Saturday, 13 July 2013 11:27

“ቀብድ የበላች ሀገር!” ማናት?

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

ከሣምንት በፊት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በጥቁምታ ያለፍኩት የግጥም መጽሐፍ “ቀብድ የበላች ሀገር” የሚለው የመንግስቱ ዘገዬ ነበር፡፡ መንግስቱ ዘገዬ በሞያው ጠበቃ ነው፡፡ በነፍሱ ዳንስ ደግሞ ገጣሚ ነው፡፡ ቃናው የወሎ ሆኖ ግጥሞቹ የተለያየ ቅርጽ ያላቸው ናቸው፡፡ አጫጭርና ረጅም ግጥሞችም አሉበት፡፡ ተራኪ ሌሪክና ሌሎችም የግጥም ዝርያዎች ተካትተውባታል፡፡ በተለይ የቋንቋው ለዛ ደስ ይላል፡፡ በዚያ ላይ የጠበቃነቱ ተፅዕኖ ሳይሆን አይቀርም “ሀገሬ - ሀገሬ” ያበዛል፡፡ የመጽሐፉ የመጀመሪያ ግጥም ያደረጋትም “ሀገሬ ፍየል ናት” የምትለዋን ነው፡፡
ሀገሬ ፍየል ናት፣ ያውም የታረደች፤ አምና ለፋሲካ፣
አላፊና አግዳሚው፣ ግጦ የጨረሳት፣ የተዝካር በረካ፣
ቆዳዋስ ወዴት ነው? ብዬ ሳፈላልግ፣ ስማስን በልቤ፣
ይደበድቧታል፣ ታምቡር አድርገዋት፤ የባለዛር ድቤ፡፡
ስለሀገር ከተፃፉት የሀገራችን ግጥሞች ሀገርን ከሞት በታች፣ ከእምባ እግር ሥር የጣላት ይህ ገጣሚ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ፍየል ናት - ብሎ፣ ቆዳዋ - እንደከበሮ ተወጥሮ እስኪደበደብ መጃጇልዋ ጥያቄ ያጭራል፡፡ ሞታ እንኳን እንዳታርፍ ያደረጉዋት እነማን ናቸው የሚል ቁጭትም ይፈጥራል፡፡ እነዚህ ግፈኞች እነ እገሌ ናቸው እንዳንል ደግሞ ሰዎቹ አንድ ቦታ የረጉ፣ በአንድ ሠፈር የፀኑ አይደሉም። ግጦ የጨረሳት አላፊ አግዳሚው ነው ይለናል - ገጣሚው፡፡ እዚህ ጋ ትንሽ መጠርጠር ከተፈቀደልኝ “ምናልባት በየጊዜው የሚለዋወጡትን መንግስታት ማለቱ ይሆን”? የሚል የማርያም መንገድ ትቻለሁ። ሁለተኛው ግጥሙ “የመንታ እናት አልጋ” የሚል ሲሆን ይሄኛውም ስለሀገር የሚተርክ ነው፡፡ ረዘም ስለሚል እናንተ ትቼዋለሁ - እንድታነቡት፡፡
“የብርሃን ትንቢት” የተሰኘው ሦስተኛ ግጥሙ ቀልቤን ስቦታል፡፡
በጥቁር በርኖስ ስር፣ ያለውን ከተማ፣
አላዋቂ ሳሚ፣ ይለዋል ጨለማ፣
ከሰነፍ ብርሃን ከጨገገ ጀንበር
ከድፍርስ ወጋገን፣ ከወየበ ጨረር፣
ብርሃን አለ እያሉ፣ በድኩም ምህላ፣
ቂም በገባው ጸሎት፣ በተረታ ገላ
ቀልብን ከማላመጥ፣
ነፍስን ከመበጥበጥ፣
በብርሃን ስስት፣ በናፍቆት ታድሶ
መጠበቅ ይሻላል መጠበቅ ጨርሶ፣
ጽልመት የዋጠውን ጥቁር በርኖስ ለብሶ፣
ብርሃን አለና፣ የጨለማን ማህፀን፣ ሽሉን ተንተርሶ፡፡
ግጥሙ፤ የብርሃን ትርጉም በከበበው ጨለማ ልክ አይደለም፤ ነው የሚለው፡፡ የብርሃን ትርጉሙ ያለው የልብ ሰማይ ላይ፣ የውስጥ አድማስ ላይ ነው፡፡ የተስፋ እሸት የጨበጠ ሰው የጨለማ ቋንጣ ዘልዘሎ አያመነዥግም ነው ነገሩ! የሰነፍ ጀንበር ቀኑን ብሩህ፣ ተስፋውን ጐረቤት አታደርግለትም፡፡ “ብርሃን አለ” እያሉ በደከመ ስሜት ቢያወሩት ፋይዳ የለውም፤ ይልቅስ የጨለማ በርኖስ ከብዶ ሳለ፣ በልብ ውስጥ በምትንተከተክ የብርሃን ተስፋ ጨለማውን እንደማሕፀን አድርጐ ብርሃን መውለድ ይቻላል ባይ ነው ገጣሚው፡፡ እኔም እስማማለሁ፡፡ ሁልጊዜ ችግር ብልሃትን ይፈጥራል፡፡ በመከራ ቀኖች ብርቱና ታላላቅ ሰዎች ይወለዳሉ፤ ትልልቅ ሃሳቦች ይፀነሳሉ፡፡ እንደ ጆን ሲ ማክስዌል አባባል፤ የዓለማችን ታላላቅ ፈጠራዎች ባለቤት የሚባሉት አብዛኞቹ ሰዎች በከባድ ችግርና መከራ ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡ ብርሃን ከጨለማ ይወለዳል የሚለው ይህንን ይጨምራል፡፡ ገጣሚ ምናበ ሰፊ ነውና ሰፋ አድርገን እናይለታለን፡፡
ገጣሚ መንግስቱ ዘገዬ ቀስ ብሎ ያንኳኳት የጐጆ በር፣ የፈተሻት ዘመነኛ ትዳር በጽኑዕ ታሳስባለች፡፡ የትዳር ዕድሜ ማጠር፣ የጐጆ ፈጥኖ መዘመም ጉዳይ ላይ አይኖችዋን ተክላለች፡፡

“የዘንድሮ ጫጉላ”
በስብስቴ ዘመን፣ በዳቦ ትራሱ፣
አባትና እናቴ፣ ጐጆ ሲቀልሱ፣
አንጀታቸው ማገር፣
ልባቸው ምሰሶ፣ ተደርጐ ነበረ፣
እኔ የእነሱ ልጅ፣ የቃል ባለአደራ፣
የፍቅራቸው ትውፊት፣ የህልማቸው ዳራ፣
ልሆን ነው መሰለኝ፣ ወግደረስ ሙሽራ፡፡
ታዲያ እኔና ሄዋን፣
ጐጆ ልንሰራ፣
አንጀታችን ሳስቶ፣ ለማገር አልበቃ፡፡
ልባችን ካስማ አይሆን ምሰሶ አያነቃ፣
የኔይቱን ሄዋን፣
ለምን ይሆን ሆዴ? ብዬ ብጠይቃት
የጐጆዬ ነገር ጨንቆኝ፣ ባስጨንቃት፣
ቁርጡን ነገረችኝ፣ አለችኝ “አንተ ሰው”
ባለው በተገኘው፣ በቶሎ እንቀልሰው!”
እንዳያስቸግረን፣ ነገ ስናፈርሰው!”
የዘመኑን ትዳር፣ ከወላጆቹ ዘመን ጋር የሚያነፃጽረው ተራኪ፣ በቀደመው ዘመን፣ ትዳር የሚመሰረተው ውስጥ ነው፤ በልብ ምሰሶነት፣ በአንጀት ማገርነት…ፍቅር እንደሀረግ ያልተጠመጠመበት ልብ አፈር ላይ ወደሚደኮነው ድንኳን ለሙሽርነት አይሮጥም ይለናል፡፡ ሥሩ ልብ ውስጥ ሲሆን ደግሞ ቶሎ አይነቀልም፡፡ ወደራሱ ዘመን ሲመጣ ግን ውዲቱ ፍቅረኛው፤ ቀለል አድርገን በተገኘው እንቀልሰው ትላለች፡፡ ምክንያቱም ለትዳሩ ዘለቄታ ብዙም ግድ የላትም…በቀላሉ ተክለን በቀላሉ እንነቅለዋለን፡፡ ጣጣ አታብዛ፣ አታካብድ ነው ነገሩ! ወይ ልጅ ለመውለድ፣ ወይም ቆሞ ቀር ላለመባል ብቻ ማግባት…ከዚያ ያለፈ ሕልም፤ ከዚያ የራቀ ራዕይ መጥፋቱን ይጠቁመናል፡፡ ይህ ታላቅ ማህበራዊ ተቋም እንደዋዛ እየታየ ነው በማለት ይወቅሳል - ገጣሚው፡፡
“ወናፉ” የሚለውና ገጽ 64 ላይ ያለው ግጥምም ትንሽ የሚመስጥ፤ የሚያሳስብና የሚያመራምር ነው።
ያ - ንፋስ አይጠግቤ፣ ያ ባዶ ስልቻ፣
ለፍም ከሰል ንዳድ፣ ካባ ለጉልቻ፡፡
የቃመውን ንፋስ፣ መልሶ እየዘራ፣
እልፍ ሺህ ጩቤዎች፣ እልፍ ሺህ ገጀራ፣
ስንት ሺህ መጥረቢያ፣ ስንት ፋስ ተሰራ፡፡ (ጥያቄ ምልክት ቢሆን ይመረጥ ነበር)
የሰጡትን ንፋስ፣ በአፉ እየቋጠረ፣
መልሶ መላልሶ እየተረተረ
እንደተነፈሰ፣ እንደተወጠረ፣
እሳት እያስነሳ፣ እሳት እየጫረ፣
አንዴም እሳት ሳይሆን፣ ወዝ እንዳቀረረ፣
ይሄው ስንት ዘመን፣
እሳት ማጋጋሚያ፣ ወናፍ ሆኖ ቀረ፡፡
ይህ ወናፍ ያለው ነገር ውስጠ ወይራ ይመስላል። ወናፉ ለብዙ ሰዎች፣ ምናልባትም ለትውልድ የለፋ ነው፡፡ ብዙ ሺህ ሰዎችን ያፈራ፣ ለሌሎች ያማጠ፣ እርሱ ግን ከአመጽ ሥር፣ ወይም ከዝቅታ ወደ ማዕረግ ሳይደርስ ኖረ! ሕይወቱ በታሰበ ቁጥር “ለእርሱ የሚገባው ሥፍራ ይህ አልነበረም” የሚባል አይነት፤ ምናልባት የብዙ ታላላቆች አባት ግን ታላቅነቱ አደባባይ ያልታየለት የሕብረተሰቡ አባል ይሆናል፡፡ የዚህ ወናፍ ሕይወት ምናልባት መምህርን የሚወክል ሊሆን ይችላል፡፡
መምህራን የሳይንቲስቱ አባት፣ የሀኪሙ ፈጣሪ፣ የሀገር መሪው ብርሃን ነው፡፡ ግን የተሰጠው ክብር ከስራው ጋር ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ እና መምህሩ እንደወናፍ ለፎቶልናል፤ ግን አልተዘመረለትም… ብንልም ያስኬደናል፡፡
በጣም አጭር ከሚባሉት ግጥሞቹ ውስጥ “የነፃነት ገዳም” በሚል ርዕስ የተፃፈችው ጥማኛለች።
ምነው ይህን ሆዴን፣ ጫማዬን ባረገው፤
ሲያሻኝ እንዳወልቀው፣ ሲያሻኝ እንዳጠልቀው፡፡
እግዜር አያርገውና ሆድ የሚወልቅ ቢሆን ማን ይሠራ ይሆን? ካልሠራስ ሰው እንዳሁኑ ሰው ይሆን ነበር ወይስ ዋሻ ውስጥ ተኝቶ እንደእንስሳ (አውሬ) ይኖር ነበር… አላውቅም፤ ግና ገጣሚው እንዲህ በዋዛ ፈዛዛ አይመስለኝም እንዲህ ያለው፡፡ ሆድ ብዙ ሰዎችን ውሻ አድርጐ፣ ሰውነታቸውን ሲያስጥል አይቶ ይሆናል፡፡ “ሆዳም” ይባል የለ! ለሆዱ የተሸጠ! ያኔ ነው እንደጫማ አንዳንዴ አውልቆ፣ ለነፃነት በነፃነት መናገር መቻልን የናፈቀው!
“ቀብድ የበላች ሀገር” ውስጥ ያሉ ግጥሞች የቋንቋ ለዛቸው ሸጋ ነው ብያለሁ፡፡ የቋንቋ አቅም፣ የቃላት ውበት የሚለኩት ደግሞ በአብዛኛው በረጃጅም ግጥሞች ነው፡፡ አንባቢ ግጥሞቹን “እስቲ የታሉ” ብሎ መጽሐፉን መፈተሽ ይችላል፡፡ መድበሉ ብዙ ረጅጅም ግጥሞችን ይዟል፡፡

Read 4873 times