Monday, 15 August 2016 08:48

የመንግስት የውጭ እዳ እየከበደ ነው

Written by 
Rate this item
(11 votes)

የኢትዮጵያ መንግስት፣ በግማሽ ዓመት 670 ሚ.ዶላር ለእዳ ክፍያ አውጥቷል

የውጭ እዳ በፍጥነት እየተከማቸበት የመጣው የኢትዮጵያ መንግስት፣ በ2006 ዓ.ም የብድር እዳ ከነወለዱ 570 ሚ. ዶላር መክፈሉ የሚታወስ ሲሆን፣ ዘንድሮ ክፍያው በእጥፍ ጨምሮበታል። ዘንድሮ እስከ መጋቢት ድረስ፣ 670 ሚ.ዶላር እንደከፈለ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ገልጿል።
ከአራት አመት በፊት፣ የመንግስት ጠቅላላ የውጭ እዳ ወደ 9 ቢሊዮን ገደማ እንደነበረ የገንዘብ ሚኒስቴር ጠቅሶ፣ ዘንድሮ እስከ መጋቢት ወር ድረስ፣ የእዳው ክምችት 20.6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውቋል።
በተለይ፣ በባቡር መስመር ግንባታ፣ በቴሌኮም እና ለአመታት በተጓተቱት የስኳር ፕሮጀክቶች ሳቢያ በፍጥነት እየተከማቸ ከመጣው ብድር ጋር፣ ለእዳና ለወለድ ክፍያ የሚውለው የውጭ ምንዛሬም እየከበደ እንደመጣ የሚኒስቴሩ ሪፖርት ያሳያል።
በ2004 እና በ2005 ዓ.ም፣ ለእዳና ለወለድ ክፍያ የሚውለው የውጭ ምንዛሬ ግማሽ ቢሊዮን ገደማ ነበር። አምና የክፍያው ሸክም ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ተጠግቷል (980 ሚ.ዶላር)።
የወለድ ክፍያው ለብቻው ሲታይም እንዲሁ፣ ከአመት አመት እየጨመረ መጥቷል። ከአራት አመት በፊት፣ 100 ሚሊዮን ዶላር የነበረው የወለድ ክፍያ፣ አምና ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል። ዘንድሮም እስከ መጋቢት ድረስ፣ ለወለድ 210 ሚ.ዶላር እንደተከፈለ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ይገልፃል። እየከበደ የመጣውን የእዳና የወለድ ክፍያ ለማሟላት፣ ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ በአምስት አመታት በእጥፍ ለማሳደግ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ከ2003 ዓ.ም ወዲህ፣ የኤክስፖርት ገቢ እስካሁን አልጨመረም። ያኔ ከነበረበት፣ የ3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ፣ ብዙም አልተነቃነቀም።
ደግነቱ፣ ለነዳጅ ግዢ ይውል የነበረው የውጭ ምንዛሬ፣ ባለፉት ሁለት አመታት ቀንሷል። ከ2006 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር፣ የቤንዚን  የአለም ገበያ ዋጋ በ70% ቀንሷል። የናፍታ ደግሞ በ60% ቀንሷል። በዚህም፣ መንግስት በአመት ውስጥ፣ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ለማዳን እድል አግኝቷል።
ይህም ብቻ አይደለም። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በየአመቱ ወደ አገር ቤት የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ መምጣቱ፣ መንግስትን ጠቅሟል። ከአራት አመት በፊት፣ በአመት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይልኩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን፣ አሁን በአመት ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይልካሉ - በኤክስፖርት ከሚገኘው የውጭ ምንዛሬ የሚበልጥ።

Read 7439 times