ቢዝነስ እና አርት እንዴት ይቆራኛሉ?
ላለፉት ስድስት ወራት መደበኛ ስራውን አቁሞ የነበረው “ጉራማይሌ አርት ጋለሪ” ወደ ስራው የተመለሰ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ “ፆር” (Ray) የተሰኘ አዲስ የስዕል አውደ ርዕይ ከፍቷል፡፡ በአውደ ርዕዩ ላይ የሰዓሊ መርዕድ ታፈሰ ከ30 በላይ የስዕል ስራዎች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን እስከ ታህሳስ 15 ለእይታ ክፍት ሆነው እንደሚቆዩም ታውቋል፡፡
ጉራማይሌ አርት ጋለሪ ላለፉት ስድስት ወራት ለምን ስራ እንዳቆመ የተጠየቀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “አለ” የስነ-ጥበብ ት/ቤት የእንግሊዝና ቋንቋና ስነ ፅሁፍ መምህር የጋለሪው ዳይሬክተርና የስነ - ጥበብ አጋፋሪው ሚፍታ ዘለቀ፤ ስነ - ጥበብ በስራ ቦታ ህይወትን የተሻለና ጥሩ ስሜት እንዲፈጥር፣ ለማድረግ እንዲሁም በተለያየ የስራ ቦታ የሚኖር ህዝብ ለስነ - ጥበብ ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር በማሰብ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አንድ ፕሮጀክት ተጀምሮ እንደነበር ገልፆ፤ ልደታ አካባቢ በሚገኘው ዛጉዬ ህንፃና መርካቶ በሚገኘው ገዳ ህንፃ ላይ ባሉት የባንኩ ቢሮዎች ጋለሪው ስድስት ወር የፈጀ የስነ ጥበብ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጿል፡፡ ባንኩን በሞዛይክ፣ በቅብና በቅርፃ ቅርፅ ስራ እንዴት ማሳመር እንደተቻለ፣ በ“ፆር” የስዕል አውደ ርዕይ መክፈቻ ላይ አጭር ዘጋቢ ፊልም ለታዳሚው አቅርቦም አድናቆትን አግኝቷል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ምክንያት አርት ጋለሪው መደበኛ ስራውን ለስድስት ወራት አቁሞ እንደነበርም አስታውቋል፡፡
አቶ ሚፍታ ጨምሮም ሙዚቃ፣ ቴአትርና ፊልም ከስነ - ጥበብ (ሥዕል) ይልቅ የተሻለ ተደራሽነት እንዳላቸው ገልፆ፤ ይሄኛው ዘርፍ ከተለያዩ ቢዝነሶች ጋር ቁርኝት እንዲኖረውና ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎች መፈጠር እንዳለባቸው ካስታወሰ በኋላ በዚህ በኩል “ክርኤቲቭ ፊውቸር” የተሰኘውና በብሪቲሽ ካውንስል በጎተ ኢንስቲትዮትና አይስ አዲስ በተባለው አገር በቀል ድርጅት ተቀርፆ፣ በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ እየተተገበረ ያለውን ስራ አድንቋል፡፡
ክርኤቲቭ ፊውቸር ለስዕል፣ ለስነ-ጥበብ አጋፋሪነት ለፎቶግራፍ፣ ለቪዲዮ ኤዲቲንግና ተመሳሳይ የጥበብ ስራዎች ለማገዝና በዚህ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ወጣቶችን አቅምና ክህሎት ለማዳበር የሚሰራ ፕሮጀክት እንደሆነ በጉራማይኔ አርት ጋለሪ ያገኘናቸው በብሪሽ ካውንስል የ “ክርኤቲቭ ፊውቸር” ፕሮግራም የግንኙነት አማካሪ አቶ መላኩ ተኮላ ተናግረዋል፡፡ እንደ አማካሪው ገለፃ፤ ፕሮጀክቱ በአውሮፓ ህብረት የሚደገፍና ለሁለት ዓመት የሚቆይ ሲሆን እስካሁን ስነ - ጥበብን (ስዕልን) ጨምሮ በርካታ ዕድል ያላገኙ የጥበብ ስራዎች ላይ የሚሰሩ ወጣቶችን በማሰባሰብ፣ የቴክኒክ ስልጠናና ከሌሎች አጋዥ አካላት ጋር የሚገናኙበትን መንገድ ሲያመቻች ቆይቷል፡፡
“ለምሳሌ የስዕል አውደ ርዕዩ በተከፈተበት ዕለት ጠዋት “ብፌክፋስት ሚቲንግ” የተባለውን ፕሮግራም አዘጋጅተን የቢዝነሱ ሰዎች ስለ አርት ግንዛቤ እንዲኖራቸውና በተለይ ብዙ ተደራሽ ያልሆነውን የኪነ ጥበብ ዘርፍ በምን መልኩ መደገፍ አለባቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ምክክር አድርገናል” ይላሉ-የፕሮጀክቱ የግንኙነት አማካሪ መላኩ ተኮላ፡፡
ማህሌት ማዕረጉ በብሪቲሽ ካውንስል የፕሮጀክቱ ዳይሬክተር ሲሆኑ የ “ክሬቲቭ ፊውቸር”ን ዋና አላማ አስመልክተው ሲናገሩ፤ በተለይ እንደ ፋሽን፣ ቪዥዋል አርትስ፣ ፎቶግራፍ፣ ስዕል፣ ቅርፃ ቅርፅና ዲጂታል አርትስ ያሉ ዘርፎች ብዙ ትኩረት ስለማይሰጣቸው ወደ ማህበረሰቡ ገብተው ተደራሽ በመሆንና ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ያላቸው ሚና ዝቅተኛ ናቸው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ብሪቲሽ ካውንስል፣ የጀርመን የባህል ማዕከል (ጎተ) እና “አይስ አዲስ” የተባለ አገር በቀል ድርጅት ከአውሮፓ ህብረት በሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ፤ በተጠቀሱት ዘርፎች ላይ የሚታዩትን ክፍተቶች ለመሙላት በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት ፕሮጀክት ዳይሬክተሯ ማህሌት፤ በጉራማይሌ አርት ጋለሪ የተገኙበት ዘርፍ “ቢስነዝና አርት” የተባለው ዘርፍ ሲሆን “አርትን እንዴት ከቢዝነስ ጋር እናገናኘው” የሚለውን የሚመለከት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በጁላይ ወር 2018 ዓ.ም በሚጠናቀቀው በዚህ ፕሮጀክት፤ ለአርቲስቶቹ በ “ኤቨንትስ ማኔጅመንት”፣ በቢዝነስና ማርኬቲንግ፣ በስነ-ጥበብ አጋፋሪነትና በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስልጠና በመስጠት፣ የባለሙያዎቹን አቅምና ጉልበት ከማጎልበት በተጨማሪ ከቢዝነሱ ሰዎች ጋር ተገናኝተው ስራቸውን እንዴት ወደ ቢዝነስ እንደሚቀይሩ እውቀት ያገኙበታል ተብሏል፡፡ “ለምሳሌ የጉራማይሌ አርት ጋለሪ ዳይሬክተርና የስነ- ጥበብ አጋፋሪው ሚፍታ ዘለቀ፣ በየስነ-ጥበብ አጋፋሪነት ምንነት ዙሪያ ከመቶ በላይ ለሆኑ ወጣቶች ስልጠና ሰጥቶልናል፡፡ እሱም ከእኛ ጋር በፈጠረው ግንኙነት እንግሊዝ አገር ሄዶ፣ የኢትዮጵያን አርት ለማስተዋወቅ ችሏል፡፡” ይላሉ ፕሮግራም ዳይሬክተሯ ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ባለሙያዎቹ “ቢዝነስ እና አርት” በሚለው ፕሮጀክት ያገኙትን ክህሎትና እውቀት ተጠቅመው፣ በራሳቸው መንገድ ስራዎቻቸውን ወደ ቢዝነስ ቀይረው፣ ሙያቸውን ዋነኛ የገቢ ምንጭ ለማድረግ ይረዳቸዋል ብለዋል ወ/ሮ ማህሌት ማዕረጉ፡፡
“ለፕሮጀክቱ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ብዙም ስላልሆነ ስራችን ትኩረት ያደረገው በአዲስ አበባ ላይ ነው” የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ እስካሁን አምስት ክርኤቲቭ ዘርፎች ላይ ውጤታማ ስራ መስራታቸውን ገልፀው፣ በተለይ ወደ ኪነ-ከጥበቡ ለመግባት በማሰብ ላይ ያሉ ወጣቶች “ወደ ፋሽን ልግባ፣ ስዕልን ልምረጥ ወይስ አኒሜሽን ላይ ልስራ” በማለት በሚያመነቱበት ሰዓት ምክርና እገዛ በመስጠት ራሳቸውን ፈልገው እንዲያገኙ ድጋፍ መደረጉን ገልፀው፤ “ቢዝነስ እና ማርኬቲንግ” በሚለው ፕሮግራም “አይስ አዲስ” የተባለው አገር በቀል ድርጅት በቀረፀው ፕሮፖዛል መሰረት፤ በቪዥዋል አርት” ፎቶግራፍ፣ በፋሽን ዲዛይን እና በበርካታ ዘርፎች ለስምንት ሳምንት የዘለቀ ስልጠና መሰጠቱንም ወ/ሮ ማህሌት ተናግረዋል፡፡ ይህ ስልጠና “ሙያዬን እንዴት ወደ ቢዝነስ መቀየር እችላለሁ” የሚለውን ጥያቄም አብረው የሚመልሱት ነው ሲሉም ይገልፃሉ፡፡ በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ በተለያየ ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጆችን በማሰልጠን ከቢዝነስ ሰዎች ጋር በማገናኘትና ወደፊትም ወደ ውጭ እየሄዱ የኢትዮጵያን አርት ለውጭው ዓለም ለማሳየት የሚችሉበትን እድልም ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
ጉራማይሌ አርት ጋለሪ ከዚህ ፕሮጀክት ምን ተጠቀመ በሚል የተጠየቁት ወ/ሮ ማህሌት፤ ሲመልሱ፤ “አንደኛ ወደ አርት ጋለሪ ሄዶ የሚጎበኘው ሰው ጥቂት በመሆኑ ከእኛ ጋር በፈጠረው ግንኙነት በርካታ ሰው ወደ ጋለሪው ይመጣል፡፡ ሁለተኛ ከእኛ ጋር በመገናኘት በእኛ በኩል ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ይፈጥራል፤ እኛ መጀመሪያ ከሰዎች ጋር ስንገናኝ ዳታ ቤዝ እንፈጥራለን፤ ከዚያ ግንኙነታችንን እናጠናክራለን” የሚሉት የፕሮግራም ዳይሬክተሯ፤ በዚያ ዘርፍ መረጃ፣ አብሮ የመስራት እድል ሲመጣም ውድድሮች ሲላኩ በዚያ በዳታ ቤዛቸው መሰረት ኢ-ሜይል በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያደርጉና በዚህም እድል ከጉራማይሌ ሚፍታህ ተመርጦ እንግሊዝ በመሄድ በዓለም ምርጥ ከሚባሉት ሙዚየሞች አንዱ የሆነውንና በዓመት 5. ሚ ቱሪስት የሚጎበኘው “ቴት ሞደርን” የተሰኘውን ሙዚየም” ለአንድ ሳምንት ከሌሎች እሱን መሰል 22 የዓለም አገራት ከተሰባሰቡ 27 ተሳታፊዎች ጋር ተሰባስቦና ልምድ ተለዋውጦ እንዲሁም የኢትዮጵያን አርት እዛ ድረስ ወስዶ ለማስተዋወቅ መብቃቱን በመግለፅ የፕሮጀክቱን ትሩፋቶች ጠቅሰው ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
Monday, 18 December 2017 13:40
በጉራማይኔ አርት ጋለሪ አዲስ የስዕል አውደ ርዕይ ተከፈተ
Written by ናፍቆት ዮሴፍ
Published in
ጥበብ