Saturday, 16 April 2016 10:35

20 ቢሊዮን ዶላር የመንግስት የውጭ እዳ የት ገባ?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(7 votes)

አዳዲስ ብድሮች - ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ!
ዋናዋ አበዳሪ ቻይና ናት - ከ7 ቢሊዮን ዶላር በላይ!
የአራት አመታት ከባድ ብድሮች
የባቡር መስመር ብድር - 4 ቢሊዮን ዶላር
የቴሌ ብድር - 2.3 ቢሊዮን ዶላር
አሳሳቢ ብድሮች
የስኳር ፕሮጀክቶች - 2 ቢሊዮን ዶላር
ሴፍቲኔት ድጎማ - 1 ቢሊዮን ዶላር

  በአራት አመታት ውስጥ፣ የመንግስት የውጭ እዳ በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ፣ በጣም አሳሳቢ እንደሆነ የአለም ባንክ እና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ቢገልፁም፣ መንግስት ትችቱን ሙሉ ለሙሉ አይቀበልም። በእርግጥ፣ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ መንግስት አምኗል። ነገር ግን፣ የእስካሁኑ ብድር፣ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በላይ አይደለም ባይ ነው። የብድሩ መጠን ከአገሪቱ ጠቅላላ አመታዊ ምርት ጋር ሲነፃፀር፣ ከ40% በታች ስለሆነ፣ ኢኮኖሚም ለአደጋ አያጋልጥም ብሎም ይከራከራል።
እውነትም፣ ላይ ላዩን ሲያዩት፣ አደገኛ ላይመስል ይችላል። አሳሳቢነቱ ጎልቶ የሚታየው፣ “እዳ መልሶ ለመክፈል፣ በቂ የውጭ ምንዛሬ ከየት ይመጣል?” ተብሎ ሲጠየቅ ነው። ከኤክስፖርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ አነስተኛ መሆኑ ብቻ አይደለም ችግሩ። ለተከታታይ አመታት፣ የኤክስፖርት እድገት አልተመዘገበም። እናም፣ የውጭ እዳው፣ ከአመታዊ የኤክስፖርት ገቢ ጋር ሲነፃፀር፣ ከ6 እጥፍ በላይ ሆኗል። ይሄ ያሳስባል።በመንግስት የሚቀርብ ሌላ ሁለተኛ መከራከሪያ አለ።
“ከውጭ የሚመጣው ብድር፣ ለጊዜያዊ ፍጆታ ሳይሆን፣ ለመሰረተ ልማትና ለአትራፊ ኢንቨስትመንት የሚውል ስለሆነ፣ አደገኛ አይደለም” ይላል መንግስት። አብዛኛው ብድር፤ ለባቡር መስመርና ለመንገድ ግንባታ፣ ለኤሌክትሪክና ለቴሌ ማስፋፊያ፣ ለአውሮፕላን ግዢ እና ለስኳር ፋብሪካ ግንባታ እንደሚውልም ይዘረዝራል። “ኤሌክትሪክና ባቡር የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ ኢኮኖሚን ስለሚያሳድጉ፣ እዳ ለመመለስ አልቸገርም” ማለቱ ነው። ለአትራፊ ኢንቨስትመንት የመጣ ብድር አሳሳቢ እንዳልሆነም ያስረዳል። ለአውሮፕላን ትራንስፖርት ማስፋፊያ፣ በአራት አመት ውስጥ የመጣው ብድር፣ ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው። ነገር ግን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የውጭ ምንዛሬ የሚያገኝ አትራፊ ድርጅት ስለሆነ፣ ብድሮቹን ራሱ ይከፍላል ይላል መንግስት።
ትንሽ ትንሽ፣ እውነት ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የውጭ ምንዛሬ የሚያገኝ አትራፊ ድርጅት ነው። ነገር ግን፣ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛሉ ተብለው የተጀመሩና ውጤት ማስመዝገብ የተሳናቸው ኢንቨስትመንቶችም አሉ - በተለይም የስኳር ፕሮጀክቶች። ባለፉት አስር አመታት የስኳር ፋብሪካዎች ምርት፣ ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል ወደ 25 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ ያስችላሉ ተብለው የተጀመሩት የመንግስት ፕሮጀክቶች፣ ዛሬም ድረስ ውጤታማ አልሆኑም። የተንዳሆ ፕሮጀክት፣ ከአመት አመት ‘ዘንድሮ ማምረት ይጀምራል’ እየተባለ አሥር አመት ደፍኗል። እንዲያውም፣ የሙከራ ምርት ጀምሯል ተብሎም ነበር። የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሰሞኑን በፓርላማ ተጠይቀው የሰጡት መልስ ግን፣ የተንዳሆ ፕሮጀክት ውስብስብ ችግር ውስጥ ገብቷል የሚል ነው። የበለስ፣ የወልቃይት፣ የኩራዝ ስኳር ፕሮጀክቶችማ ገና ናቸው። ቀደም ሲል፣ ከህንድ የመጣው ከፍተኛ ብድር ሳይጨመርበት፣ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ፣ መንግስት ለስኳር ፕሮክቶች 1.9 ቢሊዮን ዶላር ተበድሯል - አርባ ቢሊዮን ብር መሆኑ ነው።
እቅዶቹ አልተሳኩም፤ ብድሩ ግን ተከማችቷል። በየአመቱ 25 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ማምረትና 15 ሚሊዮን ኩንታሉን ኤክስፖርት ማድረግ ቢቻል ኖሮ፣ ያን ሁሉ እዳ ለመመለስ አስቸጋሪ ባልሆነ ነበር። ነገር ግን፣ የስኳር ምርት አምስት ሚሊዮን ኩንታል አልደረሰም። ለኤክስፖርት ሊተርፍ ይቅርና፣ ለአገር ውስጥ ገበያም በቂ አልሆነም።
አስጨናቂው ነገር፣ የስኳር ፕሮጀክቶች መጓተትና መዝረክረክ፣ ድንገት የተከሰተ የአንድ የሁለት አመት ችግር አለመሆኑ ነው። ለበርካታ አመታት የዘለቀና መፍትሄ ያልተበጀለት ችግር ሆኗል። በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ፣ የስኳር ፕሮጀክቶችን በተመለከተ፣ በርካታ ትንታኔዎች የቀረቡ ቢሆንም፤ መንግስት ችግሩን በግልፅ መርምሮ፣ በፍጥነት መፍትሄ አልሰጠም። የመንግስት ሚዲያማ በጭፍን፣ “ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እየተከናወኑ ነው” ከማለት ውጭ፣ ሌላ ስራ የነበራቸው አይመስልም።
ምን ዋጋ አለው? ተጨባጩ እውነታ አልተለወጠም። መንግስትም፣ እጅግ ዘግይቶም ቢሆን፣ ከችግሮቹ ጋር ፊት ለፊት መጋፈጡ አልቀረም። ከሰሞኑ የፓርላማ አባላት ባቀረቡት ትችት፣ የስኳር ፕሮጀክቶች ለረዥም ዓመታት በመጓተታቸው፣ አገሪቱ ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገች ነው ብለዋል።
እንዲያም ሆኖ፣ የውጭ ብድር በሙሉ፣ ተመሳሳይ እጣ ፋንታ ይገጥመዋል ማለት አይደለም። ዋና ዋናዎቹን ብድሮች እንመልከት። የእዳው ክምችት ብዙ ቢሆንም፣ የእዳው አይነት ግን ጥቂት ነው።
የአራት አመታት ትልቁ ብድር - የባቡር መስመር ግንባታ 4 ቢሊዮን ዶላር
የተሻለ ውጤት ሊያስገኙ ይችላሉ ተብለው ከሚጠበቁት ብድሮች አንዱ፣ ለባቡር መስመር ግንባታ የሚውለው ብድር ነው። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ማለቴ አይደለም። ብዙም እርባና የሌለው ፕሮጀክት ነው። እንደ ቁምነገር የሚቆጠሩት፣ ረዣዥሞቹ የባቡር መስመሮች ናቸው። በእርግጥ፣ እነዚህም ቢሆኑ፣ በ2002 ዓ.ም የታቀደውን ያህል አልተሳኩም። ቢሆንም፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ ዋናው የጂቡቲ መስመር ተገንብቶ ተጠናቅቋል ማለት ይቻላል።
ችግሩ፣ ምንድነው?
“ባቡሮቹ፣ የግድ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መሆን አለባቸው” የሚል ፈሊጥ አለላችሁ። እሺ ይሁን። ግን፣ ከባቡር መስመር ግንባታው ጋር፣ የኤሌክትሪክ መስመርም ተዘርግቶ አምና መጠናቀቅ ነበረበት። ግን ዘንድሮም አይጠናቀቅም። በመጪው አመትም ያጠራጥራል። እንዲያም ሆኖ፣ የባቡር መስመሩ፣ የኋላ ኋላ፣ የጂቡቲ መስመር ባቡር፣ የትራንስፖርት ፍጥነትን ለማቀላጠፍና ወጪ ለመቀነስ ማገዙ አይቀርም። እናም፣ በአብዛኛው ከቻይና የመጣው የባቡር ግንባታ ብድር፣ ለቁምነገር ውሏል ቢባል ያስኬዳል።
የመንገድ ግንባታ - 2.1 ቢሊዮን ዶላር
በኢትዮጵያ፣ ውጤታማ ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱ ሁለት መንግስታዊ ተቋማት መካከል አንዱ፣ የመንገድ ግንባታ ባለስልጣን እንደሆነ የቀድሞው የአለም ባንክ ተወካይ መናገራቸውን አስታውሳለሁ። በእርግጥም፣ የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ በኢትዮጵያ ጎላ ብሎ የሚታይ ለውጥ ነው ማለት ይቻላል። አዎ፣ የአገራችን የመንገድ ትራንስፖርት፣ ከአፍሪካ አገራት ጋር ሲነፃፀር እንኳ፣ ገና ወደ ኋላ የቀረ ነው። ቢሆንም፣ የአስፋልት መንገድ ርዝመትና ጥራት ጨምሯል።
እናም፤ ለሃዋሳ ፈጣን መንገድና ለሌሎች የመንገድ ትራንስፖርት ግንባታዎች የሚውለው፣ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ብድር፣ በቁምነገር ተርታ ብንመዘግበው ተገቢ ነው። አብዛኛው ብድር የመጣው፣ ከአለም ባንክ እና ከቻይና ነው።
በአጭሩ፤ ባለፉት አራት አመታት የኢትዮጵያ መንግስት ካገኘው 18 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ፣ ለባቡር መስመርና ለአስፋልት መንገድ ግንባታ የዋሉት የ6 ቢሊዮን ዶላር ብድሮች፣ “ደህና ናቸው” ተብለው በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው ማለት ይቻላል።

ሌሎቹ ትልቅ ብድሮች - የኢትዮቴሌኮም 2.3 ቢሊዮን ዶላርና የኤልፓ 2.1 ቢሊዮን ዶላር
በሁዋዌ እና በዜድቲኢ አማካኝነት ከቻይና የመጣውን ብድር ጨምሮ፣ ቴሌ ባለፉት አራት አመታት ለኔትዎርክ ማስፋፊያ፣ 2.3 ቢሊዮን ዶላር ተበድሯል። የኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽንም በፊናው፣ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ተበድሯል።
ጥያቄው፣ “በብድሮቹ ቁምነገር ተሰርቷል ወይ?” የሚል ነው። ይሄን ሁሉ የእዳ ክምር ከመሸከም ይልቅ፤ በተለይ በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ፣ የግል ኩባንያዎች እንዲሰሩ መፍቀድ ይሻል ነበር። ለአገልግሎት ጥራትም ይበጃል። ቢሆንም ግን፣ የቴሌ ብድር፣ በከንቱ የተቆለለ እዳ ነው ማለት አይደለም። ኢትዮቴሌኮም፣ የሞባይል ስልክ መስመሮችን፣ 44 ሚሊዮን አድርሻለሁ ብሏል። በእርግጥ፣ ያ ሁሉ የሞባይል መስመር፣ አገልግሎት የሚሰጥ መስመር አይደለም። “...ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ መስመሮች በርካታ ናቸውና። ለምሳሌ ከአገር የሚወጣ ሰው፣ ደንበኝነቱን ያቋርጣል። ለአጭር ጊዜ የመጣና ተመልሶ የሚሄድ ዳያስፖራም እንዲሁ...” የሚል እርባና የሌለው ንትርክ ውስጥ የሚገባ ይኖራል። ቁምነገሩ ግን ሌላ ነው። አዎ፣ ቁጥሩ የተጋነነ ይመስላል። በእርግጠኝነትም፣ 44 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ሆኗል ማለት እንዳልሆነ መናገር እንችላለን። እንዲሁ በግርድፉ ብታስቡት እንኳ። በከተማ፣ ግማሹ ነዋሪ ከ15 ዓመት በታች ስለሆነ፣ 10 ሚሊዮን ሰው የሞባይል ተጠቃሚ ነው ብለን ብንገምት፣... በገጠር ደግሞ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ፣ አንድ ሞባይል ይኖራል ብለን ‘ለጥጠን’ ብንገምት... በድምር 27 ሚሊዮን ይሆናል። ይሄም ብዙ ነው - ከ44 ሚሊዮን ጋር ቢራራቅም።
እንዲያም ሆኖ፣ ቴሌ እንደሚለው፣ 44 ሚሊዮን የሞባይል መስመሮችን ሸጦ ሊሆን ይችላል። እስከ 2002 ዓ.ም ከነበረው ስድስት ሚሊዮን የሞባይል መስመር፣ ወደ አርባ ሚሊዮን ከዚያም በላይ ማስፋፋት... ትልቅ ለውጥ ነው። ግን፣ ብዙ የብድር ገንዘብ የዋለውም ለዚሁ ነው። በብድር፣ በተስፋፋው ኔትዎርክ አማካኝነት፣ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ብልህነትና ታታሪነት ከተጓደለ ግን፣ በከንቱ የእዳ ክምር እንደመሸከም ይቆጠራል።
በሌላ አነጋገር፤ ለሞባይል ማስፋፊያ የመጣው ብድር ቁምነገር ላይ ውሏል ማለት ቢቻልም፤ ችግር የሚፈጠረው፣ ወደፊት ነው። በውጭ ኮንትራክተር የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን ማሳካት አንድ ነገር ነው። የእለት ተእለት አገልግሎትን በማሻሻል ስኬታማ የቴሌ ቢዝነስ ማካሄድ ደግሞ ሌላ!!
እስከዚያው ግን፣ ለሞባይል ማስፋፊያ የዋለው ብድር፣ ወጤታማ ነው ቢባል ያስኬዳል። አሃ፣ ቀልጠው የቀሩ የቴሌ ኢንቨስትመንቶችን’ኮ አይተናል። “በፀሃይ ኃይል የሚሰሩ የጎዳና ስልኮችን” ለመግዛትና ለመትከል፣ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከወጣ በኋላ ምን እንደተከሰተ ታውቃላችሁ። ዛሬ የጎዳና ስልኮቹ አይሰሩም፤ በአካባቢው የሉም። ታዲያ፣ ለሞባይል ማስፋፊያ የዋለው ገንዘብ አይሻልም?
አንዱ ችግር ምንድነው? ገንዘቡ በብድር የመጣው፣ በዶላር ነው። ቴሌ ብድሩን ለመመለስ፣ ዶላር ከየት ያመጣል? ያን ያህልም፣ ብዙ የውጭ ምንዛሬ የሚያገኝ ድርጅት አይደለም።
ኤልፓም ተመሳሳይ ችግር አለበት። ኤሌክትሪክ ወደ ጎረቤት አገራት በማስተላለፍ የውጭ ምንዛሬ አገኛለሁ እያለ ለበርካታ አመታት እቅዱን ሲናገር ሰምታችሁ ይሆናል። እስካሁን ግን፣ በአመት የሚያገኘው የውጭ ምንዛሬ፣ ከሃያ እና ከሰላሳ ሚሊዮን ዶላር አልዘለለም። ምናልባት፣ ጊቤ 3 እና ሕዳሴ ግድቦች ሲጠናቀቁ፣ ይሳካለት ይሆናል። አንዳንዶቹ የኤልፓ ፕሮጀክቶች ግን፣ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሊሆኑ ይቅርና፣ ከፈሰሰባቸው ገንዘብ ጋር የሚመጣጠን የኤሌክትሪክ ሃይል በወጉ የማመንጨት አቅም እንኳ የላቸውም። ቀደም ሲል በብድር የተሰሩ የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎችንና አሁን እየተሰሩ የሚገኙ የከርሰ ምድር እንፋሎት ጣቢያዎችን መጥቀስ ይቻላል።

Read 5263 times