Sunday, 21 January 2024 00:00

ያለፉትን 68 ዓመታት በወፍ በረር “ምርጫው የኛ ነው!!”

Written by  ቶማስ በቀለ- (ካለፈው የቀጠለ
Rate this item
(0 votes)

ካለፈው የቀጠለ

  የደርግ መንግስት
 የ1966ቱ አብዮት መፈንዳት ለፊውዳል ስርዐተ ማህበር ማብቂያ መሆኑ ጥሩ ቢሆንም፤ በምትኩ የሀገሪቱ እጣ ፈንታ “ደርግ” በሚባል ስም በሚታወቁ የወታደር መኮንኖች እጅ ላይ ወደቀ። ከመጀመሪያዎቹ የደርግ ወታደራዊ መኮንኖች መካከል ለዘብተኛ፤ አስተዋይና የፖለቲካና የአስተዳደር እውቀት የነበራቸው የተወሰኑ መኮንኖች ቢኖሩም፤ በሂደት መልካም አስተሳሰብ የነበራቸው አባላት በእርስ በርስ የስልጣን ፍትጊያ ተገድለው ፍፁም የሆነ የወታደራዊ አምባገነን ስርዐት ተፈጠረ። ሀገሪቷ የሶሺያሊዝም ስርዐት እንድትከተል የውጪም ሆነ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ሁኔታዎች ቢያስገድዱም፤ በኔ እምነት ደርግ የሚከተሉትን ሶስት ጉልህ ስህተቶች መፈፀም አልነበረበትም ባይ ነኝ።
ሀ. የወቅቱ የስልሳዎቹ ባለስልጣናት ግድያ፡ በንጉሱ ዘመን የነበሩት ባለስልጣናት በሰሩት ወንጀል መጠየቅ እንዳለባቸው የሚያከራክር አይደለም። ይሁን እንጂ ያለምንም የህግ አግባብ፤ ጉዳያቸው የፍርድ ቤት ስርዐትን ሳይከተል በደመ-ነፍስ የተወሰደባቸው የግድያ እርምጃ አግባብነት አልነበረውም። በተለይም የተማሩና ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸውን ባለስልጣናት ለውጥ የማይፈልጉና የመሬት ከበርቴ ከሆኑት ፊውዳሎች ጋር አንድ ላይ ያለፍርድ መግደል እጅግ በጣም ከባድ ስህተት ነበር። አንድ በቅርብ የማውቀው ወዳጄ ሲያጫውተኝ፤ “እነ ፀሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሐብተወልድና መሰሎቻቸው በወቅቱ የነበረውን የአለምና የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ አበጥረው የሚያውቁ በመሆናቸው ኢትዮጵያ በምን መንገድ ብትሔድ ማደግ እንደምትችል ከነሱ በላይ የሚያውቅ አልነበረም። በዚህ ምክንያት አክሊሉ ሐብተወልድ ስለወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታና ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ለማደግ ምን ማድረግ እንዳለባት የሚመራ መፅሐፍ እንዲፅፉ የቅርብ ሰዎቻቸው ይለምኗቸው ነበር፤ በመሆኑም እነ አከሊሉ ሐብተወልድን መግደል አንድ ትልቅ የታሪክና የፖለቲካ መፅሐፍ እንደማቃጠል ነው” አለኝ። በዚህ ምክንያት ተራማጅ ባለስልጣኖቹን መግደላቸው ከአእምሮአቸው የማይጠፋ ፀፀት እንደሆነባቸው አንዳንድ የደርግ ባለስልጣናት እስካሁን ድረስ ይናገራሉ። ፀፀቱ ባልከፋ፤ ነገሩ “ጅብ ከሄደ …” እንደሚባለው ተረት መሆኑ ነው እንጂ።
ለ. የቅይጥ ኢኮኖሚ ስርዐት አለመከተሉ፡ በ “UN-FAO” ውስጥ ለአርባ አመታት ያገለገሉት ዶክተር ጌታቸው ተድላ በፃፉት አንድ መፅሐፋቸው ውስጥ በምስራቅ አውሮፓ የሚገኙት ሶሺያሊስት ሀገራት (ሀንጋሪ፤ ቡልጋሪያ ወዘተ) የፊውዳል ስርዓት አስወግደው ሶሺያሊዝምን በመመስረት ሂደት ላይ ፊውዳሉን ሲያጠፉት ፊውዳል ሳይሆኑ በግል መሬት እየተኮናተሩ የሜካናይዝድ እርሻ የሚሰሩ ግለሰብ ኢንቬስተሮች ንብረታቸው ሳይነካ፤ ይልቁንም መንግስት በጋራ እንስራ በሚል ድጋፍ ይሰጣቸው ስለነበረ ሀገራቱ ከፊውዳል ስርዐተ ማህበር ወደ ሶሺያሊዝም በሚቀየሩበት ጊዜ ኢኮኖሚያቸው ብዙም ሳይጎዳ የለውጡን ጊዜ ማለፍ ችለዋል ብለው በስራቸው አጋጣሚ በቅርብ የሚያውቁትን እውነተኛ ታሪክ አስተምረውናል። በጣም ልብ በሚሰብር መልኩ በሀገራችን የዚያን ዘመን ብርቅዬ የሜካናይዝድ እርሻ ኢንቬስተሮች ከፊውዳሉ ጋር በአንድ ላይ “አድሀሪ” ተብለው ንብረታቸው በመወረሱና እርሻው እንዲወድም በመደረጉ በአስር አመት ሂደት ውስጥ (ከ1967 እስከ 1977 ዓ.ም.) ሀገሪቱ በታሪኳ አይታ የማታውቀውን የ1977ቱ ረሀብ (ከ1966ቱ ረሀብ ይበልጣል) ውስጥ ገብታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ህይወት ተቀጠፈ። እኛ የተከተልነው የሶሺያሊዝም ርዕዮት ዓይነት (version) ያተረፈልን አንዱ ቀሪ ውጤት (legacy) ይህ ነበር።                                                               ከዚህ በላይ የተጠቀሰው ችግር ሊፈጠር የቻለው ደርግ ከመጀመሪያውኑ የቅይጥ ኢኮኖሚ ስርዐት ባለመከተሉ ነበር። ደርግ ስልጣን በያዘበት ወቅት ላይ ሀገሪቷ የቅይጥ ኢኮኖሚ ስርዐት ብትከተል እንደሚጠቅማት ከዕውቀታቸውና ከልምዳቸው የተረዱ አንዳንድ በሳል የደርግ ባለስልጣናት (ለምሳሌ የደርግ ም/ሊቀ መንበር የነበሩት ኮሎኔል አጥናፉ አባተ) ነበሩ። ይሁን እንጂ የስልጣን ሽሚያ በመሀከላቸው ስለነበረ “አብዮቱን ለመበረዝ የሚጥሩ” የሚል ታፔላ ተለጥፎባቸው ሊረሸኑ በቁ። በጣም የሚገርመው ነገር ደርግ ስልጣን በያዘ በአስራ አራተኛው ዓመት፤ ማለትም በ1981 ዓ.ም. አካባቢ የቅይጥ ኢኮኖሚ ብሎ ቢያውጅም፣ አሁንም ጉዳዩ “ጅብ ከሄደ …” እንደሚባለው ተረት ሆኖበት ውጤት ሳያመጣ ቀረ። ስልጣኑ በእጃቸው የነበረው የደርግ አባላትም ነገሩ ሁሉ “አላዋቂ ሳሚ …..” እንደሚባለው ተረት ሆኖባቸው በማያባራ ጦርነትና በተሳሳተ የፖለቲካ ርዕዮትና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲደቅ ምክንያት ሆኑ።    
ሐ. የኤርትራን የፌደሬሽን ስርዐት አለመመለሱ፡ የደርግ መንግስት ስልጣን እንደያዘ ከእነ ሻዕቢያ ጋር ያለውን ቅራኔ የተባበሩት መንግስታት የወሰነውን የፈደሬሽን ጥያቄ እንዲመለስ በማድረግ ጦርነቱን ማስቆም ይችል ነበር ባይ ነኝ። ምክንያቱም “ፌደሬሽኑን እኔ አላፈረስኩትም፤ በመሆኑም ለመመለስ ዝግጁ ነኝ” የሚል በሳል አቋም ቢያራምድ ኖሮ በተባበሩት መንግስታትም ሆነ በእነ ሻዕቢያ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችልበት ሰፊ ዕድል ነበረው። ይሁን እንጂ ከአንዳንድ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በስተቀር የሰሜኑን የሻዕቢያ ጦርነት በሰላም የመፍታት አስተዋይነት ያለው የፖለቲካ ውሳኔ ሊወስድ የሚችል የጠለቀና ስትራቴጂያዊ ዕውቀት የነበረው የደርግ ባለስልጣን (ሊ/መንበር መንግስቱን ጨምሮ) ባለመኖሩ ደርግ በሚነደው የሰሜኑ ጦርነት ላይ ቤንዚን አርከፍክፎበት ለ17 አመታት በጦርነት እንድንለበለብ ምክንያት ሆኖ እልፍ ወገኖቻችንን ከሁለቱም ወገን አጣን። በወቅቱ የደርግን የውስጥ አሰራር በቅርበት የሚያውቅ አንድ ጓደኛዬ ሲያጫወተኝ፤ “ደርግ የካራማራውን የሶማሊያ ጦርነት አሸንፎ በቀይ ኮከብ ጥሪ ወደ ሰሜኑ ጦርነት ፊቱን ካዞረ ከ1974 ዓ.ም. ጀምሮ በሻዕቢያ ላይ ከፍተኛ ምት በማሳረፉ፤ ሻዕቢያ ፌዴሬሽኑ ከተመለሰልኝ ጦርነት አቆማለሁ የሚል አቋም የነበረው ቢሆንም፣ ደርግ በጀብደኝነት ጦርነቱን ቀጠለ፤ ከዚያም የሆነው ሁሉ ሆነ።” አለኝ። በ1975 ዓ.ም. አካባቢ ፌዴሬሽኑን የመመለስ ዕድል ከነበረ በ1967 ዓ.ም.፤ ማለትም ደርግ ስልጣን በያዘበት ዘመን፤ ፌዴሬሽኑን መመለስ ምን ያህል ቀላል እንደነበረ አስቡት! እንደው ነገሩ አስቆጭቶኝ ነው እንጂ እነ ፀሐፊ ትዕዛዝ አከሊሉ ሐብተወልድንና መሰል አዋቂና ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸውን ብርቅዬ የሐገሪቷን ልጆች ገድሎ ስለ ሰሜኑ ጦርነት አያያዝ ማን ይምከረው? እነሱን በማጥፋት ብቻ ሳይወሰን በሰሜኑ ጦርነትና በኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ከደርጉ መሐከል አስተዋይና ለዘብተኛ አቋም የነበራቸውን ሁሉ አጥፍቶ የለ? በመሆኑም ደርግ እንኳን አካታች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት ሊፈጥር ይቅርና ሀገሪቱን በሁሉም የፖለቲካና የኢኮኖሚ መለኪያዎች ወደ ኋላ ጎትቶና ዕድሜውን ጨርሶ ተሰናበተ።                                                 
(የ1981ዱ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተካሄደበት ወቅት ነገሮች ሁሉ ተበለሻሽተው በመጨረሻው፤ ማለትም በአስራ አንደኛ ሰአት፤ ላይ የተሞከረ በመሆኑ በግሌ ብዙ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣ ነበር የሚል እምነት አላሳደረብኝም።)
  የኢህአዴግ መንግስት፡ እንዳለፉት መንግስታት የኢህአዴግ መንግስትም የራሱ የሆነ ጠንካራ ጎን ነበረው። የግል ኢንቨስትመንት በአንፃራዊ መንገድ ሲታይ ያደገበት ወቅት ነበር። ለምሳሌ በአክሲዮን የተቋቋሙ የግል ባንኮች እንቅስቃሴን መጥቀስ ይበቃል። ይሁን እንጂ የብሔር ፖለቲካ “Ethnic politics” ከሚገባው በላይ እንዲቀነቀንና ብሔረሰቦች አንዱ ሌላውን በጠላትነትና በጥርጣሬ እንዲያይ መደረጉ፤ ወገንተኝነት፤ በተለይም የብሔር ወገንተኝነት ዓይን ያወጣ መሆኑና በሂደት ሙስና በጣም እያደገ መምጣቱ ፖለቲካው በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት እያጣ እንዲመጣና በሂደትም በውስጥ ሪፎርም አዲስ መንግስት እንዲመሰረት ምክንያት ሆነ። በመሆኑም የኢህአዴግ መንግስት ለአምስተኛ ጊዜ ያጋጠመን የታሪክ አጋጣሚ (junction) ቢሆንም፤ ወገንተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት ከመፍጠር ውጪ ያመጣው ነገር ባለመኖሩ ሀገሪቷን በትክክለኛ የዕድገት ጎዳና ላይ ሳያስገባት እሱም እድሜውን ጨርሶ ተሰናበተ።  
አዲሱ (የ2010ሩ ሪፎርም የፈጠረው) መንግስት፡ አሁን ያለው መንግስት በኔ አስተሳሰብ ስድስተኛው የታሪክ አጋጣሚ “Junction” ነው። ከላይ እንደገለፅኩት ይህም መንግስት የራሱ የሆነ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ያሉት ነው ብዬ አምናለሁ። ባለፉት አምስት አመት ከዘጠኝ ወራት አዲሱ መንግስት ጥሩ ሊባሉ የሚችሉ ሪፎርሞችንና የተለያዩ የሚታዩ ስራዎችን ሰርቷል። በአንፃሩ ደግሞ፤
ሀ. ብዙ ወገኖች እንደሚሉት በሀገሪቷ በአጠቃላይ የህግ የበላይነት በማስፈንና በድርድር ሰላማዊ ሁኔታን መፍጠር፤
ለ. የብሔር ፖለቲካን (Ethnic politics) በሂደት ማጥፋት፤
ሐ. ሙስናን ከህዝብ ጋርና በሲስተም ታግሎ ማጥፋት ወይም ቢያንስ ማዳከም፤
መ. የግል ኢንቬስተሮች የኢኮኖሚው ዋና አንቀሳቃሽ ኃይል እንዲሆኑ ለማድረግ የፖለቲካ ስርዐትና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ  የመፍጠር ፈታኝ ስራዎች ከፊቱ ይጠብቁታል። እንደ አንዳንድ ፅንፍ የረገጡ የፖለቲካ ቡድኖችና አክቲቪስቶች፣ አሁን ባለው መንግስት ተስፋ አልቆረጥኩም። ተስፋ አልቆረጥኩም ስል አሁን የሚሰራውን ሁሉንም ነገር እደግፋለሁ ማለቴ አይደለም። ለምሳሌ የብሔር ፖለቲካ፤ ማለትም፤ ብሔር-ተኮር የአስተዳደር ክልል፤ ለኢኮኖሚ ዕድገት በፍፁም አይጠቅምም፤ እንደውም የኢኮኖሚ ዕድገት ፀር ነው፤ (ምክንያቱም የዘር ፖለቲካ ከስረ መሰረቱ (from its very essence) ወገንተኛ ስለሆነ ነው።) ብለው ከሚያምኑ ወገኖች አንዱ ነኝ። በተግባር ብዙ ነገሮች አይተናልና። ይሁን እንጂ ይህንን ስርዐት ለመቀየር ጠመንጃ አንስተን መዋጋት አለብን ብዬም በፍፁም አላምንም። ምክንያቱም ለምዕተ አመታት በጦርነት የተሞላው የኢትዮጵያ ታሪክ በመደጋገም ያረጋገጠልን ሀቅ የጦርነት ውጤት መጠፋፋትና መደህየት መሆኑን ስላስገነዘበኝ ነው። (በአዲስ አድማስ ላይ “ሀገሬ ምን ተባልሽ” በሚል ርዕስ ያወጣሁት ፅሁፍ ይህን እውነት በደንብ ያሳያል።)      
   ማጠቃለያ፡ እስቲ አሁን እዚህ ላይ ቆም ብለን እራሳችንን እንመርምር። ከዚህ በላይ በወፍ በረር አንኳር ጉዳዮችን ልጠቃቅስ የሞከርኩት ያለፈውን 68 አመታት ታሪካችንን ነው። በእነኚህ አመታት በሰራናቸው ስራዎች ሀገራችንን ከድህነት ማውጣት አልቻልንም። ስለዚህ ሀገሪቷን ከድህነት ለማውጣት ምን መደረግ አለበት የሚለውን ከዚህ በታች የጠቀስኳቸው አካላት እንደሚያውቁት ባምንም፣ የኔን ነፃና ቅን ሀሳብ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
መንግሥት፡ መንግስት የሚሰራቸውን ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮች አጠንክሮ እንዲቀጥል አደራ እላለሁ። አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከሱ በፊት ከነበሩት ሦስት መንግስታት የበለጠ ዕድለኛ ነው ባይ ነኝ። ይህንን ስል ለማለት የፈለግሁት የንጉሱ፤ የደርግና የኢህአዴግ መንግስት፤ እያንዳንዳቸው የሰሩትን ጥሩ ጥሩ ነገሮች ያውቃል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከንጉሱ የፊውዳሊዝምን፤ ከደርግ በሶሺያሊዝም ርዕዮት ዓለም የተለወሰ ወታደራዊ አምባገነንነት እና ከኢህአዴግ የዘር ፖለቲካ አስከፊ ገፅታዎች ምን እንደሆኑ ክፍል ገብቶ በቲዎሪ ሳይሆን በተግባርና ከቅርብ ዘመናት የሀገራችን ታሪኮች በደንብ ትምህርት ቀስሟል። እኛም ለመማር ዝግጁ ከሆንን በደንብ ተምረናል። በመሆኑም የሦስቱን መንግስታት ደካማ ጎኖች ትቶ ወይም አርሞ፤ ጠንካራ የተባሉ ስራዎቻቸውን አጎልብቶና ዘመኑ ግድ የሚላቸውን አስፈላጊና ተጨማሪ ነገሮችን አካቶ ሀገሪቷን ቢመራ ወይም ከመራ በእርግጠኝነት ወደሚፈለገው የዕድገት ጎዳና ውስጥ መግባት አያዳግተንም ባይ ነኝ። በዚሁ መንፈስ አሁን ያለው መንግስት በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ቢያተኩር ይጠቅመናል እላለሁ።
ሀ. ሰላምን ማስፈን፡ መንግስት ሲባል የሀገር አስተዳዳሪ ስለሆነ የተለያዩ ወገኖች እንዳሉት ነፍጥ አንግበው ወደ ጫካ የገቡ ወገኖች ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመጡ ተስፋ ባለመቁረጥ በሆደ ሰፊነትና በሰጥቶ መቀበል መርህ(win-win conflict) የሚቻለውን ጥረት ሁሉ ማድረግ፤ ሰላም ሳይኖር ዕድገት ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል። (ይህን ስል መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ለሚያደርገው ጥረት አውቅና ሰጥቼ ነው።)
ለ. ሙስና፡ ሙስና የቆየ ታሪክ ቢኖረውም፤ በተለይም በኢህአዴግና በአሁኑ ዘመን በጣም የተስፋፋ ነቀዝ ነው። በመሆኑም ትግሉ እጅግ ውስብስብ እንደሆነ በግል ቢገባኝም፤ ሲስተም በመዘርጋትና ከህዝብ ጋር አንድ ላይ ሆኖ መታገል ይረዳናል። ሙስና ለግል ኢንቨስትመንት ማበብ እንቅፋት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ መንግስት በዚህ ረገድ የጀመረውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አምናለሁ።  
ሐ. የብሔር ፖለቲካ፡ በአጠቃላይ ሲታይ ይህንን ፈሪሀ እግዚአብሄር ያደረበትን ትሁት (humble) ህዝባችንን ከብሄር ፖለቲካ አስተዋይነት ባልጎደለው ተግባራዊ ርምጃ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መንጭቆ ማውጣት፤ (ከተሳሳትኩ ለመታረም ዝግጁ መሆኔን እየገለፅኩ)፤ ብሔር-ተኮር የአስተዳደር ክልል እያለ ጠንካራ፤ አስተማማኝና የማይዋዥቅ (stable) የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት የህልም አንጀራ ይመስለኛል። በብሔርና በቋንቋ መሻኮት በምንም መለኪያ ለዚህ ዘመን የማይመጥንና፤ የአላዋቂ ወይም የመሰሪ ስራ ሲሆን ከጀርባ ሀገሪቷ ከእርስ በርስ ጦርነትና ሽኩቻ እንዳትወጣ የሚፈልጉ የውጪም ሆነ የሀገር ውስጥ ቡድኖች የተንኮል ስራ ውጤት ነው ብዬ አምናለሁ። የውጪዎቹ ቡድኖች የሀገሪቷን ዕድገት የማይፈልጉ ሲሆኑ፤ የውስጥ ቡድኖች ያልኳቸው ደግሞ በብሔርና በቋንቋ ፖለቲካ ሽፋን አለአግባብ የግል ጥቅም የሚያገኙ ወገኖች ናቸው የሚል ዕምነት አለኝ። ህዝቡማ ነፃ እናወጣሀለን በሚሉ ቡድኖች ቁም ስቅሉን እያየ ነው። መፍትሔው ቀጥተኛና ግልፅ ነው። ለሁሉም እኩልነትን፤ መልካም አስተዳደርንና ዲሞክራሲን በተግባር መሬት ላይ አውርዶ መተግበር ነው።
ሐ. የግል ሀብት፡ የግል ባለሀብቱ በሂደት(eventually) የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር እንዲሆን፤ ተጨማሪ ጊዜ ሳናጠፋ፤ የፖለቲካ ስርዓትና የኢኮኖሚ ማሻሻያ በአፋጣኝ ማድረግ፤ የተጀመሩትንም አጠናክሮ መቀጠል።
መ. የፖለቲካ ትኩሳት፡ እንደ ወልቃይት ፀገዴ የመሳሰሉ የፖለቲካ ትኩሳታቸው ከፍተኛ የሆኑ ጉዳዮችን በአስተዋይነትና በጥበብ ከህዝብ ጋር ሆኖ መፍትሄ መስጠት።
በሰላም ለሚታገሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፡
ሀ. አስተያየት፡ መንግስት ጥሩ ሲሰራ ማመስገን፤ ማበረታታት፤ ሲሳሳት ደግሞ ገንቢና የሚያርም አስተያየት ለመስጠት ወደ ኋላ ባይሉ ብዙ ጠቀሜታ አለው ባይ ነኝ። እዚህ ላይ ይህን አስተያየት የሰጠሁት ሆነ ብዬ ነው። የኛ የፖለቲካ ባህል እንደሚታወቀው፤ ታሪካችንም እንደሚያስተምረን፤ የምንቃወመው የፖለቲካ ፓርቲ ጥሩ ነገር ሲሰራ ሁለቱ አይኖቻችን ይከደናሉ፤ ጆሮዎቻችንም መስማት ይሳናቸዋል። መጥፎ ሲሰራ ወይም ሲሳሳት ደግሞ ሁለቱ አይኖቻችን እንደ አራት አይን ማየት፤ ሁለቱ ጆሮዎቻችን ደግሞ እንደ አራት ጆሮዎች ሆነው መስማት ይጀምራሉ። ይህ የፖለቲከኞቻችን ዝንባሌ አጠፋፋን፤ ሀገሪቷን በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አደረጋት እንጂ ምንም የፈየደው ነገር የለም።
ለ. ጦርነት፡ መንግስትና ነፍጥ ያነሱ ወገኖች ወደ ክብ ጠረጴዛ መጥተው ልዩነቶቻቸውን በውይይት የሚፈቱበትን ሁኔታ ለመፍጠር የራሳቸውን ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ነፍጥ ያነገቡ ወገኖች፡
ሀ.“ሀገሬ ምን ተባልሽ” ብዬ በሰየምኩትና ባለፈው ጊዜ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ባወጣሁት ፅሁፌ፤ ኢትዮጵያ ላለፉት 827 አመታት (ዘንድሮ 828 አመታት ሆኖታል) ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ለአንዲት 10 ተከታታይ አመታት እንኳን ከጦርነት ነፃ የሆነችበት ጊዜ የለም የሚል ታሪክ ሰፍሯል። ይህ ታሪክ አያሳዝንም? መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲ ወይም በእንግሊዝኛው “just cause” ለማምጣት በሚል ነፍጥ ያነሳችሁ ወገኖች መቼም የጦርነት መጨረሻ ምን እንደሚሆን ለናንተ አልነግራችሁም። የትላንት ታሪካችንን፤ ማለትም የደርግና የኢህአፓን ታሪክ ዞር ብለን ማስታወስ ብቻ ይበቃናል። ከስምንት መቶ አመት በላይ በጦርነት ለኮሰመነች ሀገር ሌላ ተጨማሪ ጦርነት መፍትሔ ያመጣላታል ብሎ ማሰብ የጤና አይመስለኝምና እባካችሁ አስቡበት። ከዚህ በላይ ለመንግስትም ሆነ ነፍጥ ላነገቡ ወገኖች የተናገርኩት ሁሉ በግል ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፍላጎት ኖሮኝ ሳይሆን ብንተባበር ይህቺን ሀገር ከድህነት ለማውጣት ምንም የሚያግደን ነገር አለመኖሩን አስረግጬ ለመናገር ነው። እናንተን ጎንተል ሳደርግ “ይቺ የመንግስት ቡችላ ነች!”፤ መንግስትን ስተች ደግሞ “ይሄ የአክራሪ ተቃዋሚ ደጋፊ ነው” ልባል እንደምችል እገምታለሁ። እኔ በዚህ የጡረታ ዘመኔ የሁለቱም ሳልሆን የራሴው ነኝ። የእኔ የውስጥ ፍላጎት(Inner motive) ይህቺ ሀገር ከድህነት ወጥታ ማየት ነው። በቃ። ምክንያቱም በጋራ ሀገሪቷን ከድህነት ማውጣት ከቻልን በሌሎች ተራና በማይረቡ ምክንያቶች የምንባላው ነገር ሁሉ ይከስማል የሚል እምነት ስላለኝ ነው። እንደሚታወቀው ኢኮኖሚ ካደገ ስራ-ፈት ይቀንሳል፤ ስራ-ፈት ከቀነሰ ደግሞ “An idle mind is the workshop of devil”; ሲተረጎም “ስራ-ፈት አእምሮ የሰይጣን የስራ ቦታ ነው”፤ የሚለው አባባል እድል ፈንታ አያገኝም ወይም ቢያንስ የሚያገኘው ዕድል ይቀንሳል።  በመሆኑም ከምንም ነገር በላይ ይህቺ ሀገር ከድህነት እንድትወጣ በፅኑ ከሚመኙና ተስፋ ከማይቆርጡ እልፍ ዜጎች አንዱ ነኝ።
የተለያዩ ሚዲያዎች የሚጠቀሙ ተቃዋሚ አክቲቪስቶች፡
 በመንግስትና ነፍጥ ባነሱ ወገኖች መሀከል የሚደረገውን ጦርነት እያራገቡ ጦርነቱ እንዲፋፋም የሚጥሩ ወገኖች ለኢትዮጵያ ዕድገት የሚሰሩ ናቸው ለማለት ያዳግተኛል። እናንተም የፖለቲካ አክቲቪስቶች ለ “just cause” ነው የምንሰራው የምትሉ ከሆነ ትክክለኛውና የሰለጠነው መንገድ የትኛው እንደሆነ ለናንተ ማስረዳት ለቀባሪው ማርዳት ስለሚሆንብኝ አልሞክረውም። መንግስትን መደገፍ ወይም አለመደገፍ የናንተ ምርጫ ስለሆነም እዛ ውስጥ አልገባም። ነገር ግን የወቅቱ ዋናው ጉዳይ መንግስትና ነፍጥ ያነሱ ወገኖች በሰላም ወደ ድርድር እንዲገቡ ማድረግ ስለሆነ፤ እናንተም የራሳችሁን አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባኋችል ባይ ነኝ። ምክንያቱም ሰላም ለኢኮኖሚ ዕድገት አብይ ቅድመ ሁኔታ(prerequisite) መሆኑን ለናንተ ማስታወስ አይጠበቅብኝም፡፡  
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፡
ፅናትና አካታችነት፡ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥረት በሀገራችን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብለው ተስፋ ከሚያደርጉ ዜጎች አንዱ ነኝ። ምክንያቱም ሌላ የተሻለ አማራጭ የለማ! በመሆኑም ኮሚሽኑ እስካሁን ላደረገው ጥረት እያመሰገንኩ፤ ለወደፊቱም ስራቸውን በፅናት እንዲቀጥሉና ምክክሩም ሁሉንም ያካተተ (በተለይ ነፍጥ ያነሱ ወገኖችንም ጨምሮ) እንዲሆን የሚቻላቸውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርጉ አደራ እላለሁ።
 ህዝብ፡
ሀ. እንመርምር፡ የአንድን ግለሰብ (ቡድን) ትክክለኛ ባህርይ፤ ፍላጎትና ድርጊት ሳናውቅ የሚያወራውን ብቻ ሰምተን እንደ ትክክለኛ መረጃ ባንወስደው ይበጃል እላለሁ። የዚህን ሀሳብ እውነተኛነት የሚከተለው የእንግሊዝኛ አባባል ጥሩ ገልፆታል። “A man is what he do: not what he talks he will do.” ሲተረጎም የሚከተለውን ይመስላል። “የሰው ማንነት የሚታወቀው አደርገዋለሁ ብሎ በሚያወራው ሳይሆን በሚያደርገው ነገር ነው።” ልብ እንበል።
ለ. ልብ ያሳርፋል፡ የተወሰነው የህዝብ ክፍል በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ቢወናበድም፤ አብዛኛው የህዝብ ክፍል፤ “The silent majority” የሚባለው ሁኔታዎችን በትዕግስትና በአስተዋይነት የሚከታተልና የሚመዝን በመሆኑ ልብ ያሳርፋል ባይ ነኝ። ሀገሪቷ ወደ ብጥብጥና ትርምስ(chaos) ብትገባ ለማንም የማይበጅ ስለሆነ ከጎረቤቶቻችን ትምህርት መውሰድ እንደማይከብደን አምናለሁ።
ከዚህ በላይ ለተጠቀሱ ወገኖች በሙሉ፡
ሀ. እናስተውል፡ ሀገራችን ባለፉት ስልሳ ስምንት አመታት ውስጥ ባጋጠሟት የመጀመሪያዎቹ አምስት የታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ የመረጠችው ወይም የሄደችባቸው አማራጮች እንደ አለመታደል ሆኖ በፍፁም ትክክል ያልሆኑትን፤ በእንግሊዝኛው “worst case scenario” የሚባሉትን አማራጮች ነው። የተከተልናቸውን አማራጮች ውጤት ለመረዳት አሁን ያለንበትን ሁኔታ ከእነ ቻይና፤ ኮሪያና ማሌዢያ ጋር አወዳድሮ ማየት ብቻ ይበቃል። ከስልሳና ሰባ አመታት በፊት ሀገራችን ከእነ ቻይና፤ ኮሪያና ማሌዢያ ጋር ስትወዳደር የምትሻል ወይም ቢያንስ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ የምትገኝ እንደነበረ ይታወቃል። አሁንስ? መልሱን ለናንተ እተወዋለሁ። መቼም ለስድስተኛ ጊዜ “worst case scenario” ለመከተል የሚፈልግ ወገን እንደማይኖር እርግጠኛ ነኝ።  በመሆኑም ሁላችንም በማስተዋል ሀገራችንን ወደ ትክክለኛው የዕድገት ጎዳና ማስገባት የውዴታ ግዴታችን ነው እላለሁ። ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ቢያንስ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራ የሚፈለገውን ውጤት በማምጣት እንዲጠናቀቅ የራሳችንን አስተዋፅኦ እናድርግ እላለሁ። ለራሳችን ስንል እንወቅበት። እናስተውል።
ምርጫው የኛ ነው፡ ስሙን ለጊዜው የማላስታውሰው አንድ ትልቅ የማኔጅመንት ምሁር (Management Guru) በአንድ ወቅት “A nation gets what it deserves.” ማለቱ ትዝ ይለኛል። ይህን ሀይለኛና አስተማሪ አባባል ሲናገር ምን ለማለት እንደፈለገ በእንግሊዝኛ ያብራራውን በአማርኛ እንደዚህ ተርጉሜዋለሁ። “የአንድ ሀገር መንግስትና ህዝብ ዕድገት ለማምጣት መሰራት ያለባቸውን የተለያዩ ስራዎች በቅደም ተከተል፤ በጥንቃቄና በላቀ አፈፃፀም የሚከውኑ ከሆነ ሀገሪቷ ታድጋለች፤ ትመነደጋለች። በተቃራኒው ደግሞ መሰራት ያለበት ነገር ችላ ተብሎ ከታለፈና ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ለረዥም ጊዜ ከተሄደ ሀገሪቷ ትደኸያለች፤ በችጋር ትማቅቃለች። በሁለቱም መንገድ ሀገሪቷ የሰራችውን ወይም የእጇን ነው የምታገኘው፤ በሌላ አነጋገር የዘራችውን ነው የምታጭደው።” በመሆኑም ምርጫው የኛ ነው።

Read 345 times