Saturday, 06 July 2013 11:08

የዓመፅ ፍሬ!

Written by  ሚካኤል ዲኖ
Rate this item
(0 votes)

ወግ

የመጀመያው አብዮተኛ ሰይጣን ነበር ይባላል፡፡ በዝንተ አለማዊው የእግዚአብሔር አገዛዝ ላይ በተቃውሞ የተነሳ የመላእክት አለቃ፡፡ ይህን አባባል ተቀብለን ለተቃውሞው፣ ለአመፃው ተግባር በመንስኤነት የምናገኘው ሰበብ ቢኖር መሰልቸት ነው፡፡ መሰልቸት ከእጦትም ከቅንጦትም ይመነጫል፡፡ ሊቀ - መልዓኩ በዚያ ፅንፍ አልባ ህዋና በነዚያ ሁሉ እልፍ አእላፍ መላእክት ላይ ሰልጥኖ ሲኖር …ሲኖር አንዳች የሚጐድል፣ አንዳች የሚዛነፍ ነገር የለምና ሰለቸው፡፡ በኛ እምነትም አብዮት ከመለኮት የተገኘ የውርስ ዳፋ ነው፡፡

እንዴት? ቢሉ እልቅናውን የተነጠቀውና ወደ ጥልቁ የተወረወረው ሰይጣን፣ እሱ በተጠመደበት የመሰልቸት ወጥመድ በተራው ሰውን ስላጠመደው፡፡ እንደ ሰይጣን ሁሉ ሰውም (አዳም) በገነት በሙሉ ስልጣን ተሰይሞ ጫፍ እስከ ጫፍ እየተዘዋወረ ያሻውን ይፈጽም ዘንድ ሁሉ በፊቱ ነበር፡፡ ይሄ ፍቃድ በራሱ ለመሰልቸትና ለመተላለፍ በቂ ሆኖ እያለ ሌላ ለሰይጣን ወጥመድ የተመቸ ገደብ ከፈጣሪ ለፍጡሩ ተላለፈ፡፡ “ከህይወት ዛፍ የበላህ እንደሆነ ሞትን ትሞታለህ” የሚል፡፡ ሰይጣን አዳምና ሄዋን በገነት እየተዘዋወሩ እስኪዘሉ፣ እስኪቦርቁ፣ እስኪሰይሙ ታገሳቸው፡፡

የግዜው ርዝመት በራሱ ወደሱ ዓላማ እንዲያመጣቸው ገብቶታል ወደ መሰልቸት፡፡ ግዜው ሲደርስ በጥናቱ መሰረት ተራማጅ ነች ብሎ ወዳመነባት ሄዋን በመሄድ…”አማን ነው ሄዋን”፤ አላት ከወደ ኋላዋ ድንገት ደርሶ “ቆሌህ ይገፈፍ አቦ! ኮቴህም አይሰማም እንዴ!?” አለች እየተበሳጨች አሳቀችው….”እንዴ ኮቴ እኮ የሰው ልጅ ግዴታ ነው፡፡ የኔ መምጣት በምንም ነገር ውስጥ ታምቆ ለመገለጽ አይገደድም” አለ በአካሄዱ እንደመደነስ እየቃጣው፡፡ ለተናገረው ብዙም ትኩረት ሳትሰጥ “እሺ ምን ፈልገህ ነው?” ስትል ጠየቀች፡፡ በተራው ተበሳጭቶ “ወይኔ ሄዋን መፈለግ መመኘት ለናንተ ለስንኩሎቹ የተተወ መባዘን ነው፡፡ እኔ ከዚያ በላይ ያለ ፍቃድ ያለ እግድ የምኖር ነኝ” አላት፡፡ አግድም እያየችው “ማነው ይሄንን ላንተ ብቻ የሰጠው? እኛስ ብንሆን ምን ጐደለብን? እንዳሻን አይደል እንዴ የምንኖረው?” በማስቀናት መልክ ትከሻዋን ነቀነቀች፡፡ “ስቄ ልሞት አለች…እ ትላለች ማለቴ ወደፊት” አለ እየሳቀ፡፡

“እንዳሻን አልሺኝ --- ለዚህ ነዋ ለአዳም ከህይወት ዛፍ ፍሬ የበላህ እንደሆነ ትሞታለህ ብሎ እግዚአብሔር ያስጠነቀቀው!?” ሲል አፋጠጣት፡፡ ሳታስበው ተይዛለችና የምትመልሰው አልነበራትም፡፡ አዳም ከአንበሳ ሲላፋ ትታው የመጣችው የነገሮች ድግግሞሽ አሰልችቷት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሰይጣን ከዚህ ሁሉ የበረከት ጋጋታ አንድ ዛፍ መከልከሉን እየነገራት ነው፡፡ “ታዲያ ምን ችግር አለው? በገነት ያለው በረከት በሙሉ በእጃችን ነው-- የአንድ ዛፍ ፍሬ ቢቀርብን ምን እንሆናለን?” ስትል ጠየቀች፡፡

ከመከራከር፣ ከመከላከል ድምፀት ጀርባ ያለውን መሸርሸር፣ ከኋላ ያለውን መዳከም ሰይጣን ነጥሎ አድምጦታል፡፡ “ተይ እንጂ ሄዋን፣ ቢያንስ እኮ ከነዚህ ሁሉ ቁጥር አልባ ዛፎች ተመርጦ የከለከለበት ምክንያት አንድ ልዩ ነገር ቢኖረው ነው፡፡ ተራ ዛፍ አይደለም፡፡ ታዲያ እዚህ ፍሬ ሆድ ውስጥ ያለው ምስጢር እንዴት አያጓጓም ብለሽ ታስቢያለሽ?” ተፈታተናት፡፡ ከሰይጣን ጋር በውይይት በገፋች ቁጥር እየሰላች ከርሱ ጋርም ባልታሰበና ግልጽ ባልሆነ አቅጣጫ እየተስማማች ሄደች፡፡ “በርግጥ ሊያጓጓ ይችላል፤ ግን በውስጡ ያለውን ለማወቅ ከፍሬው መብላት የግድ ነው፡፡ ፍሬውን መብላት ደግሞ ከአምላክ ትዕዛዝ ውጭ መሆን ነው” በስውር አመነታች፡፡

“እሱ እኮ ነው ቁም ነገሩ” አለ ሰይጣን፤ተክለፍልፋ ወደ ወጥመዱ ስትገባለት “የፍሬው ሃይል ገደብ አልባ ያደርግሻል እግዚብሔር በስስት ከአንቺ የጋረደውን አለም ይገልጥልሻል፣ ከአዳዲስ ስሜቶች ጋር ያስተዋውቅሻል፡፡ ፍሬውን ከበላሽ በኋላ አዲስ ምዕራፍ ይከፈታል፣ አሁን የምታውቂውን ያህል የሚሰፋ አለም ላይ ትሰለጥኛለሽ፣ ሌላው ቀርቶ አሁን ባለሽ መረዳት ልትገነዘቢ የማትችይውን በአዳም ላይ ያለሽን የበላይነት ትቀዳጃለሽ” እራሱም በትረካው ተመስጦ ነበር፡፡ “ግን አንተ ይሄን በምን አወቅህ?” በነገሩ በመመሰጧ ስላወቀበት መንገድ እንጂ ስላወቀው ነገር እውነትነት ጥርጣሬው ከውስጧ ጠፍቶ ነበር፡፡ ሳቀ፡፡ ረጅም ሳቅ ሳቀ፡፡ በትንፋሹ ሃይል አዕዋፍ ከዛፍ ሸሽተው እስኪበሩ፣ የየዛፉ ቅጠሎች እስኪረግፉ፣ በግዮን ወንዝ ማዕበል ተነስቶ መስኩን እስኪያጥለቀልቀው፣ ሄዋን ራሷ ቋጥኝ ስር ተደብቃ እስክትንዘፈዘፍ…ሳቀ፡፡ ወዲያው ግን ነቃ ብሎ በኩራት “እንዴ እኔማ ከፈጣሪ መኖር ትንሽ ዘግይቼ ነበርኩ፡፡

ከፈጣሪ እውቀት ትንሽ ብቻ ሲጐድልብኝም ሁሉን አውቃለሁ፡፡ እናም ያንቺና የአዳም ውስንነት ያሳዝነኛል፡፡ ከጽንፍ አልባ አለም ተገድባችሁ ገነት በምትባል ትንሽ መስክ መጣላችሁ ግፍ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ለዚህም ነው ገመድሽን ፍቺ እንዳሻሽ፤ ወዳሻሽ ብረሪ የምልሽ” ይህን ሲናገር መንገድ ጀምሮ ነበር፡፡ አይኗ እሱን ከመከተል ዞር ከማለቱ ከዛፎቹ እንደ አንዱ ሆኖ ይከታተላት ጀመር፡፡ ሃሳብ ሳይሆን መንፈስ የተጋባባት ይመስል እመር ብላ ከተቀመጠችበት ተነስታ አዳምን ትታው ወደመጣችበት አቅጣጫ በትካዜ መሬት መሬቱን እያየች ሄደች፡፡ አዳም እንደተለመደው የተለመደው ተፈጥሮ ብርቅ ሆኖበት በአንክሮ ሲመለከት አገኘችው፡፡ “አዳምዬ?” አለችው እጆቿን ትከሻው ላይ ጣል እያደረገች፡፡

እንዲህ ስትጠራው ልቡ ለምን ድክም እንደሚልበት እየተገረመ “ወዬ ሄዋን” አለ፡፡ የሚሆነው ሁሉ እንደሚሆን እርግጠኛ የሆነው ሰይጣን፡፡ በቅርብ ርቀት ሆኖ በተስፋ ሲቃ የተሞላ ፈገግታው ሁለቱ ፍጡራን ላይ አብርቶ ነበር፡፡ ከሁሉም ጀርባ ሁሉንም በትዝብት የሚመለከተው ፈጣሪ የመከፋቱ ስሜት ዙሪያ ገባውን አደናግዞታል፡፡ አዳምና ሄዋን ብቻ በማይዘልቀው ሰይጣናዊ ብርሃን ስር ሆነው፣ ወደ አዲስ የጨለማ ምዕራፍ እየተሸጋገሩ ነው፡፡

Read 1852 times