Saturday, 30 January 2016 12:28

በአፍሪካ ድህነት እየቀነሰ መሆኑን አፍሮ ባሮሜትር አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በቂ ምግብና ንፁህ የመጠጥ ውሃ አሁንም የብዙ ሚሊዮን አፍሪካውያን የዕለት ተዕለት ፈታኝ ችግር ነው፡፡ ይሁን እንጂ አፍሮ ባሮሜትር ጥናት ካደረገባቸው ሦስት አገራት በሁለቱ የድህነት መጠን መቀነሱን ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ የዛሬ ሳምንት በአዲስኒያ ሆቴል 6ኛውን የ2014/15 የፖሊሲ ሪፖርት ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ ከሦስት ዓመት በፊት ከወጣው 5ኛው ሪፖርት ጋር ሲነፃፀር ይኼኛው የተሻለ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በ33 የአፍሪካ አገሮች ለ57, 700 ዜጎች ቃለመጠይቅ ተደርጎ በቂ ምግብ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ ሕክምና፣ በቂ የማብሰያ ነዳጅና ጥሬ ገንዘብ አላገኘንም ያሉት የ22 አገራት ዜጎች ስለሆነ፣ ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀር በቤተሰብ ደረጃ የሚታየው ድህነት እየቀነሰ መሆኑን ያመለክታል ብሏል፡፡
ድህነት አሁንም በአፍሪካ ተንሰራፍቷል የሚለው ሪፖርቱ፤ በተደረጉ 10 ጥናቶች፣ ቃለ - ምልልስ ካደረጉ ሰዎች መካከል ከአራት ዜጎች በላይ በቂ ምግብ አላገኘንም ብለዋል፡፡ ይህም በመቶኛ ሲሰላ 44 ከመቶ ይሆናል፡፡ ቢያንስ በዓመት አንዴ ወይም ሁለቴ በተደረገው ጥናት፤ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዳላገኙ የጠቀሱት ከመቶ 46 ሰዎች ናቸው። በቂ ሕክምና ያላገኙት ደግሞ በርካታ ናቸው - 49 ከመቶ፡፡ የማብሰያ ነዳጅ የማያገኙት ከመቶ 38 ሲሆኑ፣ ምንም ገቢ የሌላቸው 7.4 ከመቶ መሆናቸውን ጥናቱ አስታውቋል፡፡
በአኅጉሩ የሚታየው ድህነት በጣም የተለያየ ስለሆነ በተመሳሳይ ሁኔታ ሁሉንም አፍሪካ ድሃ ነው ብሎ መፈረጅ አይቻልም ይላል ሪፖርቱ። በጋቦን፣ በቶጎ፣ በላይቤሪያ ድህነት በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍቷል፡፡ በሞሪሽስ፣ በኬፕ ቬርዴና በኤልጄሪያ ደግሞ ዝቅተኛ ነው፡፡ የጋቦንና የቶጎ ዜጎች፣ ከሞሪሽስ ዜጎች ጋር ሲነፃፀሩ በአማካይ 18 ጊዜ በበለጠ ድህነት ይኖራሉ፡፡ ከኬፕ ቬርዴ ነዋሪዎች ጋር ሲተያዩ አራት ጊዜ የበለጠ እንዲሁም ከአልጄሪያ ዜጎች ከሁለት ጊዜ በላይ በድህነት ይኖራሉ፡፡
በጣም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩት በማዕከላዊና በምዕራብ አፍሪካ አገራት የሚኖሩ ዜጎች ሲሆኑ፣ አነስተኛ የድህነት ደረጃ የሚታይባቸው የሰሜን አፍሪካ አገሮች ናቸው፡፡ አፍሮ ባሮሜትር በ2011/13 ያደረገው 5ኛ ዙር ጥናት፣ ከ2014/15 ጥናት ጋር ሲነፃፀር፤ ጥናቱ ከተካሄደባቸው 33 አገራት ድህነት በ22ቱ አገራት ቀንሷል፡፡ በሁለቱም ጥናት ከተካተቱ አገሮች ድህነትን በጣም የቀነሱ አገሮች ኬፕ ቬርዴና ግብፅ ናቸው
በተቃራኒው ደግሞ በድህነት መማቀቅ በአምስት አገሮች የጨመረ ሲሆን ሞዛምቢክ፣ ቤኒንና ላይቤሪያ … የባሰ ወደ ድህነት ቁልቁለት እየተንደረደሩ ነው፡፡ ሌሎች አምስት አገራት ደግሞ ድህነት ማጥ ውስጥ ሰጥመው ከድህነት መላቀቅ አቅቷቸው፣ እዚያው ውስጥ እየዳከሩ ነው፡፡
ለረዥም ጊዜ በተከታታይነት ከድህነት ለመውጣት የሚጣጣሩት ዛምቢያ፣ ጋናና ኬፕ ቬርዴ ሲሆኑ ድህነት እየጨመረ የሚታይባቸው አገሮች ደግሞ ማዳጋስካርና ላይቤሪያ ናቸው፡፡ ድህነት እየቀነሰ የሚታይባቸው አገሮች በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በመንገድ ግንባታና በፍሳሽ ማስወገጃ ሲስተም… በተለያዩ መንገዶች ከፍተኛ ግንባታ የሚያካሂዱ አገሮች እንደሆነ አፍሮ ባሮሜትር ገልጿል፡፡
አፍሮ ባሮሜትር በ1999 (እ.ኤ.አ) የተቋቋመ ለማንም ያልወገነ የምርምር ኔትዎልክ የፓን አፍሪካን ድርጅት ነው፡፡ ጥናትና ምርምሩን በዲሞክራሲ፣ በመንግሥት አስተዳደር፣ በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችና በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ያደረገው ድርጅቱ፤ “Let the People Have a Say” በሚል መሪ ቃል ከ30 በላይ በሆኑ የአፍሪካ አገራት ሰዎችን ፊት ለፊት በሚመርጡት ቋንቋ በማነጋገር ሀሳባቸውን ይፋ ያደርጋል፡፡ 

Read 1133 times