Saturday, 14 February 2015 14:41

ዶ/ር አሸብር፤ ኢህአዴግ በምርጫው አይፎካከረኝ እያሉ ነው

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የተከበሩ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ በጥርስ ህክምናው ዘርፍ የተሠማሩ ባለሀብት ሲሆኑ በ2002 ምርጫ ተወዳድረው በማሸነፍ በፓርላማ ብቸኛ የግል እጩ ሆነዋል፡፡ ዶ/ር አሸብር በፓን አፍሪካ ፓርላማ ውስጥ በም/ፕሬዚዳንትነት እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡ በግንቦቱ ምርጫ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርገዋል፡፡

በግንቦቱ ምርጫ በእጩነት ይወዳደራሉ?
በምርጫው ለመወዳደር ጓደኞቼ ፊርማ አሰባስበውልኝ ለቦርዱ አስገብተናል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ተወዳዳሪነቴን የማረጋግጠው የእጩነት ደብተሬን ስወስድ ነው፡፡ ከእኔ  የሚጠበቀውን ሁሉ   አድርጌያለሁ፡፡
የት ነው የሚወዳደሩት?
በከፋ ዞን፣ ቦንጋ ዲንቦ ጓታ ምርጫ ጣቢያ ነው የምወዳደረው፡፡
የግል ተወዳዳሪ የመሆን ጥቅሞችና ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
አብዛኛው ጊዜ ፓርቲዎች ሚዲያ ተጠቅመው ራሳቸውን የማስተዋወቅ እድል አላቸው። ቴሌቪዥን፣ ራዲዮ ይጠቀማሉ፤ ለምርጫው ከመንግስት በጀት ያገኛሉ፡፡ ለግል ተወዳዳሪዎች ግን እነዚህ ሁሉ የሉም፡፡ እኛ የግል ተወዳዳሪዎች በራሳችን ወጪ መቀስቀስ፣ በራሳችን የቅስቀሳ አውታር መጠቀም ስለሚጠበቅብን ብዙ ፈተና ውስጥ ነው ያለነው፡፡ አንድ ግለሰብ ለመወዳደር ሲፈልግ፣ በዚህ ደረጃ ራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡
ጥቅሞቹስ?
ራሱ ኢህአዴግን ብትወስድ አባላቱ ከ10 ሚሊዮን አይበልጡም፡፡ ከህዝቡ 70 እና 80 በመቶው የፓርቲ አባል አይደለም ማለት ነው። ስለዚህ ህዝቡ እኛን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ከየትኛውም ፓርቲ ገለልተኛ መሆን ለአስተያየትም ለፍርድም ይጠቅማል፡፡ ብዙ ሰው ወደ ፓርቲ አይጠጋም፤ለዚህም ምክንያቱ ገለልተኛ መሆን ስለሚፈልግ ነው፡፡
የግል ተወዳዳሪ መሆን ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ግለሰቡ ራሱ በራሱ ነው ወሳኝ የሚሆነው፡፡ የፓርቲ ዲሲፒሊን ተብሎ የሚገዛበት ነገር አይኖርም፡፡ የምታስበውን ያመንከውን ትናገራለህ፤ታደርጋለህ። የፓርቲ ፕሮግራም ነው በሚል ያላመንክበትን በብዙኃኑ ተገዝተህ እንድታምን አይሆንም፡፡ ራስን ብቻ ነው የሚኮነው፡፡ ህዝቡም ራሱን ሆኖ የሚቀርብ  ይፈልጋል፡፡
 የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል? በምርጫው ውጤት ያገኛሉ ብለው ይገምታሉ?
በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ህዝቡ ያገባኛል፣ የራሴ ጉዳይ ነው በሚል በስፋት ወጥቶ ድምፅ የሰጠው በምርጫ 97 ነው፡፡ ያኔ ህዝብ ለውጥ ማየት አለብኝ፣ ብሎ በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለተቃዋሚዎች ሙሉ ድምፅ ሰጥቶ አሸንፈው ነበር። ሆኖም አስተዳደሩን አለመረከባቸው ዛሬ ገዥው ፓርቲ አብላጫውን ስልጣን እንዲቆጣጠር አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ አዲስ አበባ ማለት ከአንድ አገር በላይ ነው፡፡ የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም ተቋማት መቀመጫ ነው፡፡ አዲስ አበባን መያዝ ማለት ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው፡፡ ያንን ይዘው ቢሆን ኖሮ ኢህአዴግ ዛሬ አውራ ፓርቲ አይሆንም  ነበር፡፡ አዲስ አበባ መሪ ስታጣ ህዝቡ፣ “ለካ ሊያስተዳድሩኝ አይችሉም” አለ፡፡ ገዥውም ፓርቲ ግለ ሂስ አድረገና ህዝቡም ተቀበለው፡፡ ከዚያ በኋላ ገዢው ፓርቲ ልማትን፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ለመመረጥ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የኛ ተቃዋሚዎች መኖራቸውን የምንሰማው፣ አሁን ለመመረጥ ሲሯሯጡ ነው፡፡ ይሄ በቂ አይደለም፡፡ በአንድና ሁለት ወር ውስጥ ምን አቅርበው ሊመረጡ ነው? ይሄ ለህዝቡም ፈተና ነው የሚሆነው፡፡ ውጤቱን እንግዲህ ሲደርስ እናየዋለን፡፡
እርስዎስ  በምርጫው አሸንፈው ለሁለተኛ ጊዜ ፓርላማ የሚገቡ ይመስልዎታል?
ፓርላማ እንደምገባ አልጠራጠርም፡፡ ተመልሼ እመረጣለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኔ ከራሴ ህዝብ ጋር ነው የቆየሁትም፡፡ በፊት ሳያውቀኝ የመረጠኝ አሁን መልዕክተኛወ ሆኜ የላከኝን ፈፃሚ መሆኔን ከመቼውም በበለጠ ያውቃል፡፡ ስለዚህ እመረጣለሁ ብዬ በእርግጠኝነት  መናገር እችላለሁ፡፡ በእርግጥ የምወዳደረው ከኢህአዴግም ከተቃዋሚዎችም ጋር ነው፡፡ እኔ ከዚህ በፊት ም/ቤት ስገባ ኢህአዴግን እንደማልቃወም፣ ገብቼም የኢህአዴግ ደጋፊ እንደምሆን ቃል ገብቼ ነው የተመረጥኩት፡፡ በእርግጥም አንድም ቀን ኢህአዴግን ተቃውሜ አላውቅም፡፡ በዚህ የተነሳ የገዥው ፓርቲ አባል ከእኔ ጋር ይወዳደራል ብዬ አልጠበቅሁም  ነበር፡፡ እኔ እኮ የአባሉን ያህል ስሰራ ነው የቆየሁት፤ ሃገርን ወክዬ በፓን አፍሪካ ፓርላማ የተቀመጥኩ ሰው ነኛ። ይሄ የፓን አፍሪካ ፓርላማ ቦታችንን ማስጠበቅ የምንችለውም እኔ በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ ስኖር ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይሄንንም ከግምት ውስጥ የሚያስገባ መስሎኝ ነበር፡፡
 አሁን ስማቸውን የማልጠቅሳቸው ኃላፊ፣ ከኔ ጋር እንደማይወዳደሩ ሲናገሩ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ መወዳደሩ የገቡ ይመስለኛል፡፡ እኔ እንደገና ተመርጬ ፓርላማ ብገባም ኢህአዴግን አልቃወምም፡፡ በእኔ እምነት ኢህአዴግ ለሃገሪቱም ለህዝቡም ጥሩ ስራዎች ሰርቷል፡፡ ከዚህ አንጻር የእኔ ፓርላማ መግባት ድሮም አልረበሸውም፣ አሁንም የሚረብሸው አይመስለኝም፡፡ በፓን አፍሪካ ፓርላማ ኢትዮጵያ ያላትን ቦታ ለማስጠበቅ ያስችለኛል ብዬ ስለማስብ ነው ወደዚህ ምርጫ የገባሁት፡፡
ኢህአዴግን የማይቃወሙና በፖሊሲው የሚስማሙ ከሆነ ለምን አባል አይሆኑም?
ይሄን እኔን ከመጠየቅ ኢህአዴግን መጠየቅ ይቀላል፡፡ “ለምን ዶ/ር አሸብርን አባል አታደርገውም?”ተብሎ ቢጠየቅ፣ኢህአዴግ የራሱን መልስ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እኔ ግን ኢህአዴግን ተቃውሜም አላውቅ፣ልቃወምም አልችልም፡፡ በእኔ እምነት ኢህአዴግ የምወዳደርበትን አካባቢ ቢተውልኝ የሚጐዳው ነገር አይኖርም፡፡ አሁን ከሚተነበየው አንጻር፣ኢህአዴግ በሰፊው ሊያሸንፍ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ከዚህ በፊትም ኢህአዴጎች ለእነ አቶ በትሩ አደም ለቀውላቸው የተመረጡበት ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን ሠርተው የዚህ አይነት እውቅና እንዳገኙ ባላውቅም፣ እኔ እንደ አንድ ዜጋ ራሴን ሳስብ ግን የሚጠበቅብኝን ሰርቻለሁ። እውቅና መስጠት የዚያኛው ወገን ጉዳይ ነው፡፡ “ለምን አባል አልሆንክም?” ለሚለው፣ እነሱ ምን ዓይነት ሰው አባል እንደሚያደርጉ መጠየቁ የሚቀል ይመስለኛል፡፡
እርስዎ አባል የመሆን ፍላጎት አለዎት?
መጀመሪያ መታወቅ ያለበት የእነሱ ፍላጎት ነው። ማንን አባል እንደሚያደርጉ ከእነሱ ማወቅ ይቀላል። እኔ በበኩሌ፣ የፓርቲ አባል ባልሆን ለራሴም ለሌላውም እጠቅማለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ብትሆንም የሚጎዳ ነገር የለውም፡፡

Read 8554 times