Saturday, 27 July 2013 14:22

ሞስኮ ላይ ኢትዮጵያ ከኬንያ የተሻለ የሜዳልያ ስኬት ይኖራታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(8 votes)

5 የወርቅ፤ 4 የብርና 3 የነሐስ

ከሁለት ሳምንት በኋላ ሞስኮ በምታስተናግደው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከኬንያ የተሻለ የሜዳልያ ስኬት ልታስመዘግብ እንደምትችል መረጃዎች እያመለከቱ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በ13ኛው የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና ኬንያ 7 የወርቅ ሜዳልያዎችን ጨምሮ 17 ሜዳልያዎች በመሰብሰብ ስኬታማ እንደነበረች ቢታወስም፤ በሞስኮው የዓለም ሻምፒዮና ውጤታማ እና ልምድ ያላቸውን አትሌቶች በተለያዩ ምክንያቶች አለማሳተፏ የሜዳልያ ብዛቷን ሊቀንስባት ይችላል ተብሏል፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ በ1 የወርቅ እና በ5 የነሐስ ሜዳልያ ከሁለት ዓመት በፊት የተመዘገበውን ደካማ ውጤቷን በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻሏ እንደማይቀር እየተገለፀ ነው፡፡ የአሜሪካ ታዋቂ የስፖርት መፅሄት ‹‹ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ›› ከሳምንት በፊት በ14ኛው የዓለም ሻምፒዮና ባቀረበው የሜዳልያ ትንበያ ኢትዮጵያ እስከ 12 (5 የወርቅ፤ 4 የብርና 3 የነሐስ) ሜዳልያዎችን ልትሰበስብ እንደምትችል ተገምቷል፡፡ ኬንያ 2 የወርቅ፤ 3 የብርና 7 የነሐስ ሜዳልያዎች እንደምትወስድ ተገምቶላታል፡፡
14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ200 አገራት በሚኖረው የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት በአጠቃላይ እስከ 5 ቢሊዮን ድምር ተመልካች ይከታተለዋል፡፡ በሻምፒዮናው 205 አገራትን የወከሉ ከ2500 በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉም ይጠበቃል፡፡ የወርቅ፤ የብርና የነሐስ ሜዳልያ ለሚሸለሙትና እስከ ስምንተኛ ደረጃ ለሚያገኙት አትሌቶች 7.2 ሚሊዮን ዶላር ለሽልማት ቀርቧል፡፡ በሽልማቱ ዝርዝር መሰረት ለወርቅ ሜዳልያ 60ሺ ዶላር፤ ለብር ሜዳልያ 30ሺ እንዲሁም ለነሐስ ሜዳልያ 20ሺዶላር የሚበረከት ይሆናል፡፡

ለ4ኛ 15ሺ፤ ለ5ኛ 10ሺ፤ ለ6ኛ 6ሺ፤ ለ7ኛ 5ሺ እና ለ8ኛ 4ሺ ዶላር ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም አይኤኤኤፍ ከቶዮታ ጋር በመተባበር በሻምፒዮናው ሪከርድ ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች የ100 ሺ ዶላር ቦነስም አዘጋጅቷል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው የሚካሄድበት ዘመናዊው የስፖርት ኮምፕሌክስ የሆነው ሉዝኒስኪ ስታድዬም እስከ 35ሺ ተመልካች የሚይዝ ሲሆን ከ3 ዶላር እስከ 154 ዶላር የሚያወጣው የመግቢያ ትኬት ውድድሩ ከመጀመሩ ሶስት ሳምንት ቀደም ብሎ ከ80 በመቶ በላይ ተሸጦ አልቋል፡፡ የመላው ራሽያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ከፍተኛ ባለስልጣን አገራቸው የዓለም ሻምፒዮናውን በተሳካ ሁኔታ ከማካሄድ ባሻገር በሜዳልያ ሰንጠረዥ አንደኛ ሆና መጨረሷ የሚጠበቅ ነው ብለዋል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው ከመጀመሩ 5 ሳምንታት ቀደም ብሎ ሁለቱ የአጭር ርቀት ምርጥ ሯጮች አሜሪካዊው ታይሴን ጌይ እና ጃማይካዊው አሰፋ ፓውል ከዶፒንግ ችግር በተያያዘ ከተሳትፎ መታገዳቸው ሲታወቅ ጃማይካዊው ዮሃን ብሌክም በተሟላ ብቃት ላይ ባለመገኘቱ በሻምፒዮናው አይሳተፍም፡፡ ይህ ሁኔታም በ100 ሜትር በዓለም ሻምፒዮናው የሚኖረውን አጓጊ ትንቅንቅ አስቀርቶታል፡፡ ሁለቱ የጃማይካ የአጭር ርቀት ምርት ሴት አትሌቶች ቬሮኒካ ካምቤል እና ሻሮን ሲምፕሰንም በዶፒንግ ችግር ከተሳትፎ ተሰርዘዋል፡፡ የአሜሪካዋ ሳንያ ሪቻርድስ፤ የኬንያዎቹ ዴቪድ ሩዲሻ እና ቪቪያን ቼሮይት እና የደቡብ አፍሪካዋ ካስተር ሴማንያ በዓለም ሻምፒዮናው የማናያቸው ምርጥ አትሌቶች ናቸው፡፡ እውቋ የራሽያ የምርኩዝ ዘላይ ዬለና ኢዝንባዬቫ የዓለም ሻምፒዮናው ከስፖርቱ ዓለም የምትሰናበትበት ነው ተብሏል፡፡ የ31 አመቷ ዬሌና በምርኩዝ ዝላይ 28 ክብረወሰኖች ያስመዘገበች እንደሆነች ይታወቃል፡፡
የትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ትንበያ
‹‹ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ›› ከተመሰረት 65 አመት የሚሆነው እና በአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ አተኩሮ በመስራት የሚታወቅ ነው፡፡‹‹ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ›› በድረገፁ ከሳምንት በፊት ለዓለም ሻምፒዮናው ባቀረበው የሜዳልያ ትንበያ ጃማይካዊው ዩሴያን ቦልት የለንደን ኦሎምፒክ ስኬቱን በመድገም በአጭር ርቀት ሶስት የወርቅ ሜዳልያዎችን እንደሚሰበስብ ተገምቶለታል፡፡ እንግሊዛዊው ሞፋራህ ምንም እንኳን እንደ ለንደን ኦሎምፒክ በአገሩ ህዝብ ፊት ለመሮጥ ባይችልም ድርብ የወርቅ ሜዳልያ ድል ሊያስመዘግብ እንደሚችል ቢተነበይለትም ኢትዮጵያውያን ይቀናቀኑታል፡፡ የሞፋራህ ተቀናቃኞች የተባሉት በ10ሺ ሜትር ኢብራሂም ጄይላን እና በ5ሺሜትር ደጀን ገብረመስቀል ናቸው፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ በረጅም ርቀት 5ሺ እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች የወርቅ ሜዳልያ ድሎችን ከኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች ላይ የነጠቀው እንግሊዛዊው ሞፋራህ በሞስኮ ተመሳሳይ ድርብ ድል ለማስመዝገብ ሙሉ እምነት እንዳለው ተናግሯል፡፡ ሞ ፋራህ ከሁለቱ ርቀቶች በተጨማሪ በ1500 ሜትር በመወዳደርም ታሪክ የመስራትይ ፍላጎት አለው፡፡ በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ የ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሜዳልያ ትንበያ ለኢትዮጵያ በመካከለኛ ርቀቶች ብዙ ግምት አልተሰጣትም፡፡ በረጅም ርቀት ውድድሮች ግን በሁለቱም ፆታዎች የወርቅ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ እድሏ ከኬንያ የተሻለ ግምት አግኝታለች፡፡
በመካከለኛ ርቀት 1 ወርቅ 1 ብር
በመካከከለኛ ርቀት ለኢትዮጵያ ሊገኙ የሚችሉት ሜዳልያዎች በ800 ወንዶች የወርቅ እና በ1500 ሴቶች የብር ሜዳልያ በሚል የተተነበዩት ነው፡
በ3ሺ ሜትር መሰናክል በሁለቱም ፆታዎች ፤በሴቶች 800 ሜትር እና በወንዶች 1500 ሜትር ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ለኢትዮጵያ ምንም የሜዳልያ ትንበያ አልተሰጠም፡፡ ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ በሰራው ትንበያ የኬንያው ዴቪድ ሩዲሻ ሞስኮ ላይ እንደማይወዳደር በመረጋገጡ በ800 ሜትር ወንዶች ኢትዮጵያዊው መሃመድ አማን በቀጥታ የወርቅ ሜዳልያ ግምቱን ይወስዳል፡፡ የ21 ዓመቱ መሃመድ አማን ዘንድሮ በ800 ሜትር በዳይመንድ ሊግ እና በግራንድ ፕሪ ውድድሮች 7 ጊዞ ሮጦ 6 ሲያሸንፍ ሁለተኛ የወጣው አንዴ ብቻ ነው፡፡
በ1500 ሜትር ሴቶች የወርቅ ሜዳልያ እንደምታገኝ የተተነበየላት የስዊድን ዜግነት ያላት አበባ አረጋዊ ናት፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ገንዘቤ ዲባባ የብር ሜዳልያውን እንደምትወስድ ሲገለፅ ለነሐስ ሜዳልያው የታጨችው የኬንያዋ ፌዝ ኪዬፕጎን ናት፡፡ የ23 ዓመቷ ገንዘቤ ዲባባ ሞስኮ ላይ በመካከለኛ ርቀት በሴቶች ምድብ ለኢትዮጵያ ሜዳልያ እንደምታስገኝ ግምት የተሰጣት ብቸኛዋ አትሌት ናት፡፡
በ5ሺ ሁለት ወርቅ እና 1 ብር
በ5ሺ ሜትር ወንዶች የወርቅ ሜዳልያውን ደጀን ገብረ መስቀል እንደሚወስድ በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ከ3 ወራት በፊት በተሰራ ትንበያ ተገልፆ ነበር፡፡ ይሁንና መፅሄቱ ከሳምንት በፊት በድረገፁ ስለ ዓለም ሻምፒዮናው ባቀረበው ሌላ የትንብያ ቻርት ሲተነበይ የእንግሊዙ ሞ ፋራህ የወርቅ ሜዳልያውን እንደሚወስድ ተገልጿል፡፡ የብር ሜዳልያው ለኢትዮጵያዊው የኔው አላምረው ሲተነበይ፤ የኬንያው ኢሳያህ ኮች የነሐስ ሜዳልያ ተሰጥቶታል፡፡ የ26 ዓመቱ ደጀን ገብረመስቀል በ5ሺ ሜትር በለንደን ኦሎምፒክ የብር እንዲሁም በዳጉ የዓለም ሻምፒዮና ከሁለት ዓመት በፊት የነሐስ ሜዳልያዎችን የወሰደ ነው፡፡ ከደጀን ገብረመስቀል ጋር በ5ሺ ሜትር ለሜዳልያ ፉክክር ግምት የሚሰጠው የ21 ዓመቱ ወጣት አትሌት ሃጎስ ገብረህይወት ነው፡፡ ሃጎስ ዘንድሮ በ5ሺ ሜትር ከዓለም አንደኛ ደረጃ ይዞ ይገኛል፡፡ በ5ሺ ሜትር ሴቶች ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ከዓለም ሻምፒዮናው 3 ወራት ቀደም ብሎ የወርቅ ሜዳልያውን ለኬንያዋ ቪቪያን ቼሮይት ሰጥቶ ነበር፡፡ ቪቪያን በእርግዝና ሳቢያ ከዓለም ሻምፒዮናው ተሳትፎ ከቀረች በኋላ ግን የዛሬ ሳምንት የቀረበው የትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ የትንበያ ቻርት የሜዳልያ እድሉን ወደ ኢትዮጵያ አሸጋሽጎታል፡፡ እንደምታገኝ የተተነበየላት በ5ሺ ሜትር የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ መሰረት ደፋር ለወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም የርቀቱን ሪከርድ የያዘችው ጥሩነሽ ዲባባ የብር ሜዳልያ መውሰዳቸው ተጠብቋል፡፡ የነሐስ ሜዳልያ የተሰጠው ለኬንያዊቷ ቫዮላ ኪብዋት ነው፡፡
በ10ሺ 1 ወርቅ፤ 1 ነሐስ እና 1 ብር
በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ከ3 ወራት በፊት በተሰራ ትንበያ በ10ሺ ሜትር ወንዶች የኢትዮጵያው ኢብራሂም ጄይላን ለወርቅ ሜዳልያው አሸናፊነት በቀጥታ ታጭቶ ነበር፡፡ከሁለት ዓመት በፊት በደቡብ ኮርያ ዳጉ በተደረገው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ የወሰደው የ24 ዓመቱ ኢብራሂም ጄይላን ተቀማጭነቱ በጃፓን ሲሆን በዚያው አገር የሚገኘው ሆንዳ የተባለ ክለብ አትሌት ነው፡፡ ከሳምንት በፊት በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ በተሰራው የትንበያ ቻርት ግን የወርቅ ሜዳልያው ለእንግሊዙ ሞፋራህ ሲሰጥ የብር ሜዳልያው ለአሜሪካዊው ጋሌን ሩፕ እንዲሁም የነሐስ ሜደልያውን ደጀን ገብረመስቀል እንደሚወስዱ ተጠቁሟል፡፡ በሴቶች 10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያው እድል በቀጥታ ለጥሩነሽ ዲባባ ሲተነበይ የኬንያዋ አትሌት ቪቪያን ቼሮይት በትንበያው ለብር ሜዳልያው ታጭታ ነበር፡፡ ቼርዮት ዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮናውን ባለመሳተፏ ቀጣዩን የብር ሜዳልያ ግምት የወሰደችው መሰረት ደፋር ናት፡፡ የነሐስ ሜዳልያውን ኬንያዊቷ ጋላይስ ቼሩኖ ትወስዳለች ተብሎም ተገምቷል፡፡
በማራቶን ሁለት ወርቅና ሁለት ነሐስ
በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳልያው ድል የተተነበየው ለኢትዮጵያው የማነ ፀጋዬ ሲሆን የብር ሜዳልያው ለኬንያው በርናንድ ኮች ፤የነሐስ ሜዳልያው ለሌሊሳ ዴሲሳ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ የማነ ፀጋዬ ለወርቅ ሜዳልያው ድል ከፍተኛ ግምት ቢወስድም የኬንያ የማራቶን ቡድን አሰልጣኝ በዓለም ሻምፒዮናው ዋና ስጋታቸው የ2013 የለንደን ማራቶን አሸናፊ የሆነውን ፀጋዬ ከበደ ነው ብለዋል፡፡ የኬንያ ወንድ ማራቶኒስቶች በተከታታይ የዓለም ሻምፒዮናዎች ለአራተኛ ጊዜ የወርቅ ሜዳልያ ለመውሰድ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን በተለይ ፀጋዬ ከበደን በቡድን ስራ ከድል ለማስቀረት ከፍተኛ ትኩረት አድርገዋል፡፡ የ26 ዓመቱ ፀጋዬ ከበደ በማራቶን ሯጭነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬታማ ከሆኑ የዓለም ምርጥ አትሌቶች ዋናው ተጠቃሽ ነው፡፡ ከ2007 ጀምሮ በትልልቅ የማራቶን ውድድሮች መሳተፍ የጀመረው ፀጋዬ በ2008 እኤአ የፓሪስ ማራቶንን ፤ በ2008 እኤአ እና በ2009 እኤአ በጃኑ የፉካካ ማራቶን፤ በ2010 እና በ2013 እኤአ የለንደን ማራቶንን፤ በ20012 እኤአ ደግሞ የቺካጎ ማራቶንን አሸንፏል፡፡ በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ፤ በ2009 እኤአ ላይ በበርሊን የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በ2012 እኤአ ላይ በለንደን ኦሎምፒክ በማራቶን ሶስት የነሐስ ሜዳልያዎችን የሰበሰበው ፀጋዬ በማራቶን ርቀት በዓለም አንደኛ ደረጃን የያዘ አትሌት ሲሆን ከትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ትንበያ ውጭ በሞስኮ 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያውን ለማሸነፍ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል፡፡ በሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ቲኪ ገላና በዓለም ሻምፒዮናው የወርቅ ሜዳልያውን እንደምትወስድ ተተንብዮላታል፡፡ የ28 ዓመቷ ቲኪ ገላና በለንደን ኦሎምፒክ የማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት ስትሆን በዓለም የማራቶን ምርጥ አትሌቶች ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የብር ሜዳልያውን የኬንያዋ ኤድና ኪፕላጋት እንደምትወስድ ሲገመት የነሐስ ሜዳልያው ለኢትዮጵያዊቷ አበሩ ከበደ ተሰጥቷታል፡፡
የኬንያ ስጋት እና የዝግጅት ትኩረት
የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በሞስኮው የዓለም ሻምፒዮና አትሌቶች ከአንድ ውድድር በላይ እንዳይሳተፉ ከልክሏል፡፡ ከብሄራዊ ሻምፒዮናው በኋላ አትሌቶች ዳይመንድ ሊግን ጨምሮ በማንኛውም ውድድር እንዳይሳተፉ በማሰብ ፓስፖርታቸውን በመሰብሰብ ተቀብሎ ሁሉ ነበር፡፡
ሰሞኑን በወጡ ዘገባዎች ትልልቅ የኬንያ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮናው አገራቸውን በመወከል እንዳይወዳደሩ ማናጀሮች እና ኤጀንቶች ሴራ መሸረባቸውን በመግለፅ የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ባለስልጣናት ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ የአትሌቶቹ ማናጀሮች እና አትሌቶች ከዓለም ሻምፒዮና የተሻለ የገንዘብ ጥቅም ለሚገኝባቸው ውድድሮች ትኩረት ሰጥተው የኬንያን የሞስኮ ቡድን በጠንካራ ስብስብ እንዳይዘጋጅ እክል ፈጥረዋል ተብሏል፡፡ የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በበርካታ የአትሌት ኤጀንቶች ላይ የእግድ ቅጣት ለማስተላለፍ እየመከረ እንደሆነም ታውቋል፡፡ የኬንያ ቡድን ውስጥ ያሉ አንዳንድ አትሌቶች ስብስባቸው በጠንካራ እና ትኩስ ሃይል የተገነባ መሆኑን ሲገልፁ በኦሎምፒክ ከነበረው ደካማ ውጤት በመማር ሞስኮ ላይ ያልተጠበቀ አስደናቂ ውጤት እናስመዘግባለን በሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የኬንያ አትሌቶች ሰሞኑን እያደረጉ ባለው ዝግጅት በተለይ በአጨራረስ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረጋቸውን የአገሪቱ ጋዜጦች ገልፀዋል፡፡ የኬንያ ዋና አሰልጣኝ ሳሚ ሮኖ ቡድናቸው ልምድ ባላቸው እና በወጣት አትሌቶች ድብልቅ የተዋቀረ በመሆኑ በዓለም ሻምፒዮናው ውጤታማ የሚሆንበት ሰፊ እድል ይኖረዋል፡፡
አሰልጣኝ ሳሚ ሮኖ በሴቶች 10ሺ እና 5ሺ ሜትር ቪቪያን ቼሮይት አለመኖሯ፤ በወንዶች 800 ሜትር የዴቪድ ሩዲሻ አለመሳተፍ በኬንያ የሜዳልያ ብዛት ላይ መቀዛቀዝ ሊፈጥር ቢችልም ወጣት አትሌቶች ሊያገኙት የሚችለው ስኬት ሊያፅናን ይችላል ብለዋል፡፡ በ10ሺ ሜትር ወንዶች ውድድር ላይ ከባድ ፉክክር እንደሚኖር ይታወቃል ያሉት አሰልጣኙ ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባሻገር ተቃናቃኝነቱ የሚያስፈራን ሞፋራህ ነው ብለዋል፡፡ ኬንያ በ10ሺ ሜትር በዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ ከወሰደች 12 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

Read 5456 times