- የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ማንበብና መፃፍም ሆነ ሂሳብ ማስላት አይችሉም
- የኮሌጅ ተመራቂዎች የ8ኛ ክፍል ፈተናን በብቃት ማለፍ አልቻሉም
በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የትምህርት ጥራት ደረጃ በአስደንጋጭ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ሰሞኑን ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከእንግሊዙ ዱርሃም ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያደረገው ጥናት፤ በአማራ፣ በደቡብ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ 10 ኮሌጆች ላይ ያተኮረ ሲሆን የትምህርት ጥራቱ በአስደንጋጭ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ይጠቁማል፡፡ ጥናቱን በኮተቤ ኮሌጅ አዳራሽ ያቀረቡት የፊዚክስ ተመራማሪና መምህር ዶ/ር መስፍን ታደሰ፣ “ተማሪዎች በተለይም በፊዚክስና በሂሳብ ትምህርቶች እጅግ ደካማ ሆነዋል” ብለዋል፡፡ የትምህርት ጥራቱን አስመልክቶ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና አጥኚዎች ያደረጉትም ሆነ በራሱ በዩኒቨርሲቲው የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ የአገሪቱ የትምህርት ጥራት ከዓለም አቀፉ መስፈርት እጅግ ያነሰ ደረጃ ላይ ይገኛል በማለት ዶ/ር መስፍን አብራርተዋል፡፡
በ2013 እ.ኤ.አ በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የተሰራውን አንድ ጥናት ዋቢ በማድረግ ተመራማሪው እንደገለፁት፤ በአገሪቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ብዙ ተማሪዎች ወደ ት/ቤት ይገባሉ፤ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ዕድልም በስፋት አለ፤ ሆኖም ተማሪዎቹ ከት/ቤት ሲወጡ ማንበብና መፃፍም ሆነ ሂሳብ ማስላት አይችሉም፡፡
“የትምህርት ጥራቱ እጅግ አሳፋሪ ደረጃ ላይ ደርሷል” ያሉት ዶ/ር መስፍን፤ “የልጆቹ የዕውቀት ደረጃም በአለማቀፍ ደረጃ ከሰፈረው አማካይ ቫልዩ አንፃር 150 ዓመታት ወደ ኋላ መቅረቱ በጥናት ተረጋግጧል” ብለዋል፡፡ አለማቀፍ ፈተናዎችን በመስራት ረገድም ቢሆን በኢትዮጵያ የተመዘገበው ውጤት በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ጥናቱ በመምህራን ኮሌጆችና በተለያዩ ት/ቤቶች ላይ መደረጉን የጠቀሱት ዶ/ር መስፍን፤ “ከኮሌጅ ተመርቀው 7ኛና 8ኛ ክፍሎችን ለማስተማር ዝግጁ ከሆኑ መምህራን መካከል ለዚሁ ጥናት የተመረጡት የ12ኛ ክፍል ፈተናን ተፈትነው ማለፍ አለመቻላቸውንና የ8ኛ ክፍል ፈተናንም በብቃት ማለፍ እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡ “የጥናት ውጤቱ የሚያመለክተው ከኮሌጅ እየተመረቁ የሚወጡት መምህራን፣ ከደረጃ በታች መሆናቸውን ነው፤ ይህ ደግሞ እጅግ አሳሳቢ ነው” ብለዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል በሚል ከእንግሊዙ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቅርቡ የተደረገው ይሄው ጥናት፤ የተማሪዎችን የአስተሳሰብ አቅም ከሌሎች አገራት ጋር በማነፃፀር ውጤቱን ይፋ አድርጓል፡፡ “በኢትዮጵያ የሚገኙ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ፣ አሜሪካና ሲንጋፖር በመሳሰሉ የአደጉ አገራት ከሚገኙት የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ ጋር እኩል ነው” ይላል፡፡
በትምህርት ጥራት ረገድ የሚታየው ችግር ተጨባጭና በእግሩ ቆሞ የሚሄድ ነው ያሉት ዶ/ር መስፍን፤ የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል መሰረታዊ ችግሮችን በማስወገድ ለለውጥ መነሳት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ለትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል ዋነኛ ምክንያቶች ተብለው ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከል የሥርዓተ ትምህርቱ (ካሪኩለም) ክብደት፣ ለጋሾችን መሰረት ያደረገው የትምህርት ሥርዓትና ለመምህርነት ሙያ የሚሰጠው አነስተኛ ግምት የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡ “በተለይም ለመምህርነት ሙያ የሚሰለጥኑት ውጤታቸው አነስተኛ የሆነና ለሙያው ፍቅርና ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ፣ ተመርቀው ሲወጡም የሙያ ፍቅር የሌላቸው መምህራን ይሆናሉ” ያሉት ጥናት አቅራቢው፣ “እነሱም ለተማሪዎቻቸው ደንታ የሌላቸውና ለትምህርት ጥራቱ መሻሻል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ የማያበረክቱ ይሆናሉ” ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሌላው የፊዚክስ ተመራማሪና መምህር የሆኑት ዶ/ር መክብብ ዓለሙ በበኩላቸው፤ የትምህርት ጥራቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወደቀና የተማሪዎቹ የዕውቀት ደረጃም እያሽቆለቆለ መምጣቱ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልፀው፤ በአገሪቱ ትርጉም ባለው ደረጃ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ትስስር በመፍጠር፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለለውጥ መታገል ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም በአገሪቱ የሚዘረጉ መሰረተ ልማቶች በሙሉ በውጪ ባለሙያዎች እየተሰሩ መቀጠል የለባቸውም ያሉት ዶ/ር መክብብ፤ ዕውቀቱ የእኛ መሆን አለበት፤ ተማሪዎቻችን ለእንደዚህ ያሉ ተግባራት ሊሰለጥኑና ራሳቸውን ሊያበቁ ይገባል ብለዋል፡፡
በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ሰሞኑን ሲካሄድ የሰነበተው አውደ ጥናት፤ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወንና በቀጣይ አለማቀፋዊ ዎርክሾፕ ለማዘጋጀት በማቀድ መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል።
Sunday, 02 July 2017 00:00
የትምህርት ጥራቱ በአስደንጋጭ ሁኔታ አሽቆልቁሏል ተባለ
Written by መታሰቢያ ካሳዬ
Published in
ዜና