Saturday, 01 June 2013 14:08

የአፍሪካ “አንድነት” ችግሮችን የሚያትቱ መፃሕፍት

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

ጋዳፊ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል በስውር ተንቀሳቅሰዋል

ለአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ከተሰናዱ ዝግጅቶች መሐል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ሙዚየም ውስጥ የቀረበው የፎቶግራፍ፣ የስዕል፣ የቅርፃ ቅርጽና የተለያዩ አልባሳት ኤግዚቢሽን አንዱ ነበር። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከመመሥረቱ አራት ዓመት ቀደም ብሎ አፍሪካዊያንን ለማስተባበር ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ታሪካዊ ተግባር ያከናወነ ከመሆኑ አንፃር ለበዓሉ ዝግጅት ማቅረቢያነት መመረጡ ተገቢ ነው፡፡ “ትምህርት፣ ባህልና ዕድገት፤ የትዝታ ጉዞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ እስከ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋማት” በሚል ርዕስ በደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ ተዘጋጅቶ፤ማህበራዊ ጥናት መድረክ በ1998 ዓ.ም ባሳተመው ጥራዝ፣ አፍሪካዊያንን ለማስተባበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የተከናወነው ተግባር ምን እንደነበር ታሪኩን በሚከተለው መልኩ አቅርቧል፡፡ “ጋና በ1949 ነፃነቷን ተቀዳጅታ፣ በለጠቀው ዓመት አክራ ላይ የስምንት የአፍሪካ ነፃ መንግሥታትን የአርነት ንቅናቄ ታጋዮችን ያገናኘና ያቀራረበ ስብሰባ አካሄደች፡፡

“እዚያ ስብሰባ ላይ የተገኘውን የኢትዮጵያ ተሳታፊ የልዑካን ቡድን የመሩት አቶ አበበ ረታ ሲሆኑ፣ በዋናነት ከልዑካኑ ጋር የንገሡ ነገሥቱ የመጨረሻ ልጅ፣ ልዑል ሣዕለሥላሴ ሄደው ነበር፡፡ “ኢትዮጵያን በሚመለከት በዚህ ጉባኤ ላይ የተከሰተው ነገር፣ በየዓመቱ 50 የአፍሪካ ወጣቶች በኮሌጅ ደረጃ በኢትዮጵያ ለማስተማር የነፃ ትምህርት ዕድል ለተከታታይ አራት ዓመታት መሰጠቱ ነበር። ይህም በ1951 የትምህርት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ሆነ፤ ተማሪዎቹ ከምሥራቅና ከምዕራብ አፍሪካ አገሮች መምጣት ጀመሩ…፡፡” አፍሪካን አንድ የማድረጉ ራዕይ ግማሽ ክፍለ ዘመን አልበቃ ብሎት ተጨማሪ የ50 ዓመታት ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2063 ራዕዩ እውን ይሆናልም ተብሏል፡፡

መሻቱ እንዳይሳካ ቀዳሚው ግማሽ ክፍለ ዘመን በቂ ላይሆን የቻለበት ምክንያት ብዙ አነጋግሯል፤ ተጽፎበታልም፡፡ የማህበራዊ ጥናት መድረክ ባሳተመው የደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ ጽሑፍ ውስጥ ችግሮቹ ከመነሻው መታየታቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎችን አቅርቧል፡፡ የስኮላርሽፕ እድል አግኝተው ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መደረጉ “ሰፋ ያለ አንደምታ ነበረው” የሚለው ጽሑፉ፤ “ለኢትዮጵያዊያኑም ለስኮላርሽፕ ተማሪዎችም የጠቀመ መስተጋብር ተፈጠረ” ይልና በተቃራኒው አፍሪካዊያን ተማሪዎች የአንድነት ስሜት ከማዳበር ይልቅ እንዲለያዩና እንዲከፋፈሉ የሚያደርጉ የተለያዩ አካላት እንደነበሩ ሲያመለክት “ሊያለያዩን ሲያደርጉት ከነበረው እኩይ ቅስቀሳ ውስጥ፣ ኢትዮጵያዊያኑ ተማሪዎች አይወዷችሁም፣ ረጅም ታሪክ አለን ብለው ስለሚኩራሩ ይንቋችኋል። እንዲያውም፣ ባሪያ ነው የሚሏችሁ የሚል ዓይነት ነበር” የሚሉት የጽሑፉ አቅራቢ፤ ከፋፋዮች አፍሪካዊያን ተማሪዎችን ለማለያየት የተጠቀሙበት “ባሪያ” የሚለው ቃል፤ ኢትዮጵያዊያን ወላጆች ልጆቻቸውን በፍቅር የሚጠሩበት፣ ባልንጀሮችም አንዳቸው ሌላኛቸውን “ባሪያ” ወይም “ነጫጭባ” በመባባል ለቀልድና መዝናኛ የሚጠቀሙበት መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ይህንን እውነታ ለሌሎች አፍሪካዊያን ተማሪዎች ለማስረዳት መጣራቸውንም ያመለክታሉ፡፡

“ብዙ አየሁ” በሚል ርዕስ ታደሰ ገ/ኪዳን በ1999 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ ከላይ የተገለፀውን እውነታ የሚያረጋግጥ መረጃ ቀርቧል፤ “ዩኒቨርስቲ ውስጥ ብዙ አፍሪቃውያን ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያዊያን አፍሪቃዊነታቸውን አልተቀበሉም የሚል ቅሬታ ስለነበራቸው እነሱን ለማስታመምና ስሜታቸውን ለመጠበቅ ጥረት ይደረግ እንደነበር አውቃለሁ” ይላሉ፡፡ አቶ ታደሰ ገ/ኪዳን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ትዝታቸውን በስፋት ባቀረቡበት መጽሐፍ ውስጥ “ስለዘረኝነት አፋችንን ሞልተን መከራከር የማንችልበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን” በማለት ገጠመኞቻቸውን አቅርበዋል፡፡ አንዱ ገጠመኝ መርካቶ ውስጥ በሙህር ሰፈር የተመለከቱት ነው። ዘመኑ 1961 ዓ.ም ነበር፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመመሥረቻ ጉባኤ በኢትዮጵያ መደረጉ ለአገራችን ካስገኛቸው ጥቅሞች መካከል የቴሌቪዥን አገልግሎት ስርጭት በአዲስ አበባ እንዲጀመር ማስቻሉ አንዱ ነው፡፡ በዘመኑ በተመረጡ አደባባዮች ላይ ቴሌቪዥን በመስቀል ሕብረተሰቡ በጋራ እንዲገለገልባቸው ይደረግ ነበር። ከጊዜ በኋላ ቀስ በቀስ ግለሰቦች ቴሌቪዥን እየገዙ በየቤታቸው መገልገል ጀመሩ፡፡ በመርካቶ ሙህር ሰፈር ቴሌቪዥን ገዝቼ ለቤት መገልገያ እንዲሆን በማድረግ እኔ የመጀመሪያው ባለ ታሪክ ሳልሆን አልቀርም የሚሉት አቶ ታደሰ ገ/ኪዳን በ1961 ዓ.ም ያስተዋሉትን ሲገልፁ፡- “ቴሌቪዥኑ ቤት የገባ ዕለት ያካባቢው ሰው ቤታችንን አጥለቀለቀው፡፡ እበረንዳው ለተኮለኮሉት ሰዎች መስኮት ተከፈተለት፡፡

ሁለት ሰዓት ላይ የወሬ ፕሮግራም ተጀመረና የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ኬነት ካውንዳ ምሥል ስክሪኑን ሞላው፡፡ ቤቱ በአንድ ጊዜ በሣቅ ተናጋ …” ይላሉ፡፡ የሣቁ መነሻ ኢትዮጵያዊያን የጥቁር ሰው መልክ ሲያዩ ከሚሰማቸው ስሜት ጋር የተያያዘና እርስ በእርሳቸውም “ባሪያ” እያሉ ከሚቀላለዱት ጋር የሚገናኝ ይመስላል፡፡ በ559 ገፆች የቀረበው የአቶ ታደሰ ገ/ኪዳን ግለ-ሕይወት ታሪክ፤ አፍሪካዊያን እንዳይተባበሩ፣ እንዲጠላሉ፣ እንዲከፋፈሉና በራስ የመተማመን ስሜታቸው የተሸረሸረ እንዲሆን ፈረንጆች የፈፀሟቸውን ድርጊቶች በመጽሐፋቸው አቅርበዋል፡፡ “በሌሎች የአፍሪቃ አገሮች፣ ፈረንጆች ያፍሪቃውያንን ሥነ ልቦና በልዩ ልዩ መንገድ ይፈታተኑ እንደነበር ከብዙ አቅጣጫ የሰማነው ነው” በማለት የተለያዩ ማሳያዎችን ያቀርባሉ፡፡ አንዱ ማሳያቸው የማላዊው ካሙዙ ባንዳ ናቸው፡፡ ካሙዙ ባንዳ በነፃነት የትግል ወቅት የንክሩማህ የትግል አጋር የነበሩ፣ ቅኝ ግዛትን በመቃወም የሚታወቁ፣ አፍሪካዊነት ስለተደፈረ ወደ ቀድሞ ማንነታችን ለመመለስ ተባብረን መቆም አለብን የሚሉ ታጋይ ነበሩ፡፡

አፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ግን የማላዊ ፕሬዚዳንት የነበሩት ካሙዙ ባንዳ በመክፈቻው ሥነ ስርዓት ላይ አለመገኘታቸውን የሚያወሳው መጽሐፉ፤ “ገና ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው ዘረኛው የደቡብ አፍሪቃ አገዛዝ ባለስልጣኖች አፋቸውን በብር ጠቅጥቀው ዝም አሰኙዋቸው፡፡ ይባስ ብሎ፣ አፍሪቃ፣ አፍሪቃ ይሉት የነበሩት ሰው የስድብ ቃላት እየፈበረኩ የአፍሪቃ መሪዎችን ኢላማቸው አደረጉ፡፡ ህዝባቸውን ስለ አፍሪካዊያን ቋንቋና ታሪክ እንደማስተማር ቅድሚያ ለላቲን ሰጡ፡፡ በአጭሩ ነጭ አምላኪ ሆነው ቁጭ አሉ” የአቶ ታደሰ ገ/ኪዳን ግለ-ሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ስለ አፍሪካና የአፍሪካዊያን ማተት ዋነኛ ዓላማው ባይሆንም ባለ ታሪኩ ካሳለፉት የሕይወትና የሥራ ታሪክ ጋር በተያያዘ በሥራ አጋጣሚ ስለተመለከቷቸው የአፍሪካ አገራትና መንግሥታት በመጽሐፋቸው ያሰፈሩት መረጃ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ አስደማሚው ነገር ደግሞ የመረጃው መብዛት ብቻ ሳይሆን፤ አፍሪካዊያን መንግስታት ለመተባበር እንቅፋት የሆነባቸውን ሚስጥር አመላካች መሆኑ ጭምር ነው፡፡

ፍፃሜያቸው ካላማረው የአህጉሪቱ መሪዎች አንዱ የነበሩት ሙሐመድ ጋዳፊ ወደ መጨረሻው ስለ አፍሪካ ውህደት ተሟጋች በመሆን ለመታወቅ ጥረት ላይ ነበሩ፡፡ ከዓመታት በፊት ግን ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል በስውር ከመንቀሳቀሳቸውም በላይ ኤርትራና ኢትዮጵያ ራሳቸውን የቻሉ ሁለት አገራት መሆናቸውን የሚያመለክት ካርታ አሰርተው በቢሯቸው እንዲሰቀል ያደረጉ መሪ ነበሩ ይላል፡- የታደሰ ገ/ኪዳን “ብዙ አየሁ” መጽሐፍ፡፡ ዘመኑ 1970 ዓ.ም ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኩባ ሊቢያና ደቡብ የመን የአንድነት ግንባር ፈጥረው ነበር። በኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም የሚመራ የልዑካን ቡድን ይህን ወዳጅነት መሠረት ያደረገ ጉብኝት፤ በሊቢያ አድርጓል፡፡ በዚያ የልዑካን ቡድን ውስጥ የምድር ጦር፣ የአየር ኃይል፣ የባሕር ኃይል አዛዦችና የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትርም ተገኝተው ነበር። የልዑካኑ ቡድኑ እንዲያርፍበት በተዘጋጀ ክፍል ግድግዳ ላይ ነበር ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ የሚያሳየው ካርታ የተሰቀለው፡፡ ሌላው ተመሳሳይ ታሪክ በሶማሊያ የታየ ነው፡፡

በ1967 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዓመቱ ሊቀመንበር የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ዚያድባሬ ነበሩ፡፡ በአፍሪካዊያን መካከል አንድነት ስለማጠናከር ፕሬዚዳንቱ በሞቃዲሾ ያደረጉትን ንግግር፤ የስብሰባው ተካፋይ ሆነው የሰሙት አቶ ታደሰ ገ/ኪዳን ከዚያድባሬ የሰሙት ንግግርና በዘመኑ በተለይ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የነበረውን እንኪያሰላንታ ታዝበው ታሪኩን የመጽሐፋቸው አካል አድርገዋል፡፡ ያ ክስተት አፍሪካዊያን መሪዎች ለጎረቤት አገራት ብቻ ሳይሆን ለሕዝባቸውም ክብር ሳይሰጡ አህጉሪቷን ስለማዋሀድ ይደሰኩሩ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ አቶ ታደሰ ገ/ኪዳን በናይጀሪያ ጉብኝት ያስተዋሉት ነገር ይህንኑ እውነታ የሚያጐላ ነበር፡፡ በተለይ ኢትዮጵያዊያን በመሪዎቻቸው ስለመንገላታታቸው ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ “ስለ ናይጀሪያ ጉብኝት በተለይ የማስታውሰው ሊቀመንበራችን ላደረገው ንግግር ፕሬዚዳንት አባሳንጆ የሰጠው መልስ ነው፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ የኢትዮጵያ አብዮት ስላፈራረሳቸው አድኅሪ ተቋማትና ስላጠፋቸው ኋላቀር ባሕሎች ሰፊ ገለጻ አደረገ፡፡

ፕሬዚዳንት አባሳንጆ በሰጠው መልስ ሥርዓታችንና ባሕላችን ለኛ ተስማሚ ሆነው ስላገኘናቸው የምንለውጠው ነገር አይኖርም አለ። ይህን አባባል አብዮታችሁን አልወደድንላችሁም እንዳለ አድርገን ወሰድነው፡፡” ፕሬዚዳንት አባሳንጆ ለኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም የሰጡት መልስ የብልህ አገር መሪዎችን መልካም ተግባር ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው፡፡ ለሚቀጥለው 50 ዓመታት እደርስበታለሁ ያለውን ራዕይ ያኖረው የአፍሪካ ህብረት፣ በህዳሴው ዘመን አንድ ብሎ የጀመረው ታሪክ ምን ውጤት እንደሚያስመዘግብ የሚታወቀው ከፊት ያሉት የጊዜ ቋጠሮ ሲፈታ ነው፡፡ የአህጉሪቱ ህዳሴ እውን ሊሆን የሚችለው አገራቱ እርስ በእርስ መከባበር ሲችሉ ብቻ ሳይሆን ለዜጎቻቸውም ተገቢውን ክብር መስጠት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ችግር ለ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ መድረስ ግን “ተመስገን” የሚያስብል ነው፡፡

Read 2541 times