Saturday, 06 July 2013 11:42

የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ በኢትዮጵያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(17 votes)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ መብቃቱ ብዙ ነገር እየቀየረ ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ምድቡን በመምራት ከቆየ ወዲህም ለውጦች ይታያሉ፡፡ በእነዚህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የእድገት ምዕራፎች ሳቢያ በተለያዩ አገሮች በሚገኙ ክለቦች የኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ተፈላጊነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ እየተፈለጉ ያሉት በደቡብ አፍሪካ፤ በሱዳን፤ በሊቢያ እና በእስራኤል ክለቦች ነው፡፡ ፊፋ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ላይ ኢትዮጵያ ባለፈው ወር ከነበረችበት የ106ኛ ደረጃ 11 እርከኖችን ወደላይ በመምጠቅ 95ኛ ላይ ደርሳለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ተሳክቶለት ምድቡን ማሸነፍ በመቻል 10 ብሄራዊ ቡድኖች ለሚተናነቁበት የደርሶ መልስ ጥሎ ማለፍ ከሚገቡት ከበቃ እና አፍሪካን የሚወክሉ 5 ቡድኖች አንዱ በመሆን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ካለፈ ይሄው የእግር ኳስ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል በማሳየት ከ70 በታች ለመመዝገብ ይበቃል፡፡

በዚህ ደረጃም ፕሮፌሽናል ተጨዋች ለመቅጠር የአገርን እግር ኳስ ደረጃ ከሰባ በታች እንዲሆን በሚፈልጉ እና ፕሮፌሽናል ሊግ ባላቸው የአውሮፓ አገራት ኢትዮጵያውያኑ የፕሮፌሽናልነት እድል እንዲያገኙ መንስኤ መሆኑ አይቀርም፡፡ በትራንስፈርማርኬት ድረገፅ አጠቃላይ የዋጋ ተመኑ 650ሺ ፓውንድ እንደሚያወጣ የተተመነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተጨዋች ስብስብ ከዓመት በኋላ በሚሊዬን ፓውንድ መገመቱም ይጠበቃል፡፡ በተያያዘም በኢትዮጵያ ለመጫወት ከአፍሪካ 6 አገራት የተውጣጡ ከ26 በላይ ተጨዋቾች በ7 ክለቦች በመቀጠር ለቀጣይ የውድድር ዘመን ህጋዊ እውቅና ማግኘታቸው ታውቋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ለዝግጅት ክፍላችን በላከው ዝርዝር መሰረት በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ለመጫወት እውቅና ያገኙት 26 የሌላ አገር ተጨዋቾች 8 ከካሜሮን፤ 7 ከናይጄርያ፤ 6 ከጋና፤ 3 ከኡጋንዳ እንዲሁም ከኬንያ እና ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ናቸው፡፡ ከ26ቱ የሌላ አገር ተጨዋቾች ጊዮርጊስ 7፤ ኤልፓ እና ሀረር ቢራ እያንዳንዳቸው 5፤ ደደቢት 4፤ ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከነማ እያንዳንዳቸው 2 እንዲሁም ኒያላ ለ1 ተጨዋች ቅጥር በፌደሬሽኑ የእውቅና ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ ፅሁፍ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ያሉ ሁኔታዎችን ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡
የዝውውር ገበያው ድሮና ዘንድሮ
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ እየተሟሟቀ የመጣው በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ የንግድ እንቅስቃሴ ዋና መሰረት የዝውውር ገበያ ነው፡፡ የፕሪሚዬር ሊግ ፉክክር በሶስት እና አራት ክለቦች መካከል እየተጠናከረ ከመጣ በኋላ ገበያው ተሟሟሙቋል ማለት ይቻላል፡፡ የቀድሞው ታዋቂ ተጨዋች መንግስቱ ወርቁ ድሮ ኳስ ተጨዋቾች ስፖርቱን ለፍቅር እንጅ ለገንዘብ አይጫወቱም ይሉ ነበር፡፡ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ በተጨዋችነት ዘመናቸው መጀመርያ ለጊዮርጊስ ሲጫወቱ ከልምምድ በኋላ ስሙኒ ይከፈላቸው እንደነበር ያስታውሷል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የዝውውር ገበያ ብዙም የረባ ነገር የሚገኝበት አልነበረም፡፡ ካለፈው 4 ዓመት ወዲህ ግን ነገሮች ተቀይረዋል፡፡ በ50ሺ ብር የፊርማ ክፍያ ተጀምሮ፤ ወደ 100ሺ ብር ከዚያም ወደ 200ሺ ብር፤ 300ሺብር እየሆነ ቆይቶ ዛሬ የአንድ ተጨዋች የዝውውር ሂሳብ በአማካይ ወደ 500 ሺ ብር ደርሷል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳያድግ ተፅእኖ የፈጠረው በከፍተኛ የአገር ውስጥ ውድድሮች ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች ከሞላ ጎደል በመንግስት የበጀት ድጎማ በመንቀሳቀሳቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡

ለዚህም ባለፈው ዓመት የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን የተሰራውን ጥናት ሲጠቅስ በፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ ከሆኑ ክለቦች 84 በመቶ የሚሆኑት በባለቤትነት የሚተዳደሩትና የገንዘብ ድጎማ ያላቸው ከመንግስት ተቋማት መሆኑን፤ በግል ባለቤትነት የተያዙት 8 በመቶ፤ ህዝባዊ አስተዳደር ያላቸው 13 በመቶ እንዲሁም በግል እና በህዝብ የሚደገፉ ክለቦች 4 በመቶ እንደሚሆኑ በዝርዝር ማስቀመጡን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በመንግስት ተቋማት የሚደጎሙ ክለቦች በዓመት እስከ 50 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚያንቀሳቅሱ ሲታወቅ እንደ ጊዮርጊስ እና ደደደቢት አይነት ክለቦች በየዓመቱ ከ16 እስከ 25 ሚሊዮን ብር እንደሚያንቀሳቅሱ ይገመታል፡፡ ይሄ የበጀት አቅም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን የሌሎች አገራት ተጨዋቾች በተፈለገው አቅም ለማሰባሰብ፤ የአገር ውስጥ ተጨዋቾችን የዝውውር ሂሳብ እና ደሞዝ በከፍተኛ ፍጥነት ለማሳደግ እና የሊግ የውድድር ደረጃን በፕሮፌሽናል ደረጃ ለማጠናከር በቂ አይደለም፡፡ ስፖርቱን በከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ለማካሄድ የክለቦች ባለቤትነት ከመንግስት ተቋማት ይልቅ በባለሃብቶች እና በደጋፊ ማህበራት ማስተዳደር ሁነኛ አመራጭ እንደሆነም በአፍሪካ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች በሚደረጉ ፕሮፌሽናል ሊጎች ተመክሮ በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሁለቱ የዝውውር መስኮቶች እና ሂሳቦች
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋቾች የዝውውር ገበያ በአንድ የውድድር ዘመን በሁለት ወቅቶች ይካሄዳል፡፡ የመጀመርያው በውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ ወይንም በፈረንጆች አዲስ አመት መግቢያ አካባቢ ለ1 ወር ክፍት ሆኖ የሚቆየው የዝውውር መስኮት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንድ የውድድር ዘመን ካበቃ በኋላ በሰኔ ለ1 ወር የሚዘልቀው የዝውውር መስኮት ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት የዝውውር ወቅቶች ላይ ማንኛውም ክለብ በዝውውር ስምምነቱ የሚያስፈርመው ተጨዋች በፌደሬሽኑ የእውቅና ማረጋገጫ የተሰጠው ብቻ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ክለቦች በዝውርር ለሚያስፈርሟቸው ተጨዋቾች በአመዛኙ የሁለት ዓመት የኮንትራት ውል በማስፈረም ይታወቃሉ፡፡
በተጨዋቾች የዝውውር ገበያው ለአንድ ተጨዋች የሚከፈለው የፊርማ ገንዘብ ወይም የዝውውር ሂሳብ በአማካይ እስከ 500ሺ ብር ነው፡፡ እስከ 17,675 ፓውንድ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአንዳንድ ተጨዋቾች እስከ 1 ሚሊዮን ብር የዝውውር ሂሳብ እንደሚከፍል ቢነገርም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛው የፊርማ ክፍያ ሆኖ በሪከርድነት የሚጠቀሰው ደደቢት ከ2 ዓመት በፊት አዲስ ህንፃ ኮንትራቱን እንዲያራዝም የከፈለው 700ሺ ብር ነው፡፡ በተገባደደው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የውድድር ዘመን በዝውውር ገበያው ለአንዳንድ ተጨዋቾች ተከፍለዋል የተባሉትን የፊርማ ክፍያዎች በመዘርዘርም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለተጨዋቾች ያለውን የዋጋ ተመን ማገናዘብም ይቻላል፡፡ አይናለም ሃይሉ ከመከላከያ ወደ ደደቢት በ600ሺ ብር፤ ሲሳይ ባንጫ ከሲዳማ ቡና ወደ ደደቢት በ550ሺ ብር እንዲሁም በረከት ይስሃቅ ከሃዋሳ ከነማ ወደ መብራት ሃይል በ450ሺ ብር የፊርማ ክፍያ ዝውውራቸውን ፈፅመዋል፡፡
ፈርቀዳጁ ሳላዲን
ትራንስፈርማርኬት የተባለ የዩናይትድ ኪንግደም የእግር ኳስ የዝውውር ገበያ አጥኚ እና ተንታኝ ድረገፅ ድረገፅ 28 ተጨዋቾች ለሚገኙበት የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዝውውር ገበያ የዋጋ ተመኑ 650ሺ ፓውንድ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ በዚህ ተመን በብሄራዊ ቡድኑ የዝውውር ገበያ ላይ ዋጋ አላቸው ተብለው የተጠቀሱት ሶስት ተጨዋቾች ብቻ ናቸው፡፡ የመጀመርያው የ21 ዓመቱ የፊት አጥቂ እና በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የብሄራዊ ቡድኑ አባል የሆነው ፉአድ ኢብራሂም ሲሆን አሁን የሚጫወትበት ክለብ ባይኖረውም የዋጋ ተመኑ 75ሺ ፓውንድ ተብሏል፡፡ ሁለተኛው ተጨዋች ደግሞ ቶቦ ኮስተኒ ለተባለ ክለብ በመጫወት ላይ የሚገኘው፤ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የብሄራዊ ቡድኑ አባል የነበረውና የግራ ክንፍ ተጨዋች የሆነው ዩሱፍ ሳላህ ሲሆን የዋጋ ተመኑ 275ሺ ፓውንድ ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ የኢትዮጵያዊ ብሄራዊ ቡድን ውድ ተጨዋች ተብሎ በትራንስፈርማርኬት የተጠቀሰው እና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች የፕሮፌሽናል ጉዞ በርካታ ፈርቀዳጅ ሁኔታዎችን በማለፍ የሚነሳው አጥቂው ሳላዲን ሰኢድ ነው፡፡

ከ2 ዓመት በፊት ይጫወትበት ከነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ወደግብፁ ዋዲ ደጋላ ሲዛወር 158.4 ሺ ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ የተከፈለበት ሳላዲን ሰኢድ በወቅቱ የወጣበት ሂሳብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ሪከርድ የነበረ ነው፡፡ ሳላዲን ሰኢድ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ሪከርድ የሆነውን የዝውውር ሂሳብ ማስገኘቱ ብቻ ሳይሆን ወደ ግብፅ ክለብ በመሄድም ፈርቀዳጁ ነበር፡፡ ከ2 የውድድር ዘመናት በኋላም በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ለኢትዮጵያዊ በተከፈለ ሂሳብ እና በተዛወረበት አገር ሁለት አዳዲስ ፈርቀዳጅ ታሪኮችን ሳላዲን ሰኢድ ሊሰራ በቅቷል፡፡ በትራንስፈርማርኬት ድረገፅ የኢትዮጵያ ውዱ ተጨዋች የተባለው የ24 ዓመቱ ግብ አዳኝ ሳላዲን ሰኢድ የዋጋ ተመኑ ከሁለት ዓመት በኋላ በእጥፍ እድገት አሳይቶ 300ሺ ፓውንድ የደረሰ ነው፡፡ ሳላዲን አሁን በሚጫወትበት የስዊድኑ ክለብ ላርሴ ኤስኬ ክለብ በወር እስከ 10ሺ ዶላር ደሞዝ የሚታሰብለት ሲሆን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ አውሮፓ በመጫወት ፈርቀዳጅ ሆኗል፡፡
ከየመን በኋላ ወደተለያዩ 5 አገራት የሰፋው ተፈላጊነት
ከአምስት እና ስድስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች ከአገር ውጭ የመጫወት እድል ያላቸው በየመን ሊግ ብቻ ነበር ፡፡ ከ7 ዓመታት በፊት ጀምሮ የብቃት ደረጃቸው ጫፍ የደረሰላቸውና የተጨዋችነት ዘመናቸው በማብቂያ ዋዜማ ላይ የሚገኙ ከ12 በላይ ኢትዮጰያዊ ተጨዋቾች በተለያዩ የየመን ሊግ ተወዳዳሪ ክለቦች በመጫወት አሳልፈዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሳላዲን ሰኢድ በከፈተው በር ኢትዮጵያውያኑ ተጨዋቾች ከየመን ባሻገር ወደ ሌላ አገራትም በሚገኙ ጠንካራ ሊጎች በሚወዳደሩ ክለቦች እየተፈለጉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዓለም አቀፍ አምባሳደር ሊባል የሚችለውና በሁለቱ ታዋቂ የደቡብ አፍሪካ ክለቦች ሱፕርስፖርት ዩናይትድ እና ኦርላንዶ ፓይሬትስ ለመጫወት የበቃው ፍቅሩ ተፈራ በነበረው ፈርቀዳጅነት መጠቀስ ያለበት ነው፡፡

ከፍቅሩ በኋላ የመጣው ሳላዲን ሰኢድ በግብፅ እና በአውሮፓ አገር በሚካሄድ የሊግ ውድድር በሚሳተፉ ክለቦች በመጫወት መስመሩን ገፋበት፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ መብቃቱ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በተለያዩ አገራት ባሉ ክለቦች ለመፈለጋቸው አበይት ምክንያት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ እየተፈለጉባቸው ከሚገኙ አገራት ደቡብ አፍሪካ፤ ሱዳን፤ እስራኤልና ሊቢያ ይጠቀሳሉ፡፡
ከሰሞኑ የሚሰሙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከ5 በላይ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ወደ የተለያዩ አገራት በመጓዝ የሚጫወቱበት እድልን ለመጠቀም በስምምነት፤ በድርድር እና በጥናት ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ከሆኑ ተጨዋቾች ለዘንድሮው የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ክለብ ይጫወት የነበረው አዲስ ሕንፃ ለሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ሸንዲ በ80 ሺ ዶላር የዝውውር ሂሳብ ተከፍሎት እና 2500 ዶላር ሳምንታዊ ደሞዝ እየታሰበለት ለመጫወወት መስማማቱ ቀዳሚው ነው፡፡

የደደቢት እግር ኳስ ክለብ እና የብሄራዊ ቡድኑ ግብ አዳኝ ጌታነህ ከበደ እንዲሁም የጊዮርጊስ ክለብ አማካይ ተጨዋች እና የብሄራዊ ቡድኑ የመሃል ክፍል ሞተር ሽመልስ በቀለ ወደ ደቡብ አፍሪካ እና ወደ ሊቢያ ክለቦች ለመዘዋወር አስፈላጊውን የህክምና ፈተና እና የኮንትራት ድርድር ማካሄዳቸው ሌላው አስደናቂ የዝውውር ሂደት ነው፡፡ ሽመልስ በቀለ ወደ ሊቢያ በመጓዝ ለአገሪቱ ትልቅ ክለብ አል ኢትሐድ ለሦስት ዓመት የሚጫወትበት ኮንትራት እንደፈረመ እየተገለፀ ሲሆን 200ሺ ዶላር የዝውውር ሂሳብ እንደሚከፈለው እና 8ሺ ዶላር የወር ደሞዝ ሊታሰብለት ነው ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በ22 ጎሎቹ ኮከብ ግብ አግቢነቱን የያዘውና በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ በ5 ግቦቹ ከፍተኛ ግብ አግቢ የሆነው የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት በዚያ አገር ሊግ ዘንድሮ 4ኛ ደረጃ ላይ ላለው ቢድቪስት ዊትስ ዩኒቨርስቲ ክለብ ለመጫወት ተስማምቶ በ3 ዓመት የኮንትራት ውል 550ሺ ዶላር የዝውውር ሂሳብ ተከፍሎታል፡፡ ጌታነህ ከበደ በሌላው የደቡብ አፍሪካ ክለብ ኦርላንዶ ፓይሬትስ ተፈልጎ እንደነበርም ተገልፆ ነበር፡፡ ሌሎች ሁለት የብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ተጨዋቾች የሆኑት የደደቢቱ ምንያህል ተሾመ እና የመብራት ኃይሉ አስራት መገርሳ ከእስራኤል ክለቦች በቀረበላቸው የዝውውር ፍላጎት በድርድር ሂደት ላይ ናቸው፡፡

Read 9683 times