳሰብ በማስተካከል ይሆን? በተወሰነ ደረጃ አስተካክለውት ሊሆን ይችላል። ግን ሙሉ ለሙሉ አይደለም። ምክንያቱም በገፅ 201-2 ለአገሪቱ መፍትሄ ይሆናሉ በማለት ስድስት የመደምደሚያ ነጥቦችን ሲዘረዝሩ፣ አምስተኛው ነጥብ ላይ “ችጋር ከምድረ ኢትዮጵያ እስከ ዘለዓለሙ እንዲጠፋ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት እንዲሆን” ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። “ሃላፊነትህ ነው” ካልነው በኋላ ሃላፊነቱን ባይወጣስ? የራሱንና የቤተሰቡን ሕይወት ብቻ ለማሻሻል የሚጣጣርና የሚያመርት ቢሆንስ? ያው፤ እንደተለመደው ለአገር ልማትና ገፅታ፤ ለሕዝቡና ለብሔር ብሔረሰብ ጥቅም በመቆርቆር፣ ከምርቱና ከንብረቱ ቀንሰን በግድ ልንወስድበት ነው?

Read 6481 times