Saturday, 22 July 2023 13:04

የሕዝብ ፍቅር እስከ መቃብር ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   አምስት ዓመት እጅግ ርቆብን… “ጥንት ዘመን” የሚሆንብን ለምንድነው? ወሬ በዛ። የሚታይ ነገር በዛ። ስንቱን አስታውሰን እንችለዋለን? አምስት ዓመት “የጥንት ታሪክ” ከሆነብን፣ 2ሺ ዓመት ምን ልንለው ነው?
ያኔም እስር ቤቶች ነበሩ። እስረኞችን መጠየቅና በምህረት መልቀቅም፣… ያኔ በጥንት ዘመን ነበር። ንጉሦችና ባለስልጣናት ያስራሉ፤ ምህረት ይሰጣሉ። ሕዝብ ለእስረኞች ምህረት የመስጠት ስልጣን ሲያገኝ ደግሞ አስቡት።
በእርግጥ፣ የሕዝብ ምህረት በነጻ አይገኝም። ሕዝብን ማስደሰትና ተወዳጅነትን ማትረፍ የቻለ እስረኛ ግን ምህረት ይደረግለታል። ከእስር ቤት ይወጣል።
የጥንት ዘመን እስረኞች በጣም እድለኞች ናቸው? ሕዝብ አይረሳቸውም?
ይረሳቸዋል። አንዳንዴ ግን ያስጠራቸዋል።
ወደ ስታዲዮም ይጋብዛቸዋል።
በግጥሚያ ትዕይንት እንዲሳተፉ ይፈቅድላቸዋል።
ብቃታቸውን በአደባባይ እንዲያሳዩ ሜዳውን ይሰጣቸዋል።
ትጥቅ ያሟላላቸዋል።
ስታዲዮሙ ከአፍ እስከ ገደፉ በተመልካች ሕዝብ ይጥለቀለቃል። ግጥሚያ ለማየት፣ አሸናፊዎችን ለማድነቅ እና  ለጀግኖች ምህረት ለመስጠት ነው የሕዝቡ ፍላጎት።
በእርግጥ፣ የግጥሚያ ወይም የፍልሚያ ትዕይንት ማለት፣… በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ አይደለም።
ከ1500 ዓመት በፊት ነው ዘመኑ። የግሪክ የስፖርት ውድድሮች በሮም ዘመነ መንግሥት ወደ ውጊያ ተለውጠዋል። ጨዋታ ቀርቷል።
 ግጥሚያ ግጥሚያ ነው። ፍልሚያ ከምር ፍልሚያ ነው። የፍልሚያ ጨዋታ አይደለም። ሶስት ነጥብ ለማስመዝገብ የሚካሄድ ኳስ መጫወት አይደለም-ያኔው የጥንቱ ፍልሚያ። የዛሬማ ቀልድ ነው።
ኳስን መምታትና ማከባለል ይቻላል። ተጋጣሚን መጎሸም ግን አይቻልም። መግጨት ይቅርና ልብስ መጎተት ክልክል ነው። አሸናፊዎቹም ተሸናፊዎቹም አንዳች ጭረት ሳይነካቸው ጨዋታቸውን ጨርሰው ለደርሶ መልስ ይዘጋጃሉ። የሳምንት ደሞዛቸውን እየተቀበሉ።
የጥንቱ ስታዲዬም ለጨዋታ የተገነባ አይደለም።
የጥንቱ ግጥሚያ የምር ውጊያ ነው።
በጦር በጎራዴ፣ በመዶሻና በመፍለጫ የሞት ሽረት ነው ፍልሚያው።
የእስር ቅጣቴን ለመጨረስ ግማሽ ዓመት ብቻ ነው የቀረኝ፤ ፍልሚያና ምህረት ይቅርብኝ የሚል ሰው ይኖራል።
ነገር ግን ምህረት ለማግኘት የሞት ሽረቱን እንዲፋለም ህዝብ ከወሰነ የግድ ወደግጥሚያው ይገባል። ህዝብ ከወደደውና ከፈለገው ማምለጫ የለውም።
እስረኞቹ፣… አንዳንዶቹ ጨካኝ ወንበዴዎች፣ አንዳንዶቹ ጊዜ የከዳቸው ባለስልጣናት፣ ገሚሶቹ የከተማ ወረበሎች፣ ገሚሶቹ ከባለስልጣን ጋር ተጣልተው የታሰሩ ምስኪኖች ቢሆኑም፣ በፍልሚያው ሜዳ ላይ ግን ሁሉም ያው ተጋጣሚዎች ናቸው።
ጥሎ የማለፍ ገድሎ የመዳን ነው ፍልሚያው።
ተጋጥሞ ያሸነፈ በህይወት ይተርፋል፤ በምህረት ከእስር ይለቀቃል። ህዝብ ከወደደ ምን ይሳነዋል? ሕዝብ ከእስር የፈታው ሰው ንጉሥ አያስረውም።
ሕዝብ አብዝቶ የወደደ እንደሆነ ነው ችግሩ። ከሌሎች ተጋጣሚዎች ሁሉ እጅግ የላቀ ጀግና፣ በአንድ ጊዜ ከንጉስ የበለጠ ዝነኛ ይሆናል።
ህዝቡ ያብድለታል።
ከዓይናቸው እንዳይርቅ ይሳሱለታል።
ይደገም ይደገም ብለው ይዘምሩለታል።
ሌሎች እስረኞች ወደ ግጥሚያ ሜዳ ሲገቡ፣ ተወዳጁ እስረኛ አሁንም ይፋለማል። ካሸነፈ፣ ተወዳጅነቱ ይጨምራል።
አሁንም ይደገም፤ ከነብር ከአንበሳ ጋር ይጋጠም፤ ይደገም…ይላል ህዝቡ። አይጣል ነው። እጅግ የተወደደ እስረኛ፣ ከፍልሚያ ሜዳ በህይወት የመውጣት እድል የለውም።

Read 1044 times