Saturday, 01 June 2013 14:16

የኢትዮጵያ ስፖርት ህዳሴ ብልጭታዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(7 votes)

አካዳሚ፤ ማሰልጠኛዎች እና ስታድዬሞች…

             በስፖርት መስክ ዘላቂ ዕድገት ለማምጣት እና በመላው አገሪቱ ለማስፋፋት አካዳሚዎች፤ ማሰልጠኛዎች እና ስታድዬሞችን መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የኢትዮጵያ ስፖርት ህዳሴን የሚያረጋግጡ የተስፋ ብልጭታዎች እየታዩ ናቸው፡፡ ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ በመንግስት እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት በተለይ በስፖርቱ መሰረተልማቶች ዙርያ ተስፋ ሰጭ ተግባራት እና አቅጣጫዎች ተይዘዋል፡፡ የአገራችንን ስፖርት እንቅስቃሴ ከሳይንሳዊ እና ዘመናዊ ስልጠና ጋር በማያያዝ የሚሰሩት እነዚህ የውድድር መሰረተ ልማቶች የማሰልጠኛ ተቋማት ለውጥ እና እድገት እንደሚያመጡ ይጠበቃል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አካዳሚዎች፤ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማእከሎች፤ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ስታድዬሞች ተገንብተው ስራ ጀምረዋል፤ በመገንባትም ላይ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማእከሎች ስራ በመጀመር ውጤት እያሳዩ ነው፡፡

ከመንግስት ባሻገር በታዋቂ አትሌቶች የተመሰረቱ የስፖርት ልማቶች ብቅ እያሉ ናቸው፡፡ በሱሉልታ አካባቢ ያያ የስፖርት መንደር እና የቀነኒሳ በቀለ የስፖርት እና መዝናኛ ማእከል ባለፉት ሁለት አመታት ስራ ጀምረው ለአገር ውስጥ አትሌቶች አማራጭ የልምምድ ስፍራዎችን በመሆን እና ከውጭ ለሚመጡት በስፖርት ቱሪዝም አገልግሎት በመስጠት ለውጥ መፍጠር ጀምረዋል፡፡ በአርሲ በጥሩነሽ ዲባባ የተሰየመው የአሰላ አትሌቲክስ ማዕከል ባለፉት ጥቂት አመታት ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። ሰሞኑን የግንቦት 20 የድል በዓል 22ኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት ለኢትዮጵያ ስፖርት ህዳሴ ሁነኛ መሰረት እና ማነቃቂያ የሆነው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ግንባታው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

320 ሠልጣኞችንና 36 አሠልጣኞችን በአዳሪነት የማስተናገድ አቅም ያለው የስፖርት አካዳሚው ለአጠቃላይ ግንባታው እስከ 317 ሚሊዮን ብር ወጭ ሆኖበታል፡፡ በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች ማለትም አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ቦክስ፣ ብስክሌት፣ ቅርጫት ኳስና ውኃ ዋና ሥልጠና እንደሚሰጥበት ይጠበቃል፡፡ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚውን በመመረቅ ስራ አስጀምረዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ስፖርት ህዳሴ ማእከል የሆነው አካዳሚ እንዲመሰረት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አመራር በመስጠት ለከፈሉት መስዕዋትነት በታላቅ ክብር እንዲታወሱ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ በድህነት እና በጦርነት የምትታወቀውን አገራችን ያስጠሩ ጀግኖች ስፖርተኞች ካስመዘገቡት ውጤት ባሻገር መላው ህዝብ የተሻለ ስኬት እና ለውጥ የፈለገበትን ሁኔታ ለማስተካከል የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እንደተመሰረተ ገልፀው የስፖርቱ እንቅስቃሴ ጠባብ መሰረት ስለነበረውና፤ በሳይንሳዊ እና ዘመናዊ ስልጠና ያልተደገፈ ሆኖ የቆየበትን አሰራር የሚለውጥ መሰረተ ልማትይ ይሆናል ብለዋል፡፡

የስፖርት ልማት ስንል የሰው ሃብት ልማት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገራችን ስፖርት እድገት ሊለካ የሚገባው ከአትሌቲክሱ በተጨማሪ በሌሎች የስፖርት ውድድሮች ስፖርተኞችን ማፍራት በዓለም አቀፍ ውድድሮች በማሳተፍ እና ውጤታማ በማድረግ ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የስፖርት እድገት የአጠቃላይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ አካል መሆኑን በመገንዘብ መገንባቱን በመግለፅም የዜጎችን ጤናማ ህይወት እና የተሟላ የአካል ብቃት በማብቃት ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ሊኖረው የሚችል ልማታዊ ሃይል ለመፍጠር የሚያስችለን ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የገነባው ሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ጋር ከ6 አመት በፊት በተፈራራመው ውል መሰረት ሲሆን ለግንባታው ከመነሻው የተያዘው በጀት እስከ 182 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ አካዳሚው ሙሉ ለሙሉ ተገንብቶ ሲያልቅ ከፕሮጀክቱ ግዙፍነት አንፃር የግንባታው ወጭው አሻቅቦ ለሱር ኮንስትራክሽን 208 ሚሊዬን 480ሺ 178 ብር ከመንግስት ቢከፈልም አጠቃላይ ፕሮጀክቱን ለመፈፀም በኩባንያው የወጣው ወጭ 316 ሚሊዬን 354ሺ 649 ብር ነው ተብሏል፡፡

በምረቃው በዓል ላይ የተገኙት የሱር ኮንስትራክሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ የማነ አገራችን በዓለም ስፖርት አደባባይ በዘርፈ ብዙ የስፖርት አይነቶች ስሟን የሚያስጠሩ ስፖርተኞች እንድታፈራ ኩባንያችን ፍላጎት ስላለው ለፕሮጀክቱ መፈፀም 107 ሚሊዬን 874ሺ 471 ብር በተጨማሪ ከካዝናው በማውጣት የአካዳሚውን መጨረስ እውን እንዳደረገ ገልፀዋል፡፡ ሱር ኮንስትራክሽን ከህዝባዊ የልማት ድርጅቶች አንዱ እንደሆነና መንግስት እና ህዝብ ያቀዷቸውነ የልማት እቅዶች ከዳር እንዲደርሱ በመፈለግ የሚሰራ ነው ብለው የኢትዮጵያ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ይህን ያስመሰከርንበት ፕሮጀክት ነው ያሉት ተወካዩ ኩባንያቸው የስፖርት አካዳሚው ስራውን ከጀመረ በኋላ የአገሪቱን ስም የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚከተለው አቅጣጫ ሁሉ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡ የድሮው ጨፌ ወይም ቦሌ ሜዳ ከ3 አስርት ዓመታት በፊት በቦሌ አካባቢ የሚገኘውና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተብሎ የተገነባበት ስፍራ ጨፌ ሜዳ ይባል ነበር፡፡

ይህ ሜዳን አቋርጦ የሚሄድ ቀርሳ የሚባልም ወንዝ አለ፡፡ አካባቢውን በወንዙ ሰይመው የሚጠሩት ቢኖሩም በተለምዶ ቦሌ ሜዳ በመባል ይታወቅ ነበር፡፡ ይህን የቦሌ ሜዳ ያደግኩበት ሰፈር አካባቢ ስለነበር በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ የ24 ቀበሌ እና ተጎራባች ሰፈሮች ወጣቶች ፤ በተለይ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ቡድኖች፤ የተለያዩ የታዳጊ እግር ኳስ ፕሮጀክቶች እና ከተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች በእረፍት ቀናት ኳስ ለመጫወት የሚሰባሰቡ የጤና ቡድኖች የተለያዩ ውድድሮችን በማድረግ እና ልምምዶችን በመስራት ያዘወትሩበት ነበር፡፡ እነ ሃይሌ ገብረስላሴ፤ ጠይባ ኤርኬሶ እና ሌሎች ታዋቂ አትሌቶችና ተስፋ ያደረጉ ተተኪ ሯጮችም በዚሁ ሜዳ ጠዋት እና ማታ መደበኛ ልምምድ ይሰሩበት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በ15ኛው የመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ ዋንጫን እዚሁ አዲስ አበባ ላይ እንዳሸነፈች በወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት መንግስቱ ኃይለማርያም 100ሺ ሰው የሚይዝ ስታድዬም መንግስት እንደሚገነባ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ከግዜ በኋላ መንግስቱ ስታድዬሙ አይሰራም ወይ ተብለው ሲጠየቁ፤ ስሜት አታውቁም እንዴ እንዳሉ በቀልድ ተነገረ፡፡

ኢህአዴግ ከገባ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስለኢትዮጵያ ስፖርት ሲጠየቁ 100ሺ ሰው የሚይዝ ስታድዬም እንደሚገነባ በቀድሞው መንግስት ቃል መገባቱ ተጠቅሶ ይህ እቅድ ተግባራዊ አይሆንም ተብለው ነበር፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር 100ሺ ሰው የሚይዝ ስታድዬም ከምንገነባ ለገበሬው ማዳበርያ ብንገዛበት አይሻልም ብለው መለሱ፡፡ በዚህ ሁኔታ ስታድዬም የመሰራቱ ነገር ተደበስብሶ ምንም ሳይደረግ አመታት አለፉ፡፡ ከ5 ዓመት በፊት 29ኛው ኦሎምፒያድ በቻይናዋ ከተማ ቤጂንግ ተከናውኖ ድል አድራጊ አትሌቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ግን መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ለኦሎምፒክ ቡድኑ በብሄራዊ ቤተመንግስት አቀባበል ያደረጉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አሰልጣኝ ወልደመስቀል ኮስትሬ፤ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ሌሎች አትሌቶችና የፌደሬሽን ሃላፊዎችን ለምንድነው በአገራችን አትሌቲክስ የተተኪ ችግር የማይቀረፈው ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ ባሻገር በሌሎች ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ውድደሮች ለምን አትሳተፍም ብለው ጠየቁ፡፡ የአትሌቲክሱ ሰዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋራ በሰጡት ምላሽ ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት አካዳሚ መስራት ያስፈልጋል አሉ፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ምላሻቸውን በፀጋ ተቀብለው መንግስት በራሱ ወጭ ግዙፍ የስፖርት አካዳሚ እንደሚገነባ ቃል በመግባት ለሚመለከታቸው አካላት ጥናት ተደርጎ በአጭር ጊዜ ግንባታው እንዲጀመር ውሳኔያቸውን አሳወቁ፡፡ ይሄው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሃሳብ ተግባራዊ ሆኖ 100ሺ ሰው የሚይዝ ስታድዬም ይገነባበታል ተብሎ የነበረው የጨፌ ሜዳ በኢትዮጵያ ታሪክ በአይነቱ የመጀመርያው ግዙፉ እና ሁለገቡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሊገነባበት ቻለ፡፡ ፈርቀዳጁ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ዘመኑ የሚጠይቀውን የስፖርት ማሰልጠኛ መሰረተ ልማት ያሟላ እና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ሲሆን በውስጡ ካካተታቸው የስፖርት መሰረተልማቶች አንፃር ሲታይ መለስተኛ የኦሎምፒክ መንደር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር በነፃ በተሰጠው 25.4 ካሬ ሜትር ላይ የሰፈረው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የፊትነስ እና የሚዲያ ማእከሎች፤ እስከ 2ሺ ተመልካች የሚያስተናግድና የተለያዩ የቤት ውስጥ ውድድሮች የሚካሄድበት እና ስፖርተኞች የሚሰለጥኑበት ጅምናዚዬም፤ 500 ተሳታፊዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው የኮንፍረንስ አዳራሽ፤ ግዙፍ ቤተመፅሃፍት እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ህንፃ፤ 8 የመማርያ ክፍሎች እና ሌክቸር የመስጫ አዳራሽ የያዘ ህንፃ፤ ስድስት የመስክ ቤተ ሙከራዎች ፤ አራት የኮምፒውተር ክፍሎች፤ ሁለት ባለ አንድ ፎቅ የተማሪዎች ህንፃዎች ከተሟላ የጤና አገልግሎት፤ የመዝናኛ እና የመመገቢያ ክፍሎች ጋር፤ ስድስት የተለያዩ ደረጃ ያላቸው የአካዳሚው ሰራተኞች መኖርያዎች፤ የተለያዩ የስፖርት ቁሳቁሶች እና ትጥቆች ለገበያ የሚቀርቡበት ግዙፍ የገበያ ማዕከል፤ አንድ እስከ 7ሺ ተመልካች የሚይዝ የእግር ኳስ እና የአትሌቲክስ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችል መለስተኛ ስታድዬም ከተጨማሪ የመለማመጃ ሜዳ ጋር፤ አንድ ከ100-150 ተመልካቾች መያዝ የሚችልና የኦሎምፒክ ደረጃን የሚያሟላ የመዋኛ ገንዳ፤ ሁለት የሜዳ ቴኒስ እንዲሁም የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ እና የቅርጫት ኳስ ሜዳዎችን የያዘ ነው፡፡

የወጣቶች ስፖርት አካዳሚው ለአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በአካልና በአዕምሮ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ምርጥ ወጣት ስፖርተኞች ለማፍራት የተመሰረተ ሲሆን ለኢትዮጵያ የስፖርት ዕድገትና ጥራት አስተዋጽኦ የሚኖራቸውን የጥናትና ምርምር ሥራዎችን የማከናወን አቅም ይኖረዋል፡፡ አካዳሚው በ2006 የውድድር ዘመን ሥራ ሲጀምር ከመላው አገሪቱ ዕድሜያቸው ከ13 ዓመት በላይ የሆኑ ወጣቶችን በመመልመልና ስፖርታዊ ሥልጠናዎችን ለተከተታይ አራት ዓመት በመስጠት የሚሰራ ሲሆን በአጭርና በረጅም ጊዜ በሚሰጣቸው ሥልጠናዎች በአገሪቱ ስፖርት ዕድገት ላይ ጉልህ ለውጥ ለመፍጠር ታስቦበታል፡፡ በምረቃው እለት የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች ሥልጠና በመስጠት በአፍሪካ ደረጃ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ተጠቃሽ መሆኑን የሚያረጋግጡ መረጃዎች ነበሩ፡፡

ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ ለአሥር የስፖርት ዓይነቶች 13፤ ኬንያ ደግሞ ለስድስት የስፖርት ዓይነቶች ስምንት እንዲሁም ግብፅ ለስድስት የስፖርት ዓይነቶች 10 አካዳሚዎች እንዳሏቸው ሲታወቅ እሰከ 80 ዓመታት እድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ ከረጅም ጊዜ በኋላ ለዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች የሥልጠናና ምርምር አገልግሎት አንድ አካዳሚ መገንባቱ ይሆናል፡፡ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ የሃሳብ አመንጭነት እና በመንግሥት ውሳኔ ሰጪነት የተገነባው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ለሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ውድድሮች በአካልና በአእምሮ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ምርጥ ወጣት ስፖርተኞች ለማፍራት፣ ለስፖርት ዕድገትና ጥራት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለማካሄድ የሚያገለግል ነው፡፡ አካዳሚው በተጨማሪ ባነገባቸው ዝርዝር ዓላማዎች ወጣቶች በተለያዩ ስፖርት ዓይነቶች ሳይንሳዊ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና ክልሎችን ማገዝ፤ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን ማብዛት፤ የሥራ ዕድል እና የገቢ ምንጭ መፍጠር እንዲሁም ስፖርታዊ ምርምሮችን ማከናወንም ይሰራል፡፡ ሌሎች ተስፋ ሰጭ ጅማሮዎች በአትሌቲክስ እና በእግር ኳስ ስታድዬሞች በኢትዮጵያ ስፖርት ዙርያ ያሉ የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴዎች ከሞላ ጎደል በመንግስት የትራንስፈሮርሜሽን እቅድ መሰረት እየተካሄዱ ያሉት ናቸው፡፡

ከታዋቂ አትሌቶች በግሉ የስፖርት እና የመዝናኛ ማእከል በመገንባት ስራ የጀመረው ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ የቀነኒሳ የስፖርት እና መዝናኛ ማእከል ከአዲስ አበባ 10 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው ሱልልታ ውስጥ የተገነባ ሲሆን ማእከሉ በአትሌቱ የማኔጅመንት ኩባንያ ግሎባል ስፖርት ኮመኒኒውኬሽን አማካኝነት በተቋራጩ ስፖርትፒች ኢንጅነሪንግ ተቋራጭነት የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበርን እውቅና በማግኘት የተሰራ ነው፡፡ ይህ ማእከል ከፍተኛ ጥራት ያለው ሴንተቲክ የመሮጫ ትራክ፤ መለስተኛ የእግር ኳስ ቨሜዳ፤ ባለ 9 ጉድጓድ የጎልፍ መጫወቻ የቅርጫት እና የመረብ ኳስ ሜዳዎች ያሉት የሬስቶራንት እና ለአትሌቶች የማረፍያ አገልግሎት ምሰጥት የሚችል ነው፡፡ በአርሲ የሚገኘው የአሰላ አትሌቲክስ ማዕከል መሰል የስፖርት መሰረተ ልማት የሚኖረውን ውጤታማነት በተግባር በማሳየት ምሳሌ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ስር የሚተዳደረው ማእከሉ በ2002 ዓ.ም ተመስርቶ በዋናነት በሶስት ስፖርት አይነቶች በሩጫ፤ በዝላይ እና ውወራ ስፖርተኞችን የሚያሰለጥን ነው፡፡ ማእከሉ ስራውን ከጀመረ ወዲህ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ375 በላይ ወጣት ስፖርተኞችን አሰልጥኖ ያወጣ ሲሆን ከእነዚህ የማእከሉ ተመራቂዎች 175 ያህሉ ለተለያዩ ክለቦች ሲቀጠሩ 42 የብሄራዊ ቡድን ስፖርተኞች ለነሆን በቅተዋል፡፡ የአሰላ አትሌቲክስ ማእከል በሁለተኛ ዙር ስልጠና 180 ሰልጣኞችን በአትሌቲክስ እና እግር ኳስ ስፖርቶች በማሰልጣን ላይ ነው፡፡ በተመሳሳይ ከ2002 ዓ.ም ወዲህ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌሬሽን በአራት ክልሎች አራት የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማእከሎችን በማቋቋም እየሰራ ነው።

አራቱ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማእከሎች በትግራይ ክልል ማይጨው፤ በአማራ ክልል ባህር ዳር፤ በኦሮሚያ ክልል በቆጂ እንዲሁም በደቡብ ክልል ሃገረሰላም ከተማ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መሰረት በመንግስት ከሚከናወኑ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በሚጠይቁት ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም ግንባታቸው ፈታኝ የሆኑት ስታድዬሞች ናቸው፡፡ ስታድዬሞቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በመጠበቅ እና አገሪቱ ትልልቅ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም እንዲኖራት ታስበው እየተገነቡ ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ሙሉለሙሉ ግንባታቸው ተጠናቅቀው አገልግሎት እንድሚሰጡ ይገመታል፡፡ ከእነዚህ ስታድዬሞች ሁለቱ ግንባታቸው 75 በመቶ ተገባድዶ የሚገኙ እና በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ስራ እንደሚጀምሩ የሚጠበቁ ሲሆኑ ሌሎቹ ሁለት ስታድዬሞች ከሁለት ዓመት ግንበታቸው እንደሚገባደድ የሚጠበቁ ናቸው።

በ2006 ዓ.ም ስራ ይጀምራሉ የሚባሉት ሁለቱ ስታድዬሞች አንደኛው 50ሺ ተመልካች የሚይዘው የባህር ዳር ስታድዬም እና 30ሺ ተመልካች የማስተናገድ አቅም ያለው የነቀምት ስታድዬም ናቸው፡፡ 40ሺ ተመልካች ያስተናግዳል ተብሎ የሚገመተውና 30 በመቶ ግንባታው የተከናወነው የመቀሌ ስታድዬም እና 40ሺ ተመልካች የሚይዘው የሃዋሳ ስታድዬም በ2007 ዓ.ም ስራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከስታድዬም ግንባታዎች መካከል ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የኦሎምፒክ ደረጃን አሟልቶ ጀምሮ ይገነባል የተባለው ብሄራዊ ስታድዬም ነው፡፡ 60ሺ ተመልካች እንደሚያስተናግድ፤ የአትሌቲክስ ትራክ እና ውሃ ዋና ስፍራ በዙርያው የሚኖረው ይህ ስታድዬም በሚቀጥለው ዓመት ግንባታው እንዲጀመር ታቅዷል፡፡

Read 5905 times