Saturday, 26 January 2013 16:09

ሐምሊን - የአዋላጆች ኮሌጅ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(3 votes)

“ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ” በአገሪቱ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ ሲሆን የተመሰረተውም በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ኮሌጁ ተማሪዎችን በዲግሪ ደረጃ የሚያስመርቅ ሲሆን በማስተማር ሂደቱም ከፌደራል የጤና ጥበቃ ሚኒስር ጋር በትብብር የሚሰራ ነው፡፡ ሐምሊን የአዋላጆች መማሪያ ኮሌጅ የተከፈተው እንደውጭው አቆጣጠር በ2007/ ዓ.ም ሲሆን እስከአሁን ባለው ሂደትም ከመቶ በላይ አዋላጆችን በዲግሪ ከፊሉን ያስመረቀ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ሲመሰረት አላማው አዋላጆች ለእያንዳንዱዋ ሴት ያስፈልጉዋታል የሚል ነው፡፡ ኮሌጁ ተማሪዎችን በምን መንገድ እንደሚቀበል እንዲሁም ቀጣይ የስራ ተግባሩ ምን ሊመስል እንደሚችል የኮሌጁ የኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መላኩ ተድባበ አብራርተውልናል፡፡ ከአቶ መላኩ ማብራሪያ በማስቀደም የአንዲት ተማሪንና የኮሌጁን ኒውስ ሌተር ውይይት እናስነብባች ሁዋለን፡፡
***
“...ወደ ኮሌጁ የመጣሁት ከትግራይ መስተዳድር ከመቀሌ ማለትም ከአዲስ አበባ ወደ 780 ኪሎ ሜትር ርቀት ነው፡፡ እድሜዬም 19 አመት ነው፡፡ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርን ያጠናቀቅሁት ከመቀሌ 30 ኪሎ ሜትር ወጣ ባለች የገጠር ከተማ ነው፡፡ የመሰናዶ ትምህርን በመቀሌ ከተማ እንዳጠናቀቅሁ ወደ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ በ2012 ዓ.ም ለመግባት ችያለሁ”
ጥ/ ስለፌስቱላ የምታውቂው ወይንም ያየሸው ምን ልምድ አለሽ?
መ/ እኔ እራሴ የፌስቱላ ታማሚ ነበርኩ፡፡ ቤተሰቦቼ በግብርና የሚተዳደሩ ስለሆኑ እንደሀገሩ ልማድ በልጅነ ነው የተዳርኩት፡፡ ገና ሰውነ ሳይጠና በማርገዜ ልጅ ከመውለድ ጋር ተያይዞ በምጥ ምክንያት ችግሩ አጋጥሞኛል፡፡ ከዚያ በሁዋላም የ14/አመት ልጅ ሆኜም ወደመቀሌ ሄጄ ስለነበር የኤፍ ኤም ሬድዮ ስለፌስቱላ ሲናገር ስለሰማሁ እና በአካባቢው ሆስፒታሉ መኖሩንም ስለአወቅሁ ወደዚያ ሄጄ ታክሜአለሁ፡፡ አኔ መማር ብፈልግም ብዙ እንዳልማር የሚያደርጉኝ ችግሮች ገጥመውኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በሕክምናው እና በሁዋላም ለመማር ባደረግሁት ጥረት የረዱኝን ሰዎች በጣም እያመሰገንኩ እነሆ ለውጤት በቅቻለሁ፡፡
ጥ/ በሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ለመማር በመብቃትሽ ምን ስሜት አለሽ?
መ/ እኔ የፌስቱላ ሕመም ማለት ምን ማለት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ በየገጠሩ እንደእኔ ያሉ ሴት ሕጻናት ምን ያህል እንደሚሰቃዩ ሳስብ ይህንን ትምህርት መማሬና ችግሩ ወዳለበት አካባቢ በመሄድ ሴቶች ወደችግር እንዳይገቡ አስቀድሜ ለማዋለድ በመታደሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
ከምረቃዬ በሁዋላ በገባሁት ቃል መሰረት ወደገጠሪቷ ኢትዮጵያ ተመድቤ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡
ምንጭ /The Hamlin College of Midwives/volume 1 issue 8/
***
ኢሶግ፡ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ለምን ተቋቋመ?
መላኩ፡ ኮሌጁ በዋነኛነት የተቋቋመበት ምክንያት የፌስቱላን ሕመም ለመከላከል ከሚያስችሉት ምክንያቶች ዋነኛው እናቶች በሰለጠነ የሰው ኃይል መውለድ መቻላቸው በመሆኑ ለዛ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን በማስተማር ለሕብረተሰቡ ለማቅረብ ነው፡፡ ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ይህንን ኮሌጅ እንዲከፈት ሲያደርግ .....አዋላጅ የህክምና ባለሙያዎች ለእያንዳንዱዋ ሴት..... በሚል መሪ ሀሳብ ነው፡፡ ብዙ ሴቶች በየገጠሩ በተለያዩ ምክንያቶች በሰለጠነ ሰው መውለድ ባለመቻላቸው ምክንያት ከ4/ ቀን ላላነሰ ጊዜ በምጥ ስለሚሰቃዩ እና ገላቸው ባለመጠንከሩ ምክንያት በማህጸን አካባቢያቸው የሰውነት መቀደድ ስለሚደርስባቸው ፌስቱላ ለተባለው የከፋ ሕመም ይጋለጣሉ፡፡ ስለዚህ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምሩቃንን ለሕብረተሰቡ በማቅረብ በሰለጠነ ባለሙያ እንዲወልዱ ማድረግ ዋነኛ አላማው ነው፡፡
ኢሶግ፡ የተማሪዎች ቅበላ ስርአቱ ምን ይመስላል?
መላኩ፡ ኮሌጁ ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም እንደውጭው አቆጣጠር ከ2007/ ጀምሮ
በተለይም ለፌስቱላ ሕመም የተጋለጡ አካባቢዎችን በማስቀደም ተማሪዎችን እየተቀበለ በዲግሪ ያስመርቃል፡፡
ተማሪዎቹ እንደሌላው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የኮሌጁን የመግቢያ መስፈርት እንዲያሙዋሉ የሚጠበቅ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ኮሌጁ የሚያወጣውን የመግቢያ ፈተና ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ የሚቀበላቸው ተማሪዎች በሙያው ለመስራት ፈቃደኞች የሆኑትን፣ በተለይም ተመልምለው ወደመጡበት የገጠር ክፍል ተመልሰው ለመስራት የሚፈርሙትንና ቃል የሚገቡትን ይመርጣል፡፡ ምናልባትም የመሰናዶ ትምህርትን አጠናቀው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የሚገቡት ተማሪዎችና ወደ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ከሚገቡት ተማሪዎች የሚለዩት በተጠቀሱት መመዘኛዎች ነው፡፡
ኢሶግ፡ ተማሪዎቹ በጾታ ይለያሉ?
መላኩ፡ ተማሪዎቹ በሙሉ ሴቶች ናቸውምክንያቱም በአብዛኛው እናቶች ችግራቸውን ሙሉ በሙሉ ገልጸው ለመናገር ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን ይመርጣሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለሙያዎቹም ሴቶች ቢሆኑ የችግሩን ምንነት ለመረዳት ይበልጡኑ ቅርብ ይሆናሉ የሚል ግምት አለ፡፡ ተማሪዎቹ ከተመረቁ በሁዋላ የሚሰሩት በገጠሪቱዋ አካባቢ በመሆኑም በአካባቢው ላሉ አባወራዎችም ስሜት ከወንዶቹ ይልቅ ሴቶቹ እናቶቹን ቢያዋልዱ እንደሚመርጡም አንዳንድ ማሳያዎች አሉ፡፡ ወደ ኮሌጁ ስንመለስ የተሰራው የመኖሪያ አካባቢ ወንድና ሴትን በተለያየ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የማይመች ስለሆነ ተማሪዎቹ ሴቶች ብቻ እንዲሆኑ ተወሰነ፡፡
ኢሶግ፡ ምሩቃኑ ወደ ስራቸው የሚሰማሩት በምን ሁኔታ ነው?
መላኩ፡ ከመንግስት ጋር የትብብር ስምምነት አለ፡፡ ኮሌጁ ቢያስተምርም ወደስራ የሚመድባቸው
መንግስት ነው፡፡ ቀጣሪያቸው እና ደመወዝ የሚከፍላቸው መንግስት ነው፡፡ በማንኛውም ረገድ በመንግስት ሕግ የሚተዳደሩ ሰራተኞች ናቸው፡፡ በእርግጥ ለስራ ሲመደቡ ችግሩ ወደባሰበት እና ወደታወቁ አካባቢዎች ማለትም ምሩቃኑ ወደመጡበት አካባቢ እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡
በገቡት ቃል መሰረት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚገደዱት ለተወሰነ ጊዜ ሲሆን ይህንን ግዴታ ሳይፈጽሙ ተግባራቸውን ቢያቋርጡ ግን በስምምነቱ መሰረት ዶክመንታቸው የሚያዝባቸው ሲሆን በተጨማሪም ለትምህርታቸው የወጣውን ዋጋ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡
ኢሶግ፡ ተማሪዎቹ ከተመረቁ በሁዋላ በምን ሁኔታ ስራቸውን እንደሚያከናውኑ የሚታወቅበት የክትትል ዘዴ አለ?
መላኩ፡ ሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ የተማሪዎችን ምልመላና ምደባ እንዲሁም የስራ ሁኔታ የሚከታተል አንድ ክፍል አለው፡፡ ተማሪዎችን ከአራቱ መስተዳድሮች ትግራይ ፣ኦሮሚያ ፣ደቡብ እና አምሀራ ከመጡ በሁዋላ ወደትምህርቱ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ከዚያም ተምረው ከተመረቁ በሁዋላ ምን እየሰሩ ነው የሚለውን የወር፣ የሶስት ወር እና የስድስት ወር እንዲሁም አመታዊ ሪፖርት ያቀርባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ምሩቃኑ የኮሌጁን አርማ ለብሰው በሚሰሩበት የገጠር አካባቢ ላሉ የጤና ተቋማት የተለያዩ ድጋፎችን ስለምናደርግና እጥረት የሚኖርበት ሁኔታ ካለ የማሟላት ስራ ስለምንሰራ ባለሙያዎቹ የት ነወ ያሉት ብቻ ሳይሆን ምን እየሰሩ ነው ? የሚለውንም ጭምር ኮሌጁ ያውቃል፡፡
ኢሶግ፡ የሐምሊን የአዋላጆች ኮሌጅ ግብ ምንድነው?
መላኩ፡ ግቡ ፌስቱላን መከላከል ብሎም ማስቆም ነው፡፡ እንደውጭው አቆጣጠር 2015 ዓ/ም ድረስም 50/ ሚድዋይፎችን በ25/የጤና ጣቢያዎች ማሰማራት ከመነሻው የተጠቀሰ ግብ ነው፡፡ እንደስራው አካሄድ ግን እስከአሁን በተደረገው የስልጠና ሂደት በአራቱ መስተዳድሮች ወደ 34/አዋላጆች ተመድበው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
አሁኑ ወቅት ከሰባ ያላነሱ ተማሪዎች በኮሌጁ ሙያውን በመቅሰም ላይ ይገኛሉ፡፡ ባለሙያዎቹ በየመስተዳድሩ በተመረጡ ባለሙያዎችን መመደብ ብቻ ሳይሆን አምቡላንስም በማቅረብ ከእነርሱ አቅም በላይ የሆነ ችግር ሲፈጠር እናቶች ከፍ ወዳለ ሕክምና እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ አምቡላንሶቹ ክረምት ከበጋ ታካሚዎችን በነጻ በማመላለስ አገልግሎት የሚሰጡ በመሆኑ ከህብረተሰቡም ምስጋን ይደርሳቸዋል፡፡ ስለዚህ ፌስቱላን ለመከላከል በተነደፈው እቅድ መሰረት ኮሌጁ በመስራት ላይ ያለው ስራ እናቶች ለፌስቱላ እንዳይጋለጡ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎአል ብለን እናምናለን፡፡

Read 4069 times