“በ1ኛው ዙር ጓደኛዬ ስትመዘገብ የሚጠቅም ስላልመሰለኝ፣ ‹መዝግበው ምን ሊያደርጉን እንዳሰቡ ታውቂያለሽ? ከዚህ የከፋ ነገርስ ቢያጋጥመንስ? ምኑንም ሳታውቂ ዝም ብለሽ ትመዘገቢያለሽ?› በማለት አከላክለናት፡፡ እሷ ግን ‹የትም ቢወስዱኝ ከጎዳና ሕይወት አይከፋብኝም እሄዳለሁ› ስትል ተከራከረች፡፡ ‹ይቅርብሽ፤ ድረሱልኝ ብለሽ ብትጮሂ ማንም የማይሰማሽ አፋር በረሃ ወስደው ነው የሚያጉሩሽ አሉ፡፡ የእኛን ሐሳብ ብትሰሚ ይሻላል፡፡ ….› እያልን ለማሳመን ብንሞክርም እንቢ ብላ ሄደች፡፡
“እኛም ሰቆቃዋን ለመስማት ስንደውልላት፣ ‹ምንም ችግር የለም፤ እናንተ እንዳሰባችሁት አይደለም ሁሉም ነገር ጥሩ ነው፡፡ የፈራነው የውሃውን ችግር ነበር፣ እሱም አለ፡፡ ምግቡ፣ ሕክምናው፣ መኝታው፣ ሥልጠናው… ጥሩ ነው። ትንሽ ያስቸገረን ሙቀቱ ነው፡፡ ቀንና ሌሊት የለውም። ላብሽ ይንዠቀዠቃል። እሱንም ቢሆን ሻወር ስላለ ለቅለቅ ስንል ለጊዜውም ቢሆን እፎይ እንላለን። አካባቢውን ስንለማመድ ደግሞ ይተወናል።› ትለን ነበር፡፡ ‹ስትሄድ ስላከላከልናት ነው እንዲህ የምትለው፤ እኛ የእሷን ፀባይ መች አጣነው? ካሁኑ ሙቀት ምናምን ማለት ጀምራለች። ምን አለፋችሁ፣ በቅርብ ቀን ጥላ ትመጣለች› ብለን ስንጠብቅ ወራት ተቆጠሩ፡፡ ትንሽ ቆይታ ‹በአውቶሞቲቭ ሙያ ልመረቅ ነው› አለችን፡፡
እውነቱን ስንረዳ ግን እሷ ሳትሆን እኛ ነበርን ስህተተኞቹ፡፡ አሁን እሷ በአንድ ድርጅት ተቀጥራ በሙያዋ እየሰራችና ጥሩ ደመወዝ እየተከፈላት ነው፡፡ ‹ምነው ያኔ አብሬአት ተመዝግቤ ቢሆን ኖሮ› በማለት ቁጭት ገባኝና በ2ኛው ዙር ለመመዝገብ ወሰንኩ” ብላለች ከሐረር ከአካባቢ የመጣችው የ19 ዓመቷ ወጣትና በዚህ ሳምንት በአፋር ክልል በአሚባራ ወረዳ ከተቋቋመው አዲስ ራዕይ ማሰልጠኛ ማዕከል በ2ኛ ዙር በልብስ ስፌት (ጋርመንት) ሙያ የተመረቀችው ራሄል፡፡
ራሔል እናትና አባቷን በሞት ስለተነጠቀች ዘመድ ቤት ነበር ያደገችው፡፡ ወደ ታዳጊነት ዕድሜ ስትጠጋና ፍላጎቷ ሲጨምር ያደገችበት የዘመድ ቤት ሊመቻት አልቻለም፡፡ በየጊዜው ጭቅጭቅና ንትርክ ሆነ፡፡ መስማማት ስላቃታት ከቤት ወጥታ ለ5 ዓመት የጎዳና ሕይወት አሳለፈች፡፡ “የጎዳና ህይወት አይመችም፡፡ በተለይ ለሴት ልጅ በጣም አስቀያሚና አሰቃቂ ነው፡፡ መደብደብ፣ ተገዶ መደፈር፣ ህልውና ማጣት፣ ረሃብ፣ ሱሰኛ መሆን፣… በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ ከዚህ መጥፎ ህይወት ቢሻል ብዬ መስተንግዶ ጀመርኩ፡፡ ሁለቱም አንድ ናቸው - የሲኦል ኑሮ” በማለት በምሬት ገልጻለች፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ለልመናና ለጎዳና ህይወት የተጋለጡ ዜጎች በጣም በርካታ ናቸው። እነዚህ ዜጎች የአገሪቷ ሀብት ተቋዳሽ አልሆኑም፤ በጉልበትና እውቀታቸው የልማቷ ተሳታፊ መሆንም አልቻሉም። ይህን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት መንግሥት የተለያዩ ዘዴዎችን ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይናገራል፡፡
የ2ኛው ዙር ምረቃ የክብር እንግዳና ከፍተኛ ውጤት ላመጡት ሰልጣኞች ሜዳሊያ የሰጡት የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ባደረጉት ንግግር፤ የከተማው መስተዳድር ከ2003 እስከ 2005 60 ሚሊዮን ብር መድቦ፣ በአራት ዙሮች 10ሺህ ያህል የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደመጡበት ቀዬ መመለሱን፣ አሰልጥኖ በአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያደራጃቸው ሰዎች ከ30 ሚሊዮን በላይ መቆጠባቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ መንግሥት ይህን ስር ሰድዶ የቆየውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በቅንጅት ካልሆነ በስተቀር ብቻውን መወጣት አይችልም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ለዚህም የሚያቀርቡት ማስረጃ፣ መንግሥት በቅርብ ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ በልመናና በጎዳና ተዳዳሪነት ተሰማርተው የነበሩትን ዜጎች አሰልጥኖ መቋቋሚያ ሰጥቶ ወደቀያቸው ቢመልስም ጥለው ተመልሰው በለመዱት ሥራ ተሰማርተዋል ይላሉ፡፡
መንግሥትም ይህን ችግር ለመቅረፍ ከሌሎች አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት በመጀመሩ ባለፈው ዓመት መጨረሻ አካባቢ ከብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽንና ከኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ጋር በመሆን ባቋቋመው አዲስ ራዕይ ማሰልጠኛ ማዕከል፣ 3,600 የ1ኛ ዙር ሰልጣኞች ማስመረቁን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
የ2ኛው ዙር ሰልጣኞች 4130 መሆናቸውን የጠቀሱት የማዕከሉ አዛዥ ኮሎኔል ገብሩ ገ/ጻድቅ፤ ሰልጣኞቹ በቆይታቸው የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ኦፕሬሽንና ጥገና፣ የፋብሪኬሽን (የብረታብረት)፣ የጨርቃጨርቅ (ጋርመንት)፣ የኦቶሞቲቭ፣ የእርሻ መሳሪያዎችና ማሽኒንግ ሙያ በንድፈ ሐሳብና በተግባር መከታተላቸውን፣ 4003 ወንዶችና 136 ሴቶች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈተና (COC) ወስደው 4130 ሰልጣኞች በከፍተኛ ብቃት ማለፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ከተመራቂዎቹ መካል 1,777 በስኳር ኮርፖሬሽን፣ 1,068 በብረታ በረትና ኢንጂነሪንግ፣ እንዲሁም 240 በአዲስ አበባ መስተዳድር በተለያዩ ቢሮዎች በሾፌርነት መመደባቸውን ጠቅሰው፤ 1,045 ቀጣሪ እስኪያገኙ ድረስ ብረታ ብረትና ኮርፖሬሽንና ኤልሻዳይ አሶሴሽን አስፈላጊ ድጋፍ እያደረጉላቸው በብረታ ብረት ኮርፖሬሽን የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ተመድበው ይቆያሉ ብለዋል፡፡
ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የአጠቃላይ የካምፕ ግንባታና የፋሲሊቲ አቅርቦት፣ አመራር፣ አሰልጣኞችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች መመደቡን፣ ለስልጠናው የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች ማቅረቡን እንዲሁም ለማሽነሪዎቹ የነዳጅ አቅርቦትና ጥገና ማድረጉን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንድ አምቡላንስና አንድ ፒክ አፕ መኪና መስጠቱን፣ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና የሚሰጡ ባለሙያዎችን ማሰልጠኑንና የፈተናውን አጠቃላይ ወጪ መሸፈኑን፣ ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ደግሞ የምግብ የአልባሳትና የጤና አገልግሎት ወጪ መሸፈኑን አዛዡ አስረድተዋል፡፡
አምና ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ በመጀመሪያው ዙር ምረቃ፤ “ይህ ሥራ ሥልጠናና ሥራ ማስያዝ ብቻ ሳይሆን የተረሰና የተዘነጉ ወገኖችን የመለወጥ፣ መንፈስ የማንቃት፣ አመለካከትን የመቀየር ከባድ ሥራ መሆኑ፣ ወገኖቻችንን ቀስቅሶ የልማቱ ተጠቃሚም ጠቃሚም የማድረግ ትልቅ ትዕግስት ይጠይቃል” ማለታቸውን የጠቀሱት የግብርና ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሳ፤ ለዚህ ስራ ሁሉም በኃላፊነትም ይሁን በዜግነት ወይም በሰው ልጅነቱ ብቻ ያለ ቀስቃሽ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል በማለት ሊረባረብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ልመናና የጎዳና ተዳዳሪነት ከአገራችን ባህልና ታሪክ፣ ከህዝባችን ጨዋነት፣ ከሞራልና ከሥነ-ምግባር፣ ከእምነትና ማኅበራዊ እሴቶች አንፃር ሲታይ አስነዋሪ ድርጊት የመሆኑ ጉዳይ ክርክር እንደማያስነሳ የጠቀሱት የሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስትር አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ፤ ልመናና የጎዳና ተዳዳሪነት ሠርቶ የመኖር ፀጋን እየሸረሸረ፣ ተመፅዋችነትና ጥገኝነት እንዲስፋፋ፣ የመልካም አገራዊ እሴቶች ገፅታ እንዲበላሽ አፍራሽ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
Tuesday, 14 April 2015 08:34
የወገኖችን መንፈስ የማንቃት ሥራ!
Written by መንግሥቱ አበበ
Published in
ንግድና ኢኮኖሚ