(ሰብአዊ መብቶች ይከበሩ!)
የእኔ (የሰው ልጅ) ህልውና ከሌላው በእጅጉ የተለየ ነው፤ ጥልቅ፡፡ ሰፊ፡፡ ይህ የሚሆነው በሰውነት(በስጋ) አይደለም፤ በማንነት እንጂ። የማንነት ምንጭ ደግሞ ነፃነት(freedom) ነው፡፡ ‹‹But Existenz differs from other Existenz in essence, because of its freedom.›› እንዳለው አሜሪካዊው የፍልስፍና መምህር ‹‹ሮበርት ሲ ሠሎሞን››፡፡
ህልውና ይኖራል (ማንነት ነው)፡፡ ይሞታል (ስጋዊ ነው-ና)፡፡ በሂደት (በተግባር ላይ በተመሰረተ ህይወት) በየቅፅበቱ ከሞት ጋር ይፋጠጣል፡፡ ሞት ደግሞ የነገሮች (የስጋ እሩጫ) መደምደሚያ ነው፤ ለአንዳንዶቹ ከነአካቴው ወደ ምንምነት መቀየር ነው፡፡ ለአንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ሌላ ዓለም መሻገሪያ ሁነት(ሽርጉድ) ነው፡፡ ይህ ከስጋ ሞት ጋር በተያያዘ የሚመጣ አንድ የህይወት ዑደት (ሽግግር) ነው፡፡ በዚህ የስጋ ሞት የሰው ልጅ እንደማንኛውም ህይወት እንዳለው ፍጡር ሁሉ እኩል የሚጋራው ተፈጥሯዊ ክስተት ነው፤ ተለምዷዊ እና ብዙም የማያስጨንቅ ነው፡፡
ነገር ግን በህይወት(በስጋ) እያለ ሞት ደጋግሞ የሚጎበኘው የሰው ልጆችን ብቻ ነው። ማለትም ህልውናን የሚፈታተኑ የስጋም ሆነ የመንፈስ ብሎም የስሜት ስቃዮች … በአጠቃላይ ለህልውና የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማግኘት በሚደረግ ትግል ውስጥ እንቅፋት የሚሆኑ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሁሉ ግለሰብን ደጋግመው የሚጎበኙ የኑሮ በትር(ሸክሞች) ናቸው፡፡ ምክንያቱም የሰው ወይም የግለሰብ ጉዞን (የአካል፣የህሊና) ይገታል፤ ይገድላል። ለምን ቢባል ህልውና የሚቀጥለው በምልከታ (በመታዘብ)፣ ልምድን በማዳበር ሂደት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በሌለበት የግለሰብ ህልውና ‹‹አለ›› ሊባል አይችልም፡፡
በየትኛውም መንገድና ሁኔታ ሰው ወደ ምንኖርበት ዓለም ሲመጣ በአካል ተገለጠ (ተከሰተ) ማለት አይደል፡፡ ይህ የመጀመሪያ ሂደት ነው፤ በአካል፣ በስጋ መገኘት፡፡ ከዚህ ቀጥሎ አስፈላጊውና መተኪያ የሌለው እሴት (ይዞት የተወለደው) ነፃነት ነው፡፡ ነፃነቱ አጠቃላይ ህይወቱንና ሰውነቱን (ምንነቱን፣ማንነቱን) የሚያጎናፅፍ ጥልቅ ዓለሙ ነው፡፡ በአካል የትም ቦታ የመገኘት፣ የመስራት፣ የመመገብ ወዘተ… መብት ያጎናፅፈዋል፤ ያለምንም ክልከላ። በህሊናው ደግሞ ምንም የማሰብ፣ ያሰበውን በተለያዩ መንገዶች የመግለፅ፣ የመናገር፣ በማንኛውም መንገድ የማሰራጨት ሙሉ መብት አለው፤ ሰው፡፡ (ሃሳብን በመግለፅ መብት ዙሪያ ሃገራችን የፈረመቻቸው ዓለማቀፍ ህጎች መኖራቸው ሳይዘነጋ፣ በህገ መንግስቱ ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት በግልፅ ተቀምጧል፡፡)
ስለሆነም የግለሰብ ህልውና ከየትኛውም ዓይነት ጫና ነፃ እንዲሆን ህጎች፣ ስምምነቶች ቢኖሩም አለመከበራቸው በእጅጉ ይከነክናል፡፡ ምክንያቱም ሰው በምድር ላይ ሲኖር ነፃ ነውና፤ ነፃነት ማንም የማይወስድበት የግል ሃብቱ ነው። ከእስትንፋሱ ጋር አብሮት የተፈጠረ ነው፡፡ ነፃነትን የሚያክል ሃብት ተነጥቆ አንገቱን የሚደፋ ግለሰብም ሆነ ህዝብ የለም፤ በተለይም ‹‹እኛ››፡፡ ምርጫችንም ፣ ግዴታችንም ነፃ መሆን ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹ህይወት ነፃነት ብቻ ነው››። በህልውናችን ላይ በገነባነው ማንነት እና ለምንገነባው እኔነት በታሪክ ውስጥ ጊዜን ገርቶ የምንፀናበት እሴታችን ነው፤ነፃነት፡፡ እናም እኔም አንተም እንደአባቶቻችን ነፃ ነን፡፡ የምንሸከመው ቀንበር (በደል) የለም፡፡
‹‹ነፃነት በመሽኮርመም አይመጣም›› የሚሉ ግለሰቦች እውነት አላቸው፤ የተወሰደ ‹‹ነፃነት›› ካለ ማለቴ ነው፡፡ ነገር ግን ነፃነት ህልውና ነውና ቀማኛ ባለበት በቀላሉ በህግ የሚረጋገጥ አይደለም፡፡ በመስዋትነት፣ በጠንካራ ትግል ግን ይረጋገጣል፡፡ በታሪካችን ‹‹የገደለው ባልሽ፣ የሞተው ወንድምሽ…›› ዓይነቱን ክስተት መለስ ብሎ መቃኘት አቻ ጉዳይ ይመስለኛል። ምን ለማለት ነው… ነፃነትህ ከተወሰደ በአካል ብትኖርም የለህም፤ የሞት ቀፎ ሆነሃል ማለት ነው፡፡ የነፃነት እጦት ውጤቱ ሞት ነው፡፡ የከፋው ሞት ደግሞ በፍርሃት አለንጋ ተገርፎ መጎሳቆል ነው፡፡ ፍርሃት የውጥረት ውጤት ነው፡፡ ውጥረት ደግሞ ከፍተኛ ድብርት ያመጣል፡፡ ድብርት ሲከራርም ጭንቀት ወልዶ የሚያስበረግገን ነገር ሁሉ እንደጦር ይወጋናል። ይህ የቁም ሞት በሰው ልጅ ላይ ከሚደርሰው የስጋ ሞት ይበልጥ የከፋው ነው፡፡ እና’ማ ‹‹መቼ ይሆን ከዚህ የቁም ሞት የምገላገለው?›› በሚል ጥያቄ ተወጥሬ ዓመታት አለፉ፡፡ በማየው፣ በምሰማው፣ በሚደርስብኝ ሁሉ አዘንኩ። ይህ የቃል ኑዛዜ ከታወከ አካባቢ (ምድር) ጋር የሚደረግ ግብግብ ሆኖ ይሰማኛል፤ የጦር ቀጠና፡፡
በነፃነትህ የመጣን አካል ‹‹ዝንብ›› እንኳን ቢሆን በተገቢው መንገድ ማባረር ያስፈልጋል። ‹‹ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፡፡›› ቢልም ህገመንግስቱ፣ መሬት ላይ ያለው እውነት ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ስርዓት አልበኝነት ሰፍኗል፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባት ከባድ ሆኗል፡፡ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ መስራት ህልም ከሆነ ቆይቷል፡፡ በእርግጥ ህገመንግስታችን ውስጥ የተካተቱት ‹‹ዴሞክራሲያዊ መብቶች›› በሙሉ ሰብዓዊ መብቶች ናቸው፤ ለማንም ማንም ሊሰጠው የማይገባ፡፡ የመብቱ ባለቤት ግለሰቡ ነው። ለምሳሌ የመምረጥ መብት ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ የሚመነጭ ሆኖ የማንኛውም ሰው መገለጫ ነው፡፡ እንዳይወሰድበት ከለላ ማድረግ እንጂ ‹‹ዴሞክራሲያዊ መብቶች›› ብሎ ተረት ግን መለወጥ አለበት፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ልቡ ያበጠ ካድሬ ለግለሰቡ የእሱ ፓርቲ ያጎናፀፈው መብት ይመስለዋልና፣ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ህገመንግስቱን ለማንበብ በምሞክርበት አጋጣሚ ሁሉ ግርም የሚለኝ ደግሞ ‹‹የሕይወት፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው።›› የሚለው ድንጋጌ ሲሆን በእየለቱ ወጥተው የሚቀሩ፣ በየደረጃው የሚከሰቱ ግድያዎችና እንግልቶች … በአእምሮዬ እየተመላለሱ ቁጭትና ብሶት ይጠሩብኛል፡፡ ምክንያቱም ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ይሆንብኛል፡፡
በአደጉ አገሮች የግለሰብ ነፃነት የልማት መሰረት በመሆኑ የዴሞክራሲ እሴት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ቀጣይነት ያለው ሰላም፣ እድገት (በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ…)፣ ቀልጣፋ አስተዳደር ለመዘርጋት ነፃነት የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡ እንደኛ ባሉ አገራት መብትና ልማት የማይነጣጠሉ የሁሉም ነገር መሰረቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ድህነትን ማስወገድና ማህበራዊ መረጋጋትን ለመፍጠር ተግቶ መስራት የመንግስት ሃላፊነት ነው፤ ለሰብአዊ መብቶች መረጋገጥ ቅድመ ሁኔታ ናቸውና፡፡ ሰላም በሌለበት፣ ድህነት በተንሰራፋበት፣ የስራ እድል በሌለበት፣ ዜጎች በሚፈናቀሉበትና በዘራቸው ምክንያት በጅምላ በሚጨፈጨፉበት ሁኔታ ሰብአዊ መብቶች ሊከበሩም ሆነ ሊረጋገጡ አይችሉም። ያው የተለመደውን የፖለቲካ ተረት (የውሸት ትርክት) ለማነብነብ ካልሆነ በቀር። ለዚህም ነው፤ የ1968ቱ በቴህራን (ኢራን) የተደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ፤ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል መብቶች ሙሉ በሙሉ ካልተከበሩ በቀር የግለሰቦችን መብቶች ማስከበር አይቻልም በማለት ያሰፈረው፡፡ ይህንን ስምምነት ኢትዮጵያ የተቀበለችና በህገመንግስቱ ያካተተች ቢሆንም፣ ማክበርም ሆነ ማስከበር ያልቻሉ ሁለት መንግስታት ተፈራርቀውባታል። ይህም በተደጋጋሚ የህዝብ እንቢተኝነት እንዲነሳና ወደ ህልውና ትግል እንዲያድግ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፤ እየተጫወተ ይገኛል -ምቀኛ ጠላቱን ይተክል፣ ራሱን ይነቅል- እንዲሉ፡፡
‹‹የሽግግር ፍትህ›› የምክክር መድረኮች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተፈፀመባቸው ወንድሞቻችን ለመንግስትና ለሚመለከተው ክፍል ከገለጿቸው ፍላጎቶች(የመፍትሄ ሃሳቦች) መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ሰላምና ደህንነት፣ማካካሻ ማግኘት፣ እውነትን ማጣራትና ማውጣት፣ እርቅና ሰላምን መፍጠር፣የወንጀል ምርመራና ተጠያቂነት እንዲሁም ጥሰቶች(የመብት) እንዳይደገሙ ዋስትና መስጠት የሚሉት ይገኙበታል። ይህ በእውነቱ ልብ የሚሰብር ነገር ነው፡፡ ተፈናቅለውና የተለያዩ ግፎች ተፈፅመውባቸው ያሉ ተጠቂዎች ለበደላቸው አካል ያቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ ከመሆኑ ባሻገር ለሌላው ታዛቢ የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው። ምክንያቱም ተጠቂዎች የፖለቲካ የቁማር ካርድ የተመዘዘባቸውና በጉዳዩ (ለመፈናቀላቸው ምክንያቱን) ዙሪያም ምንም አይነት ግንዛቤው የሌላቸው ነፃ ሰዎች ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን የቀድሞ ቦታቸውን መልሰው ማግኘትና መኖር የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በእርግጥ ጉዳዩ ብዙ ጉዳዮችን ያዘለ ነው፡፡ያማል፡፡
(ሰላም፣ ፍትህ እና ልማት እንፈልጋለን፤ እንደ ትውልድ ይገባናል፡፡ ማንም ማንም ላይ ብረት ሊያነሳ አይገባም፡፡ ሁሉም ነገር በሰላም ሊቋጭ ይገባል፣ መልዕክቴ ነው፡፡(ፖለቲከኞቻችን አደብ ግዙ፤ አታድክሙን)
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይቻላል፡፡
Saturday, 22 July 2023 13:08
እረፍት የሚነሳ የህልውና ጥያቄ!
Written by ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Published in
ነፃ አስተያየት