Saturday, 28 March 2020 11:42

ሰውየው ከውሻው ጋር

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ሰውየው ከውሳው ጋር እየተጓዘ ነው፤ የአካባቢውን ውበት በተመስጦ እያደነቀ:: ድንገት ግን አንድ ነገር ተከሰተለት-ለካንስ ሞቷል፡፡ አዎን…ለካንስ እሱም ሆነ ይሄ እግሩ ስር ኩስኩስ የሚለው ውሻ ከሞቱ ሰነባብተዋልና፡፡ መሞቱን መዘንጋቱ ደንቆታል፡፡ ምናልባትም ገና በቅርቡ በመሞቱ ይሆን? ይሆናል፡፡ ብቻ እሱና ውሻው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ እናም ከአንድ ካማረ ቤተ መንግሰት ከሚመስል፣ የተሰራበት ዕምነ በረድ ከሚያንፀባርቅ ትልቅ ህንፃ አጠገብ ሲደርስ ቆመ፡፡ በትልቅ ኮረብታ አናት ላይ በታላቅ ግርማ ሞገስ ጉብ ያለው ህንፃ ከፊቱ በአንፀባራቂ ቅስት አሸብርቋል፡፡ በቅስቱ ስር የሚያምር መግቢያ ተመለከተ፡፡ ወደ መግቢያው የሚወስደው መተላለፊያ በወርቅ ተለብጧል፡፡ እንዴት ያለ ቅጥር ነው ሲል አሰበ፡፡ በመተላለፊያው ወደ በሩ ሲጠጋ፣ የቅጥሩ ጠባቂ የመሰለ ሰው ተመለከተ፡፡
“ይቅርታ፤ ይህ ቦታ ምን የሚሉት ቦታ ይሆን?” ጠየቀ ሰውየው፡፡
“መንግስተ ሰማያት ነው ጌታው!” ሲል መለሰ ጠባቂው፡፡
“ግሩም ነው…” አለ ሰውያችን፤ “ጥቂት ውሃ ማግኘት እንችላለን? እኔና ውሻዬ በውሃ ጥም ጉሮሯችን እንዴት ተቃጥሏል መሰለህ…”
“ምን ችግር አለ…” አለ ጠባቂው፤ “አሁኑኑ ጥም ቆራጭ ቀዝቃዛ ውሃ ይቀርብላችኋል::”
ጠባቂው ይህን ብሎ በሩን እየከፈተ፤ “ግን ጌታው…አለ፤ “ወደዚህ ወደ መንግስተ ሰማያት ገብተህ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በረከት መቋደስ ትችላለህ፤ ግን ወደዚህ መግባት የምትችለው ብቻህን ነው:: የቤት እንስሳም ሆነ ሌላ ተቀጥላ ጓደኛ ይዞ መግባት አይቻልም” አለ ሰውዬው እግር ስር ኩስኩስ እያለ የሚከተለውን ውሻ እየተመለከተ፡፡
ሰውዬው ዕጢው ዱብ አለ፡፡ ትንሽ አመነታ፡፡ ግን ወሰነ፡፡ ጓደኛዬን ውሻዬንማ ጥዬ አልገባም ብሎ በውሃ ጥም ጉሮሮው እየነደደ፣ ጀርባውን ለሚያምረው ህንፃ ሰጥቶ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ከረጅም አድካሚ ጉዞ በኋላ ደግሞ ሰውዬውና ውሻው ከአንድ ኮረብታ ቦታ ደረሱ፡፡ ከኮረብታው ስር ወደ አንዳች ቅጥር ግቢ የሚያመራ በጭቃ የላቆጠ የእግር መንገድ ይታያል፡፡ መንገዱ በእርሻ ውስጥ የሚያልፍ ሆኖ መላው ቅጥሩ አንዳችም አጥር የለውም፡፡ በሩ መቼም ተዘግቶ የሚያውቅ አይመስልም፡፡
መቼም ተዘግቶ ወደ ማያውቀው በር ሲጠጋ፤ ዛፍ ስር ደገፍ ብሎ መጽሐፍ የሚያነብ አንድ ሰው ተመለከተ፡፡
“ይቅርታ የኔ ወንድም፤ ጥቂት ውሃ ይኖርሃል…? በውሃ ጥም…” ከማለቱ፤ በቅጥር ግቢው ውስጥ ያለው ሰውዬ፤ “እንዴታ…” አለ፤ “እዛ ጋ ቧንቧ አለልህ፤ ሄደህ የፈለግከውን ያህል መጠጣት ትችላለህ፡፡”
ሰውዬው ቀጠለና ጠየቀ፤ “ይሄ ጓደኛዬ…” ብሎ ወደ ውሻው እየጠቆመ፤ “ውሃ ጥሙ ክፉኛ በርትቶበታል፤ እሱም ገብቶ መጠጣት ይችል ይሆን?”
“ይችላል” አለ ሰውዬው፤ “እንዲያውም ከቧንቧው አጠገብ መጠጫ አለልህ፡፡” ሰውዬውና ውሻው ተደስተው ወደ ቅጥሩ ገብተው ጥማቸው እስኪቆርጥ ከጠጡ በኋላ፣ ወደ ሰውዬው ተመልሰው መጡና፤ ሰውዬው እንዲህ ሲል ጠየቀ፤ “ለመሆኑ ይህ ቦታ ምን የሚሉት ቦታ ይሆን?”
“መንግስተ ሰማያት ነው” ሲል መለሰ ሰውዬው፤ አይኖቹን እንኳ ከሚያነበው መጽሐፍ ላይ ሳይነቅል፤ በታላቅ የዕረፍት ስሜት ዛፍ ስር ደገፍ ብሎ በተቀመጠበት፡፡
“ይሄማ እንዴት ሊሆን ይችላል” አለ ሰውዬው ግራ ተጋብቶ፤ “ቅድም ያጋጠመኝ ያማረ ህንጻም፤ መንግስተ ሰማያት ነው ብለውኛል፡፡ እንዴት ሊሆን ይችላል?”
“እህ…” አለ ዛፉ ስር የተቀመጠው ሰውዬ፤ መጽሐፉን እልባት አስይዞ እያጠፈ፡፡
“ያ ታላቅ ቅስት ያለው ባለ እምነበረዱ ሕንፃ…? መንገዱ በወርቅ የተለበጠው…? ከሱ ህንጻ በማምለጥህ ደስታ ሊሰማህ ይገባሃል፡፡ እሱ ህንጻ አላወቅከውም እንጂ፣ ንጽህናህ አዳነህ እንጂ ገሃነም ነው” አለ፡፡
“እንዴት” አለ ሰውዬው በጉዳዩ ይበልጥ ግራ ተጋብቶ፡፡ “እሺ ይሁን ይሄ መንግስተ ሰማያት ይሁን፤ ግን በስማችሁ ሲነግዱ እንዴት ዝም አላችሁ?”
“እንዴት ዝም አላችሁ ነው ያልከኝ…” አለ ሰውዬው፤ “ዝም ማለት ብቻ አይደለም፣ እንዲያውም በጉዳዩ ደስተኞች ነን፡፡ አየህ…”አለ ሰውዬው፤ “ያ ላዩን ያማረ ህንጻ፣ ያ ገሃነም፣ ጓደኞቻቸውን ጥለው የሚሄዱ፣ ወዳጆቻቸውን በቁርጥ ቀን ጥለው የሚሄዱ ሰዎችን አጣርቶ ስለሚወስድልን፣ ደስተኞች ነን፡፡”
(ምንጭ፡- “ግሩም  የዓለማችን ምርጥ ታሪኮች”)

Read 3588 times