ዋዜማውን የት ለማሳለፍ አስበዋል?

በዘንድሮ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ከቀድሞ ዓመታት በተለየ በርካታ የሙዚቃ ድግሶች እንደተዘጋጁ ያሰባሰብናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ጃኪ ጎሲና አንጋፋው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ታደሰ ረቡዕ ምሽት በዋዜማው ታዳሚውን በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚያዝናኑ ይጠበቃል፡፡ አንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴም በምሽቱ ዝግጅት ላይ የሚያቀነቅን ሲሆን “የተመስገን ልጆች” የባህል ውዝዋዜ ቡድን የኮንሰርቱ አካል እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ኮንሰርቱን ለመታደም ቀደም ብለው ትኬት ለሚገዙ 500 ብር፣ በእለቱ በር ላይ በእለቱ ለመግዛት 600 ብር ነው ተብሏል፡፡ የቪአይፒ ትኬት 1500 ብር ሲሆን እራትን ይጨምራል፡፡
ሃርመኒ ሆቴል
ከኤድናሞል ዝቅ ብሎ በሚገኘው ሃርመኒ ኢንተርናሽናል ሆቴልም ለአዲስ ዓመት ዋዜማ ትልቅ የሙዚቃ ድግስ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ድግስ ላይ ዋዜማውን የሚያደምቁት የጃኖ ባንድ አባላት ናቸው ተብሏል፡፡ በዚህ ድግስ ላይ ለመታደም ብቻዎን ከሄዱ በሰባት መቶ ብር የፍቅር ወይም የትዳር አጋርዎን ከያዙ ደሞ በ1200 ብር ይዝናናሉ፡፡
ሒልተን ሆቴል
በቅርቡ ስሙን ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቀየረው EBC፤ በዋዜማው ዕለት ከሒልተን በቀጥታ የሚያስተላልፈው የመዝናኛ ዝግጅት እንዳለው ታውቋል፡፡ በዋዜማ ዝግጅቱ ላይ እነማዲንጎ አፈወርቅ፣ ሃመልማል አባተ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ንዋይ ደበበ፣ ማህሌት ገ/ጊዮርጊስ፣ ዘውዱ በቀለ፣ ሃይሉ ፈረጃና ሌሎች በርካታ አንጋፋና ወጣት ድምፃዊያን ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡ በዚህ የዋዜማ ፕሮግራም የመግቢያ ክፍያ እንደሌለና እንግዶች በጥሪ ካርድ እንደሚገቡ ታውቋል፡፡  
ካፒታል ሆቴል
ከኡራኤል ወደ 22 በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው ካፒታል ሆቴልና ስፓ እንዲሁ ትልቅ የዋዜማ የሙዚቃ ድግስ ያዘጋጀ ሲሆን ምሽቱ በመሃሪ ብራዘርስ ባንድ ይደምቃል ተብሏል፡፡ በዚህ ምሽት አንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ሥራዎቹን የሚያቀርብ ሲሆን መግቢያ 1300 ብር ነው፡፡
ሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴል
ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ የሚገኘውና በዓመቱ መጀመሪያ ላይ አካባቢ ስራ የጀመረው ባለ አራት ኮከቡ ሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴልም ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ የሙዚቃ ድግስ አዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ምሽት ገነነ ሃይሌ፣ የባህል ዘፋኙ ግዛቸው እሸቱ፣ ፀጋዬ ስሜ (ሆሴ ባሳ) እና ሌሎችም የትግርኛና ጉራጊኛ ዘፋኞች የበዓል ዋዜማውን አድምቀውት ያመሻሉ፡፡ መግቢያው 380 ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡
ጨጨሆ የባህል ምግብ አዳራሽ
በአዲስ አበባ ከኢምፔሪያል አደባባይ ወደ 17 ጤና ጣቢያ በሚወስደው መንገድ የተገነባውና ባለፈው ቅዳሜ የተመረቀው አዲሱ “ጨጨሆ የባህል ምግብ አዳራሽ” ደግሞ የፊታችን ሐሙስ የአዲስ ዓመት ልዩ የሙዚቃና የባህል ዝግጅቶችን እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡

Published in ዜና

            አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በአዲሱ ዓመት ሃገራዊ ኃላፊነትን ለመሸከም መዘጋጀቱን ገለፀ፡፡ ፓርቲው ከትናንት በስቲያ ረፋድ ላይ በጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “የገዢውን ፓርቲ ምርጫ መጣ ነፃ ፕሬስ ውጣ” አይነት አካሄድ አጥብቆ እንደሚቃወም አስታውቋል፡፡
እንደነ አንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ አንዱዓለም አያሌው፣ ሻምበል የሺዋስ፣ ሃብታሙ አያሌው እና ዳንኤል ሺበሺ ያሉ ወጣት የፓርቲው አመራሮች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ወህኒ ተወርውረው የግፍ ፅዋ እየተጋቱ ነው” ያለው ፓርቲው፤  “አፈናና ስደት በአምባገነን መሪዎች አገር የተለመደና የሚታወቅ ቢሆንም አምባገነንነት በኢህአዴግ እንዲያበቃ ቆርጠን እንታገላለን” ብሏል፡፡
ፓርቲው ከ2003 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ያለውን ጊዜ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል እድሳትና ማንሰራራት ዘመን” ብሎ በመሰየም ባለፉት አመታት በከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄ የኢትዮጵያን ህዝብ ችግሮች አደባባይ እንዳወጣ አስታውቋል፡፡
“የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” እና “የእሪታ ቀን” በሚል ያካሄዳቸውን እንቅስቃሴዎች በመጥቀስ፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ “አፈናና እስራት ቢበዛብንም ትግሉ ከዚህም የባሰና የከፋ ችግር እንደሚያስከትል እያወቅን ስለገባንበት በሰላማዊ ትግላችን እንቀጥላን“ ብለዋል፡፡
ፓርቲው በ2007 “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነትና ፍትሃዊ ምርጫ “በሚል አመቱን ሙሉ የሚቆይ ንቅናቄ እንደሚያካሂድ ገልፆ፣ በዚሁ ዓመት በሚደረገው ሃገራዊ ምርጫ ላይ የምርጫ ቦርድ፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ የፍትህ ስርዓቱና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት በህገ-መንግስቱ የተደነገገውን መሰረት በማድረግ ገለልተኝነታቸውን በአንፃራዊ ደረጃ በማረጋገጥ፣ በምርጫው እንደሚሳተፍና የህዝብን የስልጣን ባለቤትት ለህዝብ እንደሚያበስር አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡
 የፓርቲውን ስትራቴጂና የአምስት ዓመት እቅድ መሰረት በማድረግ፣ በአብዛኛው የአገሪቱ ክልል ምርጫ ተኮር አደረጃጀት ለመዘርጋት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ፓርቲው አስታውቋል፡፡ “መንግስት ለ2007 ዓ.ም ምርጫ ፍጆታ ሲል ለሰራተኛው ደሞዝ ጨመርኩ ቢልም ህዝቡ ጀኑሮ ውድነት የተሰቃየበትና አሁንም እየተሰቃየ ያለበት ዓመት ሆኗል፡፡” ያሉት አመራሮቹ፣ መንግስት ገበያውን በአስቸኳይ በማረጋጋት የህዝቡን ጫና እንዲቀንስ ጠይቀዋል፡፡
 መንግስት የአዲስ አበባን ይዞታ ለማስፋፋት ሲል የሚመለከታቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ሳያወያይ ባደረገው አከላለል በተነሳ የህዝብ ቁጣ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለእስራትና ለተያያዥ ጉዳዮች ያጋለጠ በመሆኑ ከምንግዜውም በላይ ዓመቱን መራራ አድርጎት ማለፉን የተናገሩት የአንድነት አመራሮች በ2007 ዓ.ም ይህ ሁሉ ግፍ ተወግዶ ህዝቡ እፎይታ የሚያገኝበት ዓመት እንዲሆን ፓርቲው ከምንጊዜውም በላይ የሃገርን ኃላፊነት ለመሸከም መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡ፓርቲው ለኢትዮጵያ ህዝብ ባስተላፈው መልእክት፤ በመጪው አገራዊ ምርጫ ከህዝቡ ጋር በመሆን ሰላማዊ ትግሉን በምርጫ ለማሳካት በአራቱም ማዕዘናት የፖለቲካ ፕሮግራሙን እንደሚተገብርና መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት በእጁ የሚገባበት በመሆኑ ህዝቡ ከትግሉ ከጎኑ እንዲቆም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

Published in ዜና

በአሜሪካኖች ዘንድ የሚነገር አንድ ቀልድ መሳይ ተረት እንዲህ ይላል:-
ከዕለታት በአንደኛው አዲስ ዓመት ዕለት አምላክ ሶስት ታዋቂ ሰዎችን ጠራ
1ኛ/ ቢል ጌትስን
2ኛ/ ቦሪስ ዬልሲንን
3ኛ/ ቢል ክሊንተንን
ከዚያም “የጠራኋችሁ አንድ አስቸኳይ መልዕክት ስላለኝ ነው” አለ፡፡
ሁሉም በችኮላና በጉጉት “ምንድን ነው?” “ምንድን ነው?” “ፈጥነህ ንገረን” አሉት፡፡
አምላክም፤
“ይሄንን መልዕክት እንደ አዲስ ዓመት መልዕክት ቁጠሩት፡፡ ምክንያቱም በመልዕክቱ በመጠቀም ብዙ ህዝብ ታድኑበታላችሁ” አለና፤
“በመጀመሪያ፤ ዬልሲንን፤
‘ጠጋ በል ዬልሲን፡፡ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ዓለም ትጠፋለች፡፡ ስለዚህ ወደሩሲያ ህዝብ ሄደህ ይህንኑ አሳውቅ” አለው፡፡
ዬልሲን ወደ አገሩ በረረ፡፡ ቀጥሎ ክሊኒተንን “ጠጋ በል፡፡ ለአሜሪካን ህዝብ መንገር ያለብህ መልዕክት አለ፡፡ በአንድ ሣምንት ጊዜ ውስጥ ዓለም ልትጠፋ ነውና የአሜሪካ ህዝብ እንዲዘጋጅና እንዲጠብቅ ንገር!” አለው፡፡
ክሊንተንም አፍታም ሳይቆይ ወደ አገሩ በረረ፡፡
በመጨረሻም አምላክ ቢልጌትስን “ና ወደ ኔ፡፡ እንደሌሎቹ ሰዎች ለአንተም መልዕክት አለኝ፡፡ በቴክኖሎጂው ማህበረሰብ ውስጥ እጅግ ታዋቂ እንደመሆንህ ለኮምፒዩተር ሠሪውና ተገልጋዩ ህዝብ፤ በሚቀጥለው ሳምንት ዓለም እንደምትጠፋ ደጋግመህ አሳውቅ” አለው፡፡
ቢልጌትስም፤ “አሁኑኑ ባለኝ ፈጣን የቴክኖሎጂ ዘዴ በፍጥነት እገልፃለሁ” ብሎ ፈጥኖ ሄደ፡፡
ሦስቱም መልዕክቱን ያስተላለፉት እንደሚከተለው ነበር፡፡
ዬልሲን ለሩሲያ ህዝብ እንዲህ አለ:-
“አንድ መጥፎ ዜናና አንድ አስደንጋጭ ዜና ልነግራችሁ ነውና አዳምጡ:-
መጥፎው ዜና - በዕውነት አምላክ መኖሩ መረጋገጡ ነው፡፡
አስደንጋጩ ዜና - ከእንግዲህ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ አናመርትም፡፡ የአገሮችን ዕዳም ምረናቸዋል፡፡ ምክንያቱም ዓለም በሚቀጥለው ሣምንት ትጠፋለች” አለ፡፡
ክሊንተን ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጥ ስብሰባ ጠራ፡፡
ከዚያም፤
“አንድ ጥሩ ዜናና አንድ መጥፎ ዜና ስላለኝ የአሜሪካን ህዝብ ስማ፡፡
ጥሩው ዜና - አምላክ በዕውነት መኖሩ መረጋገጡ ነው፡፡ In God we Trust (በአንድ አምላክ እናምናለን) ብለን ዶላራችን ላይ መፃፋችን አኩርቶናል፡፡
መጥፎው ዜና - በሚቀጥለው ዓመት ከማንኛውም አገር ጋር ተኩስ አቁም ስምምነት እናደርጋለን፡፡ ምክንያቱም ዓለም በሚቀጥለው ሣምንት ትጠፋለች” አለ፡፡
ቢልጌትስ በበኩሉ ወደ ሬድሞንድ ሄደ፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ ስለሚሰጥ በጣም ሰፊ ስብሰባ እንዲጠራ አዘዘ፡፡ ከዚያም፤
“አንድ ጥሩ ዜናና አንድ አስደናቂ ዜና አለኝ፡፡
የመጀመሪያው - አምላክ እኔ ምን ዓይነት አስፈላጊና ትልቅ ሰው መሆኔን ማወቁ ነው!
ሁለተኛውና አስደናቂው ዜና - በሚቀጥለው ዓመት የኮምፒዩተር ጥገና ሥራ የለብንም” አለ፡፡
***
መጪውን ጊዜ ሁሉም እንደየቁቡ፤ ሁሉም እንደየፍጥርጥሩ ነው የሚተረጉመው፡፡ ሁሉም እንደየኪሱ ነው የሚመነዝረው፡፡  
“ዛሬ ባይልልን ነው እንጂ ይቺ አገር፤ ምርቃት መሬት የማይወድቅባት ነበረች”፤ ይላሉ አበው፡፡ አዲሱ ዓመት ከብዙ ችግሮች ይሠውረን ዘንድ እንመኝ፡፡ ልባችንንም ይከፍትልን ዘንድ ተስፋ እናድርግ፡፡
የፍቅር፣ የዕርቅ፣ የይቅር ባይነት ዘመን እንዲሆንልን እንደምናስብ ሁሉ ሀቀኛ ትግል፣ ሀቀኛ ፖለቲካዊ ውይይት፣ የእርስ በርስም፤ ከራስ ውጪም ተቻችሎ የመነጋገር፤ የሀቀኛ ምርጫም ዘመን ያደርግልን ዘንድ መተሳሰብን ያስርፅብን፡፡ ያነሰ ምሬት፣ የበዛ አዝመራ፣ ከቂም በቀል የፀዳ ዓመት ያድርግልን!!
አንድ ገጣሚ፤
“ነብሩን እየጋለበ፣ ሰውዬው እጫካ ገባ
ኋላ ቆይቶ ቆይቶ፣ ነብሩ መጣ ብቻውን
ላዩ የነበረው ሰውዬም፣ ሆዱ ውስጥ ነው አሁን፤
ሰው ማለት ይህ ነው በቃ
ከላይ ሲጋልብ ቆይቶ፣ ሆድ ውስጥ ነው ’ሚያበቃ!”
ይላል፡፡ በዚህ ዓመት ከዚህም ይሠውረን፡፡
በዚህ ዓመት፤ ነፃ የሀሳብ ገበያ እንደልብ የሚኖርባትና መብት የማይገደብባት ኢትዮጵያን ለማኖር ከባድ ርብርብ እንደሚጠበቅ የሚያውቅ የሠለጠነ ዜጋ እንዲኖረን እንፀልይ!
በዚህ ዓመት ውዳሴና ሙገሣን እንደምንቀበል ሁሉ ትቺንና ነቀፋንም ለመቀበል ልብና ልቦና ይስጠን፡፡
የህትመት ውጤቶች የህዝብ ዐይንና ጆሮ ይሆኑ ዘንድ፣ የጠባቂነት ሚናቸውንም በወጉ ይጫወቱ ዘንድ፤ ነፃነታቸው መጠበቅም፣ መከበርም ይገባዋል፡፡ ለእነሱም የዕውነትን፣ የመረጃን ትክክለኛነትና የሚዛናዊነትን ሥነምግባር የሚጐናፀፉበት ዓመት ያድርግላቸው፡፡
አንድ የአገራችን ፀሐፊ፣    
“በንጉሡ ዘመን (ሠራተኛው) ደሞዙ ትንሽ ስለሆነ ተብሎ የቢሮውን ጠረጴዛ እንደገቢ ምንጭ ቢጠቀምበት ከወንጀል እንደማይቆጠርበት፣ ዛሬ ደግሞ የ “ኑሮ ውድነት” ወይም አልፎ አልፎ አምልጦ የሚሰማው “ተዋጊ ስለነበር” መቋቋማያ ያሻዋል የሚሉት እየገነኑ ነው” ይላል፡፡ “የአገዛዙን አውታሮች ተገን አድርገው በተቋራጭነት፣ በዕቃዎችና አገልግሎቶች አቅራቢነት እንዲሁም በሌሎች ተግባራት ሳቢያ ጥቅሞችን ለተወሰኑ ክፍሎች ማርከፍከፍ የተለመደ አሠራር መሆኑን ሁሉም ያውቃል…” ይላል፡፡ በዚህ ዓመት ከዚህም ያውጣን፡፡ ቢያንስ ዐይን ካወጣ ሙስና ይሰውረን፡፡ ከነናይጄሪያ ዓይነት ምዝበራና ዘረፋ እንዳንጠጋ ያድርገን፡፡
ወጣቱ አገሩን ከልቡ ይወድ ዘንድ፣ ምንም ዓይነት ካፒታሊስታዊ ማማለያ እንዳይበግረው ከልብ እንመኝ!!
አስማተኛ ካልሆነ በቀር አገርን ብቻውን የሚገነባ ማንም አይኖርም፡፡ አንዱ የሌላውን አቅም ይፈልጋል፡፡ ከሌላ ጋር ካልመከሩ፣ ከሌላ ጋር ካልተረዳዱና ሁሉን ብቻዬን ልወጣ ካሉ አንድ ልሙጥ አገር ናት የምትኖረን፡፡ የተለያየ ቀለሟ ይጠፋል፡፡ ልዩነት ከሌለ ዕድገት ይጠፋል፡፡ VIVE La difference - ልዩነት ለዘላለም ይኑር ማለት አለብን፡፡ እየተራረሙ መሄድ እንጂ እየኮረኮሙ መሄድ የትም አያደርሰን፡፡ አንዱ ኮርኳሚ ብዙሃኑ ተኮርኳሚ ከሆነ እጅም ይዝላል፡፡ ራሳችን ባወጣነው ህግ ራሳችን አጥፊ ሆነን ከተገኘን፣ ለጥቂቶች ብቻ የሚሠራ ደንብ አውጥተን ብዙሃኑን የምንበድል ከሆነ፣ ራሳችን ሠርተን እራሳችን የምናፈርስ ከሆነ፣ ራሳችን አሳዳጅ ራሳችን ተሳዳጅ ከሆንን፣ ከዓመት ዓመት “የዕውነት ዳኛ ከወዴት አለ?” የምንባባል ከሆነ፤ ምን ዓይነት ለውጥ፣ ምን ዓይነት ዕድገት እየጠበቅን ነው? “ብቻውን የሚሮጥ የሚቀድመው የለ፣ ብቻውን የሚሟገት የሚረታው የለ” ነውና በርካቶችን የሚያሳትፍ ሥርዓት ይበረክታል ብለን የምናስብበት ዘመን ይሁንልን፡፡ አለበለዚያ፤ “ራሷ ከትፋው ታነቀች፤ ራሷ ጠጥታው ትን አላት፡፡ ራሷ ሰቅላው ራቀ፡፡ ራሷ ነክታው ወደቀ” የሚል ህዝብ ብቻ ነው የሚኖረን፡፡ ያለ ህዝብ የት ይደርሳል? አዲሱን ዘመን አሳታፊ ያድርግልን!!
መልካም አዲስ ዓመት  


Published in ርዕሰ አንቀፅ

          ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም እ.ኤ.አ በ2013 በአለም ዙሪያ በሚገኙ 95 አገራት በሰራው ጥናት፣ ባለፈው አመት ከአፍሪካ አህጉር አነስተኛ ሙስና የተሰራባት አገር ኢትዮጵያ እንደሆነች ማስታወቁን የኬንያው ዘ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ አልጀዚራ በበኩሉ ትናንት ባወጣው ዘገባ፣ በኢትዮጵያ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ቅንጦት ነው ብሏል፡፡
የአገራትን ዜጎች አስተያየትና ሌሎች መስፈርቶችን በመጠቀም ባወጣቸው የሙስና መለኪያዎች በ6 በመቶ ነጥብ ያገኘችው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት አነስተኛ ሙስና ያለባት አገር እንደሆነች የገለጸው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፣ ዴንማርክ፣ ፊላንድ፣ ጃፓንና አውስትራሊያም በተመሳሳይ ሁኔታ 1 በመቶ ነጥብ ይዘው በአለማችን አነስተኛ ሙስና ያለባቸው አገሮች መሆናቸውን በጥናቱ ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡
በሙስና መለኪያዎች 84 በመቶ ውጤት ያገኘችው ሴራሊዮን በአለማችን ከፍተኛ ሙስና የሚፈጸምባት አገር እንደሆነች የገለጸው ተቋሙ፣ ላይቤሪያ፣ የመንና ኬንያ እንደሚከተሏት አስታውቋል፡፡
ከአፍሪካ ሁለተኛዋ አነስተኛ ሙስና ያለባት አገር ሩዋንዳ መሆኗን የገለጸው ተቋሙ፣ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት መካከልም ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ሱዳን በቅደም ተከተል ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ይዘው እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡
አልጀዚራ በበኩሉ ትናንት ለንባብ ባበቃው ዘገባው በኢትዮጵያ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ቅንጦት እንደሆነ ገልጾ፣ ምንም እንኳን 52 በመቶ የአገሪቱ ህዝብ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የተሟላለት ቢሆንም፣ የውሃ መስመር ቤታቸው ድረስ የተዘረጋላቸው የአገሪቱ ዜጎች 10 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ አስረድቷል፡፡በአገሪቱ የገጠር አካባቢዎች ከሚኖሩት ዜጎች የንጹህ የመጠጥ ውሃ ቧንቧ መስመር የተዘረጋላቸው አንድ በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑም ገልጧል፡፡የአገሪቱ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ቢሆንም፣ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አሁንም ድረስ በበቂ ሁኔታ አለመሟላቱንና ከፍተና ስራ መስራት እንደሚገባም አስታውቋል፡፡

Published in ዜና

        ላለፉት ዓመታት የቅጂና ተዛማች መብቶች ጥሰት በፈጠረው ስጋት ተቀዛቅዞ የከረመው የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዘንድሮ የተነቃቃ ይመስላል፡
ታዋቂ ድምፃውያን ለአዲሱ አመት አዳዲስ ነጠላ ዜማቸውንና አልበማቸውን አበርክተዋል፡፡ ይሄም ለሰሞኑ የአውዳመት ድባብ ተጨማሪ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡
የአብነት አጎናፍር “አስታራቂ፣ የታምራት ደስታ “ከዛ ሰፈር”፣ የዮሴፍ ገብሬ “መቼ ነው” የሰለሞን ሃይለ “ውህብቶ”፣ የቤተልሔም ዳኛቸው “ሰው በአገሩ” እና የተስፋፅዮን ገ/መስቀል “ጀመረኒ” እንዲሁም የቴዎድሮ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ሰባ ደረጃ” ነጠላ ዜማም ለአዲስ ዓመት ከተበረከቱ የሙዚቃ ስራዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡
“ሙዚቃ እንደ በረዶ በቀዘቀዘበት ዘመን ደፍረውና መስዋዕትነት ከፍለው አዲስ ነገር ይዘው ስለመጡ አድናቆት ይገባቸዋል” ብለዋል በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስራ ኃላፊ የሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የሙዚቃ ባለሙያ፡፡
በዚህ አመት ለአድማጭ ይበቃሉ ከተባሉት የሙዚቃ አልበሞች መካከል፣ የኤፍሬም ታምሩ አልበም የሚጠቀስ ሊሆን፣ የድምፃዊው ወላጅ እናት በሳምንቱ መጀመሪያ ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው ምክንያት አልበሙ ሳይለቀቅ ቀርቷል፡
የአብነት አጎናፍር “አስታራቂ”
ከሁለት ሳምንት በፊት ገበያ ላይ የዋለው አብነት አጎናፍር “አስታራቂ” አልበም 14 ዘፈኖች የተካተቱበት ሲሆን ካሙዙ ካሳ፣ ሚካኤል ሀይሉና አቤል ጳውሎስ አቀናብረውታል፡፡  ድምፃዊው ሶስተኛ ስራው በሆነው በዚህ አልበም አገራዊ፣ ማህበራዊ እና የፍቅር ጉዳዮችን የዳሰሳ ሲሆን ከአድማጮች በተገኘ አስተያየት፣ ከአብነት ስራዎች ውስጥ ስለአገር የዘፈናቸው “አያውቁንም”፣ “ለማን ብዬ”፣ “አስታራቂ” እና “የኔ ውዳሴ” የተሰኙት ይበልጥ ተወደዋል፡፡ በAB ሙዚቃና ፊልም ፕሮዳክሽን የታተመው “አስታራቂ” አልበም፤ በአርዲ ኢንተርቴይመንት እየተከፋፈለ ሲሆን የአዲሱ ዓመት አንዱ ገጸ በረከት ነው፡፡ አብነት ከአማርኛ ሙዚቃ በተጨማሪ ሱዳንኛ እንደሚጫወት የሚታወቅ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ “አያሌሌ” የተሰኘ የጉራጊኛ ዘፈን አካትቷል፡፡ ድምፃዊው በአብዛኛው ዘፈኖቹ ላይ በግጥምና በዜማ ድርሰት ተሳትፏል፡፡
የታምራት ደስታ “ከዛ ሰፈር”
ለአዲሱ ዓመት በገፀ-በረከትነት ከቀረቡት አልበሞች ውስጥ የታምራት ደስታ አራተኛ ስራ የሆነው “ከዛ ሰፈር” አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ለአድማጭ ጆሮ የደረሰው ይሄው አልበም፤ 14 ዘፈኖችን አካትቷል፡፡ ካሙዙ ካሳ፣ ሚካኤል ሃይሉ፣ ሚካኤል መለሰና ኪሩቤል ተስፋዬ በቅንብር የተሳተፉበት ይሄ ስራ፤ በግጥም እና ዜማ ጌትሽ ማሞ አማኑኤል ይልማ፣ መሰለ ጌታሁንና ኢዩኤል ብርሃኔን አሳትፏል፡፡ በናሆም ሪከርድስ አሳታሚና አከፋፋይነት ገበያ ላይ የዋለው የታምራት አልበም፤ በስፋት እየተደመጠ ሲሆን በተለይም “ሊጀማምረኝ ነው” “አዲስ አበባ”፣ “ማማዬ” እና የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “ከዚያ ሰፈር” የተሰኙ ዘፈኖች የበለጠ እየተሰሙ እንደሚገኙ ከአድማጮች አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡
የቴዲ አፍሮ “ሰባ ደረጃ”
ከበደሌ ጋር አመቱን ሙሉ በሚዘልቅና “ወደ ፍቅር ጉዞ” በተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርት ከአድናቂዎቹ ጋር ለመገናኘት የጀመረው ስራ የተሰናከለበት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፤ ከሁለት ሳምንታት በፊት የለቀቀው “ሰባ ደረጃ” የተሰኘ  ነጠላ ዜማው በስፋት እየተደመጠ ሲሆን ማህበራዊ ድረ - ገፆችን በተለይም ፌስ ቡክን ተቆጣሮጥት ሰንብቷል፡፡ የቴዲ “ሰባ ደረጃ” ፒያሳ፣ ዶሮ ማነቂያ፣ ሰራተኛ ሰፈር፣ አራት ኪሎን፣ ታሪካዊ ክስተቶችንና አለባበሶችን ከፍቅር ጋር እያሰናሰለ ያነሳሳል፡፡ የቴዲ አፍሮ “ሰባ ደረጃ” ነጠላ ዜማ ሙሉ አልበምን የመወከል ያህል ተቀባይነት አግኝቶ በየምሽት ቤቱ፣ በየሆቴሉና በየሬስቶራንቱ በስፋት እየተደመጠ ያለ የአዲስ አመት የበዓል ድምቀት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የሰለሞን ሃይለ “ውህብቶ”
“ቆሪብኪለኩ” (ቆረብኩልሽ) በሚለው የመጀመሪያ አልበሙ በተለይም “ንኢባባ” በተሰኘው ዘፈኑ የሚታወቀው ወጣቱ የትግርይኛ ዘፋኝ ሰለሞን ሃይለም ከሳምንታት በፊት “ውህበቶ” የተሰኘ አልበም ለአድማጭ አቅርቧል፡፡ አልበሙ 12 ዘፈኖችን ያካተተ ሲሆን፣ ስለ ሃገር፣ ስለ ፍቅር ስለማህበራዊ ጉዳዮች ተነስተውበታል፡፡ ሙሉ ግጥምና ዜማው በራሱ በድምፃዊው የተሰራ ሲሆን፣ በቅንብሩ አብዛኛውን ዘፈኖች ተወልደ ገ/መድህን ሲሰራ፣ ሁለት ዘፈኖችን ዮናስ መሃሪ እና ደነቀው ኪሮስ፣ አንዱን ዘፈን ዘመን አለምሰገድ አቀናብረውታል፡፡ በስፋት እየተደመጠም ይገኛል፡፡
የዮሴፍ ገብሬ “መቼ ነው”
ድምፃዊና ጋዜጠኛ ዮሴፍ ገብሬም አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ “መቼ ነው” የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ አልበሙን ከ10 ቀናት በፊት በገበያ ላይ አውሏል፡፡ ለዝግጅት 6 አመታትን የፈጀው ይሄው አልበም፤ በአገር፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመተሳሰብ ላይ የሚያተኩር ሲሆን 7 አቀናባሪዎችና የተለያዩ የግጥምና ዜማ ደራሲዎች ተሳትፈውበታል፡፡ “መቼ ነው” የተሰኘው የአልበሙ መጠሪያ፣ “ክፉ አይንካብኝ” ሲል ስለ አገር የዘፈነው፣ “ፍቅር ነው ያገናኘኝ” እንዲሁም ስለአንድነትና መተባበር (በጉራጊኛ) የዘፈናቸው ይበልጥ ተወዳጅ እንደሆኑለት ከአድማጮች ያገኘነው አስተያየት ይጠቁማል፡፡ አልበሙ በተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎች በስፋት እየተደመጠ ይገኛል፡፡  
የቤተልሔም “ሰው በአገሩ”
በ1996 ዓ.ም ለአድማጭ ባቀረበችው “ቅዳሜ ገበያ” የተሰኘ ባህላዊ ዜማዋ የምትታወቀው ድምፃዊት ቤተልሔም ዳኛቸው፣ ሰሞኑን “ሰው በአገሩ” የተሰኘ አዲስ አልበሟን ለአድማጭ አቅርባለች፡፡
ነዋሪነቷ በስዊዘርላንድ የሆነው ድምፃዊት ቤተልሔም ያቀረበችው አዲስ አልበም፤ 13 ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች የተካተቱበት ነው፡፡ ታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪና የድምፃዊቷ ባለቤት ዳዊት ጥላሁን ባቀናበረው በዚህ አልበም ውስጥ ራሱ ዳዊትና ቤተልሔም ጥላሁን በዜማና ግጥም ደራሲነት ተሳትፈዋል፡፡
የተስፋፅዮን “ጀመረኒ”
በባህላዊ የማሲንቆ አጨዋወቱ አድናቆት የተቸረው ድምጻዊ ተስፋፅዮን ገ/መስቀል ከሰሞኑ “ጀመረኒ” የተሰኘውንና ራሱን በማሲንቆ ያጀበበትን የትግርኛ ሙዚቃዎች ለአድማጭ አብቅቷል፡፡ ከዚህ ቀደም “ቆልዑ ገዛና” የተሰኘ አልበም አውጥቶ ተቀባይነትን ያገኘው ድምፃዊው፤ በ“ጀመረኒ” አልበሙ የሰርግን ጨምሮ በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 13 ሙዚቃዎችን አካትቷል፡፡ አልበሙን ዳአማት መልቲ ሚዲያ አሳትሞ እያከፋፈለው ሲሆን፣ ለአዲሱ ዓመት በተለይ በትግርኛ ዘፈን አድማጮች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
“አራዳ” ቪሲዲ ኮሌክሽን
በመስፍን ታምሬ ፕሮዲዩሰርነት የታተመውና 14 እውቅ ድምፃዊያን የተሳተፉበት “አራዳ” ባህላዊ እና ዘመናዊ ዘፈኖች በምስል (በቪዲዮ) የቀረቡበት ነው፡፡ የዚህ ቪሲዲ አዘጋጅ “ኢቫንጋዲ ፕሮዳክሽን” ሲሆን “ፒያሳ ዘ አራዳ ኢንተርቴይመንት” አሳትሞ ከትናንት ጀምሮ እያከፋፈለው ይገኛል፡፡ በ“አራዳ” ኮሌክሽን ቪሲዲ ላይ ሸዋንዳኝ ሃይሉ፣ ብዙአየሁ ደምሴ፣ እመቤት ነጋሱሲ (ሰንዳበል)፣ ጃኪ ጎሲ፣ የኦሮምኛ ዘፋኙ አበበ ከፍኔና  ቤተልሄም ዳኛቸውን ጨምሮ 14 ያህል ታዋቂ ድምፃዊያን ተሳትፈውበታል፡፡
“አራዳ” ብቸኛው ለአዲስ ዓመት የተዘጋጀ ቪሲዲ እንደሆነ ታውቋል፡፡

Published in ዜና
Page 14 of 14