Saturday, 23 April 2016 10:41

ማስታወቂያዎቻችን - ከሚበጁት የሚፈጁት!!

Written by  ሶፎንያስ ሆሳዕና
Rate this item
(1 Vote)

      በእውቀቱ ስዩም በ“እንቅልፍ እና ዕድሜ” ልብወለድ መጽሀፉ የኢትዮጵያው ንጉስ ሹማቸውን ‹‹…ከዛሬ ጀምሮ ሕዝቡ ያለውን ቃል አሰባስቦ በግጥም ብቻ እንዲያወራ ንገር፡፡ አሻፈረኝ እምቢ ብሎ ቤት የማይመታ ነገር የሚናገር ቤቱ ይወረስበታል ብለህ ተናገር፡፡›› (ገጽ21) ብለው አዋጅ እንዲታወጅ ያደርጋሉ፤ ታዲያ ‹‹ይህ በሆነ በሁለተኛው ቀን አንድ ገበሬ ግማሽ ቀን ሲያርስ ውሎ ወደ ቤቱ ከገባ በኋላ መደቡ ላይ ተደላድሎ ተቀምጦ በግራ እጁ አመዳም እግሩን በቀኝ እጁ ሆዱን እያከከ፤
‹‹ኧረ ምሳ›› አለ ባል
‹‹የበላኸውሳ!›› አለችው፡፡›› (ገጽ 22) ባልና ሚስቱም ቤት ለመምታት በሚል ያልፈለጉትን ሲያወሩ፣ አለመግባባት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ንጉሱም ደርሰው ሲጠይቁ፤ አስሮ ገረፈኝ ብላ በግጥም ታስረዳቸዋለች፡፡ ንጉሡም፡-
‹‹ሚስቱን የገረፈ አስከፋሽኝ ብሎ
ይጠበቅበታል እንዲከፍላት ካሳ›› አሉ በልባቸው፡፡ ግን ቤት እንደማይመታ   ሲያውቁ ሌላ ይፈልጉ ጀመር፡፡
‹‹ሚስቱን የገረፈ አስከፋሽኝ ብሎ
ያለምንም ምህረት ይሰቀል ተገድሎ!›› ካሉ በኋላ ፍርዱን አስፈጽመው ባጀብ ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡›› (ገጽ 23) ይለናል፡፡
ሰሞንኛ ማስታወቂያዎቻችን ያለ ግጥም ማስታወቂያ መስራት አይቻልም የተባሉ ይመስል ከመልዕክቱ ይልቅ ቤት ለመምታት መከራቸውን ሲበሉ ይታያሉ፡፡ ማስታወቂያ ሰሪዎችም ቤት በመምታት አባዜ ለመለከፋቸው ማሳያ የበእውቀቱ ምሳሌ በልክ የተሰፋች ትመስለኛለች፡፡
ከቤት መታ አልመታ አባዜ ስንወጣ ደግሞ ከአንድ አመት በፊት ባህልንና የህብረተሰቡን ኑሮ ያላገናዘበ ማስታወቂያ በቴሌቪዥን መስኮት ድንገት ሰማሁ፣ ምናልባት በደንብ አላደመጥኩት ይሆናል ብዬም ድጋሚ ለመስማት እጠብቅ ጀመር። ያው የማስታወቂያዎቻችን ነገር የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ ነውና በድጋሚ ሲተላለፍ ጆሮዬን ሰጥቼ አደመጥኩት፤ አንዲት ወጣት የምስራች ነጋሪ ይመስል ጮክ ብላ ለተሰበሰቡት ሰዎች እንዲህ ትላለች፤ ‹‹እንደ ወጥ ባሉ ቆሻሻዎች የመነቸኩ ልብሶችን …..›› ወጥ ከመቼ ወዲህ ነው ከቆሻሻነት የተመደበው? ወጥን ያህል ክቡርና የኢትዮጵያዊያን መደበኛ ምግብ ቆሻሻ ማለትስ ተገቢ ነው? አሁን ልጆች (ታዳጊ ህጻናት) ልብሳቸውን ወጥ ቢነካባቸው ቆሻሻ ነካኝ ወይስ ወጥ ነካኝ እንዲሉ ነው የተፈለገው?... የሚሉት ሀሳቦች ውስጤን ስለረበሹት በፌስ ቡክ ገጼ ላይ ‹‹ወጥ ምግብ እንጂ ቆሻሻ አይደለም…››የሚል ርዕስ ሰጥቼ ፃፍኩበት፡፡ ታዲያ ማስታወቂያውም ምክንያቱን ባላወቅሁት ሁኔታ ቶሎ ተቀየረና እንዲህ በሚል “ተሻሽሎ” ቀረበ፡፡ ‹‹በወጥ የመነቸኩ ልብሶችን….›› ለዚህም ነው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ጣቢያዎች የሚተላለፉት ማስታወቂያዎቻችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው በሚል የራስ ወዳዶች መርህ መመራት የጀመረው የሚል እምነት በውስጤ ማሳደር የጀመርኩት፡፡ ይህ ለምን ሆነ? እነዚህ ማስታወቂያዎች እንዴትስ የአየር ሰዓት ሊፈቀድላቸው ቻለ? መልስ የለኝም፡፡
መገናኛ ብዙኃን ሀገርን በመገንባትም ሆነ ሕብረተሰብን በማነጽ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ግልጽ ነው፣ በሰለጠነው አለም ልጆች የሚያዩት ብቻ ጣቢያ እንዳለ መስማቴን አስታውሳለሁ ( “ሳያዩ ያመኑ…” እንዲል መጽሃፉ ሄጄ ባላይም የተነገረኝን አምኛለሁ)፣ በእኛ ሀገር ግን እንኳን ለልጆች ብቻ ተብሎ ጣቢያ ሊከፈትና ለአዋቂዎቹም የተከፈቱት ጣቢያዎች አዋቂዎቹን አልመጥን ብለው አለመግባባትን እያስነሱ ይገኛሉ፡፡ በዚህች እድሜ የማይለዩ ጣቢያዎች ባሉባት ሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ለህፃናትና ታዳጊዎች ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ይታመናል፡፡
ግደይ ገብረኪዳን በቅርቡ “አብዮት የሤራ ንድፈ ኃሳብ” በሚል ርዕስ ባወጣው መጽሐፉ (ገጽ 18) ላይ የመገናኛ ብዙሃንን ሚና እንዲህ ይገልጸዋል፤ ‹‹መገናኛ ብዙኃን የማህበረሰብ ቀራጮች ወይም መሃንዲሶች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በመገናኛ ብዙሃን ቦታ የማይሰጠው እውነታ ሕልውና አይኖረውም፡፡ ዘመናዊው ግለሰብ ከሚያውቀው በላይ የአመለካከቱንና እምነቱን ስፋትና ጥልቀት የሚወስኑት አምኖ የሚከተላቸው መገናኛ ብዙሃን ናቸው፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ዴስክ የዘመናዊው ዓለም የመስበኪያ መድረክ ወይም አውደ ምህረት ነው፡፡›› መገናኛ ብዙሃን ለሕብረተሰቡ ባላቸው የእለት ተለት ቅርበትና በሕብረተሰቡ በኩል ያላቸውን በጎ ምላሽ መሰረት አድርገው መልካምም ሆነ ተገቢ ያልሆነ መልዕክቶችን ቢያስተላልፉ ተቀባይነታቸው ያንኑ ያህል የጎላ ነውና የደራሲውን ሀሳብ እጋራለሁ፡፡
ታዲያ ሰሞኑን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ‹‹በቢራ ማስታወቂያ የሬዲዮና ቲቪ ጣቢያዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው›› በሚል ርዕስ ያነበብኩት ዜና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንን ማስጠንቀቂያ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ይሉት ፈሊጥ ሆነብኝ፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቢራ ማስታወቂያዎቹ የአየር ሰዓታቸውን ከጨረሱና ማስተላለፍ የፈለጉትን ነገር ሁሉ ለህዝቡ ካደረሱ በኋላ የሚተላለፉባቸው ጣቢያዎች ስህተታቸውን እንዲያስተካክሉ ማስጠንቀቅ ምን ይሉት ቀልድ ይሆን? ጣቢያዎቹ ከዚህስ በኋላ አለማስተላለፍ ይችሉ ይሆናል፡፡
ታዳጊ ህጻናት አዕምሮ ውስጥስ የተቀረጸውን በምን ማውጣት ይቻል ይሆን? ባለስልጣን መስሪያ ቤቱስ ማስጠንቀቂያ ሊሰጥባቸው የሚገባቸውና ታዳጊ ህጻናትን ከግምት ያላስገቡት ማስታወቂያዎችስ የቢራ ማስታወቂያዎች ብቻ ናቸው? ሌሎች ማስታወቂያዎች ስለ ታዳጊ ህጻናት የሚመጥኑ ሆነው ይሆን? በሚዲያዎቻችን ላይ ህጻናቱን ያካተቱት ማስታወቂያዎች ለታዳጊ  ህጻናቶች ምን ያስተምሩ ይሆን? እነዚህ ማስታወቂያዎችስ ላይ ማስጠንቀቂያ ሊሰጥበት አይገባም ነበር? ማስታወቂያዎቻችን ወደ ታዳጊ ህጻናቱ አዕምሮ ውስጥ በቀላሉ በመግባት ዕዳቸውን ለምስኪኑ ቤተሰብ አስተላልፈው አላለፉም?
ለጥያቄዎቻችን መልስ ይሆነን ዘንዳ በቅርብ ጊዜ ታይተው የአየር ሰዓታቸውን ከጨረሱ ማስታወቂያዎችንን አንዱን መዝዤ ለማሳየት እሞክራለሁ፤ ማስታወቂያው የሰንሴሽን ኮንዶም ሲሆን በዚህ ማስታወቂያ አንድ ወጣት በመዝናኛ ስፍራ ውስጥ ሆኖ ሁለት ፍቅረኛሞችን ይመለከታል፣ ወዲያውኑ ስልኩን አንስቶ ወደ አንዲት ሴት (ፍቅረኛው ወይም ሚስቱ) “ናፈቅሽኝ” ብሎ የጽሁፍ መልዕክት እንደ ላከ፣ ሴቲቱም መልሳ “ናፈቅኸኝ” ብላ ትመልስለታለች፣ ይሄን ጊዜ ወደ ቤቷ ይሄድና ሲያንኳኳ ብቅ ስትል፤ ‹ያን ጊዜ ሰነሴሽን › የሚል ድምጽ ይመጣና ማስታወቂያው ያበቃል፡፡ በዚህ ጉዳይም በፌስ ቡክ ገጼ ላይ ጻፍኩ፣ ከአንባቢ ጋር ተወያየንበት፤ ከሁሉም ተወያዮች ግን ውስጤን የነካኝ ከአንዲት እናት በውስጥ መስመር (inbox) የተላከልኝ መልዕክት ነበር፡፡ እንዲህ ይላል፤ ‹‹አንተ ይህን ስትጽፍ ሰሞኑን እኔ ቤት ውስጥ የተፈጠረውን ነገር ሳላካፍልህ ማለፍ አልቻልኩምና ይህን ጽሁፍ በውስጥ መስመር ልሰድልህ ተገደደድኩ። ነገሩ እንዲህ ነው፡- ከሳምንት በፊት መስሪያ ቤት ሆኜ ልጄ ናፈቀኝና ሰራተኛዬ ጋር ደውዬ፣ ልጄን አገናኚኝ” አልኳት፡፡
ስልኩን ሰጠችው፣ ልጄ ሦስት አመት ከስምንት ወሩ ነው፡፡ ናፈቅሽኝ ሲለኝ እኔም “በጣም ነው የናፈቅኸኝ አልኩት፡፡ ይሄን ጊዜ ያልጠበኩትን ነገር ከልጄ ጣፋጭ አንደበት ሰማሁ፡፡ ‹‹ማሚ ያን ጊዜ ሰንሴሽን” አለኝ…. ታዲያ ይሄ ማስታወቂያ በህብረተሰቡ ውስጥ አልገባም? የዚህስ ማስታወቂያ ጥላ በየቤቱ አጥልቶ አላለፈም? እነዚህ ማስታወቂያዎችስ ታዳጊ ህጻናትን ከግምት ውስጥ ያላስገቡ አይደሉም? የገንዘብ ጥቅምን ብቻ ታሳቢ በማድረግ በህዝብ ዘንድ ቅሬታን ሊያስነሱስ አይችሉም? ሳይቃጠል በቅጠል ነውና ነገሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቢራ ማስታዎቂያዎች ላይ ብቻ ዘግይቶ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በሌሎች ማስታወቂያወችም ላይ ያለ አንዳች መዘግየት ይሰጥ ዘንድ እንደ ዜጋ ላስታውሰው እሻለሁ፡፡

Read 1755 times